Print this page
Tuesday, 07 April 2020 21:16

‹‹በዕድሜዬ አባቴን ጨብጫቸው አላውቅም” (አያልነህ ሙላቱ፤ ፀሐፌ ተውኔት)

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

የመጣው ችግር ዓለም አቀፍ  ነው፡፡ ወረርሽኙን ለመከላከል ይጠቅማሉ የተባሉ መንገዶች ባጠቃላይ ከአኗኗራችን አንፃር ትልቅ ተፅዕኖ የሚያስከትሉ ናቸው፡፡ ያንን ልማድና ተፅዕኖ  ወደ ሌላ ልማድ፣  ወደ ሌላ ሁኔታ ለማስቀየር “አትገናኝ አትነካካ” ወደ ማለት ለመመለስ ጊዜ እንደሚፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ይሁን እንጂ የሚነገረውን የሚቀበል፣ በተለይም መንግሥት እያካሄደ ያለውን ጥንቃቄና ሚዲያው እያስተላለፈ ያለውን መልዕክት የሚተገብር የሕብረተሰብ ክፍል አለ፡፡ ችግሩ ሳይንቀሳቀስ ቢውል የዕለት ጉርስ የሌለው፤ ለልጆቹ ዳቦ መስጠት የማይችልን ሰው “ቤትህ አርፈህ ቁጭ በል” የሚለውን ትዕዛዝ መተግበር አለመቻሉ ነው፡፡ ለራሱም ለልጆቹም የዕለት ጉርስ ማምጣት ስላለበት እንጂ ቤቱ ተሰብስቦ ቢቀመጥ ደስ ይለዋልኮ!
በሌላ በኩል መግለጽ የምፈልገው፤ ይሄ የመጣብን ችግር ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አዲስ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ከራሴ ተሞክሮ ብነግርሽ፤ እኔ በዕድሜ ዘመኔ የአባቴን እጅ ጨብጬ፣ ሰላምታ አቅርቤ አላውቅም፡፡ አባቴን እጅ ነስቼ ሰላምታና አክብሮቴን እገልጻለሁ እንጂ እጃቸውን ጨብጫቸው አላውቅም፡፡ ይሄ ነው አስተዳደጌ፡፡ ይሄ ዘመናዊ አስኳላ ያመጣብን ችግር ነው፡፡
ይኸው ዛሬ ከመጨባበጥና መተሻሸት መላቀቅ አቅቶን መከራ እናያለን:: ዛሬ እጅ መንሳትን እንደ አዲስ እየተማርን ስመለከት፣ የራሳችንን አኩሪ ባህል እየጣልን በሌላ ወረራ እየተሰቃየን ያለን የምናሳዝን ሕዝብ መሆናችንን እገነዘባለሁ፡፡ አሁን ሰሞኑን እኔ፣ ሙላቱ አስታጥቄና አለማየሁ እሸቴ በቀይ መስቀል መኪና እየዞርን፣ በማይክራፎን ስንለፍፍ ነው የዋልነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ስንዞር ሰው ሲገናኝ መጨበጥ፣ አቅፎ መሳም የሚፈልግ ሁሉ ተመልክተናል፡፡ ይሄንን ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ጊዜ ካለፍን በኋላ ለቀጣይ ሕይወታችን መሰረት ጥሎልን ያልፋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ወደ ቀደመ ባህላዊ ሥርዓታችን ይመልሰናል ባይ ነኝ፡፡ በሌላ በኩል እኔም በነበርኩበትና በማውቀው፤ በአገራችን በተለይም በገጠሩ የአገሪቱ አካባቢ ‹‹ተስቦ›› የሚባል ወረርሽኝ አለ፡፡ ይሄ በገጠር በተደጋጋሚ የሚከሰት በሽታ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ምን ይደረጋል አንድ ሰው በተስቦ ተጠቃ ሲባል ወይ የዚያ ሰው ቤተሰብ ከቤት ይወጣል፡፡ ካልሆነም ተጠቂውን ከጤነኛው በመለየት ከቤት ውጪ ጎጆ ነገር በመስራት ለብቻው ያስቀምጠዋል፡፡ ያ ሰው ‹‹ወሽባ ገባ›› ይባላል፡፡ ያ ሰው ከጤነኛው ተለይቶ ሰባት ቀን ከቆየ በኋላ በቃ አይሞትም፤ ለምን እንደሆነ አይገባኝም፡፡ ያ ሰው ሰባት ቀን ታሞ በሕይወት ከቆየና በነዚህ ቀናት ውስጥ ካልሞተ ያገግማል፡፡ ካገገመ በኋላ ወደ ቤተሰቡ ከመቀላቀሉ በፊት በገበያ ቀን የገበያተኛ መንገድ ላይ አውጥተን እናስቀምጠዋለን፤ ከሕዝቡ ጋር ይቀላቀላል፤ ሕይወቱን ይቀጥላል፡፡
