Sunday, 05 April 2020 00:00

መጪዎቹ ሁለት ሳምንታት የበለጠ ፈታኝ ይሆናሉ ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

  - በአገሪቱ አራቱም አቅጣጫ የሚገባም የሚወጣም የሕዝብ ትራንስፖርት የለም
        - አትክልት ተራን ጨምሮ ሰው የሚበዛባቸው የገበያ ሥፍራዎች እየተነሱ ነው
        - ክልሎች የየራሳቸውን የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ላብራቶሪ ስራ አስጀምረዋል
        - ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥሪ አቅርበዋል
       - ኮሮናን ለመከላከል ባለሀብቶች ድጋፍ እያደረጉ ነው
            
              ሕብረተሰቡ አሁን ባለው አካላዊ መቀራረብ የሚቀጥል ከሆነና ከዓለም ጤና ድርጅትና ከመንግሥት የሚሰጡትን አካላዊ ርቀትን ተግባራዊ የሚያደርግ ከሆነ መጪዎቹ ሁለትና ሶስት ሳምንታት ለኢትዮጵያውያን የበለጠ ፈታኝ እንደሚሆንና ሊያስከትለው የሚችለው ጉዳትም እጅግ እንደሚከፋ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ እርምጃዎችን መገምገማቸውን ገልፀው፤ ሕብረተሰቡ አካላዊ ርቀቱን በመጠበቅ የበሽታውን ስርጭት መስፋፋት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት በማገዙ በኩል እያከናወነ ያለው ተግባር እጅግ አሳሳቢ መሆኑ እንደታየ አመልክተዋል፡፡ በተለይም በገበያ ስፍራዎች፣ በጎዳናዎችና በትራንስፖርት መገልገያዎች ውስጥ አሁንም አካላዊ ርቀትን የመጠበቁ ጉዳይ ተግባራዊ አለመደረጉ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል ብለዋል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የሚያስከፍሉት ዋጋ እጅግ ከባድ በመሆኑ መንግሥት አካላዊ ርቀትን የማስጠበቁን ተግባር በሕግ አስከባሪ አካላት በኩል በግድ እንደሚያስፈጽምም አስታውቀዋል። በመንግስት የወጣውን አካላዊ ርቀት የማስጠበቅ ተግባር ለማከናወን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በርካታ ሕዝብ የሚሰበሰብባቸውን የገበያ ስፍራዎች ለጊዜው ሰፊ ቦታ ወዳላቸው ሌሎች ቦታዎች የማዛወሩን ሥራ መጀመሩንም ይፋ አድርጓል፡፡ በዚሁ መሰረትም የፒያሳውን የአትክልት ስፍራ ከሰኞ መጋቢት 28 ቀን2012 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ጃንሜዳ የሚያዛውር መሆኑን አመልክቷል፡፡ በቀጣይነትም ሌሎች ሰው የሚበዛባቸውን የገበያ ቦታዎች የነዋሪውን እንቅስቃሴ በማይረብሽ መልኩ የማዛወሩን ሥራ የሚቀጥል መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ፤ ምዕመናን በቤታቸው ተወስነው ፀሎት እንዲያደርጉና ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚካሄዱ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በተወሰኑ ካህናት ብቻ እንዲያደርጉ፣ አገልግሎቱን የሚሰጡ ካህናትም በቤተ ክርስቲያናቱ ውስጥ እንዲቆዩና የምግባቸውም እዛው እንዲቀርብ እንዲደረግ ውሳኔ አሳልፋለች:: ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባ አገረ ስብከት ውስጥ የሚገኙ መንፈሳዊ ኮሌጆች፤ የካህናት ማሰልጠኛዎችና ትምህርት ቤቶች ለማቆያነት እንዲያገለግሉ ወስናለች፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ በአገራችን ስርጭቱ እየጨመረ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመግታት ቤት ውስጥ የመስገድ ሃይማኖታዊ ፈት (ብያኔን) ባለፈው ማክሰኞ ሰጥቷል:: የበሽታው ስርጭት ፍጥነትና አስቸጋሪነት የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የጁምአና የጀመአ ሶላትን ለማስቆም የሚያስገድድ ሸሪአዊ ምክንያት በመሆኑ ከመጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በሽታው በሰው ልጅ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት መቆሙ በጤና ባለሙያዎች እስከሚረጋገጥ ጊዜ ድረስ የጁምአ ሶላት ታግዶ እንዲቆም የዑለማ ምክር ቤት መወሰኑን ይፋ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትም በጋራ የሚደረጉ አምልኮና ፀሎት እንዲቋረጥ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የፀረ ተህዋስያን መድሃኒት ርጭት ሰሞኑን አከናውኗል፡፡ በትራንስፖርቶች ላይ የሚታየውን መጨናነቅ ለመቀነስም አንበሳ አውቶቡስ በነጠላ አውቶቡሱ 30 ሰዎች፤ በተደራራቢ አውቶብሶቹ ደግሞ 50 ሰዎችን ብቻ እንዲያሳፍር ተወስኗል፡፡
ቤተ እምነቶች የአምልኮና የፀሎት ተግባርን በየቦታቸው ማከናወናቸውን ማቋረጣቸውን ተከትሎ መስተዳድሩ የስበት ቅዳሴ፣ የጁምአ ሶላትን፣ የወንጌላውያንና የአድቬንቲስት አብያተ ክርስቲያናትን አምልኮና ፀሎትን በመስተዳድሩ የቴሌቪዥን ጣቢያ /በአዲስ ቲቪ/ እንደሚያስተላልፍ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ አስታውቀዋል፡፡
በዓለማችን ሚሊዮኖችን ያጠቃውንና ከሃምሳ ሺ በላይ የሚሆኑትን ለሞት የዳረገው የኮሮና ቫይረስ በሽታ በአገራችን መከሰቱ ከታወቀበት ከመጋቢት 4 ቀን2012 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው በሽታው እንዳለባቸው ከታወቁት 35 ሰዎች መካከል ሶስቱ ማገገማቸውንና ሁለቱ ጃፓናውያን ወደ አገራቸው መላካቸውን እንዲሁም ሃያ አራት የሚሆኑት በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደሚገኙ ያስታወቀው የጤና ሚኒስቴር፤ በጡረታና በተለያዩ ምክንያቶች ከስራ የተገለሉ የጤና ባለሙያዎች፣ በጤና ሙያ ተመርቀው ወደ ሥራ ያልተሰማሩ ተመራቂዎች፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና በመንግሥትና በግል ኮሌጆች ውስጥ የሚማሩ የጤና ተማሪዎች ከመጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በጤና ሚኒስቴር ድረ ገጽ እንዲመዘገቡ አገራዊ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ወደፊት የወረርሽኙ ሁኔታ እየከፋ ከመጣ በርካታ የበጎ ፈቃድ ባለሙያዎችን ማሰማራት ስለሚያስፈልግ ባለሙያዎቹ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡም አሳስቧል፡፡
በአገራችን እስካሁን ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተረጋገጡት 35 ሰዎች መካከል ሶስቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት ሲሆኑ የ61 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ፣ የ48 ዓመት ጎልማሳና የአስራ አራት ዓመት ታዳጊ እንደሆኑም ታውቋል:: በትናንትናው ዕለት በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡት ስድስት ሰዎች መካከል አምስቱ በአዲስ አበባ ከተማ አንደኛው ደግሞ በድሬዳዋ ከተማ፣ ውስጥ የተገኙ መሆናቸውንና ሁለቱ ከዱባይ የመጡ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ የጉዞ ታሪክ የሌላቸው እንደሆኑ ተመልክቷል፡፡  
