Print this page
Saturday, 07 July 2012 10:03

“ቆይ እንጂ ትዕዛዛችሁን ልርሳ!”

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

ጅማ ዩኒቨርሲቲ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ እለት 2390 ተማሪዎችን አስመረቀ፡፡ በክብረ በዓሉ ላይ እንገኝ ዘንድ በተጋበዝነው መሰረት በዋዜማው ወደዚያው ሄጄ ነበር፡፡ የተማሪዎች ምረቃ ብቻ ሳይሆን ለፕሮፌሰር ገቢሳ እጀቴ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷል፡፡ የክብር እንግዳ የነበሩት ክቡር አቶ ሙክታር ከድር የኢፌዲሪ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ናቸው፡፡ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ለካርል ቦኸም፣ ለአበበች ጐበና፣ ለደራርቱ ቱሉ፣ ለኃይሌ ገ/ሥላሴ፣ ለሽመልስ አዱኛ፣ ለአሊ ቢራ፣ ለዙምራ ኑሩ እና ለሙላቱ አስታጥቄ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

የዛሬውን የጅማ ጉዞ ማስታወሻ ጅማ ከተማን ካየሁ በኋላ የተሰማኝን ስሜት በገለጽኩበት ግጥም ልጀምር!

ምነው ጅማ?

ሰው በየለት ከሚሞት፣ አንዴ ቢሞት ይሻል፤ ሲሉ

አይገባኝም ነበር ቃሉ፡፡

ይኸው ጂማ ባንቺ አየሁት

ነግ - ሠርግ እየተገነዘች፣ ከተማም እንደሰው ስትሞት!

ሰው ውስጡ ነው እሚሞት ሲሉ

አይገባኝም ነበር ቃሉ

ይኸው ጂማ ባንቺ አየሁት

ከአናትሽ ከግርጌሽ ሳይቀር፣ ውስጥሽ ተቦርቡሮ ሲሞት!

ምነው ጅማ?

ጅማ ያገር ንግድ ጀማ

የጧት ስልጣኔ ማማ

ምነው ጅማ?

ጅማ የአባ መስጠት አገር፣ የግብር ድር - ማግ ነሽ ሲሉ

የጧት ልማትሽ የት ገባ፣ የንጋት ቡናሽ ጠበሉ?

የንግድ መግቢያና መውጫ፣ ለየዐረብ አገሩ ሁሉ

የአባ - ጅፋር አምስት በር፣ ተዘጋ ጉሮሮሽ ውሉ?

ምነው ጅማ?

ገጣሚ እንዳለሽ በቃሉ

የዑስማን ሸርኬን ጣር ጉንፋን፣ ዛሬም ትስያለሽ አሉ!

ምነው ጅማ? መንገዶችሽ ወዴት አሉ?

መክሊቶችሽ ወዴት አሉ?

እንዳቃቢት ግብር - ውሃ፣ ተስፋሽ ሜዳ እየተደፋ

ዋናው አስፋልትሽ ቀን በቀን፣ የነቃ አንገቱን ሲደፋ

ጐዳናሽ ውሃ ሲተፋ

እንደጀዘበ ጫት ቃሚሽ

ኮረኮንችሽ በየጉያሽ

ፈዞ ነፍዞ እያንቀላፋ

ወዝሽ አመድ እየነፋ

ያው ያለዕዳው ዘማች ህዝብሽ፣ እንደቆዳው

እየለፋ

አድሮ ‘ሚያቀጭጭሽ እንጂ፤ የሚያወፍርሽ ቀን ጠፋ!

ምነው ጅማ?

ስንቱ ከኋላሽ ሲለማ

ያንቺ አካል ቁልቁል ሲደማ

ድምጽሽ እንደሟች ሰለለ፣ ጣርሽ እንኳ እንዳይሰማ

ምነው ጅማ?

ምነው?

ከተማ ቢሞት ተስፋ አይሞት

ተስፋ - ፀሎቴ አይለይሽ

ደሞ ሌላ ጊዜ ልይሽ

እስከዚያው ከአጥፊ - ቀጣፊ፣ ምህረቱን

ይላክልሽ

ከወሬ ናዳ ያድንሽ!

