Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 07 July 2012 09:36

ወተትስ ‘ያወፍር’ ነበር…የጠርሙሱ አፍ ባይጠብ!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ይቺን ታሪክ ስሙኛማ…ቄሱ ለቤተክርስትያን ማሠሪያ ተብሎ ከተሰበሰበ ገንዘብ ላይ የተወሰነውን ይገነድሳሉ፡፡ ታዲያላችሁ…ወደ አካባቢው አቡን (ስም መጥቀስ ምን ያደርጋል!) ይሄዱላችሁና “አባቴ፣ በጣም ትልቅ ኃጢአት ሠርቻለሁ፣” ይሏቸዋል፡፡ አቡኑም ምን አይነት ኃጢአት እንደሠሩ ቄሱን ይጠይቋቸዋል፡፡ ቄሱም “ለቤተ ክርስትያን ማሠሪያ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ ስድስት ሺህ ብር ሴይጣን አሳስቶኝ ጠፋብኝ” ሲሉ ይናዘዛሉ፡፡ አቡኑ “እንግዲህ ምን ይደረጋል፤ ሰው ሆኖ የማይሳሳት የለም” ይሏቸውና ነገርዬው በዚሁ ፋይሉ እንደተዘጋ ይታለፋል፡፡በሌላ ቀን አቡኑ ጉባኤ ላይ ትምህርት እያስተማሩ ሳለ ርዕሳቸውን በምሳሌ ለማስረዳት አንድ ተረት ያመጡላችኋል፡፡

“አንድ ቀጭን እባብ ነበር፡፡ ይህ እባብ አንድ ቀን በወተት የተሞላ ጠርሙስ ውስጥ ይገባል፡፡ ይገባናም ወተቱን እንዳለ ምጥጥ አድርጎ ይጠጣና ተመልሶ ልውጣ ቢል እንዴት ተደርጎ! ያለ ሀሳብ የጠጣው ወተት ሆዱን ነፍቶት ስለነበር የገባበት የጠርሙስ አፍ መልሶ አላስወጣው አለ” ይሉና ምእመናኑን “እንግዲህ ይህ እባብ ምን ይደረግ ትላላችሁ?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ምእመናኑም በአንድ ድምጽ “የጠጣውን ይትፋ!” ይላሉ፡፡

ለካስ እኛ ስድስት ሺህ ብር ያጎደሉት ቄስ እዛው ነበሩ፡፡ እመር ብለው ይነሱና “ይሄ ነገር እኔን ለመንካት ነው!” አሉና አረፉላችሁ፡፡

እናላችሁ…ዘንድሮ ወተት የሞላ ጠርሙስ ውስጥ እየገባ መውጫ የሚያጣ መአት ነው፡፡

ምን መሰላችሁ…  በመስከረም መባቻ ከመቅጠኑ የተነሳ “እንደው ወፈር ያለ አጠና ጎን ቢቆም ሰው መሆኑ ይለያል?” የተባለለት ሰው በጥቅምት አጋማሽ ሁለት አገጭ፣ ሦስት ሆድ ምናምን የሚያወጣውን ስናይ…መቼስ ምን ማድረግ እንችላለን… “ደግሞ ምን አይነት በወተት የሞላ ጠርሙስ አግኝቶ ይሆን!” እንላለን፡፡እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ወተትዬው ስልጣን፣ ገንዘብ፣ ውሽሜ…ብቻ ምን አለፋችሁ፣ መአት ነገር ሊሆን ይችላል፡፡

ታዲያ የእኔ ቢጤ ባየው ነገር ላይ ሁሉ “ዘሎ የሚከመር”… ወተት የሞላ ጠርሙስ ባየ ቁጥር፣ የጠርሙሱ አፍ ምን ያህል ጠባብ ይሁን፣ ሳይለይ ዘው ብሎ ይገባላችሁና ማጣፊያው እያጠረ ሲሄድ በየት በኩል ይውጣ! ብዙ ነገር ላይ አይታችሁ እንደሆነ ስትገቡበት እንደ ካምቦሎጆ በር ወለል ያለው ስትወጡበት የአይጥ ጎሬ መሹለኪያ ሆኖላችሁ ቁጭ! (አንድ ጊዜ ካዛንቺስ ሱፐርማርኬት አካባቢ ባለ አፓርትማ በሩ ሰፊ ሆኖልህ ሰተት ብለህ ገብተህ ባል ድንገት ሲያንኳኳ ከአራተኛ ፎቅ የዘለልከው ወዳጃችን…‘የመግቢያ ስፋትና የመውጫ ጥበት ከሚሌኒየሙ ምናምን ግብ አንጻር ሲቃኝ’ አይነት ነገር የሚል መጽሐፍ አሳትምልንማ! እግርዬው ሰላም ነው አይደል! ብቻ ምን መሰለህ…ዘመንን ለትንሽ ቀደምከውና ዘንድሮ ነገርዬው ሁሉ ‘የስለት ዕቃ’ ሆነና “በእንተ ስሟ ማርያም” ሳትል ‘የምትዘከርበት’ ጊዜ ሆኖልሀል! በፈለፍኸው ኤፍ.ኤም. ላይ “እባክህ ተመለስ ልጅነት በሞቴ…”

የሚለውን ዘፈን መርጠንልሀል! ለነገሩ እንኳን…ምን መሰለህ፣ የዘመኑ ‘የኃይል አሰላለፍ’ ገብቶህ የ‘ጂም’ ደንበኛ ከሆንክ የዘፈን ማነቃቂያም አያስፈልግህ ይሆናል፡፡

ቂ…ቂ…ቂ…ወይ የጂምና የአገረ ኢትዮዽያ ነገር!)

ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… የአቢሲንያ ምድር ‘ቦተሊከኞች’ ብዙዎቹ (እንክት አድርገን ‘ብዙዎቹ’ እንላለን!) የፕሪንሲፕል፣ የምናምን ሊበራሊዝም፣ የምናምን ሶሻሊዝም ጉዳይ ሳይሆን የሚገቡበትን ቡድን ጠርሙስ ወተት አይተው የሚመርጡ ነው የሚመስለኝ፡፡

እኔ የምለው…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ፤ ምን ሰለቸህ አትሉኝም…ከዓመት ዓመት ያንኑ ‘ቦተሊካ’ መስማት፡፡ የ’84 ዓ.ም. መግለጫና የ2004 ዓ.ም. መግለጫ ሬድዮ ላይ ‘የታሪክ ማስታወሻ’ ምናምን እንደሚሉት አቧራው ተራግፎ የሚነበብ እየመሰለን ተቸግረናል፡፡ እንደው ከሁሉም ወገን አንዲት አዲስ ሀሳብ እንኳን አትፈልቅም! ዘላላም ውግዘት፣ ዘላላም እርግማን!

ሀሳብ አለን…በሁሉም ወገን ላሉ ‘ቦተሊከኞች’…አለ አይደል… የፖለቲካ ‘አፕቲቱድ ቴስት’ ምናምን ይሰጥልን፡፡ ያኔ ጉድ ይወጣ ነበር፡፡ ከረባትና አሪፍ ሱፍ እንደሁ አይናገሩ! ምን መሰላችሁ…ይሄኔ ከ‘ጥይት ቦተሊከኞች’ መሀል የሰገሌ ጦርነት ከደቡብ አፍሪካው የዓለም ዋንጫ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ የተጠናቀቀ የሚመስለው ‘ቦተሊከኛ’ ሊኖር ይችላል፡፡ (የእውነተኛ ፖለቲካ ዘመን ሲመጣልን ‘ቦተሊካ’ የሚለውን ቃል እንደማርም ይሰመርበትማ! ፖለቲካው የ‘ሰፈር ጨዋታ’ መምሰሉን ይተው እንጂ ሂስም ካለ…ግጥም አድርጌ ነው የምውጠው! ጥያቄ አለን…“ሂሴን ውጫለሁ…” እንደሚባለው ሁሉ ለምንድነው “ግምገማዬን ውጫለሁ…” የማይባለው!)

እናላችሁ…ዘንድሮ ነገርዬው ወተት አይቶ ጠርሙስ ውስጥ ዘሎ ጥልቅ ሆኗል፡፡ ምን መሰላችሁ…ወተት አለ ብሎ ዘሎ ከመግባት በፊት…አለ አይደል…መውጫንም ማሰብ አሪፍ ይሆናል፡፡

ስሙኝማ…ደግሞ ሌላ ነገር አለላችሁ…ቄሱ ስድስት ሺዋን ሙጥጥ አድርገው በማይመለከታቸው “ይሄ ነገር እኔን ለመንካት ነው!” ያሏት ነገርም ብትሆን ዘንድሮ ለአንዳንዶቹ ‘እስከ ዶቃ ማሰሪያ መንገሪያ’፣ ለአንዳንዶቹ በወጣቶቹ ቋንቋ ‘ማስቦኪያ’ ሆናለች፡፡ እናላችሁ…ለሌላው የተናገራችሁት ነገር ዙሪያ ክብ ሦስት መቶ ዲግሪ ይዞርና “ይሄ ነገር እኔን ለመንካት ነው!” ትባላላችሁ፡፡

እናማ…ከዚሀ በፊት እንዳወራናት… የእኔ ቢጤ፣ ቁመት ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣ የደረሰበትን ጓደኛችሁን “የሴት አጭር ሴት ወይዘሮ፣ የወንድ አጭር አውራ ዶሮ…” አይነት ነገር ስትቀልዱበት ራቅ ብሎ የተቀመጠው ‘…አውራ ዶሮ’ (እኔም ልሆን እችላለሁ!) ሊያፈጥባችሁ ይችላል፡፡ በቃ… ዘመኑ በማይመለከተን ሁሉ “ይሄ ነገር እኔን ለመንካት ነው!” ማለት ያበዛንበት ነዋ!

