Monday, 13 April 2020 00:00

የአገራትን አቅም የሚፈትን፣ ታሪክን የሚቀይር ነው - አደጋው፡፡

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)

 • በአገራችን እስካሁን ከከባድ ስህተት ተርፈናል፡፡ ከሌሎች አገራት እንማራለን እንጂ፣ በጭፍን አንኮርጅም ብለዋል ጠ/ሚ ዐቢይ፡፡ በሽታን በመከላከል አገርንና ዜጎችን እናድናለን እንጂ፤ ኢኮኖሚን ቆላልፈን ህዝብን በረሃብ አንጨርስም ሲሉም ተናግረዋል::
         • ‹‹ድህነትና ረሃብ፣ ከሰው ሰው አይተላለፍም›› በሚል ስሜት፣ አገርን ከርችሞ ሚሊዮኖችን ለረሃብ ማጋለጥ፣ የሰዎችን ሕይወት ያረግፋል:: ኢኮኖሚን አጽድቆ የአገርን የወደፊት ሕልውና ይሸረሽራል - በሆይ ሆይታ እየተደናበሩ፣ በዘፈቀደ ኑሮን መዝጋት::
       
               ‹‹ኢንዲስትሪያቸው ጠንካራ፣ ፖለቲካቸው የተረጋጋ›› ከሆነ፣ ጥሩ ስንቅ ይዘዋል፡፡ የብቃት ስንቅ፣ ፈተናን ለመቋቋምና ለማሸነፍ የሚረዳ ትልቅ አቅም ነው፡፡ እነ ደቡብ ኮሪያ እና ታይዋን… የበሽታ መከላከያ፣ መመርመሪያና ማከሚያ ቁሳቁስ፣… በብዛትም፣ በጥራትም፣ በፍጥነትም ለማምረት የቻሉት፣ በድንገተኛ እድል አይደለም፡፡
ጠንካራ ኢንዱስትሪ፣ የዘወትሩን ኑሮ ለማደላደልና ለማበልፀግ ብቻ ሳይሆን፣ አደጋን ለመከላከልና ፈተናን ለማሸነፍ ምን ያህል እንደሚጠቅም በነደቡብ ኮሪያ በግልጽ ታይቷል፡፡ ጠንካራ የቴክኖሎጂ፣ የኢንዱስትሪና የቢዝነስ አቅማቸው፣ ለአደጋ ጊዜ፣ ትልቅ አለኝታ ሆኖላቸዋል፡፡
- ለበርካታ ቀናት፣ ብዙ የስራ እንቅስቃሴዎች ሲስተጓጐሉና ሲቋረጡ፣ በአገር ኢኮኖሚና በዜጐች ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ይደርሳል፡፡ የትኛውም አገር፣ የቱንም ያህል ቢበለፅግ እንኳ፣ አምራች እጆች ከስራ ሲፋቱ፣ ማሽኖች ሲተኙ፣ የፋብሪካና የቢዝነስ በሮች ሲከረቸሙ፣ ኢኮኖሚ ይቃወሳል፤ ኑሮ ይናጋል፡፡
የመጠንና የደረጃ ጉዳይ እንጂ፣ አንድም አገር ከጉዳት አያመልጥም፡፡ የመጠንና የደረጃ ልዩነት ግን፣… ተደናቅፎ የመንገዳገድና ተደናቅፎ የመሰበር ያህል፣ እጅግ የተለያዩ ውጤቶችን ሊያስከትል ይችላል፡፡
በኢኮኖሚ ደረጃ ውራ የሆኑ ብዙዎቹ አገራት፣ ገና በወጉ ያልደረጁ ጅምር አገራት ናቸው፡፡ አደጋ ሲገጥማቸው ይንኮታኮታሉ፡፡ የበለፀገ ኢኮኖሚንና ደልዳላ ኑሮን የተቀዳጁ አገራትስ? አውሮፓ ውስጥ አደጋ ሲከሰት፣ ብዙ ሰዎች መቸገራቸው ባይቀርም፣ በሳምንት ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ አያጡም፡፡
ጠንካራና ምርታማ ኢኮኖሚ የሌላቸው ድሃ፣ ደካማ፣ ወይም ጥገኛ አገራት ውስጥ ግን፤ አብዛኛው ሰው ፈተናን የመቋቋም አቅም የለውም፡፡ የእርሻ ምርት በ2% ከቀነሰ፤ ሚሊዮኖች ለረሃብ ይጋለጣሉ፡፡ ደካማ ኢኮኖሚና የድህነት ኑሮ፣ ገደል አፋፍ ላይ፣ በትንሽ ሽውታ ቁልቁል እንደሚንሸራተት አሸዋ ነው፡፡ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ፣ ዛሬ እጅ ካጠረው ነገ ይራባል፡፡ በአጭሩ፣ ድሃ አገራት፣ የሚያወላዳ የኢኮኖሚ አቅም ወይም፣ ለሳምንት የሚበቃ ስንቅ የላቸውም::
