Saturday, 07 July 2012 10:26

“እያሃ ያብባል ገና”

Written by  ትእግስት ታፈረ ሞላ Tg.moll@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

ጠዋት

ድሮ በጎንደር ዙሪያ የሚኖሩ ገበሬዎች አንዱ ታቦት የአመት ሲሆን ወይ ለጥምቀት በዓል ጎንደር ከተማ ሲመጡ ግማሹ “አረ እሰይ ስለቴ ሰመረ” ሲል ሌላው “በወት ግባ በወት፤ ያገራችን ታቦት” ይላል፡፡ የከተማው ጎረምሳ ደግሞ ያሆ…ያሆ… ይላል፡፡ እየተጋፋ እየተተራመሰ፡፡ የገጠር ኮበሌዎች ግን ክብ ሰርተው “አዲሳበባ አዲሳበባ ያብባል ገና” እያሉ ወዛቸው በግንባራቸው ላይ በተለያየ አቅጣጫ እየወረደ ይጨፍራሉ፡፡ ልጅ ሆኜ አዲስ አበባ የሚኖሩባት ቀዬ ትመስለኝ ነበር፡፡ ከዛ ሁሉ ዘማሪ ከዛ ሁሉ ዘፋኝ እነሱ ብቻ የሚያሞግሷት፤ “ያብባል ገና” እያሉ የሚፎክሩላት መንደራቸው፤ ልዩ ተራሮቿ በአደይ አበባ ፍክትክት ያሉ ሆነው መሬቱ ሁሉ ፈክቶ ግጦሽ የሚፈልጉ በሬዎች ጥርሳቸውን የሚቦርሹበት ጉማጅ ሳር በማጣታቸው ሲበሳጩ፤ ገበሬዎቹ “እያሃ ያብባል ገና …እያሃ ያብባል ገና…” እያሉ የሚያበሽቋቸው ይመስለኝ ነበር፡፡

ደግሞም ሁሉ ነገር ፈክቶ ፈክቶ ደረቁ የጎጇቸው የሳር ክዳን አሳስቧቸው “ያብባል ገና” የሚሉ ይመስለኝ ነበር፡፡ ያኔ አዲሳባ በእነሱ ፉከራ ውስጤ ገባች፡፡ “እያሃ…እያሃ…ያብባል ገና፤ አዲስ አበባ..ያብባል ገና”

ነፍስ ሳውቅ ለካ አዲሳባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ መኪና የሚተራመስባት ሰፊ ሀገር እንጂ በሬና ገበሬ የሚኖርባት ትንሽ የገጠር መንደር አይደለችም፡፡ ለካ እነኛ ገበሬዎች ወዛቸው ጠብ እስኪል በወኔ የፎከሩላትን አዲሳባን ጨርሶ አያውቋትም፡፡ አዲሳባም አታውቃቸውም፡፡ ግን ልጅ ወልደው ለክርስትናው ሲጨፍሩም “እያሃ ያብባል ገና እያሃ ያብባል ገና … አዲስ አበባ አዲስ አበባ ገና” ይላሉ፡፡

ያኔ አዲሳባ የገበሬዎቹ መንደር ትመስለኝ በነበረ ጊዜ፣ ለአንድና ለሁለት ሰንበት ለፀበል እኛ ቤት ከገጠር የሚመጡ ዘመዶቻችን ስር አልጠፋም ነበር፡፡ አዲሱና ሚስቱ ደብሬ የመጡ ሰሞን “እስኪ አዲሳባ ያብባል ገና በልልኝ” እያልኩ አዲሱን ስለምን “ቆይማ እኔን ስሚኝ … እሱ የወንዶቹ ነው፤ እኛ ሴቶች ምን እንደምንዘፍንላት ልንገርሽ” ትልና

“አንቺ ቢራቢሮ ብረሪ ብረሪ

አዲስ አበባ ላይ ሂጅና ከትሚ

ተደላደይና ወፊቷን ላኪብኝ

ጨክኜ እመጣለሁ እኔም እንዲያልፍልኝ” በዜማ ታንቆረቁረዋለች፡፡

በሴቱም በወንዱም በሚዘፈንላት አዲሳባቸው እየቀናሁ እሰማት ነበር፡፡

ይቺ እድላም ሀገር በጠዋት እኔ ውስጥ እንዲህ ገባች፡፡

ረፈደ

ማን ምን እያደረገ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን እኔ ምን እያደግሁ እንደሆነ አላውቅም፡፡

ግን እያደረግሁ ነው፡፡ እየተወዛወዝኩ፤ እየተራመድኩ፤ ቁጭ እያልኩ እየተነሳሁ፡፡ እየፈለጥኩ እየቆረጥኩ፤ እየበላሁ እየጠጣሁ እውላለሁ፡፡ ይሄ ድርጊት ካልሆነ ግን እዚች ምድር ላይ ምን እያደረግሽ ነው ቢሉኝ መልስ የለኝም፡፡ ታዲያም ዝም ብዬ ስኖር ስኖር … አንድ ቀን እየመሸ ሳለ ከካዛንቺስ በእግሬ ወደ ኡራኤል ስሄድ ከኋላ “ቸብ…ቸብ..” የሚል የብዙ ሰው የእግር ኮቴ ሰማሁ፡፡ ከዳናው እኩል ሆታ ይሰማኛል፡፡ ከየገጠሩ መጥተው አዲሳባ የሚሰሩ ሴቶች የማታ ትምህርታቸው ረፍዶባቸው፣ ሥራ ያጎበጠው ወገባቸው አስጎንብሷቸው በአጠገቤ እየተጣደፉ ያልፋሉ፡፡ ሆታው እየቀረበ መጣ፡፡ “እያሃ ያብባል ገና … እያሃ ያብባል ገና …አዲስ አበባ አዲስ አበባ ያብባል ገና…” ድምፁ እጅግ እየቀረበኝ እየቀረበኝ ወደ እኔ ይመጣል፡፡ ግን አጠገቤ የምሰማው ሳይሆን ከሰማየ ሰማያት የሚወርድ ይመስለኛል፡፡

