Tuesday, 07 April 2020 21:19

‹‹ከተደማመጥንና ከተደጋገፍን ይህን ጊዜ እናልፈዋለን›› (ሰይፉ ፋንታሁን፤ ጋዜጠኛ)

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

ኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፍ ስጋት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በአገራችንን ቁጥሩ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ፣ ስጋቱም በዚያው ልክ እያደገ ነው የመጣው፡፡ ከዚህ አንጻር ሕዝቡ መንግሥት የሚያስተላልፈውን መልዕክትና ማስጠንቀቂያ እየተገበረ ነው ወይ ከተባለ፣ ዋናው እንደ መፍትሄ የተነገረው ከቤት አትውጡ ነው። ሙሉ ለሙሉ ከቤት አትውጡ የሚለው ትንሽ  ከባድ ነው፤ ምክንያቱም የዕለት ጉርስም ነገር አለና፡፡ ጠዋት ከቤቱ ሲወጣ ምሳው ምን እንደሆነ የማያውቅ ብዙ ሰው አለኮ! ለምሳሌ የእኛ ሥራ ቤት ውስጥ ሆኖ የሚሰራም ቢሆን ቤት ሆኖ መስራት የማይቻል በርካታ የስራ አይነት አለ፡፡ ከዚህ አንፃር፤ ሙሉ ለሙሉ ቤት ቁጭ በሉ ለማለት ይከብዳል። ይሄ ከኮሮና በፊት ሰውን በረሃብ መግደል እንዳይሆን በዋናነት መመከር ያለበትና እኛም የምናስተላልፈው “ሥራ ይሰራ ግን በመራራቅ፣ ንፅህና በመጠበቅና ከንክኪና ከመጨባበጥ በመታቀብ ይሁን” የሚል መልዕክት ነው፡፡ እርግጥ ነው ሌሎች አገራት በራቸውን ዘጋግተዋል፡፡ ነገር ግን እኛ ይህን ማድረግ አንችልም፡፡ ምክንያቱም እስኪ አስቢው… የ15 ቀን ወይም የ1 ወር ቀለብህን ይዘህ ግባ ቢባል፣ ምን ያህሉ ነው ይህን ማድረግ የሚችለው?
በፊት በደጉ ጊዜ ጤፍ ሲፈጭ አስታውሳለሁ፤ መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ የእኛ እናቶች ለ3 ወር የሚሆን ያስፈጫሉ፡፡ አሁን ግን ጊዜው እንደዛ አይደለም፡፡ ከዚህ ከዚህ አንፃር በራችንን ለመዝጋት ስለምንቸገር ዋናው ትኩረት መሆን ያለበት ሕዝቡ እንዲጠነቀቅ ማድረጉ ላይ ነው:: የሚችል ይግባ የማይችል ይንቀሳቀስ” ብንል እንኳን የአንዱ መግባት ለሌላው እንጀራ ማጣት ምክንያት የሚሆንበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡ ይሄ እንዳይሆን መንግሥትና በዙሪያው ያሉ ሰዎች መተጋገዝ ይኖርባቸዋል፡፡ በጎዳና ለሚኖሩ ልጆች አንድ ቦታ መፈለግ ይገባል፡፡ ለምሳሌ ሩዋንዳ የጎዳና ልጆቿን ስቴዲየም ውስጥ ከትታለች:: ጎረቤት ለጎረቤትም መረዳዳት አለበት፡፡ አሁን በድሬዳዋም በመቀሌም በሐረርም የቤት ኪራይ የሚተው ደጋግ ሰዎች ተፈጥረዋል:: ይሄ በሕንጻ አከራዮችም፣ ራሱ መንግሥት በሚያስተዳድራቸው የኪራይ ቤቶችም ኪራይ በመተው አርአያ መሆን ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት እንደነ ጣሊያን አቅም ባይኖረውም “ግዴለም ተጎድቼም ቢሆን ይሄ ቀን ይለፍ” ብሎ ኪራይ ቢተው፤ ሌላውም ይከተለዋል፡፡ በሕብረተሰቡም ዘንድ የሥነ ልቦና መረጋጋትና ብርታት ይፈጠርና ይሄ ክፉ ቀን ያልፋል:: ምክንያቱም ቤት ኪራይ ላሟላ ብሎ ስራ የሚወጣው እፎይታ ሲያገኝ ቤቱ ይውላል፡፡ የግል የቤት አከራይም ለጎረቤታቸው “ግዴለም ለአንድ ወር አትጨነቅ” ሲሉ፣ ያም የግለሰብ ተከራይ ቤት ውስጥ ሲቀመጥ ብዙው ሰው ቤት ይሆናል፡፡ ይሄም ቀን ያልፋል፡፡ ከተደማመጥን ከተረዳዳንና ከተጋገዝን እመኚኝ፤ ይሄ ክፉ ቀን መከራችንን ሳያረዝመው ያልፋል፡፡