እናም ታማሚን ከጤነኛ አግልሎ ብቻውን የማቆየት ጉዳይ፣ ታማሚውን ከውጭ ሆኖ መርዳት  ከጥንት ጀምሮ አገር በቀል ሀብታችን እንጂ ማንም ሊያስተምረን የሚገባ አልነበረም:: ችግሩ ምንድን ነው ካልሽኝ፣ አገር በቀል እውቀታችንን አውጥተን መጣል መናቅና ላልረባ መጤ ባህል ማጎብደድ ነው እንደ አዲስ ተማሪ ያደረገን፡፡ አሁን “ተገለል ለብቻህ ቆይ” እየተባልን እየተማርን ሳይ ይገርመኛል:: እንዳልኩሽ ከጥንት ከጠዋት ጀምሮ የገጠሩ ያልተማረው ማህበረሰብ እንኳን ታማሚን ከጤነኛ ነጥሎና ለብቻው አድርጎ በመርዳት ማስታመም፣ ሰፊውን ሌላውን ማህበረሰብ ለማዳንና ለመጠበቅ ትልቅ መፍትሄ መሆኑን ጠንቅቆ ተረድቶ ሲጠቀምበት ኖሯል፡፡ ይህንን የጥንት ባህልና ሀብታችንን በደንብ መንከባከብና ለአዲሱ ትውልድ ማሳወቅ የሁላችንም ግዴታ ነው እላለሁ፡፡ አሁን እኮ ፈረንጅ መጥቶ በአስኳላ ያበላሸብንን ነገር ነው ለማስተካከል ግራ የገባን፡፡ “አንተ ታመሃል፤ እኔም ገና ራሴን አላወቅኩትም፤ እስኪ ተለያይተን ራቅ ራቅ ብለን እንቆይ ስንባል ግራ ገባን፤ መለያየት ከበደን፤ ጥንት ግን ስናደርገው ቆይተናል፡፡ ተጠቅመንበት ውጤታማ ሆነን ኖረናል፡፡
የሰሞኑን ቅስቀሳ በተመለከተ በወጣንበት ጊዜ እየዞርን ስንመለከት፣ ሕዝቡ አንድ ላይ ነው የተቀመጠው፤ ሻይ ቤትም አንድ ላይ ከቦ ነው ያለው፡፡ እናም ‹‹እኔ ደራሲ አያልነህ ሙላቱ እባላለሁ፡፡ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያ ነኝ፣ የኔ ጽሑፍ የሚነበበው እናንተ ስትኖሩ ነው፣ ቴአትር የምሰራው የሚመለከትልኝ ሲኖር ነው፣ መምህርም ነኝ፤ የማስተምረው ተማሪ ሲኖር ነው፣ እናም ላጣችሁ ስለማልፈልግ በመራራቅ ትንፋሽ ባለመቀያየር፣ ከታማሚው በመለየት ከቻልን በቤት እንቆይ፤ ይህን ጊዜ ተባብረን ተደማምጠን እንለፈው›› እያልኩ ከጓደኞቼ ጋር ስቀሰቅስ ነበር፡፡ ያው እኔ ቤቴ ቁጭ ማለት ይኖርብኛል፤ ነገር ግን ጉዳዩ  መስዋዕትነት ይጠይቃል፡፡
መንግሥት “እናንተ ይህን ማድረጋችሁ ሕዝቡን ያስተምራል፤ ይለውጣል” ሲል “አይ እኔ እፈራለሁ” ከቤቴ አልወጣም” ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ እየወጣን እየቀሰቀስን ነው፤ በእርግጥ በመኪና ነው፤ የለበስነው ልብስ ያደረግነው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ፣ ጓንትና ሳኒታይዘር በደንብ የተዘጋጀ ስለሆነ ብዙ ተጋላጭነቱ የለም፡፡ ዞሮ ዞሮ ይህን አድርገን የከፋ ነገር ቢመጣ እንኳን የምንችለውን በማድረጋችን ከፀፀት እንድናለን፡፡
በመጨረሻም የመከራውን ጊዜ በአጭር ለማለፍ የሚችል ከቤቱ አይውጣ፣ የሚወጣም ርቀቱን ጠብቆ ይንቀሳቀስ፤ በሚቻል መጠን የንፅህና መጠበቂያ ሳኒታይዘርና አልኮል ከእጅ አይጥፋ:: የመንግሥትን በተለይም የጤና ሚኒስቴርን መመሪያ ተግባራዊ እናድርግ የሚል መልዕክት አለኝ፤ እኔ ይህን እያደረግኩ ነው፡፡






Read 2244 times