የውጭ ኩባንያዎች በሚያመርቱት ነዳጅ ላይ ብቻ፣ ወይም በቱሪዝም ላይ ብቻ የሚተማመኑ ደካማ እና ጥገኛ አገራትም፤ ከባባድ ፈተናዎችን ለረዥም ጊዜ የመቋቋም አቅም አይኖራቸውም፡፡
ብቃት ያላቸው የውጭ ኩባንያዎች፣ እንዲሁም ከበለፀጉ አገራት የሚመጡ ቱሪስቶች፣ ለአንድ አገር ኢኮኖሚ፣ በጣም ጠቃሚና አጋዥ አቅም ሊሆኑ ይችላሉ:: ከውጭ በሚመጣ ብቃትና በቱሪስት ዶላር ላይ ብቻ ተማምኖ፣ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ግን፣  ምናልባት ‹‹የድሎት›› ኑሮን እንጂ፣ ለፈተና የማይበገር ‹‹ደልዳላ›› ኑሮን አያስገኝም፡፡
ምርታማ ኢኮኖሚ፣ በተለይም ኢንዱስትሪ ነው ጠንካራ ስንቅ፡፡
ይህንን መገንዘብ፣ በአንድ ወገን፣ አቅማችንን አውቀን፣ አቅማችንን የሚመጥን፣ ውጤታማና የሚያዛልቅ ትክክለኛ መንገድ ለመቀየስ፣ እያንዳንዷን ተግባራችን ቅንጣት ሳናባክን ፋይዳ ባለው ስራ ላይ እንድናውል ይጠቅመናል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ለወደፊት ጥሩ ትምህርት ይሆነናል፡፡ ኢንዱስትሪ ላይ መዘናጋትና መቀለድ እንደማያዋጣ እንማርበታለን፡፡ ለ15 ዓመታት፣ ‹‹ኢንዱስትሪ›› ተቀልዶበታል፡፡ ‹‹ታዳሽ ሀይል››፣ ‹‹የካርቦን ልቀት››፣ ምናምን እየተባለ፣… ‹‹የሰሜን ዋልታ በረዶ እንዳይቀልጥ››፣ ‹‹ከመቶ ዓመታት በኋላ የዓለም ሙቀት በ2 ሴንቲ ግሬድ እንዳይጨምር›› በሚሉ ወገኛ ፈሊጦች ሳቢያ፣ የደሃ አገራችን ሃብት ባክኗል፡፡ የኢንዱስትሪ እድገት ተጓትቷል፡፡
በአላስፈላጊ የዘፈቀደ ቁጥጥርና በተንዛዛ ቢሮክራሲ፣ በታክስ ጫናና በአባካኝ የመንግሥት ‹‹የኢንዱስትሪ›› ፕሮጀክቶች ሳቢያ፣ ኢንዱስትሪን የሚያሳድግ የግል ኢንቨስትመንት አልተስፋፋም፡፡ ቢስፋፋ ኖሮ፣ የስራ እድል በብዛት ለመፍጠርና የዘወትር ኑሮን ለማሻሻል በተቻለ ነበር፡፡ ዛሬ ለአደጋ ጊዜም በጠቀመን ነበር፡፡
‹‹ኢንዱስትሪ የሌለው የእውቀት ዲጂታል ኢኮኖሚ›› ቅዥት ነው፡፡
በኢንዱስትሪ ላይ መቀለድ፣ እንኳን ለድሃ አገራት ይቅርና፣ ወደ ብልጽግና ሲገሰግሱ ለነበሩት ለአውሮፓ አገራትም አልበጀም። ‹‹የፋብሪካ ዘመን አልፏል፤ የማምረት ሥራ አርጅቷል›› እስከማለት የደረሱ አዋቂ መሳይ ወገኞች፣ ‹‹የእውቀት ኢኮኖሚ ላይ ደርሰናል›› (Knowledge Economy)…፣ ወደ ‹‹ Digital Economy ›› ተሸጋግረናል ምናምን… ሲሉ ደስኩረዋል፡፡
እውቀት ሁሉ፣… ዲጂታል ሆነ ሌላ ቴክኖሎጂ ሁሉ፣ ዞሮ ዞሮ፣ አንዳች ፋይዳ ወይም አንዳች አገልግሎት የሚሰጥ ምርትን በብዛትና በጥራት ለማምረት የሚውል ስለሆነ ነው፤ ዋጋ የሚኖረው፡፡ የኢንዱስትሪ አብዮት ዋና ባህርይ ምን ሆነና?
