Saturday, 04 April 2020 13:09

የዘመናችን ጦርነትና የኛ ትምክህት!!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(4 votes)

    ‹‹-ይህ ቸልተኝነት የጣልያናውያን ትልቁ ችግር ነበር፡፡ በሽታውን ተራ ነገር አድርገን ነበር የቆጠርነው፤ ንቀነው ነበር፡፡-››

በዓለማችንና በሃገራችን አስፈሪ ቀናት፣ ወራትና ዓመታትም በምጥ ታልፈው ‹‹ታሪክ›› በሚል ስያሜ በየድርሳናቱ ተቀምጠው ይነበባሉ፡፡ ከጥንትም ጀምሮ የሰው ልጆች በጦርነት፣ በረሃብ፣ በበሽታና በስደት ማለፍ የዕጣ ፈንታቸው አንዱ አካል ይመስላል፡፡
ዛሬ ሃገራችንም ሆነች ሌሎች ሃገራት ትናንትና በረሃብ ተቆልተው፣ በጦርነት ተንጠው፣ በፈተና እሳት ነጥረው የወጡ ናቸው፡፡ ታላቋ አሜሪካ በሚዘገንንና ከ600 ሺህ በላይ ለሆነ ሕዝብ ዕልቂት ምክንያት በሆነ ጦርነት ውስጥ ስታልፍ፣ ከመራራ ጦርነት ታላቁን አሜሪካዊ ፕሬዚዳንት ሊንከንና ጄነራሎቹ ሸርማን፣ ግራንትና ሌሎችንም ወልዳ የፀና መሰረት ጥላለች፡፡
ብዙ ታላላቅ ሰዎችን የወለደው የአየርላንዱ ረሃብና ስደት፣ ጆን ኤፍ ኬኔዲን የመሰለ ታላቅ መሪና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መነሻ በእንግሊዝ ዲፕሎማት የነበረውንና በኋላም የሩዝቬልት አማካሪ የነበረውን ትልቁን ኬኔዲን አበርክቷል:: የካናዳው ረሃብና ችግር ለዓለም የበጎ አድራጎትን መሰረት ጥሎ አልፏል፡፡
በሌላ በኩል፤ የከፋና ጭካኔ የተሞላበት የጀርመኑ ናዚ ፋሺስት የግፍ ስራ በዓለም ላይ ጥቁር ጠባሳውን ጥሎ መማሪያ ሆኗል፡፡ ይህ ማለት ዓለምና በዓለም ላይ የሚያልፈው የትኛውም በጎና ክፉ ምግባር፣ በሰው ልጅ ህይወት ላይ አስተምሮ ጉዞውን ያበቃል፡፡ በዚህ የማስተማር ሂደት ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች ከፊሉ ዓለምን በእሾህ ሲያሰቃይ፣ሌላው ለሰው ልጆች የዘንባባ ዝንጣፊን  ያለብሳል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ክፉ ቀን ያረረውን ምድረበዳ በውሃ የሚያረሰርሱ፣ በጽጌረዳ የሚያሸበርቁ ሆኖ መገኘት ግን ዕድለኝነት ነው፡፡
ጠቢቡ ሰለሞን በመክብበ መጽሐፍ እንዳለው፤ ‹‹እግዚአብሄር ስራን ሁሉ፣መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን ወደ ፍርድ ያመጣዋልና›› ሁላችንም በሕይወት ወንፊት ማለፋችን አይቀርም፡፡
