Saturday, 11 April 2020 15:22

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እጅጉን አሳሳቢ ነው!!

Written by  ዳ.ኢ
Rate this item
(1 Vote)

     የኮሮና ቫይረስ ከወደ ቻይና ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ በቅርበት ስከታተል ቆይቻለሁ:: ከቀን ወደ ቀን በሽታው እጅግ በሚያስደነግጥ  ፍጥነት የሰዎችን ህይወት እየቀጠፈና እየተዛመተ በመምጣት፣ የሰው ልጆች ትልቅ ስጋት ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በሽታዉም የሰው ሁሉ ጠላት በመሆን እጅጉን እያስገመገመን ይገኛል፡፡ በሽታው እያስከተለ ስላለው ተጓዳኝ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ በስፋት እየተተነተነ ነው፡፡ በሽታው ምህረት የለሽ ሲሆን ዓለምንም  እንደ ሰደድ እሳት እየፈጀ ይገኛል፡፡
በሀገራችንም ወቅቱንና የበሽታውን አደገኝነት በቅጡ ያገናዘበ ነው ባይባልም፣ አበረታች እርምጃዎችና ዝግጅቶችን እያየን ነው፡፡  በርግጥም እርምጃዎችንና ዝግጅቶችን በተለይ ደግሞ የበሽታውን ስርጭት ለማወቅና ለመግታት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ በመንግስትና በህዝብ ደረጃ ያለውን ዝግጅት በተግባር ማጤን ተገቢ ይሆናል፡፡ በሚዲያና በማህበራዊ የትስስር ገጾች ከሚዘዋወረው መረጃ ባለፈ በአካባቢያችን ያለውን እውነታ በማየትና ሁሉንም ቀዳዳ በመድፈን፣ በሽታውን ለመከላከልና ስርጭቱን ለመግታት በጋራ መስራት ይጠይቃል፡፡
በሀገራችን በመንግስት ደረጃ ያለው በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥርን ከበሽታው ባህሪና አለም ላይ ከሚነገረው አንፃር ስናይ፣ እጅጉን ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ደካማ የጤና ስርኣታችንና የሀገራዊ አቅም ውሱንነትን ከግንዛቤ ውስጥ በማሰገባት ካሰብነው፣ እነዚህን መረጃዎች በጥርጣሬ አለማየት በፍጹም የማይቻል ነው፡፡
እኔም በግሌ በአካባቢዬ ከምሰማውና ከማየው ተነስቼ፣ በርግጥም መንግስት የሚላቸው ነገሮች በተለይ ደግሞ የበሽታው ምልክት የታየበትን ሰው በመለየት፤ ቀሳ በማውጣትና ምርመራ በማካሄድ የበሽታውን ማህበረሰባዊ ስርጭት ከመግታት አንፃር ያለውን ሁኔታ፣ የተወሰኑ ጤና ጣቢያዎችን መርጬ በማየትና ቃለ-መጠይቅ በማድረግ በጣም አጭር ጥናታዊ ዳሰሳ ለማድርግ ሞክሬያለው፡፡
ወደ ሶስት የሚሆኑ ጤና ጣቢዎችን ከአዲስ አበባ ለናሙና በመውሰድ ያገኘሁት መረጃ፣ እጅጉን አሳሳቢና በሚዲያና የምንሰማቸው ነገሮች መሬት ላይ አለመኖራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ በርግጥ የዳሰሳ ጥናቱ ሁሉን የሚወክል (representative) አለመሆኑንም እገነዘባለሁ፡፡ በየዕለቱ እንደምንሰማው ከፈደራል እስከ ክልል ታችኛው እርከን ድረስ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገረን ሰንብቷል፡፡ በተለይ ደግሞ በጤና ተቋማት፡፡ እኔም በዋናነት ወደ ጤና ተቋማት የሄድኩበት ምክኒያት ሰዎች በመጀመሪያ የሚጎበኙትና ለአብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ በመሆኑ ነው:: በነዚህ ተቋማት በሽታውን በተመለከተ ስላለው ዝግጅትና እያጋጠማቸው ስላሉ ነገሮች አሳጥሬ እንደሚከተለው አቅርቤያለሁ፡፡