የእውቀት ግኝትንና የቴክኖሎጂ ፈጠራን፣ ወደ ተትረፈረፈ ምርትና ወደ ሰፊ የቢዝነስ ግብይት ያሸጋገረ ነው - የኢንዱስትሪ አብዮት:: በፋብሪካ አሰራር እና በገበያ ሥርዓት፣ የቢሊዮኖችን ሕይወት ያሻሻለ፣ ሰርቶ የመኖር ክብርን ያቀዳጀ፣ የሰዎች ድንቅ ታሪካዊ ስኬት ነው - የኢንዱስትሪ አብዮት፡፡
ዛሬ፣ በተገላቢጦሽ፣ እውቀትን ከምርት ነጥለው እየለያዩ፣ ቴክኖሎጂን ከፋብሪካ ቆንፅለው እየገነጣጠሉ በድሎት መኖር እንደሚቻል የሚሰብኩ፣ ለማስመሰል የሚሞክሩ ቀሽሞች በዝተዋል፡፡ ፀረ ብልፅግናና ፀረ ኢንዱስትሪ አጥፊ አስተሳሰብና ጠማማ ስሜት ተትረፍርፏል፡፡
በ25 ዓመታት ውስጥ፣ የነጣሊያንና የነፈረንሳይ ኢንዱስትሪ ቀስ በቀስ እየደነዘዘ፣ የፋብሪካ ሰራተኞች ቁጥር በሩብ ያህል ቀንሷል:: እና በተዘጉት በርካታ ሚሊዮን የፋብሪካ ስራዎች ምትክ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አዋቂዎችና ሳይንቲስቶች፣ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ጠበብቶች በአውሮፓ ተፈጠሩ? አልተፈጠሩም፡፡ ቀንሰዋል እንጂ፡፡
በተቃራኒው፣ የፋብሪካ ስራ በተዘጋ ቁጥር፣ የችርቻሮና የመስተንግዶ ንግዶች ናቸው በዝተው አገራት የተጨናነቁት:: የፋብሪካ ምርት የኋሊት እየቀረ፣ የምርት ችርቻሮ “ቢትረፈረፍ” ምን ዋጋ አለው? ከዚያ ውጭ የመንግሥት ቢሮክራሲ ተቀጣሪዎችና ሥራ አጦች ናቸው የተበራከቱት፡፡
ችርቻሮ፣ የመንግሥት ተቀጣሪ፣ እና ስራ አጥነት፣… በጭራሽ ‹‹የእውቀት ኢኮኖሚ ወይም የዲጂታል ኢኮኖሚ ውጤቶች›› አይደሉም:: እውቀትና ምርት፣ ቴክኖሎጂና ኢንዱስትሪ ሲነጣጠሉ ነው፤ እንዲህ አይነት ውድቀት የሚፈጠረው፡፡
በእርግጥ፣ እንዲህ አይነቱ የነጣሊያንና የነፈረንሳይ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ወዲያውኑ አገሬውን ሲያብረከርክ፣ ዜጎችን ሲያደኸይ በግልጽ ጎልቶ ላይታይ ይችላል፡፡ ግን ተጎድተዋል፡፡ ብዙዎቹ የአውሮፓ አገራት፣ 2% የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ካቃታቸውኮ፣ 10 ዓመት አልፏል፡፡ ገና ባይደኸዩም፤ ኑሮ እየከበደ መጥቷል። ገና አገር ባይተራመስም፣ ፖለቲካቸው እየተቃወሰ ነው፡፡
የበሽታ ወረርሽኝ፣ የተዳከሙ አገራትን ሲያጠቃ፤ ከድጡ ወደ ማጡ ነው፡፡
በየሰበቡ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ ኢንዱስትሪያቸውን የሸረሸሩ አገራት፣ ከኢኮኖሚና ከፖለቲካ ቀውስ ባሻገር፣ ዛሬ ደግሞ፣ ሌላ ተጨማሪ ፈተና ውስጥ ገብተዋል፡፡