እውነት ለመናገር ችግሩ ኢኮኖሚውን የሚፈትን፣ ማህበራዊ ቀውስን የሚፈጥር፣ ዝቅ ብለን ማለፍ ካልቻልን ትልቅ አደጋ ሊያደርስ የሚችል ወረርሽኝ ነው፡፡ እንኳን እኛ ደሃዎቹ የበለፀጉ አገራት ዋጋ እየከፈሉና እየተፈተኑ ነው ያሉት፡፡ እኔ አሁን ጠቅልዬ ቤቴ ገብቻለሁ፤ ስራ በስካይፒ ነው የምሰራው፡፡ ቤቴ ከልጆቼ ጋር ነው የማሳልፈው፡፡ ነገር ግን የኔ መጠንቀቅ ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ ሁሉም በየቤቱ እንዲህ የመሆን ደረጃ ላይ ካልደረሰ ለውጥ አይመጣም፡፡ እኛ አሁን ከቀይ መስቀል ተደውሎልን ስንዘዋወር፣ በተለይ መርካቶ ቦምብ ተራ፣ ጭድ ተራ ውስጥ ውስጡን ያሉት አካባቢዎች ላይ ሰው እንደ ቀድሞው መደበኛ ሕይወቱን ቀጥሏል፡፡ ሽሮ ሜዳ እንዲሁ አይነት ስሜት አለ፡፡
አሁን መጠነኛ ለውጥ አመጡ የሚባሉት መገናኛ፣ ሜክሲኮ፣ ቦሌ አይነት አካባቢዎች አሉ፡፡ አቅም ኖሮን ሁላችንም ቤት ብንገባ ነው ዋናው መፍትሄ ይሄን ማድረግ ስለማንችል እኛ ትላንት በሬዲዮ የቼክ ሪፐብሊክን ጥሩ ልምድ ተናግረናል፡፡ እነሱ ምንድነው ያደረጉት ቤት መቀመጥ ቁጥር አንድ መፍትሄ ነው፡፡ መውጣት የግድ ከሆነ ርቀት መጠበቅ ሁለተኛ ነው፤ ይህ ካልሆነ ሁሉም ሰው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ እንዲያደርግ ነው የወሰኑት:: ሁሉም ማስክ ካደረገ፤ እኔ ባስል ባስነጥስ ወደ ሌላው አላስተላልፍም፡፡ ሲኤንኤንም በስፋት እየመከረ የነበረው “ሰው ከወጣ ማስክ ያድርግ” እያለ ነው፡፡ እኛ ለዚህ ሁሉ ሚሊዮን ሕዝብ ማስክ ከየት እናመጣለን ነው ጥያቄው፡፡ መንግስት ልብስ ሰፊና ዲዛይነሮችን አደራጅቶ የሚሰፉት ጨርቅ በጤና ሚኒስቴር ደረጃ ወጥቶለት  በስፋት እየሰፉ እንዲያከፋፍሉ ሁኔታዎችን በፍጥነት ቢያመቻች ጥሩ ለውጥ ማምጣት እንችላለን ብዬ አምናለሁ፡፡
እኔ በልቤ ሁለት ነገር አለ፡፡ አሁን ኮሮና ቫይረስ ሀብትና ብልፅግና አልገደበውም፡፡ ኮሮና ቫይረስ ያልገባባቸው እነ ሶማሌላንድ፤ የመን፣ ደቡብ ሱዳንን ስናይ በኢኮኖሚ ዝቅ ያሉ ናቸው:: ምናልባት የኔ ግምት ደሀ ስለሆንን፣ ኑሯችን ሁሌ ትግል ስለሆነ፣ በሽታ የመቋቋም አቅማችንን ገንብቶት ይሆን እላለሁ፡፡ ሁለተኛው ግምቴ ደግሞ አየሩ ካገዘንና እግዜሩ ከራራልን እንጂ እኛ በሰራነው ስራ አይመስለኝም፡፡ አሁን ላይ ትንሽም ቢሆን የተሻለ ነገር ላይ የተገኘነው ብዬ አምናለሁ:: አሁን መረጃዎች ስለ ኮሮና ሰርች ማድረግ አፍሪካዊያን በርትተዋል:: በተለይ ኢትዮጵያና ኡጋንዳ አልተቻሉም:: ኢንተርኔት አክሰስ ያለው ስለ ኮሮና ለማወቅ እያሳየ ያለው ጥረት ተስፋ ይሰጠኛል፡፡ በሌላ በኩል ትላንት አድማጭ ደውሎ የነገረኝ አስደንግጦኛል:: 6 ወጣቶች ናቸው፤ የኮሌጅ ተማሪ ሁኔታ ያላቸው ናቸው:: ማስክና ጓንት ሁሉም አድርገዋል፡፡ ሲጋራ ግን እየተቀባበሉ ያጨሳሉ:: አያስደነግጥም? ኧረ በሕግ እንላለን እነዚህን፡፡ በመጨረሻ ማለት የምፈልገው ችግራችንን ዋጥ አድርገን፣ ትንሽ የምትበላ ነገር ይዘን፤ ለጎረቤታችንም እያካፈልን መንግስትም እያገዘ መጥፎ ነገር እንሰማበታለን የተባለችውን ሁለት ሳምንት እንደምንም ዳገቷን እንውጣ እግዚያብሄርም ይጨመርበት፤ አመሰግናለሁ፡፡  


Read 573 times