Saturday, 11 April 2020 14:06

‹‹ከዱባይና ሳዑዲ አረቢያ በርካታ ኢትዮጵያውያን መባረራቸው ስጋት ላይ ጥሎናል››

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(20 votes)

  - በ2 ሳምንት ውስጥ ከሳውዲ የተባረሩ ከ3ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ይገባሉ
     - እስካሁን ቫይረሱ ከተገኘባቸው ግማሽ ያህሉ ከዱባይ የገቡ ናቸው
     - ትናንት በኮሮና ቫይረስ 1 ተጨማሪ ሰው ሲሞት፤ ከፍተኛው በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ተመዝግቧል
              
              ከዱባይና ከሳኡዲ አረቢያ፣ በርካታ ሺ ኢትዮጵያውያን ለበሽታ በሚያጋልጥ ሁኔታ እየተባረሩ መሆናቸው፤ ከባድ ስጋት ላይ ጥሎናል ሲሉ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ከበደ ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
ከሳዑዲ በሁለት ሳምንት ውስጥ ወደ አገራቸው የሚገቡ ከ3 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን፣ ለበሽታ በሚያጋልጥ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ናቸው ሲሉ  ሁኔታው ክፉኛ እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል - ዶ/ር ሊያ፡፡ ያለ ምንም የጤና ምርመራ የሚመጡ መሆናቸው ደግሞ አደጋውን እንደሚያከብደው ሚኒስትሯ ገልፀዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በጣም ከፍተኛ ጥንቃቄና ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትሯ  ተለይ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት ከሳውድ አረቢያ ወደ አገራቸው የሚመለሱት ከ3ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ምንም አይነት የጤና ምርመራ ሳያደርግላቸው የሚመለሱና የቆይታቸው ጊዜም ጥንቃቄ የተሞላበት ባለመሆኑ ትልቅ ስጋት ላይ ጥሎናል ብለዋል፡፡ እነዚህን ተመላሽ ኢትዮጵያውያን ለአስራ አራት ቀናት ለይቶ ማቆየት የሚቻልባቸውን ቦታዎች የማዘጋጀቱ ሥራ መጠናቀቁን የገለፁት ዶ/ር ሊያ፤ ተመላሽ ዜጎቹ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንድ ክፍል ለአንድ ሰው ብቻ እንዲሆን ለማድረግና የምግብ አቅርቦትና የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንዲቆዩ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ የጤና ሚኒስቴር፣ ከሰላምና ከሳይንስ ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመተባበር እንደሚሰራም ዶ/ር ሊያ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሯ ትናንት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው ምርመራ ከተደረገላቸው 442 ሰዎች መካከል ዘጠኝ ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ እስካሁን በአጠቃላይ 3232 ሰዎች ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን 65 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ከእነዚህ መካከል የትላንቱን ጨምሮ በበሽታው ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ ሁለት ጃፓናውያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ አንድ ታማሚ በጽኑ ሕክምና ክፍል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን አራት ያህሉ ደግሞ ከበሽታው ማገገማቸው ተገልጿል፡፡ በቫይረሱ መያዛቸው ከተገለፀው 65 ሰዎች መካከል 48 ያህሉ የጉዞ ታሪክ ያላቸው ሲሆን ከእነዚህ መካከል ደግሞ 27 የሚሆኑት ዱባይን አልፈው ወይም ከዱባይ ተነስተው የመጡ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ገቢ መንገደኞቹ ቆይታቸው በዱባይ የነበረ ይሁን ወይም በዱባይ አየር መንገድ ትራንዚት አድርገው የገቡ ይሁኑ ለጊዜው የተገለፀ ነገር ባይኖርም፤ በርካታ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች የጉዞ ታሪክ ዱባይ ላይ ያተኮረ መሆኑ ግራ መጋባትን ፈጥሯል፡፡ በዚሁ መሰረትም በተለይ ከዱባይ የሚገቡ መንገደኞችን ለብቻ ለይቶ ለማቆየት የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ ስለመታሰቡ ለጤና ሚኒስትሯ ለዶ/ር ሊያ ታደሰ ጥያቄ አቅርበን፤ የተለየ ማቆያ ለዱባይ ገቢ መንገደኞች ለማድረግ አለመታሰቡንና ቀደም ሲል በተዘጋጁት ለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉ ገቢ መንገደኞችን የቅርብ ክትትል እንዲሁም አስተማማኝ ጥበቃና ምርመራ በማድረግ፣ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ጥረት እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡
በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ከሳውዲ ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁትን ከ3ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ለመቀበል እየተደረገ ያለው ዝግጅት፣ ምናልባት ቫይረሱ የሚገኝባቸው ዜጎች ቢኖሩ እርስ በርስም  ሆነ ከቤተሰቦቻቸውና ከማህበረሰቡ ጋር በመገናኘት የበሽታውን ስርጭት እንዳያስፋፋ ለማድረግ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ከሳውዲ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ3ሺ ሊበልጥ እንደሚችል ያመለከቱት የጤና ሚኒስትሯ፤ እነዚህን ኢትዮጵያውያን በየዕለቱ 200 ያህል እንዲገቡ በማድረግ በመጪዎቹ 2 ሳምንታት ውስጥ ተጠናቀው የሚገቡ ይሆናል ብለዋል፡፡   


Read 19795 times