Sunday, 05 April 2020 00:00

እውን የኮሮና ቫይረስን ለመመከት የሚያስችል አደረጃጀትና ብቃት አለን?

Written by 
Rate this item
(4 votes)

  ግልጽ ደብዳቤ ለኢንጅነር ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ

          ክቡርነትዎ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተሾሙ ጊዜ ጀምሮ በከተማዋ የተጠራቀመውን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ እያደረጉት ያሉትን አርአያነት ያለው ተግባር በከፍተኛ አድናቆት ነው የምንመለከተው። ይኸን አበረታች ጅምር ዳር ለማድረስ እኛም እንደ ከተማዋ ነዋሪና ባለሙያ የበኩላችንን ማድረግ አለብን ብለን እናምናለን።
ክቡር ከንቲባ፤ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መከሰቱ ከተሰማ ወዲህ መንግስት ሥርጭቱን ለመግታት የሚያስችል መጠነ ሰፊ ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆኑን የሥራው አካል በመሆናችን በቅርብ የምናውቀው ነው፡፡
ለክቡርነትዎ ይኸን ግልፅ ደብዳቤ ለመፃፍ የተነሳንበት ዋናው ምክንያትም ይኸው ከቅን ሀሳብ፣ የሙያ ግዴታ፣ ወቅቱ የሚጠይቀውን ቆራጥ አመራር አስፈላጊነትና በእከክልኝ ልከክልህ መሸፋፈን በሕዝባችን ላይ የሚያስከትለውን ችግር ግምት ውስጥ በመክተት፣ እንደዚህ ቀደሙ በፍርሀት ዝም ማለት ስላልቻልን፣ የራሳችንን ህይወት አደጋ ላይ ጥለን፣ ህብረተሰቡን ለማዳን መሆኑ እንዲታወቅ እንፈልጋለን፡፡ እርስዎም ከዚህ በመነሳት ሀገርና ህዝብ የጣለብዎትን አደራ እንደሚወጡ በሚገባ እናምናለን፡፡
ክቡርነትዎ፤ እኛ የጤና ባለሙያዎች በአያሌው ያሳሰበን ይኸን ወረርሽኝ በበላይነት ለመምራት ከባድ ኃላፊነት ከተጣለባቸው ተቋማት ግንባር ቀደሙ የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ፣ በአቅም ማነስና በብልሹ አሠራር ችግሮች የተተበተበ መሆኑ ነው። በዚህ ምክንያት ቢሮው በዚህ ወቅት ይህን ከባድ ኃላፊነት እንደምን ይወጣል የሚለው በብርቱ አሳስቦናል፡፡
እርግጥ ነው፤ ክቡርነትዎ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ የጤና ቢሮ ቁልፍ አመራሮችን ሹም ሽር አድርገዋል። ነገር ግን በአሁን ሰዓት የመጣብንን ከባድ የወረርሽኝ አደጋ ለማሸነፍ አሁን እየተወሰዱ ካሉ ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች በተጨማሪ፣ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አደረጃጀትና የሰው ኃይል ዝግጁነትን መፈተሽ በሚከተሉት ምክንያቶች ወሳኝ ነው ብለን እናምናለን፡፡
1ኛ. ነርስ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች፣ በዚህ አስፈላጊ ወቅት የት ነው ያሉት?