አሁን ዓለማችን ያለችበት ሁኔታ፣ የተፈጠረው  የሞትና የወረርሽኝ ዜናም በእያንዳንዳችን ልብ የተለያየ መልዕክትና ስሜት ይፈጥራል፡፡ ችግሩ በዘመናችን ይፈጠራል ተብሎ ያልተገመተና ሳይንስና ቴክኖሎጂን አብረክርኮ ይሄን ያህል ጥፋት ያደርሳል ተብሎ ያልተጠበቀ  ነበር:: ይሁን እንጂ በሽታው ታላቋን ቻይናን ማህጸን አድርጎ፣ የአሜሪካንን ደጅ በርግዶ፣ የአውሮፓን ከተሞች በሬሳ ሲሞላ የከለከለው የለም፡፡ የሰው ልጆች የሺህ ዓመታት የሳይንስ ግስጋሴ ሊገታውና ሊያቆመው አልቻለም፡፡ ወይም እንደ ሙሴ ዘመን የፋሲካ በግ እያረዳችሁ፣ መቃኖቻቸው ላይ ቀብተው ሞት እንዲያልፍ የሚደርግ የእምነት ኪዳን የለም፡፡ ስለዚህም ደሃውንና ሃብታሙን፣ ምሁሩንና ማይሙን ሳይመርጥ እያስጨነቀውና እያስማጠው  ነው፡፡
ታዲያ ሃገራቱ እንደየ አቅማቸው ሕዝባቸውን ለማዳን፣ ከመቅሰፍት ለመታደግ ያላቸውን መዥርጠው የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ የህክምና ባለሞያዎችም አቅማቸውንና ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ መስዋዕትነት ሲከፍሉ እያየንና እየሰማን ነው፡፡
በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ማንም ማንንም አይሰማም፤ መላውን ዓለም እያሸበረው ቀጥሏል፡፡ ሁሉም ቤተሰቡንና ራሱን ለማዳን እየተጋደለ ነው፡፡ እንደኛ ሃገር የባሰበት እምነቱንና ሳይንሱን በቅጡ ሳይለይ፣ በአንድ በኩል ፍጹም ፈጣሪውን አማኝ መስሎ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የጤና ባለሞያዎች የሚነግሩትን ችላ ብሎ በየአደባባዩ እየተንቀዋለለ ነው:: እኛ ሃገር ጥፋት ሲመጣ እውነት መሆኑ የሚታመነው ሰው ሲሞት ብቻ ይመስላል:: ዛሬ ያለ ምንም ክፍያ የሚያስፈልጉትን ጥንቃቄዎች በማድረግ፣ራሳችንን መጠበቅ እየቻልን የወረርሽኙ ጅረት መጥቶ እስኪጠራርገን እየጠበቅን ይመስላል፡፡ እንዲያውም የአንዳንዶቻችን ሁኔታ የኮሮናን አፍንጫ ለመንካት የምንሮጥ ያስመስለናል:: ቤታችን ከመቀመጥ ይልቅ በየመዝናኛው ቦታ ከሰዎች ጋር መተፋፈግ ሥራዬ ብለን ይዘናል፡፡
ከሁሉ ከሁሉ የሚገርመው ‹‹ይህ በሽታ የሚይዘን እግዚአብሔር የት ሄዶ ነው?›› የሚለው አባባል ነው፡፡ ለመሆኑ ሌሎቹን የፈጠረው እግዚአብሄር አይደለም ልንል ይሆን?!...ወይስ እኛ ከሌሎቹ የተለየ ጽድቅ አለን! ለዚያም ቢሆን ማስረጃ ያስፈልጋል:: መጽሐፍ ቅዱስ የተለየና የተመረጠ ዘር የሚለው ‹‹እስራኤልን›› ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ያም በአዲስ ኪዳን ሁሉን እኩል በሚያደርገው ወንጌል ተለውጦ፣ መጽሐፉ አይሁድና ግሪካዊ፣ ሴትና ወንድ ሁሉ እኩል እንደሆነ ይነግረናል፡፡
ይህንን ጽሑፍ እየጻፍኩ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያነበብኩትን ጽሑፍ ለዚህ መጣጥፍ ግብዐት ይሆነኝ ዘንድ የተወሰኑ ሃሳቦችን እወስዳለሁ፡፡ የወሰድኩት አሳየኸኝ ለገሰ ከተባለ ወዳጄ ገጽ ሲሆን ጸሐፊው አንድሪው ዴኮርት፣ተርጓሚው ደግሞ ገዛኸኝ ዘነበ ነው፡፡ እነሆ…