በይ እናቴ አላህ ይማርሽ!!

23-10-04

(ለጅማ ልጆች)

ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ

ጂማ ዩኒቨርሲቲ በአሮጌ ከተማ መካከል የተቆረቆረ አዲስ ከተማ ይመስላል፡፡

ጂማ ዩኒቨርሲቲ በመደበልን ኮስትር ባስ ነው ወደ ጂማ መንገድ ለመጀመር ያኮበኮብነው፡፡

ነጩ ኮስትር አንድ ጋዜጠኛና የጅማን ዩኒቨርሲቲ ህዝብ ግንኙነት ይዞ ካዛንቺስ ድረስ መጣልኝ፡፡ 6 ሰዓት ከ50 ደቂቃ ግድም፡፡ ከቀኑ 7 ሰዓት ከኢቴቪ አንድ ሰው ያዝን፡፡ አንድ ሌላ ጋዜጠኛ ጨምረን ሦስት ሆንን ማለት ነው!

7 ሰዓት ከ09 ደቂቃ ግሎባል አንድ ዕቃ ለመጫን ሄድን፡፡

ቀጥሎ አየር ጤና ነው ቀጠሮአችን፡፡ በአየር ጤና አድርገን ወደ ሰበታ ከማምራታችን አስቀድመን NOC ለምሣ ወረድን፡፡ ምሣ ላይ ያልታዘዘ አንድ ጥብስ መጣና አነጋገረን፡፡ የአስተናጋጆቹ ኃላፊ “ምሳው አንዴ ትኬት ከተቆረጠበት አይመለስም” ይላል፡፡

ከእኔ ጋር ያለው ጋዜጠኛ “ወር ላይ አገር ውስጥ ገቢ ሄደህ ማስተካከል ትችላለህ፡፡ መመለስ ትችላላችሁ” ይለዋል፡፡

“እንደዛ ማድረግ በጄ አይሉም አገር ውስጥ ገቢዎች” ይላል ኃላፊው፡፡

“ለምን አይቻልም እናንተ ሰንፋችሁ ነው” ይላል ጋዜጠኛው

አብራን ያለች አንድ ሌላ ሴት

“እናንተ እንደምትሉት እዛ ሲሄዱ ቀላል አይደለም” አለች፡፡

“ለማንኛውም ይምጣና እንብላው እንከፍልበታለን” አለንና ህዝብ ግንኙነቱ እንደሁልጊዜው ጉዳዩ በተመጋቢው ተሸናፊነት አበቃ፡፡ ሰላም ግን ወረደ!

መንገድ ጀመርን፡፡ ብዙ ትራፊክ ስለሌለ አልተጨናነቅንም፡፡ ወሊሶ ትንሽ ቆምን፡፡ ፀሐያማ ነው መንገዱ፡፡ እኔና ህዝብ ግንኙነቱ ስለዓለም አቀፍ ጉዳይና አብዛኛውን ስለብሉስ፣ ስለስዕልና ስለሥነጥበብ እያወራን፤ አንዴ ብሉስ አንዴ የማሊ ዘፈን እየከፈተልኝ ጨዋታ እየኮመኮምን ነው የምንጓዘው!

ስለ ጥበበ ተርፋና ስለ ሰዓሊና ገጣሚ መስፍን ሀ/ማርያም አወራሁ፡፡ ስለ ጥበብ መጀመሪያ ነገርኩት፡፡

“ከልምድ ያገኘሁት የስዕል ሙያ አለኝ” አለኝ፡፡ ብዙ የስዕል መጽሐፎች እንዳሉት አወጋኝ፡፡ ቪዚት ካርዱን ሲሰጠኝ ካርዱ ላይ አንድ ስዕሉ አለች፡፡

ደስ ብላኛለች፡፡ “ካልዘነበ አታፈስም” ትላለች አርዕስቷ!

