Sunday, 12 April 2020 15:26

ክርስትና ለኮሮና - ቫይረስ መልስ አልሰጠም፤ እንዲሰጥም አይጠበቅበትም

Written by  ትርጕም፦ ሰሎሞን አበበ ገብረ መድኅን
Rate this item
(4 votes)

  “--ራሳችንን አግልለን ባለንበት ጊዜ እንኳ፥ ቅዱሱ መንፈስ በእኛ ውስጥ ኾኖ ሲቃትት፥ የእግዚአብሔር መገኘትና ፈዋሽ ፍቅሩ ያረበበብን ንዑሳን ቅዱሳን ማኅደራት እንኾንለታለን። ከዚያም ውስጥ፥ ዐዳዲስ የመቻል ዕድሎች፥ ዐዳዲስ የደግነት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች፥ ዐዲስ ሳይንሳዊ ዕውቀት፥ ዐዲስ ብሩሕ ተስፋ ተገልጠው ሊወጡ ይችላሉ።--”
              ጸሐፊ፦ ኤን. ቲ. ራይት
   
               ሳንባ-ቆልፍ (ኮሮና ቫይረስ) ሰፊ ማኅበራዊ ተዐቅቦ አስከትሏል። ለብዙ ክርስቲያኖች፥ በኮሮና መዘዝነት የተግተለተሉ ተያያዥ ተዐቅቦዎች የመጡባቸው ሁዳዴ (ወይም ዐቢይ ጾም) በሚባለውና ከበርካታ ነገሮች በመታቀብ “ክተት-ዝጋ” በሚታወጅበት ትውፊታዊ ወቅት ላይ መኾኑ ግልጽ ነው። ነገር ግን፥ ከሁዳዴ ተዐቅቦ በተለየ ኹኔታ፥ ኮሮና ጠበቅ ያሉ አዳዲስ ግዴታዎችን ጨምሮባቸዋል፤ ቲያትር አያዩም፤ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፤ ዕድሜያችን ከ70ዎቹ በዘለለውና መጠነኛ የሁዳዴ ሥርአቶቻችንን ብቻ እንወጣ በነበረው ላይ፥ እንደ ቀልድ፥ በተግባር የቁም እስር ላይ ያለን ዐይነት አድርጎናል፤ ወዳጅ ጓደኞቻችንን ወይም የልጅ ልጆቻችንን ከማግኘት ከመታገዳችን ወይም ወደ ማንኛውም የመዝናኛ ተቋማትና አብያተ ክርስቲያናት እንዳንኼድ ከመታቀባችን ጋር ሲወዳደር፣ ውስኪ ወይም ቸኮሌት ቀረብን ማለት የልጅ ጨዋታ ያኽል ይቆጠራል።
ሥጋችን በመደበኛነት የሚፈልገውን ነገር ለማግኘት መፈለጉ ጤናማ ምክንያት አለው። ጭርታ በተጫነው የብቸኝነት ስፍራ መዘጋት ቅጣት የኾነው ለዚህ ነው። አኹን የተያያዝነው “ሁዳዴ” የሚጠናቀቅበት፥ በናፍቆት የሚጠበቅና ዕቅጩ ቀን የሚታወቅ የፋሲካ በዓል የለውም። እየዋለ እያደር እየጨረስነው ነው የምንለው የቀን ቁጥር አልተሰደረልንም። ይህ እንቅስቃሴ ኹሉ የተገደበበት መታቀብ ነው እንጂ ዕረፍት አይደለም፤ እንዲያውም፥ የእርጋታ መንፈስ የተጫነው፥ ሥጋትም የሞላው የኀዘን ጊዜ ኾኖብናል።