የበሽታው ምልክት የሚታይባቸው ታካሚዎችን በተመለከተ
የበሽታው ምልክት የሚታይባቸው ሰዎች፣ በሀገር ደረጃ በተገለጹ ስልክ ቁጥሮች በመደወል ተገቢውን አገልግሎት እንደሚያገኙ መገለጹ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በጤና ተቋማት ከበሽታው ጋር በተያያዘም የመለየትና የማሳወቅ ስራ እንደሚሰራ ተቀምጧል፡፡ በዚህም መነሻ በተለያየ ምክኒያት ወደ ጤና ጣቢያ የሚሄዱ ታካሚዎች ቅድመ ምርመራና ተያያዥ የቫይረሱ ምልክቶችን የመለየት ስራ እንደሚሰራ ለማየት ተችሏል፡፡ ሆኖም ግን ከበሽታው ባህሪ አንፃር ምርመራ ከማድረግና ቀሳ ከማውጣት ጋር በተያያዘ እጅግ አደገኛና ሀላፊነት የጎደላቸው የሚመስሉ ሁኔታዎች ተስተውለዋል፡፡ ይህን በተመለከተ ከጤና ጣቢያዎች የተገኙ አራት  ኬዞች እንደሚከተለው ቀርበዋል፤
“አንድ የ17 ዓመት ልጅ ከ አባቱ ጋር በጠና ታሞ በአቅራቢያው ወደ ሚገኝ ጤና ጣቢያ ይመጣል፡፡ የህክምና ባለሙያዎች ኣስፈላጊውን ቅድመ ምርመራ ሲያደርጉ ልጁ የኮሮና ቫይረስ በሽታ ዋና ዋና ምልክቶችን ማለትም ከፍተኛ ሙቀት (39)፣ ከባድ የመተንፈስ ችግርና ደረቅ ሳል እንዳለበት ያረጋግጣሉ፡፡ የጤና ባለሙያዎችም በክፍለ ከተማ ላለው አካል እንዲሁም በተገለጸው ስልክ ቁጥር ሲደውሉ እዛው ተጨማሪ ምርመራ ይደረግለት የሚል ትዕዛዝ ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህም መሰረት ተጨማሪ ምርመራ እንዲያደርጉ አባትና ልጁ ሲጠየቁ ገንዘብ የለንም የሚል ምላሽ በመስጠታቸው ምንም ሳይደረግላቸው ወደ ቤታቸው ተመለሱ“ (27 ዓመት፤ ነርስ)
“አንድ ከጅቡቲ በቅርብ ቀን የመጣ ታካሚ ወደ ጤና ጣቢያ በመጣበት ጊዜ ተገቢውን ቅድመ ምርመራ በማድረግ፣ በግለሰቡም ላይ በጣም አጠራጣሪ ምልክቶችን ማለትም ከፍተኛ ሙቀትና ራስ ምታት እንዲሁም ድካም ስላየንና በተጨማሪም ከጉዞ ስለተመለሰ ደውለን ስናሳውቃቸው ቤቱ ሄዶ እረፍት ያድርግ የሚል መልስ ነበር የተሰጠን፡፡ በመሆኑም ምንም ማድረግ ስላልተቻለ ወደ ቤቱ ተመልሷል፡፡ በጣም የሚገርመው ግለሰቡ ላይ ያየነው ሁኔታ እጅግ የሚያስፈራ በመሆኑ በወቅቱ በግቢ ውስጥ የነበሩ ታካሚዎች ተደነባብረው ከግቢ ሲወጡ ነበር፡፡ እንደዚህ ያሉ ኬዞች በተገቢው ሁኔታ መያዝና አስፈላጊውን ቀሳ ማውጣት ካልተቻለ፣ ስለ በሽታውና ስርጭቱ እርግጠኛ ሆኖ  መግለጫ መስጠት የይስሙላ ይሆናል፡፡ አሁን አሁንማ እኛም መደወሉን ወደ መተው እየሄድን ነው፡፡“
“ አንድ ወጣት ልጅ ወደ ጤና ጣቢያችን ሲመጣ በተደረገለት ምርመራ ከፍተኛ ትኩሳትና ደረቅ ሳል እንዳለበት ይረጋገጣል:: ይህም ሁኔታ ቀጥታ ከኮሮና ምልክቶች ዋናዎቹ ስለነበረ ማድረግ የነበረብን ቀጥታ ወደ 8335 መደወል ነበር፡፡ ነገር ግን የተሰጠን ምላሽ ቤቱ ሄዶ እንዲያርፍ ንገሩት የሚል ነበር፡፡ አሁን ላይ ስለ ልጁ የጤና ሁኔታ የምናውቀው ነገር የለም፡፡“