‹‹የቤቴን ያህል የማያቸው ኢትዮጵያና አሜሪካ አንድ የሚያመሳስላቸው ነገር አለ:: ሁለቱም ራሳቸውን ‹አዲሲቷ እስራኤል› እንደሆኑ ይቆጥራሉ፡፡ የሁለቱም ሃገራት ተጽዕኖ ፈጣሪ ልሂቃን፣ ራሳቸውን በእግዚአብሄር እንደተመረጡ አድርገው የሚያቀርቡ መሳጭ ትርክቶችን ለሕዝባቸው አዘውትረው ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ እነዚህ ትርክቶች፣ በሕዝቦቹ ዘንድ ጠንካራ የሆነ የ‹‹ተለየሁ ነኝ›› ብሔራዊ ስሜት ማቀጣጠል ችለዋል፡፡ እግዚአብሄር በልዩ ዐይን እንደሚያየው፣ ከሌላው ሕዝብ በተለየ መንገድ እንደሚያደላለትና በተለይም ልዩ ጥበቃ እንደሚደረግለት አድርጎ የሚቆጥርን ማኅበረሰብ ፈጥረዋል፡፡ የሁለቱም ሃገር ዜጎች ‹‹ይሄኮ ኢትዮጵያ ነው!›› ወይም ‹‹ይሄኮ አሜሪካ ነው!›› ብለው በተደጋጋሚ በኩራት ሲናገሩ እሰማለሁ፡፡ ‹‹እንዲህ ባለችዋ በተመረጠችና እግዚአብሄር በሚወዳት ምድር ክፉ ሊደርስ አይችልም›› ማለታቸው ነው፡፡ ‹‹በእግዚአብሄር ተጋርጃለሁ›› ይሉት ዓይነት የ‹‹የጽዮናዊነት  ስሜት›› አላቸው፡፡
ይህ ሕመም እኛንና አሜሪካንን መጠቅለሉ ገርሞኛል፤ ለካስ የኛ ብቻ አይደለም፡፡ እነርሱ ግን ‹‹ያለው ሲያምርበት!›› ሆኖ ቡድናችን ይለያያል፡፡ እንግዲህ፣ ከእግዚአብሄር ጋር ለየት ያለ ኪዳን ያለን አዲሲቷ እስራኤል ነን ብለው የሚያስቡ ኢትዮጵያውያንና አሜሪካውያን ቢኖሩ፣ በቀላሉ ተዛማጅ ስለሆኑ በሽታዎች፣ ለመጀመሪያዋ እስራኤል እግዚአብሔር የሰጣትን ታዲያ በምን ምክንያት ነው ወረርሺኙ ለኛ የተለየ ምህረት የሚያደርገው! ለአመጽ ለአመጽ ከሆነ እኛ በአደባባያችን በደቦ ወንድማችንን ዘቅዝቀን ስንሰቅል አላፈርንም፤ ጌታን አላስታወስንም:: ...እኔ በታሪክ ውስጥ ሰው ተዘቅዝቆ መሰቀሉን የማውቀው በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ያደረገውም ሰው ሐዋርያው ጴጥሮስ በገዛ ፈቃዱ ነው፡፡ ‹‹እንደ ጌታዬ ሳይሆን ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ›› ማለቱም ተጠቅሷል:: ያም የትህትና ሕይወትን ብቻ ሳይሆን የትህትና ሞት  መሞትን ያሳየበት ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች ቤቶች ስናቃጥል፣ ወገኖቻችን ላባቸውን ጠብ አድርገው ያፈሩትን ሀብት ነጥቀን ስናባርር፣ እግዚአብሄር መኖሩን ያለማሰባችንን ያስታወስን አይመስልም፡፡ መች ‹‹ያዝንብናል›› ብለን ከክፉ መንገዳችን ተመለስን?! ወንድሞቻችንን ልናርድ በቡድን ቢላ ስንስል ጌታችንን መች አስታወስነው?...ታዲያ በምን ሁኔታ ነው ዛሬ ‹‹እግዚአብሔር ይጠብቀናል›› ወደሚል መጓደድ የመጣነው:: የሌባ ዐይነ-ደረቅ መልሶ ልብ አድርቅ መሆኑ አይደለ?