 

“የግጥም ርዕስ ይመስላል” አልኩት፡፡

ስለግጥሙም አወጋኝ፡፡ አንድ ግጥሙን በቃሉ ወጣልኝ፡፡ ኋላ ያሳተመውን መጽሐፍ ሲሰጠኝ ግጥሟን አገኘኋት፡፡

በስዕል የታጀበች ናት! (“ምናልባት ስዕሉ ባይኖር ይሻል ነበር” አልኩ በሆዴ፡፡ ራሱን የቻለ ግጥም ማጠናከሪያ ስዕል አያስፈልገውም፤ የሚል ዕምነት ስላለኝ ነው)

“ጥበብ በትዕዛዝ አይሰራም” አለኝ፡፡

“”አዎ እንዲያውም አንድ ነገር አስታወስከኝ” አልኩት፡፡

አንድ ጊዜ ሰዓሊና ገጣሚ መስፍን ሀ/ማርያም አንድ ስዕል ሊሠራ ይዋዋላል፡፡

አሠሪዎቹ ነጋ ጠባ ስዕሉን ጀመርክልን ወይ በሚል ሰው ይልኩበታል፡፡ መስፍን ስራውን ገና አልጀመረም፡፡ አሰሪዎቹ ተጨነቁና ደወሉለት፡፡

“ቀኑ እየደረሰ ነው፡፡ አንተ ግን ገና ሥራውን አልጀመርከውም፡፡ እንዴት ነው ነገሩ?” ሲሉ ጠየቁት፡፡ መስፍን ሲመልስ፤

“ቆይ እንጂ ትዕዛዛችሁን ልርሳ!” አለ፡፡

“ወደራሴ ልመለስ ወደ ነብሴ ልመለስ፤ እናንተ እዚያው ቅሩና እኔና ስዕሌ እንነጋገር ማለቱ ነው፡፡”

“እውነቱን ነው ባክህ ቆይ ትዕዛዛችሁን ልርሳ አለ፡፡ ይገርማል“ አለኝ በአድናቆት፡፡

Border ግን ያስፈልገዋል፡፡ የጥበብ ስሜት እንደካይት (Kite) ነው፡፡

ካይት በአየር ላይ ስትበር ከሥር ክር ይጐትታታል፡፡ ንፋስ አንዳይወስዳት ክሩ አለ፡፡ ክሩ ስቧት ወደመሬት እንዳትወርድ ደሞ ሽቅብ ተወርውራለች፡፡ በዚህ ማህል በሚዛን አየር ላይ ትንሳፈፋለች፡፡ ጥበብ እንደዚያ ነው” አለ፡፡

“ልክ ነህ የፔይን (ሥቃይ) እና የፕሌዠር (ደስታ) ውጤት ነው፡፡”

ወደ ጅማ በጣም ስንቀርብ ነው ውይይታችንን ያቋረጥነው፡፡ ሴንትራል ጅማ ሆቴል ነው ማረፊያ የተዘጋጀልን፡፡

ሴንትራል ጅማ ሆቴል ማታ - ሞባይሌን ቻርጅ እንዲያደርጉልኝ ሰጥቼ ቢራ አዝዤ ተቀመጥኩኝ፡፡ ከጐኔ ቢራ የሚጠጡ ወጣቶች አሉ፡፡ ከጓሮ በኩል ነው፡፡

መዋኛው ይታያል ከሩቅ፡፡ እንደጐጆ የተሠሩ የሣርም የፕላስቲክም ጣራዎች ያሏቸው ዣንጥላዎች አሉ፡፡ ግድግዳ የሌላቸው ወንበርና ጠረጴዛ ከግርጌያቸው ያሉ፡፡

የወጣቶቹ ጨዋታ ማርኮኛል፡፡ በጣም ይስቃሉ፡፡

ሳዳምጣቸው ጨዋታቸው ይስባል፡፡

በጣም ያስቃሉ፡፡ ተማሪዎች መሆናቸውን ከጨዋታቸው መገመት ይቻላል፡፡ ስለፈተና ነው የሚያወሩት! ምናልባት የነገ ምሩቃን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለፈተና እንዲህ አሉ፡-

“አንድ የክፍላችን ልጅ ፈተናው በጣም ከብዶታል! ከላይ እስከታች ቢያነብ ቢያነብ የሚያውቀው አንድም ጥያቄ የለም! አንድ ዘዴ አሰበ፡፡ እጁን እንደዘረጋው ወረቀቱ ላይ ገትሮ አስቀረውና፤

“ወይኔ! ወይኔ! ቲቸር! ቲቸርዬ!” ሲል በሥቃይ ድምጽ ተጣራ!