“አዲስ አበባ … አዲስ አበባ… ያብባል ገና

እያሃ ያብባል ገና … እያሃ ያብባል ገና”

ድምፁ እውነትም አጠገቤ ቢሆንም ብቻውን ስስ ነው፡፡

ከእሱ ላይ ከልጅነቴ ውስጥ ፈልቅቄ ያወጣሁትን ድምፅ ስደርበው ዳጎሰ፡፡ ለካ እነኝህ ባለ ማተቦች ድሮ ሳያውቋት በየበዓሉ ላዲሳባ እንደዘፈኑላት ሁሉ፤ አውቀዋትም እየዘፈኑላት ነው፡፡

“ቸብ…ቸብ…ቸብ…” ይላል አስፋልቱ

እነሱ ደግሞ “እያሃ ያብባል ገና…” ይላሉ

ድንገት ሁሉም ነገር ፀጥ ረጭ አለ፡፡ ቆም ብዬ ወደ ኋላዬ አየሁ፡፡ በርከት ያሉ የቀን ሰራተኞች ማ ቤከሪ የሚል ዳቦ ቤት በር ላይ ላባቸውን ከግንባራቸው

እየጠረጉ ቆሙ፡፡

አንዱን ጠጋ ብዬ “ምነው ጭፈራው ተቋረጠ?” አልኩት፡፡

“ዳቦ ልንገዛ” አለኝ፡፡

“የትኛው ህንፃ ላይ ነው እምትሰሩት?” አልኩት ከሁኔታቸው የቀን ሠራተኞች እንደሆኑ ገምቼ፡፡ “ኸዚያ ላይ” አለኝ፤ በአንዱ እጁ ወደ አራት ኪሎ መንገድ እየጠቆመኝ፡፡ ከሥራ ብዛት የጠጠረውን እጁን ድንጋይ ቢያልቅባት ዔሊ ልትለብሰው ትመኘዋለች፡፡

“ሁላችሁም የዚህ ሀገር ተወላጆች አይደላችሁም አይደል?” አልኩት መንገዴን ትቼ፤ መቆሜን ረስቼ

“ሙላው ሀገሩ ወዲያ ነው፡፡”

“ሥራ እንዴት ነው?”

“አየ … እንዴው ነው አንችው”

“የቀን ስራ እኮ አሁን ክፍያው ጥሩ ነው”አልኩት

“መቼም” አለኝ ቁጥብ እንዳለ

“ግን ሥትሰሩ ውላችሁ ስትሮጡ አይደክማችሁም?”

“ካልተሮጠ ይደረሳል ብለሽ ነው?”

“የት ነው መድረሻችሁ?”

“ኮተቤ”

“ምነው?”

“እዛ ቤት እርካሽ ነው፡፡”

“እና በአውቶብስ አትሄዱም?”

“አየ ተሰብስበን እያንጎራጎርን ስንሮጥ መንጌዱን እቃ ብለነው ነው?”

ወዲያው ዳቦ ሊገዙ የተወከሉት ፌስታል ሞልተው ብቅ አሉ፡፡ እኔ የማዋራው ልጅም አይኑ ሄደብኝ፡፡

ጥቂት ማውራት ፈልጌ ዳቦውን እስኪቀበል ጠበቅሁና ጠጋ ስለው ድንገት “ኧረ ጎበዝ እየመሸ ነው፡፡” አለና አንዱ “እያሃ ያብባል ገና…” እያለ ወደ ፊት ሮጠ፡፡ ወታደራዊ ትዕዛዝ የተሰጣቸው ይመስል ሁሉም ከመቅፅበት ግር ብለው ወደፊት እየሸመጠጡ ዜማውን ተቀበሉት፡፡

ሳዋራው የነበረው ወጣትም ድንጋይ እጁን ለስንብት እያንከላወሰ ጉንጩን የሞላው ዳቦ ወደ ጉሮሮው ሳይወርድ “እያሃ ያብባል ገና…” እያለ ሮጠ፡፡

ተሽቀዳድሜ “ግን ያብባል?” አልኩት፡፡

ፈገግ ብሎ “ቢያብብም ባያብብም፡፡” አለኝ ፍጥነቱን ጨምሮ፣ እንደ ጓደኞቹ ወደ ፊት እየሮጠ “እያሃ ያብባል ገና…እያሃ ያብባል ገና…” ተቀላቀለ፡፡ ዳናቸውም ድምፃቸውም እየራቀ ሄደ፡፡ የቤት ሰራተኞች አሁንም እየተጣደፉ በአጠገቤ ያልፋሉ፡፡ የአዲሱ ሚስትና የአዲስ አበባ ዘፈኗ ትዝ አሉኝ፡፡ ቀስ በቀስ ግን የፈለፈልኩት የልጅነት ማህደሬ ውስጤ እየሰጠመ ሔደና ጆሮዬ ውስጥ ሌላ ነገር ተወዘፈ፡፡ “ቢያብብም ባያብብም…”

ልቤ ደግሞ “እያሃ ያብባል ገና … እያሃ ያብባል ገና…” ይል ጀመር፡፡

ሲመሽ …

ወይ ያብባል ወይ አያብብም፡፡

 

 

Read 1854 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 10:32