ከጤና ባለሙያዎች ምላሽ እንደምንረዳው፤ ሁኔታው በጣም አደገኛና በፍጹም ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው:: ምክኒያቱም ዋና ዋና የበሽታው ምልክት የሚታይባቸው ሰዎች ቢቻል ምርመራ፣ ካልሆነ ደግሞ ቀሳ በማውጣት ክትትል ማድረግ፣ አማራጭ የሌለውና ከበሽታው መሰረታዊ ባህሪ አንፃር ግዴታ ጭምር ነው:: ግን የተደረገው ነገር ሀላፊነት የጎደለውና በሽታውም እንዲስፋፋ ትልቅ ምክኒያት ሊሆን የሚችል ነው፡፡ በሽታውን ልዩ የሚያደርጉ ምልክቶች የሚታይባቸውን ሰዎች እንኳን ምርመራ አድርጎ ለማወቅ ያልቻለ የጤና ስርዓት፤ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት በእጅጉ እንደሚቸገር መገመት አያዳግትም፡፡ ስለ በሽታው በወቅቱ መረጃ ያለማቀበልና የሚሰጡ መረጃዎችም ተዓማኒነት የጎደላቸው በመሆናቸው ህብረተሰቡ አማራጭ የመረጃ ምንጮችን በመጠቀም ላይ ያለ ይመስላል፡፡ በማህበራዊ የትስስር ገጾች ላይ ያለው መረጃም መንግስት ከሚሰጠው መረጃ ጋር የሚጣረስ ሲሆን ይህም ህዝቡን ላልተፈለገ ውዥንብርና ስጋት እየዳረገ ይገኛል፡፡
የሰው ሀይልና የህክምና ቁሳቁሶች
በሽታውን ለመከላከልና ስርጭቱን ለመግታት ሊደረጉ ከሚገቡ ዝግጅቶች አንዱ የሰው ሀይል ነው፡፡ ይህም ለጤና ባለሙያዎች ተገቢውን ስልጠና በመስጠት በቂ ግንዛቤና እውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ ይጠይቃል:: በዚህ ረገድ በሶስቱም የጤና ጣቢያዎች በቂ ባይሆንም የተሰሩ ስራዎች እንዳሉ መረዳት ተችሏል፡፡ በጤና ጣቢያዎች ሁለት ሰዎች ተምረጠው ስልጠና ወስደው ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርገዋል፡፡ ስልጠና የወሰዱ ባለሙያዎችም ለቀሪ ሰራተኞች እንዲያካፍሉ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ሆኖም ግን ከጤና ባለሙያዎች እንደተረዳሁት፣ ሥልጠናው በጣም አጭር ስለነበር ጥልቅ አይደለም፡፡ መረጃ ልውውጥ እንጂ ስልጠና ለማለት ያስቸግራል፡፡ ይህን ጉዳይ አንዲት የ26 ዓመት ነርስ እንደሚከተለው ገልፃዋለች፤
“ስለ ቫይረሱ በሰማንበት ወቅት ከመስሪያ ቤታችን ሁለት ባለሙያዎች ወደ አዳማ በመሄድ ስልጠና ወስደው መጥተዋል:: እነሱም ሲመለሱ ለእኛ አጭር ገለፃ ነገር ለማስጠት ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን ይህ በቂ አይመስለኝም፤ ምክኒያቱም በሽታው አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙ የማናቃቸው ነገሮች አሉ፡፡ ቢያንስ እኛ የጤና ባለሙያዎች ከህብረተሰቡ የተሻለ እውቀት ሊኖረን ይገባል፡፡ ይህም ሁኔታ ስራችንን በራስ መተማመን እንዳንሰራ ያደርገናል፡፡“
