Saturday, 04 April 2020 11:45

የፓርላማው የሥራ ዘመን ከመጠናቀቁ 1 ወር በፊት ቀጣይ ሀገሪቱ የምትመራበት ሁኔታ ይወሰናል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

   የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በቀጣዩ ምርጫ እጣ ፈንታ እና ሀገሪቱ በምትተዳደርበት ጉዳይ የሥራ ዘመኑ ከመጠናቀቁ 1 ወር በፊት ይወሰናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ስጋት መደቀኑን ተከትሎ በነሐሴ 23 እንዲካሄድ አስቀድሞ መርሃ ግብር የወጣለት ምርጫ የተስተጓጐለ መሆኑን ያስታወቀው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቀጣዩ ምርጫ እጣ ፈንታ ላይ ፓርላማው የስራ ዘመኑ ከመጠናቀቁ 1 ወር በፊት ውሣኔ እንዲያሳልፍ ይጠበቃል ብሏል፡፡
ለዚህም ውሣኔ ቀደም ብሎ የቫይረሱን ስጋት እና ለምርጫው ምቹ ሁኔታ ያለመኖሩን ያረጋገጠበትን ዳሰሳ ጥናት ውጤት ቦርዱ ለፓርላማው የሚያቀርብ ሲሆን ጥናቱን መነሻ አድርጐ ፓርላማው በምርጫው እና ቀጣይ ሀገሪቱ ልትመራ የምትችልበት አግባብ ላይ ውሣኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአሁን ወቅት ቀደም ብሎ ያወጣውን የምርጫ ማስፈፀሚያ መርሃ ግብር ሙሉ ለሙሉ መሠረዙን እና የወረርሽኙ ስጋት ተወግዶ ሁኔታዎች ሲመቻቹ እንደገና ግምገማ ማድረግ እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡
ቦርዱ በቀጣይ ምርጫ ማስፈፀም የሚችልበትን ሁኔታ እያመቻቸ ችግሩ እስኪወገድ ድረስ እንደሚቆይም አስታውቋል፡፡
ቦርዱ ቀደም ብሎ ያወጣውን የምርጫ እቅድ ለመሰረዝ የተገደደው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የደቀነውን ስጋት እና የቆይታ ጊዜውን የተመለከተ ጥናት በባለሙያዎች አስጠንቶ ካገኛቸው ምክረ ሃሳቦች በመነሳት መሆኑንም አስገንዝቧል፡፡
ቀጣይ ሀገሪቱን በህግ አስተዳድሮ ለማስቀጠል በሚደረግ ጥረት ውስጥ ምን አይነት ሁኔታዎች ሊገጥሙ ይችላሉ? ምንስ መደረግ ይገባዋል? በሚለው ጉዳይ አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው ፖለቲከኞች በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ ስጋትን ተከትሎ ምርጫ ቦርድ የወሰነው ውሣኔ ተገቢነት ያለው መሆኑን ገልፀው ነገር ግን ቀጣይ ምን ይሁን የሚለው በሚገባ ውይይት ሊደረግበት ይገባል ብለዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በህገመንግስቱ የተሰጣቸውን ስልጣን ተጠቅመው የፓርላማው የስራ ዘመን ከመጠናቀቁ 1 ወር በፊት ፓርላማውን ሊበትኑ የሚችሉበት አማራጭ መኖሩን የጠቆሙት የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ ምርጫውንም በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ማካሄድ የሚቻልበትን ሁኔታ ሊፈጥሩ የሚችሉበት አማራጭ እንዳለ ያስረዳሉ፡፡
በዚህ የህገመንግስት አግባብ መሠረት ምርጫውን ከዚህ በኋላ ማራዘም የሚቻለው 6 ወር ድረስ ብቻ መሆኑን በዚህ ወቅትም ሀገሪቱ ያለ ፓርላማ እንደምትተዳደር ያስገነዘቡት አቶ ሙሉጌታ ባልተረጋጋው የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ በእንዲህ አይነት መንገድ ለመጓዝ መሞከር ለሀገሪቱ አደጋ ሊሆን ይችላል ባይ ናቸው፡፡
ለዚህ ያለው አማራጭ ፓርላማው ከመበተኑ በፊት ብሔራዊ የሽግግር መንግስት አቋቁሞ በሀገሪቱ በቀጣይ ብሔራዊ እርቅ ተፈጽሞ ለምርጫ ዝግጁ የሚኮንበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል ይላሉ - አቶ ሙሉጌታ፡፡
