Tuesday, 07 April 2020 00:00

ጠጣሩ እንዲላላ - የሕዳሴው ግድብ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(2 votes)

          ከዘጠኝ ዓመት በፊት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ታላቁ የሕዳሴ ግድብ፣ ጉባ መሬት ላይ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በይፋ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በገለጡበት ዕለት በቦታው ከነበሩት ጋዜጠኞች አንዱ ነበርኩ፡፡ አስቀድሜ እንኳን አደረሳችሁ እላለሁ፡፡
ለነገሩ በዚያን ቀን የግድቡ ሥራ ተጀመረ እንበል እንጂ ከቦታው ስንደርስ የጠበቀን ግድቡ የሚያርፍበት ቦታ ተጠርጎ፣ ዋና ዋና ቦታዎች ምልክት ተቀምጦባቸው፣ ሰራተኞችም ወዲያና ወዲህ እየተራወጡ ነበር፡፡
ዓባይ ውኃ ለዘመናት እየሰነጠቀ ሲያልፍበት የኖረውን አለት ድንጋይ ዘቅዝቆ ለማየት የነበረው የሰው መሯሯጥና መጋፋት፣ ከብዙዎች ፊት ላይ ይነበብ የነበረው ፈገግታና ደስታ የሚረሳ አይደለም:: ጉባ ላይ ሲሳሳቅ የነበረ ሕዝብ አዲስ አበባ ላይ ሲመለስ የጠበቀው የሕዳሴ ግድቡ የፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡ አንደኛው ወገን፤ መንግሥት ግድቡን የጀመረው ያለበትን ተቃውሞ አቅጣጫ ለማሳት ነው ሲል፤ ሌላኛው ደግሞ ሰባ ቢሊዮን ብር የሚጠይቅ ፕሮጀክት እንዴት ሕዝብ ሳይመክርበት ይጀመራል የሚል ነበር:: ብዙ አልገፋም ሰሚም አላገኘም እንጂ  የዓባይን ግድብ እንዲጀመር ያደረጉ ሰዎች፤ ኢትዮጵያንና ግብፅን ለማጣላት የፈለጉ ናቸውም ያሉም ነበሩ፡፡ መንግሥት ዓባይ ዘንድ ምን ወሰደው፤ ሌላ ሌላውን አይገድብም ነበር ያሉም አልጠፋም፡፡ ብዙ ያከራከረውና ያነጋገረው ግን ለምን ሕዝብ ሳይመክርበት ግድቡ ተጀመረ የሚለውና የሕዝብን ተቃውሞ አቅጣጫ ለማስለወጥ ታስቦ የተጀመረ ፕሮጀክት ነው የሚለው ነበር፡፡
መንግሥት ግድቡን “ፕሮጀክት ኤክስ” በማለት ደብቆ ይዞት መቆየቱና ጉዳዩ አስቀድሞ ተገልጦ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን ከተነሳው ተቃውሞ በላይ ተቃዋሚ ኃይል ተፈልፍሎ ሥራው እንዳይጀመር ሊያደርገው ይችል እንደነበር ደጋግሞ የተገለጠላቸው፣ አቋማቸውን አርመው ቀስ በቀስ ወደ ደጋፊነት መግባታቸው ይታወቃል፡፡ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ደግሞ የፖለቲካ ግፊት ማርገቢያ አድርገው ሲያዩ የነበሩትንም አስተሳሰባቸውን እንዲመረምሩ እንዳደረጋቸው መናገር ይቻላል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በሀገር ውስጥ በሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የከረረ የአቋም ልዩነት ማንጸባረቂያ አጀንዳ እየሆነ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በተለያየ ምክንያት ፀረ ሕዳሴ ግድብ አቋም መያዝ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ የሚያስጠላና መገለልም የሚያመጣ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በአንድ ያልታደለች ቀን ለግብፆች መሳሪያ ለመሆን ተሰልፈው የነበሩም ሰዎች፤  በአደባባይ የሚያሳፍር ሥራ ሰርተናል ባይሉም፣ በራሳቸው እያፈሩ ስለመሆኑ ምስክር መጥራት አያስፈልግም፡፡
የሕዳሴ ግድቡን ተቃውሞ መቆም ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም በነበረው ፀረ የጣሊያን ወረራ ባንዳ ሆኖ ከጣሊያን ጎን ከመሰለፍ፣ የጣሊያን መሳሪያ ሆኖ ወገንን ከመግደል፣ ለጣሊያን አድሮ ለጣሊያን የተደገሰን ሞት ከመሞት እኩል ወራዳ ተግባር መፈፀም መሆኑ አያጠራጥርም:: ባንዳዎች የውሻ ሞት ሞተው፣ አርበኛው የአገሩን ነፃነት ለማስከበርና ወራሪውን ጠላት ከአገሩ መሬት ለማስወጣት ያደረገውን ተጋድሎ ሊያስቀሩት እንዳልቻሉ ሁሉ፣ የሕዳሴ ግድብ ተቃዋሚዎችም ፍፃሜ ከዚህ ያለፈ አይሆንም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡
የግድቡ ግንባታ ወደፊት እየተራመደ ነው፡፡ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ደጋግመው እየገለፁት ያለው ጉዳይ፤ በ2012 ዓ.ም ክረምት ውኃ መያዝ እንደሚጀምር፤ በቀጣዩ ዓመት ላይም የመጀመሪያዎቹ ሁለት የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ሥራ የሚጀምሩ መሆናቸውን ነው፡፡
የግድቡ ግንባታ፣ የውኃ መሙላቱና ኃይል ለማመንጨት የሚደረገው እንቅስቃሴ እየቀጠለ፣ መንግሥት ከግብፅና ከሱዳን ጋር የሚያደርገውን ድርድር እንደሚገፋበትም ክቡር ሚኒስትሩ አያይዘው አስረድተዋል:: ኢትዮጵያ የራሷ የመደራደሪያ ሰነድ እያዘጋጀች መሆኑም ተመልክቷል፤ በሰሞኑ የክቡር ሚኒስትሩ መግለጫ፡፡
‹‹አበው አስተውሎ ላያት ሽምብራም አፍንጫ አላት›› ይላሉ፡፡ የሕዳሴው ግድብ ውኃ የሚይዝበትና ውሃ የሚለቅበት ሁኔታ ዋና መደራደሪያ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ቀደም ብለው የተደረጉት ድርድሮች የፈረሱት በዚህ ጉዳይ ላይ በተፈጠረ የመጠንና የጊዜ ልዩነት መሆኑ ይታወቃል፡፡
የውኃ ድርሻ ክፍፍል ድርድር፤ በሦስቱ አገሮች መካከል የሚደረግ ሳይሆን በናይል ኢንሽየቲቭ አገሮች መካከል የሚመከርበት ጉዳይ መሆኑ በሚኒስትሩ ተመልክቷል:: ውኃ መያዝ ድርሻን ማስቀረት፤ ውኃ መልቀቅ ድርሻን መስጠት፤ በሌላ ቋንቋ፤ የውኃ ክፍፍል የማይሆንበት መመዘኛ ምንድን ነው? ብዬ እራሴን ስጠይቅ መልስ ለማግኘት ይቸግረኛል፡፡ ግብፅ ድርቅ ሆኖ የአስዋን ግድብ እንዳይጎድል፣ ኢትዮጵያ ውኃ መያዝ የለባትም ስትል የውኃ ድርሻዬን እንዳትነኩ አላለችም ማለት ነው?
የሕዳሴው ግድብ የመጀመሪያውን 4.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ከመያዙ በፊት ስለ አሞላሉ መስማማት አለብን ስትል፣ “በራሳችን ውኃ እስቲ ንክች” እያለች አይደለምን? ለእኔ የሕዳሴ ግድብ ውኃ መሙላትና በውኃ ልቀት ላይ የሚደረግ ድርድር በጀርባው ያዘለው የውኃ ድርሻ ክፍፍልን በመሆኑ አጥብቆ መቃወም ያስፈልጋል እላለሁ፡፡
በዚህ አጋጣሚ መንግሥት አዲስ የትግል መስመር መጀመር እንዳለበት መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ ያ የትግል መስመር ደግሞ ግብጾችን አልፎ የአረቡን አለም የሚመለከት መሆን አለበት፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት በዚሁ ጋዜጣ ላይ ያቀረብሁት የኡስታዝ አህመዲን ጀበል ንግግር አንድ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጥያቄ ሃይማኖታዊ ድጋፍ ያለው መሆኑን አስገንዝቧል፡፡ በእሱ መንገድ ብዙ መራመድ ይገባል፡፡
በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያንን አስተባብሮ፣ ለአረቡ አለም በአረብኛ ቋንቋ የኢትዮጵያን ፍላጎት እንዲያስረዱ ማድረግ ከመንግስት ይጠበቃል:: ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን የገነባችውና እየገነባችው ያለው፣ ለኃይል ማመንጫ ለመጠቀም ብቻ መሆኑን በማስረዳት ዘመቻ መክፈት ያስፈልጋል:: የግብፅን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በአፀፋ ፕሮፓጋንዳ ማፍረስ ግድ እንጂ ምርጫ አይደለም፡፡
ይህ መንግሥት ብቻ የሚሰራው ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊረባረብበት የሚገባው ጉዳይም ነው፡፡
አልሳካ ብሎ ነገሩ ሲጠጥር
               ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር - አለ ገሞራው፡፡
በዚህ አጋጣሚ፤ አቶ መለስ ዜናዊንና ኢንጂነር ስመኘው በቀለን በአክብሮት እያሰብኩ፤
“ድል ለኢትዮጵያውያን” እላለሁ!


Read 7416 times