በርግጥም በቂ ግንዛቤና የተሻለ እውቀት በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት መሰረታዊ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የጤና ባለሙያዎች በቂ እውቀት ጨብጠው ማህበረሰቡን ሊያገለግሉ ይገባል፡፡ ከዚህ ስራ ጎን ለጎን፣ የህክምና ቁሳቁሶችን ማዘጋጀትና ማቅረብ ሌላኛው እጅጉን አስፈላጊ ተግባር ነው፡፡ በጤና ጣቢያዎች በተደረገው ዳሰሳ ከፍተኛ ሊባል የሚችል እጥረት እንዳለ ለማረጋገጥ ተችሏል:: የጤና ባለሙያዎች ስራቸው በጣም ተጋላጭ ስለሚያደርጋቸው፣ የተለየ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን መሰረታዊ የሚባሉ ቁሳቁሶች ማስክ፤ ሳኒታይዘርና ጓንትን የመሳሰሉ በሽታውን ለመከላከል ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸውን  በአግባቡ እያገኙ እንዳልሆነ እስረድተዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ አንድ የጤና መኮንን እንደሚከተለው ገልፃዋለች፤
“በጣም የሚገርመው የሚሰጡን በሳምንት አንዴ ሁለት ማስክ ነው፡፡ በተጨማሪም የእጅ ማጽጃ ቁሳቁሶችም ችግር አለ፡፡ ለምሳሌ አልኮል አንድ ቦታ ይቀመጣል፤ በመሆኑም ለሁሉም ሰራተኛ ለአጠቃቀም  አይመችም፡፡ እንደሚታወቀው አንድ ማስክ የሚያገለግለው ለአራት ሰዓታት ብቻ ቢሆንም እኛ ግን ለአንድ ሳምንት ሁለት ማስክ እንድንጠቀም ሆኗል፡፡ እነዚህና መስል ችግሮች ስራችንን ያለ ምንም ስጋት እንዳንሰራ እንቅፋት ሆነውብናል፡፡ በዚያ ላይ ከፍተኛ የውሃ ችግር አለ፡፡“
ይህ ውስን ጥናታዊ ዳሰሳ እንደሚያመለክተው፤ እንኳን በሀገር ደረጃ ከበሽታው ጋር በተያያዘ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ማቅረብ ይቅርና በጤና ተቋማትም ማዳረስ አልተቻለም፡፡ ይህም በሽታውን ለመከላከልና ስርጭቱን ለመግታት ተግዳሮት ሆኖ እንደሚቀጥል ግልጽ ነው፡፡                
ይህ ውሱን ዳሰሳዊ ጥናት በሶስት የጤና ተቋማት ብቻ የተደረገ ቢሆንም፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለይ ደግሞ ከከተማ ወጣ ባሉ ቦታዎች ሁኔታው በእጅጉ የከፋ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያስቸግርም:: ስለሆነም ከተለያዩ የፖለቲካና ተያያዥ ተጽዕኖዎች ነፃ ሆኖ፣ ለህዝብ ደህንነት አስቀድሞ መስራትን ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ በግልጸኝነት ያለውን ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በየቀኑ እየሰጡ፣ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚያስፈልጉ ተገቢ ስራዎች ላይ መረባረብን ይጠይቃል፡፡ ትክክለኛ መረጃዎች ካልቀረቡ ግን ህዝብ እንዲዘናጋና በሽታውን ለመከላከል መደረግ ያለባቸውን ተግባራት በአትኩሮት እንዳይተገብር አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ የማህበረሰብ ስርጭቱን ለመግታት ከማስተማርና ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጎን ለጎን፣ እጅግ አጠራጣሪ ምልክቶችና የበሽታው ልዩ የሆኑ ምልክቶች የሚታይባቸውን ሰዎች መለየት፤ ቀሳ ማውጣትና ምርመራ ማካሄድ፤ አሁንም ተገቢና በዋናነት የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡

Read 3053 times