በአሁን ወቅት ዋናው ጉዳይ ስለ ፓርላማ መበተን እና ስለ ሽግግር መንግስት መወያየት ሳይሆን ህዝባችንን ከዚህ የበሽታ ስጋት እንዴት እንታደግ የሚለው መሆን አለበት የሚሉት አቶ ሙሉጌታ ከዚያ በመለስ ግን ሀገር በቀጣይ እንዴት በህግ እየተመራች ትቀጥል የሚለውም እኩል ሊያሳስበን ይገባል ብለዋል፡፡
ህግን፣ ነባራዊ ሁኔታን ማዕከል ያደረጉ የተለያዩ የመፍትሔ ሃሳቦች ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ቀርበው ከወዲሁ ውይይት ሊደረግባቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ከመጀመሪያውም የሽግግር መንግስት ይቋቋም ሃሳብ ሲያራምዱ የቆዩት አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ዋነኛ ትኩረት ህዝብን ከወረርሽኙ ስጋት መታደግ ላይ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ ሀገርን ከወረርሽኝ መከላከል መቻላችንን ካረጋገጥን በኋላ ስለ ሽግግር መንግስት መነጋገር ይገባናል ብቸኛ አዋጪ መንገድ የሽግግር መንግስት ብቻ ነው ይላሉ አቶ ልደቱ፡፡
አሁን ምርጫ ቦርድ ያሳለፈውን ውሣኔ ተከትሎ ጠ/ሚኒስትሩ ሊያደርጉ የሚችሉት ብቸኛ አማራጭ የም/ቤቱ የስራ ዘመን ከመጠናቀቁ 1 ወር በፊት ፓርላማውን በትነው በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫ ማካሄድ መሆኑን የሚያስረዱት ሌላው ፖለቲከኛ የመድረክ አመራር አቶ ጐይቶም ፀጋዬ ሀገሪቱም በ6 ወሩ ጊዜ ውስጥ የተለየ ችግር ቢያጋጥማት ተጨማሪ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንኳ መደንገግ የሚያስችል ሁኔታ ስለማይኖር ለሀገሪቱ አደጋን የሚጋብዝ ነው ባይ ናቸው፡፡
በ6 ወር ውስጥ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ ሊኖር ይችላል ወይ ሲሉ የሚጠይቁት አቶ ጐይቶም “በኔ ግምገማ ማካሄድ የሚቻልበት ሁኔታ አይኖርም፤ ስለዚህ አዋጪው መንገድ ብሐራዊ የአንድነት መንግስት ማቋቋም ነው ባይ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ህገመንግስት የከሸፈ እና ሰንካላ መሆኑን ከሚያረጋግጡት አንዱ በምን አይነት ምክንያት በስልጣን ላይ ያለ መንግስት ለምን ያህል ጊዜ በስልጣን ሊቆይ እንደሚችል አለመግለፁ ነው የሚሉት ደግሞ የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ ናቸው፡፡
በተጨማሪም ህገመንግስት በስልጣን ላይ የሌሉ የስልጣን ሃይሎችም በምን አይነት መንገድ ወደ ስልጣን እንደሚወጡ እንደማይደነግግ የሚያስረዱት አቶ ግርማ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካሏቸው እድሎች አንደኛው በቀጣይ መስከረም ወር አጋማሽ ም/ቤቱን በትነው በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫ ማመቻቸት ነው ይላሉ፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ም/ቤቱን በትነው 6 ወር በሚቆዩበት ጊዜ ተመሳሳይ አደጋ ቢያጋጥም፣ ችግር ቢፈጠር ግን ነገሩ በምን የህግ አግባብ እንደሚተዳደር አይታወቅም ያሉት አቶ ግርማ ህገመንግስቱ ይህን ጨምሮ ብዙ ሰንካላዎች ያሉት የከሸፈ ህገመንግስት ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋትን መነሻ አድርጐ ቦርዱ ምርጫውን በማራዘሙ ላይ ቅሬታ እንደሌላቸው ነገር ግን ምክክር አለመደረጉ ተገቢ አለመሆኑን በጋዜጣዋ መግለጫቸው ያስታወቁት ኦነግ እና ኦፌኮ በበኩላቸው መንግስት በቀጣይ በምርጫውም ሆነ ሀገሪቱ እንዴት ትመራ የሚለውን ብቻውን መወሰን አይኖርበትም ብለዋል፡፡
የፓርላማው የስልጣን ዘመን ማለቁን ተከትሎ ሀገሪቱ ልትመራበት የሚገባው አግባብ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሚያደርጉት ውይይት እንዲወሰንም ኦፌኮ እና ኦነግ ትናንት ባወጡት የጋራ መግለጫቸው ጠይቀዋል፡፡


Read 4498 times