እስካሁን ድረስ ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጡት ከውጪ የገቡ ሰዎች የለይቶ ማቆያ ስፍራዎቹ ተግባራዊ ከመደረጋቸው በፊት የገቡ መንገደኞች እንደሆኑም ተገልጿል፡፡ መጋቢት 14 ቀን2012 ዓ.ም በወጣው መመሪያ መሰረት/ ሁሉም ከውጪ አገራት የሚገቡ መንገደኞች ለአስራ አራት ቀናት ተለይተው የሚቆዩባቸው ሆቴሎችና የለይቶ ማቆያ ስፍራዎች ተዘጋጅተው መንገደኞቹ ወደዚሁ የለይቶ ማቆያ ስፍራዎች እንዲገቡ እየተደረገ ቢሆንም፣ ከእነዚህ የለይቶ ማቆያ ስፍራዎች በገንዘብና በተለያዩ መንገዶች እያመለጡ ወደ ሕብረተሰቡ የሚቀላቀሉ ሰዎች መገኘታቸውን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል፡። በዚሁ መሰረት እስካሁን ድረስ ሶስት ሰዎች በክትትል መያዛቸውና ወደ ማቆያዎቹ እንዲመለሱ መደረጋቸው ተገልጿል፡፡ መንግሥት በዚህ አይነት ሁኔታ ወደ ሕብረተሰቡ በሚቀላቀሉ ሰዎች ላይ የሚወስደውን እርምጃም ጠንከር አድርጎ እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡
ይህንኑ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋትን ለመግታት ክልሎች የየራሳቸውን እርምጃዎች በመውሰድ ላይ የሚገኙ ሲሆን ለቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት በአገሪቱ አራቱም አቅጣጫዎች የሚወጡም ሆነ የሚገቡ መንገደኞች እንዳይኖሩ ለማድረግ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ ተወስኗል፡፡
ትግራይ ክልል፤ በክልሉ፤ ውስጥም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለሁለት ሳምንት እንዲቋረጥ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፤ በክልሉ የኮቪድ 19 ቫይረስ ላብራቶሪ መመርመሪያ መሳሪያ ሥራ መጀመሩንና በክልሉ በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩ የተደረጉ ሰዎችን ናሙና በመመርመር ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ የኦሮሚያ ክልል በበኩሉ፤ ወደ ክልሉ የሚገቡና የሚወጡ የሕዝብ ትራንስፖርት መኪኖች ላይ እገዳ የጣለ ሲሆን በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ውስጥ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችንም አግዷል:: በክልሉ አራት ከተሞች ላይ የኮቪድ 19 በሽታ መመርመሪያ ላብራቶሪዎች ሥራ እንዲጀምሩ ማድረጉንም አመልክቷል፡፡ አማራ ክልል፤ ወደ ክልሉ የሕዝብ ትራንስፖርት መግባትም ሆነ መውጣት እንዳይችሉ እገዳ የጣለ ሲሆን በክልሉ በሽታው የተገኘባቸው ሁለት ግለሰቦች መኖራቸውን ተከትሎ በባህር ዳር፣ በአዲስ ቅዳምን፣ በእንጅባራና በቲሊሊ ከተሞች ማንኛውም አይነት የተሽከርካሪና የሕዝብ እንቅስቃሴ እንዲታገድ አድርጓል፡፡ ከበሽታው መስፋፋት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ተጋላጭነት አላቸው የተባሉትን የጎዳና ተዳዳሪዎች በት/ቤቶች ውስጥ የማስጠለል ተግባር መጀመሩንና ከ30 ሺ በላይ ለምኖ አዳሪዎችና የጎዳና ተዳዳሪዎች መኖራቸውን በመግለፅ፤ እነዚህን ዜጎች ወደ ተዘጋጀላቸው የመጠለያ ስፍራ የማስገባቱን ተግባር መጀመሩንም አመልክቷል:: በሽታው ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር ንኪኪ እንደነበራቸው የተጠረጠሩ 70 ሰዎችን ወደ ለይቶ ማቆያዎች ማስገባቱንም ክልሉ ገልጿል፡፡
ደቡብ ክልል በበኩሉ፤ ወደ ክልሉ የሚገቡ የሕዝብ ትራንስፖርት መኪኖችን ሙሉ በሙሉ ያገደ ሲሆን በክልሉ ዋና ከተማ በአዋሳ የሚንቀሳቀሱ የሞተር ሳይክሎችን ከመጋቢት 24 ቀን2012 ዓ.ም ጀምሮ እንዳይንቀሳቀሱ አግዷል:: በአዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ 14 ሺ ሰራተኞችም በጊዜያዊነት ከሥራቸው እንዲሰናበቱ ተደርጓል፡፡ 22 ኩባንያዎች በፓርኩ ውስጥ የየራሳቸውን የማምረቻ ሼዶች ወስደው በከፊልና በሙሉ የተጠናቀቁ አልባሳቶችን ለአገር ውስጥና ለውጪ ገበያዎች ሲያመርቱ የቆዩ ቢሆንም፣ በኮረና ቫይረስ ስርጭት ሳቢያ ገቢያቸው በመቀዝቀዙና በርካታ ሰራተኞችን በአንድ ቦታ ላይ አፍጎ ማቆየቱ ተገቢ ባለመሆኑ እርምጃው መወሰዱ ተገልጿል፡። በክልሉ እስካሁን ድረስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች አለመኖራቸው ይታወቃል፡፡  