ደግሞላችሁ…እንትናዬ ጓደኛዋን “አንቺ ክብደትሽን ቀንሺ እንጂ! አንደኛውን ጡትሽና ሆድሽ አብሮ እስኪሰፋ ነው እንዴ የምትጠብቂው!” ብትል ሌላዋ ኩዊን ላቲፋህ ነገር “ይሄ ነገር እኔን ለመንካት ነው!”  ብላ አገሩን ልትቀውጠው ትችላለች፡፡

ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… በተለይ ሰው ሰብሰብ ያለበት መዝናኛ ቦታ ከጓደኞች ጋር ቀልድ መወራወር አስቸጋሪ የሆነው ለምን መሰላችሁ…ሳይመለከተው ‘ይመለከተኛል’ ባይ ስለበዛ፡፡

እናማ…‘ለብቻችን የምንቀላለደው’፣ ‘ሰው ባለበት የምንቀላለደው’ ብለን የ‘ጆክ ብቃት መመዘኛ’ እንዳወጣን ይመዝገብልንማ!

ልክ ነዋ…ዘንድሮ የሆነ ስም ነገር ሌላው ላይ ‘መለጠፍ’ እንዲህ ቀላል ‘ማስ ሰፖርት’ አይነት ነገር በሆነበት ጊዜ ‘ዝም አይነቅዝም’ ማለት ብልጥነት ነው፡፡ ድፍን አገር ጆሮ ነስቶት ምላስ ብቻ በሰጠው ባለንበት ጊዜ አዳማጭ በሌለበት ነገር “ምን መሰለህ፣ ነገሩን እንደ ሰው ሆነን ስናየው…” ምናምን ሳርትር፣ ፕሌቶ አይነት “ወይ አሳምነኝ፣ ወይ ላሳምንህ” ዋጋ የለውም፡፡

እናማ…በሆነ ባልሆነው “ይሄ ነገር እኔን ለመንካት ነው” የምንል በበዛበት ጊዜ…አለ አይደል… ጋዜጠኞች ወዳጆቼ ብዙ ጊዜ ቢሳቀቁ እውነት አላቸው፡፡ ዘንድሮ…የምትወጡበትን የመሰላሉን ከፍታ መስመር እስካላሳለፋችሁ ድረስ… መፎከር ይቻላል፡፡ መአት ‘ቦተሊከኛ’ ፎካሪ አለ፣ መአት ‘አርቲስት’ ፎካሪ አለ፣ መአት ‘የስፖርት አለቃ’ ፎካሪ አለ…መአት ዘመናዊ ‘ጭቃ ሹም’ ፎካሪ አለ…ብቻ  ምን አለፋችሁ “ይሄ ነገር እኔን ለመንካት ነው!” የሚለው ብዛት የህዝብ ቁጥር መዝገብ ላይ ራሱን የቻለ ዓምድ ያስፈልገዋል፡፡ እናማ…አብዛኛው ፎካሪ ነገሩን ቶሎ ብሎ “እዛ አትድረስ እንጂ…” የተባለው ቦታ አድርሶ በር ያንኳኳል፡፡ ነገሩን ሁሉ…አለ አይደል… ‘ትራንስፎርሜሽን ለማደናቀፍ’፣ ‘የሚሌኒየም ግብ ለማበላሸት’ ምናምን ይባልና ከሌላ መጽሐፍ የተገነጠለ ምዕራፍ ይገባበታል፡፡ እናላችሁ…ነገረ ሥራችን ‘ለፍቅር ቢሳሙ ለጠብ የማርገዝ’ ይሆንና ለሩኒ የተሰጠውን ትችት የእንትን መሥሪያ ቤት አለቃ “ይሄ ነገር እኔን ለመንካት ነው!” ሊል ይችላል፡፡ እናላችሁ… አእምሮን በሙሉ ኃይሉ የማሠራት ነገር “ከሀያ ሳንቲም በቆሎ ጋር ድሮ ቀረ” አይነት ይሆንና ሊሉት የሚፈልጉት ተጠመዝዞ “ይሄ ነገር እኔን ለመንካት ነው” የሚል ‘ጉልበተኛ’ ወይም ‘የጉልበተኛ ንክኪ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ብቅ ይላል፡፡እናማ የጠርሙሱን ወተት ለብቻ መጦ ከመጨረስ…አለ አይደል… እንደው በስኒም፣ በመለኪያም ብንቃመስ እኮ “ይሄ ነገር እኔን ለመንካት ነው!” ምናምን አንባባልም ነበር፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…እንትና ከብሔራዊው ሀብት ድርሻችን ይሰጠን ያልከው ነገር…እስቲ ለክፉም ደጉም ስሌቱን ሥራውማ! እናማ…ጠርሙስ ውስጥ ገብቶ ሙሉ ወተት መጠጣቱ ቀላል ነው — መውጫው ባያስቸግር ኖሮ የወፋፍራሞች አገር በሆንን ነበር፡፡

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

Read 1935 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 10:02