በዓለም አቀፍ ደረጃ በዚህ ሰዓት ከፍተኛ የጤና ባለሙያዎች እጥረት ማጋጠሙ እሙን ነው፡፡  በሀገራችን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፣ በትምህርትና በጡረታ ላይ ያሉትን የጤና ባለሙያዎች ጨምሮ በተጠንቀቅ ለሀገር ግዳጅ ተዘጋጅታችሁ ተጠባበቁ ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ ሆኖም የአዲስ አበባ የጤና ቢሮ፣ ከደሀ ማህበረሰባችን በሚሰበሰብ ቀረጥ ደሞዝ ተከፍሏቸው የሚሰሩትን ነርስ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ወደ ሥራ ማስገባት አለመቻሉ፣ እንደ ባለሙያም ሆነ እንደ ዜጋ እያየን ቸል ማለት የሙያ ሥነ ምግባራችን የሚፈቅድልን አይደለም፡፡
በአዲስ አበባ ደረጃ በሽታን አስቀድሞ መከላከልን ቅድሚያ የሚሰጠው የጤና ፖሊሲያችንን መሠረት በማድረግ፣ ለ500 አባወራ ቤተሰብ አንድ ነርስ የጤና ኤክስቴንሽን ተመድቦ፣ የቤተሰቡን አጠቃላይ የጤና ሁኔታ እንዲከታተል መደረጉና  ጅምር ላይ አኩሪ ሥራ መሠራቱ ይታወሳል:: ሆኖም ግን ይህን አደረጃጀት በንዑስ የሥራ ዘርፍም፣ በቅርቡም በዳይሬክተር ደረጃ የሚመሩት አካላት፣ በሸፍጥ የጤና ኤክስቴንሽን ክፍልን መምራት ከጀመሩበት ሰዓት ጀምሮ፣ ሥራውን በተገቢው ደረጃ ከፊደራል ጤና ሚኒስቴርና አጋር ድርጅቶች የሚደረጉትን ድጋፍና ግብዓቶች በአግባቡ ተጠቅሞ ሥራ እንዳይሰራ በማድረጋቸው በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የነርስ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያ (የቤተሰብ የጤና ቡድን) በየቤቱ በር አንኳኩተው የማስተማር፤ የመለየት ብሎም የመከላከል ሥራቸውን  በአግባቡ እንዳይወጡ ሆኗል፡፡ ስለሆነም በዚህ ወቅት ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች የተመደበ ነርስ (የቤተሰብ የጤና ቡድን) ካየናቸው፤ ካነጋገርናቸውና ካወያየናቸው ስንት ጊዜ እንደሆነ፣ እርስዎ ከታች ያለውን ህዝብ እንዲያነጋግሩና ሃቁን እንዲረዱት እንጠይቃለን::
በከተማ ጤና ቢሮ ደረጃ ይኸን ሥራ የሚመራው ዘርፍ፣ ለሥራው የሚያስፈልገውን ግብዓትና ተልዕኮ ሰጥቶ የማሰማራት ውስንነቶች የተነሳ ህዝቡ የሚገባውንና መብቱ የሆነውን አገልግሎት እንዳያገኝ አድርጎታል፡፡ የቢሮው ከፍተኛ አመራር ይህ ሥራ ያለበትን ክፍተት ተረድቶ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ በተለያየ ወቅት ችግሮቹን ያመላከትን ቢሆንም፣ በማናውቀው ምክንያት ተገቢው የማስተካከያ እርምጃ አልተወሰደም፡፡
2ኛ. የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ በከተማችን በዋናነት የሚመለከተው  የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ተቋም የት ገባ?
ማንኛውም ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ ድንገተኛ የጤና አደጋዎች፣ በዓለም ደረጃና በየትኛውም ሀገራት ከመከሰታቸው በፊትና ከተከሰቱ በኋላ፣ በቀጥታ ሥራውን ወስደው የሚሰሩ የሚመለከታቸው አካላት አሉ:: ለምሳሌ የዓለም ጤና ድርጅት፣ በዚህን ወቅት የኮሮና ወረርሽኝን በዓለም ደረጃ በመምራትና ሥራዎችን በማስተባበር ላይ የሚገኝ ተቋም ነው::  በአሜሪካ፤ በቻይና፤ በአውሮፓ፤ በአፍሪካ  እንዲሁም በሌሎች ሀገራት ይኸንን የሚመራ ተቋም  ሲዲሲ (የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል) ይባላል፡፡ ወደ ሀገራችን ስንመጣ፣ ይህ ዓለም አቀፋዊ የአሠራር ሂደትን ተከትሎ፣ በፌደራልና በክልሎች (አማራ፤ኦሮምያ፤ ትግራይ..) የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተቋቁሞ፣ ለህብረተሰቡ እስከ ታች ድረስ የመረጃ ፍሰቱንና የሥራ ሂደቱን እያቀላጠፈ፤ እየመራና እያስተባበረ እንዳለ ይታወቃል:: ሆኖም ግን የአለም  የዲፕሎማቶች መቀመጫ፣  የአፍሪካ መዲና እና  መግቢያ በር የሆነችው ከተማችን አዲስ አበባ ሆን ተብሎ ይኸ ተቋም እንዳይኖራት ተደርጓል፡፡
