Print this page
Saturday, 04 April 2020 11:36

ፖለቲካውና የኮሮና ቫይረስ ስጋት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

     በሽታውን ለመቆጣጠር አቅማችን የሚችለው ቤት የመዋል እርምጃ መውሰድ ብቻ ነው

               ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፤ ከምርጫው በፊት የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት የሚል ሞጋች ሃሳብ ማቀንቀን የጀመሩት አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው፤ የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ አገራዊ ምርጫው መራዘሙን በተመለከተ ምን ይላሉ? ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ሁሉ ከውይይት አጀንዳነት ውጭ ያደረገውን የኮሮና ቫይረስ ስጋትን በተመለከተም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አሁን ሁሉም ትኩረቱን ወረርሽኙ ላይ ማድረግ እንደሚገባው የሚመክሩት ፖለቲከኛው፤ ምርጫው በሁለት ዓመት ተራዝሞ የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት በሚል ሃሳባቸው እንደፀኑ ይገኛሉ፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት የለውጥ ሂደት ላይ የሚያጠነጥንና የሽግግር መንግስት የማቋቋም ሃሳብን የሚያቀነቅን መጽሐፍ ለማሳተም በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ የአዲስ አድማሱ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-

            በቅርቡ ለንባብ የሚበቃው መጽሐፍዎ በምን ላይ ያተኩራል?
መጽሐፉ በአጠቃላይ ላለፉት ሁለት አመታት የተጓዝንበት የለውጥ ሂደት ከምን ተነስቶ የት ደረሰ?  ለውጡ እየተሳካ ነው ወይስ እየከሸፈ? የሚለውን አጠቃላይ ሁኔታ የሚገመግም ነው፡፡ በኔ እምነት፤ የለውጡ ሂደት ወደ ክሽፈት አቅጣጫ አቅንቷል፡፡ ይሄ ለምን ሆነ? የሚለውን በሚገባ የሚያሳይና መፍትሔውንም የሚያመላክት መጽሐፍ ነው፡፡ አሁን ረቂቁ አልቋል፤ ማተሚያ ቤት ይገባል፤ በቅርቡም ለንባብ ይበቃል፡፡ አሁን የኮሮና ጉዳይ ስላለ ብዙም ተጣድፎ የሚወጣ አይሆንም፡፡ በዚህ ጊዜ ፖለቲካውን ትተን ዋናው ጉዳያችንን ወረርሺኙን መግታት ላይ ማድረግ አለብን፡፡
የሽግግር መንግስት ይቋቋም የሚል ሃሳብ ማራመድዎን አሁንም ቀጥለዋል፡፡ በሌላ በኩል ምርጫው በኮሮና ምክንያት ተራዝሟል፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ የሽግግር ጊዜ መንግስት የማቋቋም ጉዳይ ምን ያህል ተጨባጭ ነው?