እውነት ነው መጽሐፍ እንደሚል፣ጌታ እጅግ የሚራራና የሚምር ነው፡፡ የሚምረው ግን ጥፋታቸው ጸጽቷቸው፣ በተሰበረ ልብ በፊቱ የሚቀርቡትን እንጂ ጻዲቅ መስለው ከትናንት ጥፋታቸው ለመመለስ ያልተዘጋጁትን ግብዞች አይደለም፡፡ በሌላ በኩል፤ ሌሎች  በሳይንሱ የሚያምኑት በሳይንሱ ቀዳዳ እየፈለጉ ነው፡፡ ኮሙኒስታዊ መንግስት ያላት ቻይና ወረርሺኙ ከተከሰተ በኋላ ሳይንሳዊ መንገድ ተጠቅማ የተሻለ እመርታ እያሳየች ነው፡፡ ሌሎቹም ሀገራት በተቻለ መጠን ተጠንቅቀው ራሳቸውን ለማዳን እየተጋደሉ ነው፡፡ ቸል ብለው በየኳስ ሜዳው የዋሉት ሃገራትም የሚከፍሉት ዋጋ ከሌሎች የከፋ እንደሆነ እያየን ነው፡፡ ምንም ይሁን ምንም፣ ሃብትና ዕውቀት ያላቸው በሽታውን የመቆጣጠርና በአነስተኛ ዋጋ የማለፍ ዕድላቸው ከኛ የተሻለ ነው፡፡
እኛ ግን በሳይንሱም ብንመዘን በርትተን ከመስራት ይልቅ ፊደል ቆጥረናል ያሉት፣ ሳይንቲስት ነን ብለው ከበሮ ያስደለቁት ሳይቀሩ ሲያጠኑና ሲያስጠኑ የነበረው ስለ ዘር ፖለቲካና ስለ ብሄር ግጭት ነበር፡፡ ስለዚህ ከድህነትና ድንቁርና ውጭ ምርምሩ ሰፈር መድረስ አልቻልንም፡፡ በእምነቱ በኩል ከሄድንም፣ ፖለቲከኞቻችን ሙስሊምም ነን አሉ፣ ክርስቲያን ያስተማሩት ጥፋት ስለነበር ፈተናውን ወድቀዋል፤ እኛንም  ጥለውናል፡፡
ታዲያ ድፍረቱ ከየት መጣ እንበል? ቅዱስ መጽሐፍ፤ ‹‹ጻዲቅ እንዳንበሳ ደፋር ነው፤ ሀጥዕ ግን ሳይነኩት ይሸሻል›› ይላል:: የእኛ ግራ የሚያጋባው ለዚህ ነው፡፡ ዞሮብናል፡፡ እምነትና ድርቅናን መለየት አቅቶናል፡፡
ስለ ሃገር ስናስብ ሃገር ከሰፈር ይጀምራልና ያስተዋልኳቸውን የተለያዩ ቀለማት በዋቢነት ብጠቅስ ደስ ይለኛል:: ሰሞኑን ለስራ በሄድኩባቸው አካባቢዎች የገጠሙኝ ሁኔታዎች ሁለት መልኮቻችንን አሳይተውኛል፡፡ በአንድ ከተማ ሱቅ ውስጥ የነበረች አንዲት እናት ‹‹እህል አልዋጥ ብሎኛል፡፡›› አለች፡፡ እኔና አብሮኝ የነበረው ሰው ለምን እንደዚያ እንደሆነች ጠየቅናት፡፡ መልስዋ ያሳዝን ነበር፡፡ ‹‹ይህ ሁሉ የሰው ልጅ እየረገፈ እንዴት ይዋጥልኝ!›› የሚል ነበር፡፡ ይገርማል፤በዚህ ትይዩ ብቅ የሚሉብን ሰዎች አሉ፡፡ ከነዚህ መካከል ከሰው ደም ጅረት ሳንቲም የሚለቅሙ፣ በወገኖቻቸው ሞት መካከል ለራሳቸው የተድላ አበባ የሚቀጥፉ ናቸው፡፡ ያቺ ሴትና የሚመስሉዋት ሌሎች ሰዎች በቁጥር ጥቂት አይደሉም፡፡ ድሮም በጦርነትና በጀግንነት ታሪካችን እርሷን የመሰሉ የሀገር ልጆች ነበሩን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ለሆዳቸው ባንዲራቸውን የሸጡ ባንዳዎችም እልፍ ናቸው፡፡