ከተማችን እንደ ኮሮና ላሉ ወረርሽኞች ተጋላጭነትዋ ከፍተኛ ይሆናል በሚል ታሳቢ ተደርጎ ከሌሎቹ የሀገራችን ክልሎች በተለየ  ለአፍሪካዊያን ብሎም ለዓለም ሞዴል በሚሆን መንገድ  የአዲስ አበባ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የማuuሚያ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ፣ ቀደም ሲል ለነበረው የአስተዳደሩ ካቢኔ እንደቀረበ ይታወሳል፡፡ ራሱን ችሎ እንዲደራጅ ብዙ ከተራመደ በኋላ የጨነገፈው በቢሮው ውስጥ ተደራጅተው የተሰገሰጉ፤ ወረርሽኝን እንደ አንድ የገቢ ምንጭ የሚቆጥሩ አካላት፤ ይህ አደረጃጀት ከእኛ እጅ ከወጣ ጥቅማችን ይቀርብናል ከሚል የዘቀጠ አስተሳሰብ በመነሳት በሰሩት ደባ ነው። ይኸ ተቋም ራሱን ችሎ ተደራጅቶ ቢሆን ኖሮ፣ እንዲህ እንደ ኮሮና አይነት ወረርሽኝ ሲከሰት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ትልቅ አቅም መሆን በቻለ  ነበር። ይህንን ማረጋገጥ ይችሉ ዘንድ በእርስዎ ጽ/ቤት የተቋሙን ማቋቋሚያ ሰነድ አስወጥተው ሊያዩት እንደሚችሉ እናስታውሳለን:: በዚህም አጋጣሚ መልካም ፈቃድዎ ከሆነ፣  ከተማዋ የሚገባትን የተደራጀና የተቀናጀ ብሎም ራሱን የቻለ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲያቋቁሙልን እንጠይቃለን፡፡
በተጨማሪም፤ በተለያየ ወቅት የተከሰቱት ወረርሽኞች (ለምሳሌ አተት)ላይ በተግባር ተፈትኖ፣ ውጤታማ የሆነና ልምድ ያለውን የድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች፣ እስከ ወረዳ የሚወርደውን መዋቅር፣ ለህዝብ ግድ በሌላቸው ሰዎች ምክንያት፣ ሆን ብለው በወረዳ ብሎም በክፍለ ከተማ ደረጃ አደረጃጀቱን ወደ ራሳቸው የሚመሩት ክፍል ስር በመውሰድ፣ ትኩረት ተነፍጎት እንዲዳከም ተደርጎ፣ ወረርሽኝ በመከላከልና በመቆጣጠር ልምድ ያካበተውን ባለሙያ እንዲበተን አድርገውታል፡፡ ይህም ድርጊት የሚያስከትለውን የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቀድመው የተረዱት እነዚህ  ባለሙያዎቹ፣ እስከ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ድረስ ሄደው በአስቸኳይ ይህ ችግር እንዲስተካከል በጠየቁት መሠረት፣ በወቅቱ የነበሩት የጤና ሚኒስትር የተቋሙ መታጠፍ አደጋ እንዳለው ተገንዝበው፣ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ደብዳቤ የጻፉ ቢሆንም፣ በተገቢውና በሚገባው መንገድ  ሳይስተካከል፣ ልምድ ያለው ሠራተኛ እንደተበተነ ቀርቷል፡፡  
አሁን በዚህ የኮሮና ወረርሽኝ ወቅት በቀጥታ ሥራውን ተረክቦ መሥራት፤ ማስተባበርና ማቀናጀት ብሎም መምራት የነበረበት ይህ አደረጃጀት በመዳከሙ፣ ሥራዎች በየአካባቢው በተቀናጀና በተሰናሰለ ሁኔታ  እንዳይካሄዱ እየሆነ ነው:: ከብዙ በጥቂቱ ቤት ለቤት የበሽታውን ምልክት የሚያሳዩ ሰዎችን አስሶ የማግኘትና (active surevilance) ተጠርጣሪውን ከህብረተሰቡ የመለየት ሥራ እየተሰራ አይደለም:: በሌሎች ዓለማት እንደምናየው የቤት ለቤት የሙቀት መለካትና በተለያዩ ቦታዎች  የሙቀት ልየታ ጣቢያዎችን በማቋቋም ሥራ አለመሰራቱ የሚታይ ሀቅ ነው፡፡