ምርጫ ቦርድ በኮሮና ምክንያት ምርጫውን አራዝሞታል፡፡ እስከ መቼ ይራዘም የሚለውን ደግሞ ‹‹ፓርላማው ይወስን›› ብሏል፡፡ ምርጫ ቦርድ ይሄን ይበል እንጂ በኛ እምነት ይሄ ኮሮና ቫይረስ ቢመጣም ባይመጣም መራዘሙ አይቀርም ነበር፡፡ ምክንያቱም ቀድሞም ቢሆን ምርጫ ቦርድ በቂ ዝግጅጽ እንዳልነበረውና አለማድረጉን እናውቃለን፡፡ ዝም ብሎ ፕሮፖጋንዳ ነው ሲሰራ የነበረው፡፡
ነሐሴ ላይ ምርጫ እንደማናካሂድ በሚገባ እናውቅ ነበር፡፡ ለዚህ ነው በድፍረት የሽግግር ጊዜ ሃሳብ ያቀረብነው፡፡ አሁን ኮሮናን ሠበብ ተደርጐ ምርጫው መራዘሙ አንድ እድል ይፈጥራል፤ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ፓርላማው ምርጫውን ሲያዝራም 6 ወር 4 ወር ማራዘሙ ጥቅም የለውም፡፡ በኛ እምነት ቢያንስ ለሁለት አመት ያህል ነው መራዘም ያለበት፡፡ በዚያ የሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ተቋቁሞ ሀገሪቱን ለምርጫ ዝግጁ የሚያደርግ አጠቃላይ ዝግጅት ውስጥ መገባት አለበት:: በጽሑፍ ያቀረብኳቸው ጉዳዮች መከናወን አለባቸውም፡፡
የሽግግር መንግስት ማቋቋም የሚለው ሃሳብ ከጊዜው ጋር አብሮ የማይሄድ እየተረጋጋች የመጣችውን ሀገር መልሶ ወደትርምስ የሚከት ነው የሚሉ አሉ…
ሁለት ነገር ማነፃፀር ያስፈልጋል የሽግግር መንግስት ላይ የሚገኝ ስልጣን የለም፡፡ ሁሉም አካል የሚወከሉበት የጋራ መንግስት እንጂ የእገሌ መንግስት የሚባል ነገር አይደለም:: የጋራ መንግስት ነው እንጂ የአንድ ሃይል የተለየ ስልጣን የሚያገኝበት አይደለም፡፡ ይሄን በድርድር እና በመተማመን የምንፈጥረው ነው፡፡ ስለዚህ ለትርምስ የተጋለጠ አይሆንም፡፡ ሁለተኛው ማነፃፀሪያ አሁን ብሔር በነገሠበት፣ የኔ የኔ በበዛበት ሁኔታ የማትሄድ ምርጫስ አትራፊነቱ ምን ያህል ነው፡፡ ሁለቱን በንፁህ ህሊና ማመዛዘን ነው፡፡ የትኛውም ሀገር ወደ በዚህ ሁኔታ ወደ ምርጫ ዘመቻ ሲገባ ነገሮች የበለጠ ይ;;;;፡፡ ስለዚህ የሽግግር ጊዜ አቋቁመን ብሔራዊ እርቅ አድርገን ወደ ምርጫ መግባት እና እርስ በእርስ በተካረርንበት ሁኔታ ወደ ምርጫ መግባት በራሳቸው በአንድ ሚዛን ሊመቀመጡ አይችሉም፡፡
ሃሳቡን ካቀረቡ በኋላ ከመንግስት አካባቢ ምን ምላሽ አግኝተው ይሆን?
ህዝቡ በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ እየተነጋገረበት ነው፡፡ መገናኛ ብዙሃንም ትኩረት ሰጥትዎታል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አካባቢም አንዳንድ ማይስሙባቸው ነጥቦች ቢኖርም በጉዳዩ እየተወያዩ እየተነጋገሩበት ሃሳቡንም እየገዙት መሆኑን ተረድቻለሁ:: በግልጽ በተኩራራ መንገድ እስካሁንም የተቃወመው የለም፡፡ ይሄ ትልቅ ውጤት ነው ብለን እንወስዳለን፡፡ በመንግስት አካባቢ ዶ/ር ዐቢይ፣ የሽግግር መንግስት ጥያቄ የስልጣን ጥያቄ ነው ብለው ሲቃወሙት እየሰማን ነው፡፡ በአቋራጭ ስልጣን የማግኘት አድርገው እያጣጣሉት ነው፡፡ እኛ ባለን መረጃ ግን በራሱ በብልጽግና ፓርቲና በመንግስት ዙሪያ ያሉ በርካቶች ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው እየተነጋገሩበት መሆኑን እናውቃለን፡፡ አንዳንዶች ትልልቅ ባለስልጣናት ሳይቀሩ ሰነዱን አንብበው ያላቸውን በጐ አስተያየት እየሰጡን ነው:: ዲያስፖራው በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶታል፡፡ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ከግምታችን በላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶት እየተነጋገረበት ነው፡፡ ሰነዱ እየተተረጎመ እንዲሰጣቸው እየጠየቁ ነው፤ ስለዚህ እኛ ብልፅግና ተቀበለን አልተቀበለን ብዙም አያሳስበንም። ጥያቄው ግን መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ኢትዮጵያ በእንዲህ አይነት የሽግግር ሂደት ውስጥ ካላሳለፈች በምንም ተዓምር ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ተካሂዶ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የኔ የሚለው መንግሥት ሊያገኝ አይችልም፡፡ በዚህ ሁኔታ ማለፍ ግዴታችን ነው፡፡
ወቅቱ ኮሮና ያየለበትና ብዙ ገደቦች የሚደረጉበት ነው፡፡ በዚህ ወቅት የሽግግር መንግሥት ጉዳይ ምን ያህል ተሰሚነት ይኖረዋል?