ሞኝ ተጠራጣሪ፥ እንደ ልማዱ፥ “እግዚአብሔር ይኸን ለምን ያመጣብናል?” ብሎ ሊነግረን ይሞክር ይኾናል። ቅጣት ነው? ማስጠንቀቂያ ነው? ምልክት ነው? ኹሉ ነገር የግድ የተብራራ ምኵንያዊ ምላሽ ሊኖረው እንደሚገባ የሚያምንና የብዙ ትውልዶች ዘመን በተሻገረ ባህል ውስጥ እነዚህ ነገሮች ብዙም ያልተጤነ ክርስቲያናዊ ምላሽ ተደርገው ሊቀርቡ ይችላሉ። ነገር ግን፥ ባይኾንስ ብለን ብናስብስ? እንበልና፥ አግባብ ያለው የሰው ልጅ ጥበብ ማንኛውንም አጠራጣሪ መላምቶችን አንድ ላይ ሰብስቦ ውሃ የሚቋጥር ነገር አጥቶ፥ “በቃ፥ ነገሩ እንዲያ ነው ማለት ነው?” ዐይነት ማመንታት ቢደቀንበትስ? ጨርሶውኑ፥ ቲ. ኤስ. ኤሊየት በ1940ዎቹ እንዳስተዋለው፥ ተስፋ አድርገን የምንጠባበቀው ልክ ያልኾነ ነገር ከመኾኑ የተነሣ፣ ብቸኛው ምክር ያለ ምንም ተስፋ መጠባበቁ ቢኾንስ?
ምኵንያውያን - “ራሺናሊስቶች” (ክርስቲያን ምኵኒያውያንን ጨምሮ) የተብራራ መግለጫ ይፈልጋሉ፤ ወሸነኔዎች-“ሮማንቲኮች” (ክርስቲያን ወሸነኔዎችን ጨምሮ) የእፎይታ ፋታ ማግኘት ይሻሉ። ነገር ግን፥ ምናልባት ከኹለቱም አማራጮች በተሻለ የሚያስፈልገን መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ሙሾ (እንጕርጕሮ) ወደ ተገቢ ቦታው መመለስ ነው። ሙሾ ማለት ሰዎች “ለምን?” እያሉ ጠይቀው ምላሽ ባላገኙ ጊዜ የሚፈጠር ነገር ነው። ከራሳችን ኀጢአትና ውድቀቶቻችን የተነሣ ከምንወጠርበት ራስ-ተኰር ጭንቀት ተሻግረን ስለ ዓለሙ ሥቃይ በስፋት መመልከት ስንጀምር የምንገባበት ኹኔታ ነው። በኒው ዮርክ ወይም በለንደን [ወይም በአዲስ አበባ] ዓለማቀፍ ወረርሽኝ መጋፈጥ ከመጥፎም በላይ ነው። በግሪክ ደሴት ውስጥ ስደተኞችን አጨናንቆ ያከማቸው የስደተኞች ጣቢያስ? ጋዛስ? ደቡብ ሱዳንስ?
አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ችላ ያሉት ቢመስልም፥ በዚህ ጕዳይ ላይ የተሳካ ሥራውን ሊከውን የሚችለው የመጽሐፍ ቅዱስ የራሱ የዜማ መጽሐፍ የኾነው መዝሙረ ዳዊት ነው። ስድስተኛው መዝሙር፥ “አቤቱ፥ ማረኝ” በማለት ይማጸናል፤ “ድውይ ነኝና…፤ ዐጥንቶቼ ታውከዋልና ፈውሰኝ” ይላል። ዐሥረኛው መዝሙር በፈንታው “አቤቱ፥ ለምን ርቀህ ቆምህ? በመከራም ጊዜ ለምን ትሰወራለህ?” በማለት በሠቀቀን ይጠይቃል። በዚሁ መልክ ይቀጥልና፥ “አቤቱ፥ እስከ መቼ ፈጽመህ ትረሳኛለህ? እስከ መቼስ ፊትህን ከእኔ ትሰውራለህ?” (መዝሙር 13) ይላል። የበለጠ የሚያስደነግጠው፥ ኢየሱስ ራሱ በመስቀል ላይ በተጨነቀ ጊዜ እንዲህ በማለት አንዱን መዝሙር ጠቅሶ መጮኹን ስለምናገኝ ነው፤ “አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ?” (መዝሙር 22)።  
እውነት ነው፤ እነዚህ ቅኔያት ችግሩን ለማብራራት ሳይኾን፥ በዚያው በችግሩ ውስጥ ተኹኖም፥ አስተማማኝ ዋስትና ለመስጠት በማሰብ በስተመጨረሻ በብርሃን ጸዳል አጊጠውና በሀለዎተ-እግዚአብሔርና ተስፋ በተሞላ የታደሰ ስሜት ደምቀው ነው የሚጨርሱት። ኾኖም አንዳንድ ጊዜ በሌላ ጎዳና ሲጓዙ ይገኛሉ። ለምሳሌ፥ መዝሙር 89 የእግዚአብሔርን መልካምነትና ተስፋዎች በማድነቅ ይጀምርና፥ በድንገት አቀራረቡን ለውጦ ነገሩ በሚያስፈራ መልክ መበለሻሸቱን ያውጃል። መዝሙር 88ም በችግር ከፍቶ በጨለማ ይዘጋል፤ “ወዳጄንና ባልንጀራዬን ከእኔ አራቅህ፤ ጓደኛዬ ጨለማ ብቻ ኾኖ ቀረ” (አመት) እስከ ማለት ደርሷል። ራሳችንን ላገለልንበት ጊዜ የሚኾን ቃል።