የበሽታ ወረርሽኝን፣ በላቀ ፍጥነትና በአስተማማኝ ብቃት ለመከላከል ተቸግረዋል:: አንደኛ ነገር፣ አስፈላጊ ቁሳቁስ ለማሟላት፣… በብዛትና በፍጥነት፣ እንዲሁም በጥራትና በአነስተኛ ወጪ ቁሳቁስ ለማምረት የሚችል፣ ንቁ የኢንዱስትሪ አቅም አጥሯቸዋል፡፡
በሁለተኛ ነገር፣ ኢንዱስትሪን የሚያዳክም አጥፊ አስተሳሰብ፤ ኢኮኖሚን ብቻ ሳይሆን፣ የበርካታ አገራትን ፖለቲካ አቃውሷል:: የአውሮፓ አገራት ፖለቲካም ሳይቀር ተናግቷል::
ያልተረጋጋና ያልተደላደለ ፖለቲካ፣ ቀልብ የለውም፡፡
አደጋን ለመከላከልና ቀድሞ ለመዘጋጀት፣ ንቃትም ስክነትም ያስፈልጋል፡፡ የተቃወሰና የተናጋ ፖለቲካ ግን፣ ገና ባይተራመስም እንኳ፣ በስክነት ፋንታ ደንዝዞ የመዝረክረክ፣ በንቃት ምትክ የመደናበር ግርግር ያመዝንበታል፡፡
አንድም፣ በጭፍን ብዥታ መፍዘዝና ጭፍን ትችትን በመፍራት መደንዘዝ ይነግሳል፡፡ አሊያም፣ በጭፍን መቅለብለብና መቅበዝበዝ፣ ቅጽበታዊ የሆይ ሆይታ ስሜትን እየተከተሉና እየተነዱ፣ በዘፈቀደ መሯሯጥና እየተንጋጉ መደናበር ይበረክታል::
እውነታን ከመጋፈጥ ይልቅ፣ በጭፍን ስሜት የሚሰነዘሩ ትችቶችን በመፍራት፣…ለምሳሌ ለወረርሽኝ የሚያጋልጡ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችን ለጊዜው አለማስቆምና በዝምታ ማለፍ፤ አቅመ ቢስ ድንዛዜ ነው፡፡
ደግነቱ፣ ጠ/ሚ አብይ፣ ወረርሽኝን ለመከላከል ካከናወኗቸው የቅድመ ጥንቃቄ ትክክለኛ ጥረቶች መካከል አንዱ፣ ሃይማኖታዊ ስነስርዓቶች ላይ ያተኮረ እጅግ ጠቃሚ ማሳሰቢያና ያላሰለሰ ትኩረት መስጠታቸው ነው፡፡ ከድንዛዜ ስህተቶች ድነናል፡፡ ከሁለተኛው ስህተትስ?
‹‹ረሃብ አይተላለፍብኝም›› በሚል ስሜት፣ ኢኮኖሚንና ኑሮን ለመዝጋት መደናበር፡፡
‹‹ምን አደከመኝ?›› በሚል የስንፍና ስሜት፤ እንዲሁም አላዋቂዎች በሚፈጥሩት የሆይ ሆይታ ስሜት የመነዳት፤ እዚህና እዚያ የመቅበዝበዝ ችግር ነው - ሁለተኛው ስህተት:: እናም ከሌሎች አገራት በጭፍን እየኮረጁ፣ ሰማይ ምድሩን ዘጋግቶ፣ አገር ምድሩን ቆላልፎ ለመቀመጥ መደናበር ይመጣል፡፡
በዚህም በኩል፤ በአገራችን እስካሁን ከከባድ ስህተት ተርፈናል፡፡ ከሌሎች አገራት እንማራለን እንጂ፣ በጭፍን አንኮርጅም ብለዋል ጠ/ሚ ዐቢይ፡፡ በሽታን በመከላከል አገርንና ዜጎችን እናድናለን እንጂ፤ ኢኮኖሚን ቆላልፈን ህዝብን በረሃብ አንጨርስም ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ድህነትና ረሃብ፣ ከሰው ሰው አይተላለፍም›› በሚል ስሜት፣ አገርን ከርችሞ ሚሊዮኖችን ለረሃብ ማጋለጥ፣ የሰዎችን ሕይወት ያረግፋል:: ኢኮኖሚን አጽድቆ የአገርን የወደፊት ሕልውና ይሸረሽራል - በሆይ ሆይታ እየተደናበሩ፣ በዘፈቀደ ኑሮን መዝጋት፡፡