በየወረዳው የበለጠ ተጋላጭ ቦታዎች (Vulnerability assessment and risk mapping) ተለይተው የመከላከል ሥራ ሲከናወንም አይስተዋልም፡፡ ለምሳሌ ለዚህ ወረርሽኝ ተጋላጭ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ የህብረተሰብ በአንድነት ተከማችቶ የሚገኙባቸው ቦታዎች እንደ ኮንዶሚኒየምና የተጠጋጉ የመኖርያ ቤቶች እንዲሁም የንጹህ ውሀ እጥረት ያለባቸው ቦታዎች ከብዙ በጥቂቱ እንደሆኑ ቢታወቅም፣ እስከ ዛሬ ድረስ በግልጽ በሰነድ በተደገፈ መሠረት ለዚህ ወረርሽኝ የበለጥ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችና የመከላከያ መንገዶች  (ለምሳሌ የውሃ እጥረት ያለባቸው ቦታዎች ላይ በቦቴ ውሃ እንዲቀርብ የማስተባበር ስራ ሲሰራ አይታይም) ተለይተው ተገቢው ሥራ አለመከናወኑ የዚህ ተቋም እንዲዳከም መደረግ አንድ መገለጫ ነው፡፡
በተጨማሪም በእግር ኳስ ደጋፊዎችና ከተለያየ የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ የበጎ ፍቃድ አገልጋዮች በሚገርም ሁኔታ የሚያሳዩትን ተነሳሽነትና በጎ ተግባር አቀናጅቶና በሙያ ደረጃ ያለሙለትን የበሽታ መከላከል ጥረታቸውን አስተባብሮና አቀናጅቶ ሃሳባቸው ከግብ እንዲደርስ የሚመራው ተቋምና ተገቢው ባለሙያ ባለመኖሩ ወይም ስራው ባለመስራቱ ምክንያት በጎ ፍቃደኞቹ በገባቸው ልክ የሰሩት ስራ እራሳቸውን ብሎም ህብረተሰቡን ለበሽታው የመጋለጥ አደጋ ውስጥ እንዳይከት ሥጋት አለን:: ይህንን ስንል የበጎ ፍቃድ አምባሳደሮቻችን ጥረትና ተነሳሽነት ተገቢው ዋጋ የሚሰጠው መሆኑን ሳንዘነጋ፣ ለወደፊቱ ለሚደረጉ ሥራዎች ሙያዊ ድጋፍና ክትትል ቢታከልበት፣ የበለጠ ወደ ጋራ ግባችን ያደርሰናል ከሚል አለማቀፋዊ አስተሳሰብ ተነስተን ነው፡፡
በሀገራችን ውስጥ ያሉ ክልሎችና የድሬደዋ የከተማ አስተዳደር የየራሳቸው የሆነ የአስቸኳይ ጊዜ ስልክ (Hote line) ያላቸው ሲሆን ይህን ማድረጋቸው በክልላቸው የሚከሰቱ የበሽታ የመጋለጥ ጥርጣሬዎችንና ጥቆማዎችን በአፋጣኝ ለጥሪው መልስ ለመስጠትና የበሽታውን መስፋፋት በጊዜ ለማቋረጥ እንዲያስችላቸው ነው፡፡ ከሁሉም ክልሎች የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ብቻ የራሱ የሆነ የአስቸኳይ  ጥሪ ስልክ የሌለውና በዚህም ምክንያት በአሁኑ ሰዓት እንደሚታየው የክልሉን በሽታ የመለየት ሥራ በራስ አቅም መሥራት አለመቻል፣ በፌደራሉ የስልክ መስመር ላይ የተደራሽነት ችግር እንዲባባስ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው::
ክቡርነትዎ፤ አሁን በዚህ ሰዓት በጠረጴዛዎ ላይ ይህንን በሽታ ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦች፣ አካባቢዎች፣ በሽታን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ግብአቶች የሰው ኃይልንና መፍትሄዎችን ጨምሮ የትና መቼ እንዴት የሚሉት  የከተማችን የኮሮና ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ዝርዝር አቅድ አግኝተዋል ወይ? በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ መሠረት የተገመተ ለበሽታው ሊጋለጡ የሚችሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ቁጥርና እነሱን የምናስተናግድበት የለይቶ ማቆያ ሥፍራዎች፣ የአልጋ ብዛት፣ በተለይ ህሙማንን የምንታደግበት ቬንትሌተር በምን ያህል ደረጃ አይነትና ጥራት ተዘጋጅተው በተጠንቀቅ ላይ እንዳሉ የሚያሳይ ሰነድ አልዎት ወይ?
