Saturday, 11 April 2020 14:07

ጠ/ሚኒስትሩና ፖለቲከኞች በኮሮና ዙሪያ ምን ተወያዩ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  * ኮሮና በፖለቲካ አስተሳሰባችን ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም
         * የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የአገር ህልውናን የሚፈታተን ጉዳይ ነው

ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ በሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ ሰሞኑን ውይይት አድርገዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩና የአገሪቱ ፖለቲከኞች ባደረጉት ውይይት ምን አንኳር ጉዳዮች ተነሱ? ምን ዓይነት የመፍትሄ ሐሳቦችስ ተሰነዘሩ? በውይይቱ ላይ ተሳታፊ ከነበሩት አንዱ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀ መንበር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፤ከአዲስ አድማሱ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በውይይቱ ዙሪያ ተከታዩን አጭር ቆይታ አድርገዋል፡፡
***
መንግሥት የኮሮናን ሥርጭት ለመግታት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዴት ይገመግሙታል?
መንግሥት ኮሮናን ለመዋጋት የአቅሙን ያህል እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገምግመናል፡፡ በአገር ደረጃ ያለውን ሁኔታ በጥብቅ እየተከታተለ መሆኑን ተረድተናል፡፡ እሁድ ዕለት ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር በነበረን ስብሰባም ይሄንን ነው የተገነዘብነው፡፡ በአገሪቱ ኮሮናን ለመግታት እየተደረገ ያለውን ጥረት አስመልክቶ ከጤና ሚኒስቴር የተብራራ ሪፖርት ቀርቦልናል፡፡ መንግሥት በሽታውን ለመከላከል ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ከሪፖርቱ መረዳት ችለናል፡፡ ችግሩ እንግዲህ የሁላችንም የጋራ ችግር ነው፡፡ ሁሉንም የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ የአገር አድን ጉዳይ ስለሆነ እኛም ከመንግሥት ጎን ተሰልፈን ስርጭቱን ለመግታት እንጥራለን፡፡ በሕዝቡ ዘንድ ግን ከፍተኛ መዘናጋት እንዳለ እንረዳለን፡፡ በሚገባው ልክ ምላሽ እየሰጠ አይደለም፡፡ በቤተ ክርስቲያን፣ በመስጊድ፣ በሱቆች፣ በሥራ አካባቢ፣ በትራንስፖርት አጠቃቀም ረገድ ችግሩን አቅሎ የማየት ሁኔታ ተስተውሏል፡፡ በዚህ ላይ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው ሁሉ ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው እናምናለን፡፡ መንግሥትም በዚህ በኩል ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለበት  ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ተነጋግረናል፡፡ ምክረ ሀሳቦችም ቀርበዋል፡፡
ምን አይነት ምክረ ሃሳቦች ቀረቡ? እርስዎስ ምን ተጨማሪ እርምጃ መወሰድ አለበት ይላሉ?
ይሄ ነገር ድንገተኛ ክስተት ስለሆነ አዲስ የግብረ መልስ አደረጃጀት ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ተጨማሪ ኮሚቴዎችን በማዋቀር ሁለገብና የተቀናጁ እርምጃዎች መውሰድ አለበት፡፡ የወጡ መመሪያዎች ተፈፃሚነት ላይም ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ይኖርበታል፡፡ መንግሥት እስከ አሁን ለወቅቱ አስፈላጊ የሆነውን ሁሉ እያደረገ እንደሆነ በግሌ አምናለሁ፡፡ በቀጣይ ችግሩ የሚሰፋ ከሆነ ግን ተጨማሪ አለማቀፍ ተሞክሮዎችን ያማከሉ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል፡፡
ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ባደረጋችሁት ውይይት ሌሎች ምን ጉዳዮች ተነሱ?