በአሁኑ ወቅት በአገራችን ስርጭቱ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የመጣውን የኮረና ቫይረስ  ለመግታት የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ የዓለም ባንክ፤ ኢትዮጵያ ይህንኑ ችግር ለመግታት ለምታደርገው ጥረት የሰማንያ ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን በትላንትናው ዕለት አስታውቋል:: የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለብዙ የአለማችን አገራት ፈታኝ መሆኑን ያመለከተው የድርጅቱ መግለጫ፤ ገንዘቡ ለበሽታው መከላከያነት የሚውሉ የሕክምና ዕቃ ግዥዎች፣ ለበሽታው ምርመራና ማሰልጠኛ እንዲሁም ወደ አገሪቱ የሚገቡ መንገደኞችን የሚመረምሩ መሳሪያዎች፣ ለይቶ ማቆያዎችንና የሕክምና ማዕከላትን ለመገንባት ይውላል ተብሏል፡፡ ከዚሁ ገንዘብ ውስጥ 41.3 ሚሊዮን ዶላሩ በልገሳ የተሰጣት ሲሆን ሌላኛው ግማሽ ደግሞ በብድር የተሰጠ እንደሆነ የባንኩ መረጃ ያመለክታል፡፡ የዚህን በሽታ ስርጭት ለመግታት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለማገዝ ሕብረተሰቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ሼህ መሀመድ አላሙዲን 120 ሚሊዮን ብር መስጠታቸውን 3.8 ሰዎች ሆቴላቸውንና ሕንጻቸውን፣ 15 ሰዎች ደግሞ ተሽከርካሪዎቻቸውን የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ለሚደረገው እንቅስቃሴ አጋዥ እንዲሆን መስጠታቸውን የከተማዋ ም/ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ አስታውቀዋል፡፡ በታዋቂው አርቲስት ታማኝ በየነ የሚመራው የ “ጎፈንድሚ” እርዳታ ማሰባሰብ ሂደት እስካሁን 500 ሺ ዶላር መድረሱ አስታውቋል፡፡ ይህ የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራም እንደሚቀጥል ታማኝ በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ይፋ አድርጓ፡፡ ከታዋቂ ሰዎች መካከል ተወዳጁ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ድምጻዊት ሃመልማል አባተ የመኖያ ቤቷን ለዚሁ ተግባር አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረጓ ተገልጻል። ሆቴሎች፣ ሕንጻዎች፣ ሆስፒታሎችና ያልተጠናቀቁ ሕንጻዎች ሁሉ ለዚሁ ተግባር እንዲውሉ ከተለያዩ ግለሰቦች ለከተማው መስተዳድር እየተሰጡ መሆናቸውን የከተማዋ ም/ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ አስታውቀዋል፡፡
በተመሳሳይ በትግራይ በክልሉ ውስጥ የሚገኙና ለምንም ተግባር የተከራዩ ቤቶች ላይ የሃምሳ በመቶ ቅናሽ እንዲደረግ መወሰኑን ይፋ አድርጓል፡፡ በአዲስ አበባ በዱከምና በአዳማ ከተማዎች ደግሞ ግለሰቦች ለመኖሪያ ቤትነት ባከራይዋቸው ቤቶች ላይ ለአንድ ወር ነፃ ማድረግን ጀምሮ የሃምሳ በመቶ ቅናሾችን ማድረጋቸው ታውቋል። የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በግለሰቦች ተነሳሽነት የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም የከተማዋ ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ አስገንዝበዋል፡፡   



Read 9366 times