አደጋን ለመከላከልና ፈተናን ለማሸነፍ፣ ፅናትና ጥበብ፣ ትጋትና እርጋታ ያስፈልጋል:: የሩቁን እያሰቡ የዕለት ተዕለቱንም ለመትጋት፣ ትንሽ የተደላደለ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ያስፈልጋል:: አብዛኞቹ ድሃ አገራት ለዚህ አልበቁም፡፡
ደህና የነበረው የአውሮፓ ፖለቲካ እንኳ፣ እንደ ድሮው ደልዳላ አይደለም፡፡ ነባሮቹ የአውሮፓ ፓርቲዎች፣ በአብዛኛው ከስልጣን ብቻ ሳይሆን፣ ከተፎካካሪነትም ተገፍትረዋል፡፡ በጣሊያንና በፈረንሳይ፣ ለስልጣን እንግዳ የሆኑ ፓርቲዎች ናቸው የመንግሥት መሪዎች፡፡
አንዳንዶቹ ፓርቲዎች፣ 30% የድጋፍ ድምጽ ካገኙ፣ እንደ ትልቅ የምርጫ ድል የሚቆጥሩ ሆነዋል፡፡ እንደ ድሮ፣ ከ50% በላይ የድጋፍ ድምፅ የሚያገኝ ፓርቲ ጠፍቷል፡፡
ሁለት ሦስት ፓርቲዎች፣ ‹‹በስልጣን ቅርጫ›› ላይ ለመደራደርና ጥምረት ለመፍጠር የሚያደርጉት ሙከራ፣ በብዙ አገራት አስቸጋሪ ሆኗል:: ቢችሉም እንኳ አያዛልቅም፡፡ የስፔን እና የጣሊያን የዘንድሮ የፖለቲካ ድራማዎችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
በአጠቃላይ በጠንካራ ኢንዱስትሪ ላይ የተመሰረተ፣ ደልዳላና አምራች ኢኮኖሚ፣ የዘወትር ኑሮን ያበለፅጋል፤ የተረጋጋ ፖለቲካን ለማስፈን ያግዛል፤ ይህም ተመልሶ ኢኮኖሚን ለማሳደግ ያገለግላል፡፡ አደጋን ለመከላከልና ፈተናን ለማሸነፍም፣ አለኝታ ይሆናል፡፡
ኢንዱስትሪያቸው ጠንካራ፣ ፖለቲካቸው የተረጋጋ ከሆነ፣ ጥሩ ስንቅ ይዘዋል:: ፈተናውን ለመቋቋምና ለማሸነፍ የሚረዳ አቅም ይሆናቸዋል (ደቡብ ኮሪያንና ታይዋንን መመልከት ይቻላል)፡፡
ጣሊያንና ስፔን፣ ፓሪስና ኒውዮርክ፣ በብዙ ሚሊዮን ጐብኚዎች ዘንድ፣ ተመራጭ የቱሪዝም ማዕከላት መሆናቸው፤ ፈተናቸውን አጣዳፊና ከባድ አድርጐባቸዋል፡፡
በርካታ የአውሮፓ አገራት ከኢኮኖሚ ቀውስ ከማገገም ይልቅ፣ የፖለቲካ ቀውስ እየታከለበት፤ የተረጋጋ መንግስት ማጣታቸው ደግሞ፣ አቅማቸውን በማዳከም ጐድቷቸዋል፡፡
የድሃና የኋላቀር አገራት ችግር ደግሞ ብዙ ነው፡፡ ከሌላው አለም ጋር ያላቸው የቢዝነስም ሆነ የቱሪዝም ግንኙነት አነስተኛ ስለሆነ፣ እንዳየነው ለበሽታ ወረርሽኝ ቶሎ ላይጋለጡ ይችላሉ፡፡ በሽታው ዘግይቶ ቢመጣም ግን፣ ድሃ አገራት፣ ብዙም የመከላከልና የመቋቋም አቅም አላሳዩም:: ችግራቸው ድርብ ድርብርብ ነው፡፡ አለመደንዘዝና አለመደናበር ይበጃቸዋል፡፡

Read 8475 times