በኮሮና ጉዳይ ላይ ብቻ ነው የመከርነው፡፡ ለበሽታው መንግሥት እየሰጠ ያለው ምላሽ ላይ ነው ሰፊ ውይይት ያደረግነው፡፡ ተሳታፊዎችም ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ሕዝቡ የወረርሽኙን አደገኛነት በትክክል ተገንዝቦ፣ ራሱን ከበሽታው እንዲጠብቅ መጠነ ሰፊና ቀጣይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ቅስቀሳዎች ማድረግ እንደሚገባ ምክረ ሀሳብ ቀርቧል፡፡ የሚታዩ ቸልተኝነቶች በፍጥነት እንዲታረሙ አስገዳጅ የሆኑ መመሪያዎችም  ጭምር መተግበር  እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡ ሕዝቡ ከጤና ጥበቃ የሚሰጡ መመሪያዎችን በትክክል እንዲተገብር ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚያስፈልግም በስፋት ተነጋግረናል፡፡
ከምርጫው መራዘም ጋር በተያያዘ የተነሱ ጉዳዮች ነበሩ?
በምርጫው መራዘም ጉዳይ ላይ ከምርጫ ቦርድ ጋር ተወያይተንበት ስለነበር አልተነሳም፡፡ አሁን ሙሉ ትኩረታችንን ማድረግ ያለብን ወረርሽኙን መግታት ላይ ነው፡፡ በዚህ ሰዓት ምርጫ መነጋገር አሁን ቅንጦት ነው፡፡ ስለዚህ አልተነጋገርንበትም፡፡ አሁን ዋና ጉዳያችን በሁላችንም ላይ የመጣው የኮሮና ወረርሽኝ ነው፡፡ ለሱ እንዴት ምላሽ እንስጥ የሚለው ነው መግባቢያችን ሊሆን የሚገባው፡፡ ይሄን ከቋጨን በኋላ ለምርጫው እንደርስበታለን፡፡ በውይይታችንም ያልነው ይሄንኑ ነው፡፡
ኮሮናን ከመከላከል ባሻገር አገር እንዴት ሥርዓትና ሕግን በተከተለ መልኩ ትቀጥል የሚለውም አሳሳቢ ነው ብለው የሚሞግቱ ወገኖች አሉ፡፡  እርስዎ ምን ይላሉ?
በእውነቱ ማንም ሰው ይሄ ጉዳይ ያሳስበዋል፡፡ ለኔ ግን አሁን ስለ ምርጫ ማሰብ በሁለተኛ ደረጃ የማስቀምጠው እንጂ ቅድሚያ የምሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ አሁን ማሰብ ያለብን ስለ ህልውናችን ነው፡፡ ወረርሽኙን እንዴት እንግታው የሚለው ላይ ነው ማተኮር የሚገባን፡፡ ይሄም እኮ የአገርን ሕልውና የሚፈታተን ጉዳይ ነው። በአግባቡ ካልተያዘ በጣም አደገኛ ነገር ነው፡፡ ጉዳዩ በምክክር በመናበብ ካልተያዘ መስመሩን ሊስት ይችላል፡፡ ለዚህ ነው አሁን ሁሉም ፖለቲካውን ወደ ጐን አስቀምጦ፣ ወረርሽኙን መከላከል ላይ ሙሉ ትኩረቱን እንዲያደርግ የሚፈለገው፡፡ ቀጣይ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ ደግሞ ከዚህ ወረርሽኝ ከተላቀቅን በኋላ፣ በወቅቱ በሚኖሩ ተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ ተመስርተን ማከናወን እንችላለን፡፡ ምናልባት ኮሮና ቫይረስን በምንዋጋበት ጊዜ ሁላችንም ስለ መጪው ፖለቲካችን ማሰባችን አይቀርም፡፡ ማሰባችን ጥሩና መልካም ነገር አለው፡፡ ኮሮና መምጣቱ ራሱ በፖለቲካ አስተሳሰባችን ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ቢያንስ አሁን ስለ ሰውነታችን ማሰብ ጀምረናል፡፡ እንደ ሰው ስለ መደጋገፍ፣ በአንድነት ስለ መቆም እያሰብን ነው፡፡ ከዚህ ወረርሽኝ ስንላቀቅ ለየት ያሉ አካሄዶችን ተከትለን፣ ፖለቲካችንን በአዲስ መንፈስ እንቃኘዋለን የሚል ተስፋ አለኝ፡፡
ከኮሮና በኋላ ፖለቲካችን በአዲስ መንፈስ የሚቃኘው እንዴት ነው?
