Saturday, 11 April 2020 15:23

“ቅንዝንዝንና የቀን ጐባጣን ስቀህ አሳልፈው ሲያምርህ ሰው መሆን”

Written by 
Rate this item
(10 votes)

 ሻም/አፈወርቅ ዮሐንስ
አንድ ንጉሥ ሶስት ልጆች አሉት፡፡ ከጊዜ በኋላ ዕድሜው እየገፋ መጣና መንግሥቱን ለማንኛው ልጁ እንደሚያወርስ ሲያሳስበው ቆይቶ፣ በመጨረሻ አንድ ዘዴ ይመጣለታል፡፡ ይኸውም፡-
ሦስቱንም ልጆቹን ይጠራና፤
“ልጆቼ፤ እንደምታዩት ዕድሜዬ
እየገፋ፤ የመገነዣ ክር እየተራሰ፣
መቃብሬ እየተማሰ ነው፡፡ ሰፊ ግዛት፣ ሀብትና መንግሥት አለኝ፡፡ ይህንን ለአንዳችሁ ለማውረስ ዘዴ ስሻ ቆይቼ አንድ መላ አገኘሁ፡- ፈተና ልሰጣችሁ ነው” አላቸውና በቤተ መንግሥቱ ካሉት ክፍሎች ሁሉ በጣም ሰፊ ወደሆነው ክፍል ይወስዳቸዋል፡፡ ከዚያም፤
“ይሄውላችሁ ይሄንን ባዶ ክፍል በጣም ርካሽ በሆነ ዋጋ በምትገዙት ዕቃ እንድትሞሉት እፈልጋለሁ፡፡ በዚህ መሠረት በርካሽ ዋጋ ክፍሉን ለሞላ ልጅ ሀብቴን ሁሉ አወርሰዋለሁ፡፡ ለሦስት ቀን አስባችሁበት ተመለሱ” ብሎ አሰናበታቸው፡፡
በሦስተኛው ቀን ባላቸው ቦታና ሰዓት ተመለሱ፡፡
የመጀመሪያው ልጅ:- በርካሽ ዋጋ ጭድ ገዝቶ መጣና ቤቱን ሞላው፡፡
ሁለተኛው ልጅ:- በአገሩ ገበያ ርካሽ በሆነ ዋጋ ጥጥ ገዝቶ መጣና ሞላው፡፡
ሦስተኛው ልጅ ግን:-
አንዲት ሻማ ብቻ ገዝቶ አመጣና ለንጉሡ ሰጠ፡፡
ንጉሡም ወደ ክፍሉ ወስዶ ሻማውን አበራው፡፡
የሻማው ብርሃን ክፍሉን ከአፍ እስከ ገደፉ ሞላው፡፡
ንጉሡም፤
“ሀብቴንና ዙፋኔን የማወርሰው ለዚህ ለብልሁ ልጄ ነው፡፡ ባልኩት መሠረት ለሦስተኛው ልጄ አስረክቤዋለሁ፤ ቅሬታ ያለው አለን?” ሲል ጠየቀ፡፡
ሁለቱ ወንድሞቹ ሳያንገራግሩ ውሳኔውን ተቀበሉ፡፡
ሶስተኛው ልጅ፡- “ከሁለቱ ወንድሞቼ ጋር እኩል እንድንካፈል ፍቀድልን” ብሎ አባቱን አስፈቅዶ እኩል እኩል ተካፈሉ፡፡
*   *   *
ልጆቹን እኩል የሚያይ፤ የማያበላልጥ አባት ምርጥ ሰው ነው፡፡ ሳይጣሉ፣ ሳይስገበገቡና እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ሳይባባሉ የሚግባቡ ወንድማማቾች የታደሉ ናቸው፡፡
ሀብት ሲያነሆልለው ወንድሞቹን የማይረሳ፣ ቀናና ብልህ የመጨረሻ ልጅ መኖሩ ለማንም ታላቅ ዕድል ነው! በተለይ እንደዛሬው ክፉ ክፉ የሚሸትት ዘመን ሲመጣ ትዕግሥቱን፣ ጥንካሬውንና አስተውሎቱን ይሰጠን ዘንድ ፀሎቱ አይለየን፡፡
ባለንበት ጊዜ ቀዳሚውና ለሁሉ የሚበጀው የሐኪም ምክር መስማት ነው! እንደ ሸንቁጤ ጊዜ የጋራ ስቃይና መከራ ወቅቱን ጠብቆ መጥቶብናል! የኮሮና አደጋን በጥንቃቄ ለማሸነፍ ግን እንችላለን፡፡ የኩፍኝንም ዘመን አልፈናል!
ለማንኛውም፤
“ተመስገን ይለዋል ሰው ባያሌው ታሞ
ካማረሩትማ ይጨምራል ደሞ!”
የሚለውን ምህላ ደጋግመን የምንልበት የፀሎትና የልመና ጊዜ ነው! ቀና ቀናውን መንገድ የምናይበት የምንተሳሰብበት ወቅት ነው፡፡ የምንመገበውን፣ የምንነካውን ሁሉ ተጨንቀንና ሰግተን የምናስተውልበት ሰዓት ነው!
“እከድ እከድዬ ነገር ተበላሸ
በሥጋ ገበያ ስልከሰከስ መሸ
የልባችንን የምናሰማበት፤ የምንፀልይበት፣ ልመናችንን የምናመጥቅበት፤ የግልም፣ የማህበራዊም ሱባዔን የምትሻበት ዘመን ነው፡፡ “ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጐረቤቱ አይኖርም” የሚለውን ለውጠን፤ እንደ ቤታችንም እንደጐረቤታችንም መኖር ማስፈለጉን በምናስተውልበትና አገራዊና ዓለማዊ ሥጋትን ያሰመርንበት ጊዜ መምጣቱን እነሆ ልብ ብለናል፡፡
“ሳጥኑን ከፈትኩት ብለህ የምትኮራው
ውስጡ ሌላ ሳጥን ከሌለ ብቻ ነው!”
የሰንሰለታዊ ብልልት (Chain reaction)  ሥጋት በጉልህ እየታየ ነውና፣ ለኮሮና ቫይረስ የመከላከያ ክትባትም ሆነ የመደበኛው ፈውስ እስኪገኝ መጠንቀቅ ዋንኛው አቅጣጫ መሆኑን መገንዘብ ግዴታችን ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በተለይ እንደኛ ባለ የድህነት ወለል ላይ ባለ ሀገር፤ የኢኮኖሚ ድቀቱ ከናካቴው የሚያደቀን ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ስለሆነም ዋንኛ መመሪያችንን፤ ጽዳትን የሙጥኝ ማለት ወቅታዊ መርሃችን ሊሆን ይገባል (The order of the day እንዲሉ) ነገሩን እንጠንቀቀው ስንል፤ ዘናና ፈታ ብለን መሆን እንዳለብን ከጥልቅ ብስለት ጋር መጫን ብልህነት ነው፡፡ ለዚህም ነው፤
“ቅንዝንዝንና የቀን ጐባጣን
ስቀህ አሳልፈው ቢያምርህ ሰው መሆን” የሚለውን ቁም ነገር በመደጋገም የጥንቱን ፀሐፊ ሻምበል አፈወርቅን የምናስታውሰው፡፡
ምህረቱን ያምጣልን!

Read 13645 times