በቅዱሳት መጻሕፍት ትውፊት ድርና-ማግ ውስጥ የተሸመነው የሙሾ ቍም ነገሩ የቍጭታችን፥ የኀዘናችንና የብቸኝነታችን እንዲሁም፥ ምን እየተከናወነ እንደ ኾነ ወይም ለምን እየኾነ እንዳለ ለመረዳት ፈጽሞ ልንገነዘብ ያለመቻላችን ማስተንፈሻ ፉካ አይደለም። የታሪከ መጽሐፍ ቅዱስ ምሥጢሩ፥ እግዚአብሔርም [ስለ ዓለሙ ስብራት] የሚያለቅስ መኾኑ ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ከኹሉ በላይ የላቀ፥ እያንዳንዱን ነገር የሚቆጣጠርና በገዛ ዓለሙ ውስጥ የሚከናወነው ነገር ምንም ግድ ሳይሰጠው፣ በአርምምሞ የሚታዘብ ዐይነት አድርገው ማሰብ ይፈልጋሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኘው መገለጫ ግን ይኸን መሳይ አይደለም።
የዘፍጥረት መጽሐፍ እንደሚናገረው፥ እግዚአብሔር በሰብአውያን ፍጡራኑ መራራ ክፋት ምክንያት ከልቡ አዝኖ ነበር። የቃል ኪዳን ሙሽራው፥ ሕዝበ እስራኤል፥ ፊቷን አዙራ ጥላው ስትኼድ በጽኑ ማዘኑን እናነባለን። ደግሞም፥ አምላክ [መዋዕለ ሥጋዌው] በአካል ወደ ሕዝቡ ሲመጣ— ትርጕሙ ያ ካልኾነ የኢየሱስ ታሪክ ከንቱ ነው ማለት ነው—በወዳጁ የመቃብር ደጃፍ ላይ ቆሞ አልቅሷል። ቅዱስ ጳውሎስ፥ እኛ ራሳችን በፍጥረተ ዓለሙ ሕማም ውስጥ በመቃተት ላይ ባለንበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ “በመቃተት” ላይ እንደ ኾነ ይናገራል። ጥንታዊው ትምህርተ ሥላሴ፥ በኢየሱስ እንባ እና በመንፈስ ቅዱስ መቃተት ውስጥ አሐዱ አምላክን እንድናውቅ ያስተምረናል።
እንግዲያስ፥ እየኾነ ያለውን ነገር ምንነትና ምክንያት አብራርቶ ለማስረዳት መቻል የክርስቲያናዊ ጥሪ አካል አይደለም። በርግጥስ፥ ለማስረዳት አለመቻል በምትኩ ደግሞ ለማልቀስ መቻል የክርስቲያናዊ ጥሪያችን አካል ነው። ራሳችንን አግልለን ባለንበት ጊዜ እንኳ፥ ቅዱሱ መንፈስ በእኛ ውስጥ ኾኖ ሲቃትት፥ የእግዚአብሔር መገኘትና ፈዋሽ ፍቅሩ ያረበበብን ንዑሳን ቅዱሳን ማኅደራት እንኾንለታለን። ከዚያም ውስጥ፥ ዐዳዲስ የመቻል ዕድሎች፥ ዐዳዲስ የደግነት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች፥ ዐዲስ ሳይንሳዊ ዕውቀት፥ ዐዲስ ብሩሕ ተስፋ ተገልጠው ሊወጡ ይችላሉ። ለመሪዎቻችንም ዐዲስ ጥበብ? [ሊገለጥ ይችላል።] እንግዲያስ፥ የተሻለው ሐሳብ ይህ ይመስለኛል።

Read 2723 times