Saturday, 11 April 2020 13:19

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሰጠ ምላሽ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ባለፈው ሳምንት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ቅጽ 21 ቁጥር 1055 ህትመት ላይ የአየር መንገድ ሠራተኛ የመቀነስ እርምጃ ተቃውሞ ገጥሞታል” በሚል ርዕስ ለተስተናገደው ዘገባ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሰጠ ምላሽ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

          “ሠራተኞች እረፍት እንዲወጡ ተደረገ እንጂ አልተቀነሱም”
በመጀመሪያ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ውስጥ አንጋፋውና ትልቁ የሰራተኛው ማህበር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሰራተኛ ማህበር የሚባል አብዛኛውን ሰራተኛ ያቀፈ ማህበር እንዳለ በዚህ አጋጣሚ ለአንባቢዎቻችሁ እንድታሳውቁልን በአክብሮት እንጠይቃለን።
አሁን በደርጅቱ ውስጥ ያለው የሰራተኛ ጉዳይ ከዚሁ ከቀዳማዊ መሰረታዊ የሰራተኛ ማህበር ጋር አብረን እየሰራን እንገኛለን። በመሆኑም ትክክለኛውንና በድርጅቱ ያለውን ሁኔታ ከዚሁ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሰራተኛ ማህበር ሊቀመንበር ጠይቃችሁ መረዳት የምትችሉ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።
ከላይ የጠቀስነው እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬ አለማችን ከአንድ ሶስተኛ (1/3) በላይ የሚሆን ህዝብ ከቤቱ እንዳይወጣ አስሮ የያዘ በታሪክ ትልቁ ወረርሽኝ ባስከተለው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ብዙ አየር መንገዶች ኪሳራ ውስጥ ስለሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞቻችውን ከስራ በማሰናበት ላይ ይገኛሉ። ለዚህም የኤምሬትስ አየር መንገድን እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።  
በዚሁ የአለም ኢኮኖሚ ቀውስ ክፉኛ የተጠቃው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብዙ የወጪ ቅነሳ ስራዎችን እያከናወነ ቢሆንም አንድም ቋሚ ሰራተኛ ያልቀነሰ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።  
ከ87 በላይ የሚሆኑ ዓለምአቀፍ መዳረሻዎቻችን ስለተዘጉ እና ከ80 በላይ የሚሆኑ አውሮፕላኖቻችን ስራ ስላቆሙ የተወሰኑ ሰራተኞች የተጠራቀመ የአመት እረፍታቸውን ደሞዝ እየተከፈላቸው እንዲወስዱ አድርገናል።  
ይህም የሆነው ስራ ባለመኖሩ ምክንያት ሳይሆን የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ማህበራዊ ፈቀቅታን
(Social Distancing) ለመጠበቅ በግቢ ውስጥ በርከት ያለ ሰራተኛ ስላለና  አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ
ለሰራተኛ ጤንነትም በማሰብ ጭምር ነው።
በዚህ አጋጣሚ በሰራተኛ አቅራቢ ድርጅቶች በኩል በጊዜያዊነት ሲሰሩ የነበሩ ሰራተኞች ለጊዜው
ከድርጅቱ ጋር በመነጋገር እቤት እንዲቆዩ ተደርጓል።  
ከዚህ ውጪ በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚወሩ ወሬዎች ፍፁም ሀሰት መሆናቸውን ለማሳወቅ
እንወዳለን።  
ስለውጪ ሰራተኞች የቀረበው መረጃም ሀሰት በመሆኑ እንዲስተካከል ስንል እየጠየቅን አየር መንገዱ ኢትዮጵያዊያንንም ሆነ የውጭ ሀገር ሰራተኞችን በረራ ሙሉ በሙሉ በሚጀምርበት ጊዜ ስለሚፈልጋቸው የአመት እረፍታቸውን እንዲጠቀሙ ብቻ ነው ያደረገው።  
ሁሉም ሰራተኞች የስራው አስፈላጊነት እየታየ እረፍት እንዲወጡ እየተደረገም ይገኛል።
ሰራተኞች ስራ በቀዘቀዘበት ወቅት የዓመት እረፍታቸውን እንዲወስዱ ማድረግ የትኛውንም የሀገራችን የአሰሪ እና ሰራተኛ ህግ የሚፃረር አይደለም።


Read 1358 times