Saturday, 11 April 2020 13:39

የቫይረሱን ስርጭት መግታት ካልተቻለ የሚያስከፍለን ዋጋ እጅግ ከፍተኛ ነው ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

  - አገሪቱ በአጠቃላይ ያላት የመተንፈሻ መሣሪያ ከ300 አይበልጥም
   - ከ6 ፅኑ ታማሚዎች አንዱን ያለ መተንፈሻ መሣሪያ ህይወቱን ማትረፍ አይቻልም
            
               የኮረና ቫይረስን ስርጭት መግታት ካልተቻለና ህብረተሰቡ በቫይረሱ ላለመያዝ ከፍተኛ ጥንቃቄ ካላደረገ በስተቀር እጅግ ከፍተኛ የሆነ አደጋ እንደሚደርስ የተጠቆመ ሲሆን በቫይረሱ ተይዘው ለጽኑ ህመም የሚጋለጡ ሰዎችን ህይወት የማትረፉ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በአግባቡ እንዳልተረዳውም የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
የህብረተሰብ ጤና ሃኪሙ ዶ/ር ግርማ ሰለሞን እንደሚናገሩት፤ በሽታው የተለያዩ ደረጃዎች ያሉት ሲሆን ለጽኑ ህመም የሚዳረጉትን ህሙማን ለማዳን እጅግ መሠረታዊ የሆነው የመተንፈሻ መሣሪያ የሌለን በመሆኑ ያለን አማራጭ፣ በሽታውን በመከላከል ሥራ ላይ ተግተን መሰራት ብቻ ነው ብለዋል፡፡
በቫይረሱ ከሚያዙ ሰዎች 80 በመቶ ያህሉ በቀላል ህክምና ሊያገግሙ የሚችሉ ናቸው ያሉት ዶ/ር ግርማ፤ ከ5-6 በመቶ ያህሉ ግን ለጽኑ ህመም የሚጋለጡና አብዛኛዎቹም የመተንፈሻ መሣሪያ የሚያስፈልጋቸው ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል፡፡ ከእነዚሁ ስድስት ጽኑ ህሙማን መካከል ቢያንስ አንደኛውን ያለመተንፈሻ መሣሪያ ህይወቱን ለማትረፍ እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በአጠቃላይ ያሉት የመተንፈሻ መሣሪያዎች ቁጥር ከ300 የማይበልጥ እንደሆነም ዶ/ር ግርማ ተናግረዋል፡፡
የመተንፈሻ መሣሪያ እንኳንስ እንደ ኢትዮጵያ ላሉና የጤና ሥርዓታቸው ደካማ ለሆኑ አገራት ቀርቶ ለአለም ታላላቅ አገራትም ፈተና ደቅኖባቸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን እንዳጠቃ ለሚነገርለት የኮረና ቫይረስ ህሙማን እጅጉ አስፈላጊ የሆነው የመተንፈሻ መሣሪያ መርጃ እጥረት የአለም አገራትን ሁሉ መፈተን ብቻ ሳይሆን የሕይወትም ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ ልዕለ ሃያሏ አሜሪካ ከ960ሺ በላይ የመተንፈሻ መረጃ መሣሪያዎች እንደሚይስፈልጓት ‹‹ሶሳይቲ ኢፍ ክሪቲካል ኬር ሜድስን›› ይፋ ቢያደርግም በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ያላት አጠቃላይ የመተንፈሻ መሣሪያ ከ30ሺ ያነሰ ነው ተብሏል፡፡
የእንግሊዙ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት አገሪቱ ከገጠማት የጤና አደጋ አንፃር 30ሺ ያህል የመተንፈሻ መሣሪያ እንደሚያስፈልገውና በእጁ ላይ ያለው ግን 8175 ብቻ እንደሆነ አስታውቋል::
ህንድ በበኩሏ፤ 48ሺ የፈተንፈሻ መሣሪያዎች እንዳላት ብትገልጽም ከዚህ ውስጥ ምን ያህሉ በትክክል እንደሚሰራ አላውቅም ብላለች፡፡
የቫይረሱን ስርጭት ለመግታትና አገራት ዜጐቻቸው ምን ያህል በቫይረሱ እንደተያዙ ለማወቅ የሚያደርጉት ምርመራም ፈታኝ ሁኔታዎች እየገጠሙት  ነው፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች መርምሮ የቫይረሱን ስርጭት መጠን ማወቅ እንደሚነገረው ቀላል አይደለም፡፡
በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች የተሟላ ቤተ ሙከራና ትክክለኛው የላብራቶሪ ሪኤፍንት ሊሟላለት ይገባል፡፡
ከዓለም አገራት እስካሁን በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎቿ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ በማድረግ በቫይረሱ ክፉኛ የተጠቃችው አገረ አሜሪካ ቀዳሚነቱን ይዛለች፡፡ ብትብጠለጠልም እስካሁን1.3 ሚሊዮን ሰዎችን መርምራለች:: በቀን የመመርመር አቅማም ከመቶ ሺ ከፍ ይላል:: ወረርሺኙን ተከትሎ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ላይ ያዋለችውና በህክምናና ተያያዥ ኢንዱስትሪዎቿ ዕድገት የምትታወቀው ጀርመን እስካሁን ከአንድ ማሊዮን በላይ ሰዎችን መርምራለች፡፡ እስካሁን አገሪቱ ለዜጎቿ በቂ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ አላደረገችም ተብላ በገዛ ሚዲያዎቿ ክፉኛ ወቅትም በሳምንት 500ሺ ሰዎችን የመመርመር አቅም ላይ ደርሳለች፡፡
በርካታ ዜጐቿን በቫይረሱ የተነጠቀችው ጣሊያንም ከጠቅላላ ሕዝቧ ከግማሽ በላይ ዜጐቿን መርምራለች፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ፤ የመጀመሪያውን የቫይረሱን ተጠቂ ሪፖርት ካደረገችበት ከመጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ 3232 የሚሆኑ ሰዎችን የመረመረ ሲሆን ትላንት ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ 65ቱ በቫይረሱ መያዛቸውን አረጋግጣለች፡፡ የአገራቱ የመመርመር አቅም የጤና ዘርፍ ዝግጅትና አገራቱ ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት ያላቸውን አቅም የሚያመለክት እንደሆነ ይነገራል፡፡    Read 10498 times