ይህ ባንዳነት በአንድ ዘመን የነበረና ያበቃ አይደለም፤ዛሬም አለ፡፡ አሁን የምናየው ባለ ሱቁ፣ባለ መድሃኒት ቤቱ ወገኑን ከማዳን ይልቅ ሳንቲም ዘረፋ መግባቱ፣የጭካኔውና የባንዳነቱ ማሳያ ነው፡፡ ሰሞኑን የትራንስፖርት መቋረጥን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅመው፣ ከመንግስት ሰዎች ጋር በመመሳጠር አስር እጥፍ ዋጋ በማስከፈል በጨለማ ሰዎች የሚጭኑ ተፈጥረዋል፡፡ ባንዳነት ማለት ይህ ነው፡፡
ዛሬ የቆምንበት ጊዜ ለሃገራችን የጦርነትና የፈተና ጊዜ ነው፡፡ ሃገሩን የሚወደውን ሆዱን ከሚወደው ለይተን እናውቃለን፡፡ በጦርነት ውስጥ ታላላቅ የጦር ጀነራሎች እንደሚፈጠሩ፣ በዚህም የፈተና ወቅት እውነተኞች በእሳት ተበጥረው ይወጣሉ፡፡ ሰሞኑን ያየነውም ይህንን ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ያላቸውን ቤት፣ መኪና፣ ገንዘብ ለችግር ቀን ማለፊያ ይሆን ዘንድ ሰጡ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ አሁንም ይሰርቃሉ፤አሁንም ሸቀጥ ከዋጋው በላይ እየሸጡ ገንዘብ ያከማቻሉ፡፡ ይሁንና ችግሩ በእኛ አቅም ሊገፋ የሚችል አይመስልም፡፡
ሰሞኑን የኒውዮርክ ከንቲባ ያስተላለፉትን የእርዳታ ጥሪ የሰማ ሰው መደንገጡ አይቀርም፡፡ የዓለም ፖሊስ የሆነችው ታላቋ አሜሪካ! ለዚያውም ትልቋ የዓለም ገበያ ኒውዮርክ አቅም አጠራት፤ተጠቂዎችዋን የምታስተኛበት መኝታ አጣች?... ያስደነግጣል፡፡
እኛ ደግሞ ጊዜያችንን ያሳለፍነው በስራ ሳይሆን “ትግራይ አንደኛ!... ኦሮሞ አንደኛ…! አማራ አንደኛ!...” በሚል የጅል ቅዠት ነው:: ምን ያደርጋል? ብሔር ስንቅ አይሆንም፤ አልጋ አድርገን አናነጥፈውም፡፡ …እስቲ ስለ አንደኝነት ያወሩን ፖለቲከኞች፣ አንዱን አድርገው ያሳዩን!! ...