በአጠቃላይ ሲታይ በአሁኑ ሰዓት ከወረርሽኝ ጋር የተያያዙ ቴክኒካል ሥራዎች እየተሰሩ ያሉት በፌዴራል ጤና ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሙያተኞች ነው:: በከተማ ደረጃ በዚህ ተቋም መሰራት ያለበትን ሥራ ሙሉ በሙሉ በተደራቢነት እየሰሩ ያሉት እነዚህ አካላት ናቸው፡፡ ይህ ተክቶ መስራት  በሽታው በአገራችን በከፍተኛ ደረጃ እየተሰራጨ ከሄደ ቀጣይነት የሌለው በመሆኑ  ይህንን ተቋም ማጠናከርና  በተገቢው ሁኔታ ራሱን ችሎ ወደ ሥራ በአስቸኳይ ማስገባት፣ በተለይ በዚህ ወቅት በይደር የሚተው ተግባር መሆን የለበትም፡፡
3ኛ.ቢሮው በኪራይ ሰብሳቢነት የተተበተበ መሆኑ፣
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ረዘም ካለ ጊዜ ጀምሮ በጥቅም ተሳስረው የራሳቸውን ኔትወርክ በዘረጉ፣ በሙስና እና ብልሹ አሰራር በደረጁ ግለሰቦች የተሞላ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በኮሮና ወረርሽኝ ህዝብ ከባድ ሥጋት ውስጥ በወደቀበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት፣ የጤና ቢሮው፣ የሌብነት ኔትወርክ የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ መሯሯጥ የዕለት ስራው ሆኗል።
ለአብነት ያህል እንደ ሀገር ለዚህ በሽታ የሚውል የገንዘብ እርዳታ በአንድ ቋት ውስጥ ብቻ እንዲሰበሰብ የወጣ አቅጣጫ የወረደ ቢሆንም፣ ይህ ቡድን ግን በስሩ ያሉትን መንግስታዊ ያልሆኑ በጤና ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች (NGO) ፕሮግራማቸውን አጥፈው፣ ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ገንዘባቸውን ገቢ እንዲያደርጉ አዟል፡፡ ይህ በመሠረቱ በአስተሳሰብ ደረጃ ተገቢ ነው፤አይደለም የሚለውን ትተን በተለምዶ ከዚህ በፊት በተለያየ ጊዜ በከተማችን በተከሰቱ ወረርሽኞች እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ ትዕዛዝ እየተላለፈ፣ በዚሁ አካል ገንዘቡ ለታሰበለት ዓላማ አለመዋሉን መታዘብ ችለናል (በተደጋጋሚ ተከስቶ የነበረ የአተት ወረርሽኝን መጥቀሱ ብቻ በቂ ነዉ)፡፡
ክቡር ከንቲባ ሆይ፤ ከዚህ ቀደም በተከሰቱ ወረርሽኞች፣ በጤና ተuማት ወረርሽኙን በመከላከልና በማከም ለተሳተፉ ባለሙያዎች የትርፍ ሰዓት ክፍያዎች ማስፈጸሚያ የተበጀተውን በጀት በማን አለብኝነትና በኔትወርክ ትስስር ቡድናቸው በመጥቀም፣ ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው በማዋላቸው ተገቢውን ሥራ ሰርተው ክፍያ ባላገኙ ሠራተኞች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታና አለመተማመን መፍጠሩ ይታወቃል፡፡
ይኸም ጉዳይ የሚመለከተው ሠራተኛ፣ ኮሚቴ አዋቅሮ፣ እስከ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከንቲባ ጽ/ቤት ድረስ ቅሬታ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ይህንን የፈጠረው አመራር፣ አሁንም በቦታው ላይ የበለጠ ተደራጅቶ የሚገኝ በመሆኑ በቀጣይ በዚህ ወረርሽኝ ላይ የባለሙያውን ሙሉ እምነትና የአመራር ተቀባይነት አግኝቶ ለመምራትና ለማስተባበር የሞራል ብቃት የለውም:: ስለዚህም እንዲህ ዓይነቱ ዓይን ያወጣ የሙስናና ብልሹ አሠራር እንዳይደገምና በወረርሽኝ መከላከል ሥራ ላይ ተጽእኖ እንዳያሳድር፣ እስከ ዛሬ ያልተነካውንና ከሥር ተሰግስጎ የሚገኘውን የሌብነት ኔትወርክ መበጣጠስና ብልሹ አመራሮችን ማስወገድ፣ ወረርሽኙን የመከላከል አንዱ አካል ተደርጎ መወሰድ አለበት ብለን እናምናለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ በአሁኑ ሰዓት በአገራችን ያጋጠመንን የኮሮና ወረርሽኝ፣ ከህዝባችን ጋር በመሆን እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ በመክፈል በነፃ ለማገልገል ያለንን ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡
4ኛ. የጤናው ሴክተር አመራር እውነታ፣
ክቡር ከንቲባ፤ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በዋነኝነት የሚመለከታቸው በአዲስ አበባ ጤና ቢሮው ሁለት ዳይሬክቶሬቶች አሉ። እነሱም የጤና ማበልጸግና በሽታ መከላከል ዳይሬክቶሬትና የህብረተሰብ ጤና ምርምርና ድንገተኛ አደጋዎች ዳይሬክቶሬት ይባላሉ። እነዚህ ሁለት ቦታዎች እንደተለመደው እስከ አሁን በከተማችን እንዲሁም በሴክተራችን እንደምናየውና እንደምንታዘበው፣ አቀናጅቶና አደራጅቶ የመምራት ችግር እንዳለ ይታወቃል:: በተለይ ደግሞ በዚህ ወሳኝ ወቅት ከአቅም በታች በሆነ የአመራር ሁኔታ እንዲጓዙ መፍቀድ እስከ ዛሬም ድረስ ዋጋ አስከፍሎናል፤ ለወደፊቱም ከፍተኛ ዋጋ እንዳያስከፍለን የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ እንጠይቃለን፡፡  
በተጨማሪም፣ በአስሩም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች፣ የጤና ጽ/ቤቶች ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ ያሉ አንዳንድ አመራሮች፣ ከጤናው ሴክተር ጋር ግንኙነት የሌለው ሙያ ያላቸው በመሆኑ  በዚህ ፈታኝ ወቅት ይህን ወረርሽኝ ለመምራት አሉታዊ ተጽዕኖ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ዋጋ ስለሚያስከፍሉ፣ የሠራተኛውን ቅሬታ በመፍታት ማስተካከያ እርምጃ መወሰድ አለበት ብለን እናምናለን፡፡
ከቻይና ተሞክሮ እንደምናየው፤ ወረርሽኙ በተከሰተበት ሁቤ ግዛት ላይ የአመራር ማስተካከል እርምጃ በመወሰዱ የተነሳ በአሁኑ ሰዓት በሽታውን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ መቆጣጠር የቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: ስለሆነም ሁሉም አደረጃጀት ተፈትሾ በጤና ሙያ ብቻ ሳይሆን በሥነምግባር ታማኝነት ያተረፉና ወረርሽኝን መምራት የሚያስችል የትምህርት ዝግጅትና ልምድ ያላቸው አመራሮች ወደፊት ማምጣት በበሽታው የሚመጣውን አደጋ ለመቀልበስ አማራጭ የሌለው መንገድ መሆኑን አጥብቀን እንመክራለን፡፡ ይኸንን ማድረግም ከሀገር ወዳድና ለህዝብ አለኝታ ከሆነ መሪ የሚጠበቅ ነው፡፡  
በአጠቃላይ ስናየው አሁን ያለው ክፍተት የመጣው በሀገራችን ብሎም በከተማችን የተጀመረው ሪፎርም ገና ጅምር በመሆኑና ዳር ለማድረስ ጊዜ ስለሚጠይቅ መሆኑን እንረዳለን:: በዚህ አጋጣሚ በሴክተሩ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ከጅምሩ የተጠለፉ በመሆናቸው ሪፎርሙን ማዳን፣ እንደ አንድ ተግባር ተደርጎ እንዲወሰድ እንጠይቃለን፡፡
አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው፣ አገራዊ ለውጡ ያልጎበኘው፣ በጥቅም ኔትወርክ የተሳሰረው ቡድን በዚህ ፈታኝ ወቅትም የራሱን ሂሳብ የሚያሰላ፣ የገጠመንን አገራዊ ችግር ከርሱ ጥቅም አንፃር እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ያሰፈሰፈ መሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ኮሮናን ለመከላከል የሚያደርገውን መጠነ ሰፊ ጥረት የሚያመክን ነውና ጉዳዩን በጥንቃቄ በማየትና ተገቢውን ምልከታ በማድረግ፣ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ ምክራችንን እንለግሳለን።
ይኸን በማስተካከል የጤና ባለሙያው ለከተማው ህብረተሰብ ቤት ለቤት ድረስ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላትና ከህዝባችን ጋር በጋራ በመሆን የሚታይና ተጨባጭ የሆነ ሥራ እንድናደርስ ያስችለናል፡፡
መልካሙን ሁሉ ለከተማችን፣ ለሀገራችን ብሎም ለአለማችን ህዝብ እንመኛለን!
(ከተቋርቋሪ የጤና ዘርፍ ሙያተኞች)


Read 6275 times