ቲቸር መጣና

“ምን ሆንክ?” አለው፡፡

“እጄ! ኧረ እጄ ቲቸር! ተገትሮ ቀረ!..ኣ! ኣ! ነርቭ ነው መሰለኝ! ወይ እጄ!”

ቲቸር ደነገጠና፤

“የት ይደወልልህ? ሆስፒታል የሚወስድህ ሰው ይኖርሃል?”

ያንድ ጓደኛውን ስልክ እያማጠ ተናገረ!

ጓደኛው ደንግጦ መጥቶ ደግፎት ከፈተናው አዳራሽ አወጣው፡፡ ተገላገለ

ጣራ እስኪነካ ሳቃቸውን ለቀቁት!

ሌላው ልጅም የፈተና ወሬ ቀጠለ፡፡ “እንትናስ ትዝ አይላችሁም?” ብሎ አንድ ስም ጠራ፡፡ ታስታውሱ እንደሆነ ሁሌ ነጠላ ጫማ አድርጐ ነው ፈተና እሚቀመጠው፡፡

መጽሐፍ ደብቆ ይዞ ይገባና ቻፕተሩን ገልጦ መሬት ላይ ይዘረጋዋል፡፡ ከዛ በእግር አውራ ጣቱ ገፁን ይገልጣል፡፡

አስተማሪው ምን እያደረገ ነው ብሎ ተጠራጥሮ ትኩር ብሎ አየው፡፡

ይሄኔ ልጁ፤ “ቲቸር! እኔ ትኩር ብለው ሲያዩኝ እፈራለሁ!” አለ፡፡ ቲቸር ደንግጦ ወደ ኋላ ሄደ፡፡ ቲቸር ሄደለት ማለት ነው፡፡ መሸ ብንሄድ ይሻለናል” አሉ፡፡ እኔ ቢቆዩ ደስ ይለኝ ነበር!

ጠዋት ጅማ እየነቃች ናት፡፡ ሌሊቱን ዘንቧል፡፡

አስፋልቱ ረጥቧል፤ በከርካሳው የጅማ መንገድ ወደ ጂማ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ምረቃ አመራን፡፡ ፕሮግራሙ የሚጀምረው ከንጋቱ 12 ሰዓት ነው፡፡ ወላጆች ከንጋቱ 10 ሰዓት መጥተዋል፡፡ ፈስሰዋል ማለቱ ይቀልላል፡፡

የሰርከስ ጂማ ባንድ ይጫወታል፡፡ የእለቱ የክብር እንግዳ ከሴኔት አባላት ጋር በመሆን በዩኒቨርሲቲው የውጪ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሲኒየር ዳይሬክተር እየተመሩ ቦታቸውን ያዙ፡፡

ዶክተር ፍቅሬ ለሜሳ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ሪፖርት አቀረቡ፡፡ በሪፖርታቸውም በዩኒቨርሲቲው ከሚገኙት 5 ኮሌጆች፣ 2 ተቋማትና የድህረ ምረቃ ት/ቤት መካከል በዛሬው እለት ከሁለቱ ኮሌጆች ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩትና ከድህረ ምረቃ ት/ቤት በተለያዩ ሙያዎች የሚሰጠውን ስልጠና በብቃት በማጠናቀቅ ለሁለተኛ ዙር ምረቃ የበቁትን ተማሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል! የኮሌጅ ዲኖች ተራ በተራ ተመራቂዎችን እያስቀረቡ ማስመረቁን ተያያዙት፡፡ የላቀ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ሽልማት ተሰጠ፡፡

ልዩ ሽልማት ለተሰናባቹ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ህብረት ተሰጠ፡፡ ከዚያም ለፕሮፌሰር ገቢሳ እጀታ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተሰጠ፡፡ ፕሮፌሰሩ ንግግር አደረጉ፡፡ ቀጥሎ የእለቱ የክብር እንግዳ ተጋብዘው ንግግር አድርገው የፕሮግራሙ ፍፃሜ ሆነ!

(ይቀጥላል)

 

 

Read 2937 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 12:35