ሕዝቡስ የሚያስፈልገው ዘር ቆጠራና ስራ ፈቶ መሰዳደብና ሜንጫ መምዘዝ ነበር ወይስ ዳቦና ሃብት? እነዚያ ያገራችን የፖለቲካ ሳይንቲስቶች መልሱኝ ቢነግሩን ደስ ይለኛል፡፡ ከየትኛው መጽሐፍ እንዳነበቡትና የትኛው ሃገር በዚህ መንገድ እንደለማ ቢነግሩን፣ ለወደፊቱ ብንጠቀምበት ደስ ባለኝ፡፡ …የሆዳሞች ወሬ ፍሬው ሞት ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በየዘመኑ የችግር ምንጭ የሚሆኑት ጥቅመኛ የሃይማኖት ሰዎች ናቸው፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቶማስ ጀፈርሰን እንደሚለው፤ የዴሞክራሲና የልማት ጠንቆች ብዙ ጊዜ ይህንን ካባ የለበሱ ግብዞች ናቸው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ታሪክ ስንመጣ፣ በንጉስ ኀይለስላሴ ዘመነ መንግስት ለተካሄደው የማይጨው ጦርነት ሽንፈት አንዱ ሰበብ፣ የአራዳው ጊዮርጊስ መነኩሴ እንደነበሩ የደች ተወላጅ የሆነው የንጉሱ ወጥ ቤት ሃላፊ በጻፈው መጽሐፍ፣ በቁጭት አስታውሷል፡፡ ጦርነቱን ያሸንፋሉ፤ እግዚአብሄር ከርስዎ ጋር  ነው ብለዋቸው ነበር፡፡ ውጤቱ ግን የተለየ ነበር:: ትንቢቱ ምናልባትም ንጉሱ አንዳንድ እርምጃዎችን በጊዜ ከመውሰድ ይልቅ ተዐምራት እንዲጠብቁ አድርጓቸው ይሆናል ብሎ ለመገመት ያስችላል፡፡
አሁንም የዚህን ወረርሽኝ መግባት ተከትሎ ከሃይማኖት አስተማሪዎችና ነቢያት ነን ባዮች የሚሰማው ወሬ የሚያዘናጋና ሕዝቡ እንዳይጠነቀቅ የሚያደርግ ተጨማሪ ችግር ነው፡፡ አንዳንዶቹ ወረርሽኙ ኢትዮጵያ አይገባም›. ብለው ገብቶም አፍረው አልተቀመጡም፡፡ አሁንም ያወራሉ፤ ያሳስታሉ፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ ጉባኤ አታካሂዱ ተብሎ ሰዎች ጉባዔ እንዲመጡ ይጋብዛሉ፡፡ መንግስትም የፈራ ይመስል ሕግ ማስከበሩ ላይ ቸል ብሏል፡፡ መንግስት ከዝንጉነቱ መላቀቅ አለበት፡፡ ህዝቡም ሌላውን ምክንያት አልባ ወሬ ትቶ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ፣ ቀድሞ ለበደለው በደል ፈጣሪውን ይቅርታ እየጠየቀ ኑሮውን ይቀጥል፡፡ ይህ ቅንጦት ለእስራኤልም አልተፈቀደም፤ ለብሉይ ኪዳንዋም!! በአዲስ ኪዳንማ ሁሉ በክርስቶስ እኩል ነው ተብሏል፡፡
 በመጨረሻም ነጋሲ ክብሮም የተባሉና ነዋሪነታቸው በጣልያን ሀገር የሆነ ሰው፤ እርሳቸውና ባለቤታቸው በኮሮና ከተያዙ በኋላ በማገገሚያ ሳሉ ያሉትን ጠቅሼ ጽሁፌን ልቋጭ፡- ‹‹ይህ ቸልተኝነት የጣልያናውያን ትልቁ ችግር ነበር፡፡ በሽታውን ተራ ነገር አድርገን ነበር የቆጠርነው፡፡ ንቀነው ነበር፡፡››
 የናቁት ያዋርዳልና እንጠንቀቅ!!!

Read 13063 times