ይሄ ቫይረስ ሰከን ብለን ስለ ሰውና ሰውነት እንድናስብ እያደረገን ነው፡፡ በብሔር ተሰፍቶ የነበረ አመለካከት ወደ ሰውነት ከፍ እንዲል አስችሏል፡፡ ስለ ሰው፣ ስለ ሕብረተሰብ፣ ስለ ዓለም በሰፊው እንድናስብ አድርጎናል፡፡ ስለ መደጋገፍ፣ ስለ መተባበር፣ ክፉ ጊዜን በጋራ ስለ መሻገር እንድናስብ አድርጎናል፡፡ ‹‹እኔ ትግራዋይ ነኝ››፣ ‹‹እኔ አማራ ነኝ››፣ ‹‹እኔ ኦሮሞ ነኝ››፣ ‹‹እኔ ጉራጌ ነኝ›› የሚሉ የክፍፍል አስተሳሰቦችን አቁመናል፡፡ ይሄ በጎ ነገር ነው፡፡ ለቀጣይ የአገራችን ማህበረሰባዊ ውቅርም አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው የሚሆነው፡፡ ወደ ሰውነት ከፍ ብለን ነገሮችን ወደፊት እንድናይ ይረዳናል ብዬ አምናለሁ፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ እንዴት መከላከል ይቻላል ይላሉ?
እርግጥ ችግሩ እንኳን በኛ በሃያላን አገራት ላይም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያስከተለ ነው፡፡ እንደዚያ አይነት ቀውስ መከተሉ አይቀርም፡፡ ነገር ግን መንግሥትም ይሄን አስቀድሞ አስቦ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን አይተናል፡፡ ባንኮች አካባቢ በውጪ ንግድና በመሳሰሉት ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች አሉ፡፡ የኢኮኖሚ ተቋማት ይበልጥ ጉዳት መቀነስ ላይ ማተኮር አለባቸው እንጂ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት አይቻልም፡፡ መንግሥትም በዚህ ረገድ ብዙ ውይይቶችን እያደረገና መፍትሄዎችን እያፈላለገ መሆኑን እረዳለሁ፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ፋይዳው ምንድን ነው?
ይሄ ከዚህ በፊት ከነበረው አካሄድ አንዱ የተለወጠ ጉዳይ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ የሚያደርጉት ነገር በእውነቱ በመካከላችን የሐሳብ መቀራረብን እየፈጠረ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ቁም ነገሩ ደግሞ የሐሳብ መቀራረብ መፈጠሩ ላይ ነው፡፡ ለፖለቲካችን ዋናው ጠቃሚው ነገር በሐሳብ መቀራረቡ ነው፡፡ በሐሳብ ስንቀራረብ ነው አገር እንዴት ትቀጥል የሚለውን ሁላችንንም ወደሚያግባባ ምዕራፍ ማስኬድ የምንችለው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ይሄን አጋጣሚ ለዚህ በጎ ነገር እየተጠቀሙበት ያለ ይመስለኛል፡፡ ተከታታይ ስብሰባዎች እያካሄዱ መሆኑን እሰማለሁ፡፡ ስለዚህ በአገር ደረጃ የአስተሳሰብ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አካሄድ ነው፡፡ ለብዙ ዘመናት የናፈቀንን የጋራ ችግርን በጋራ የመፍታት አካሄድ ጠ/ሚኒስትሩ እውን እያደረጉት ያለ ይመስለኛል፡፡
በመጨረሻ  ለሕብረተሰቡ በበሽታው ዙሪያ መልዕክት ያስተላልፉልን---
ሕብረተሰባችን ራሱን ከዚህ ወረርሽኝ እየጠበቀ፣ የጤና ባለሙያዎችና መንግሥት በሚያስቀምጡት አቅጣጫ መሰረት፣ አጋጣሚውን ለበጎ ነገር መጠቀም አለበት፡፡ እየተፈጠሩ ያሉ የአስተሳሰብ መቀራረቦችን ማዳበር ማበልፀግ አለበት፡፡ ሕብረተሰባችን ይሄ ቀን እስኪያልፍ በተረጋጋ መልኩ መመሪያዎችን እየተከተለ፣ ራሱን ከዚህ አስከፊ ወረርሽኝ እንዲጠብቅ መልዕክቴን አቀርባለሁ፡፡  


Read 1853 times