በዚህ ወቅት እኛም የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ብለን አልጠየቅንም፤ አንጠይቅምም፡፡ በዚህ ወቅት የሁሉም ትኩረት መሆን ያለበት የኮሮና ወረርሽኝ መግታት ላይ ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ ጉዳዮች ወደ ጎን ትተን፣ ወረርሽኙ ላይ ማተኮር አለብን፡፡ በጣም ጠንካራ የሆኑ ውሳኔዎችን ወስነን በሽታውን መቆጣጠር አለብን:: የሽግግር መንግሥትም ሆነ ምርጫ ከዚያ በኋላ የምንነጋገርበት ጉዳይ ነው መሆን ያለበት፡፡ ሁሉም ሰው በሽታውን መቆጣጠር ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት፡፡ አሁን ፖለቲካ የሚሰማበት ጊዜ አይደለም፡፡
መንግሥት ኮሮናን ለመግታት የሚያደርገውን ጥረት እንዴት ይመለከቱታል:: ተጨማሪ ሊከናወኑ ይገባል የሚሏቸው ምክረ ሀሳቦችስ ምንድን ናቸው?
ሰው የበሽታውን ክብደት እንዲረዳው፣ የበሽታው መከላከያ መንገዶች ምን እንደሆኑ፣ እየተሰጠ ያለው ትምህርት በጣም አበረታች ነው፡፡ በተለይ መገናኛ ብዙኃን በዚህ ረገድ እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ በጣም የሚያስመሰግን ነው:: ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን አንዳንድ ነገሮች ላይ ቸልተኝነት ይታያል፡፡ በክልሎች መካከል እንዲሁም ከአዲስ አበባ ወደ ክልል ያለውን እንቅስቃሴ አስቀድመን ተቆጣጥረን ቢሆን ኖሮ አሁን በክልሎች የታየው ምልከታ ባልታየ ነበር፡፡ ዘግይተን ነው የጀመርነው:: በሙሉ አቅም እየሰራን አይደለም፡፡ በሌላ በኩል፤ ማህበረሰቡን የሚያዘናጉ መረጃዎችም ሲለቀቁ እየታዘብን ነው፡፡ ብልፅግናዎች ስብሰባ ማድረጋቸው ተገቢ አልነበረም፡፡ ከሁሉም በላይ ግን አሳዛኝና አደገኛው፤ ኢትዮጵያ ለበሽታው መድሃኒት እያገኘች ነው የሚለው መግለጫ ነው:: ይሄ መግለጫ እጅግ አደገኛና መደገም የማይገባው ነው፡፡ ለተሰጠው መግለጫ ራሱ ይቅርታ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ጎልቶ ሊነገር የሚገባው ሕዝቡ የሚያዋጣው ጥንቃቄ ማድረግ ብቻ ነው የሚለው ነው፡፡
ሌላው መንግሥት ሊወስደው የሚገባው እርምጃ፤ በወጥነት ሁሉም ቤት ውስጥ እንዲውል ማድረግ ነው፡፡ ይሄ ሲደረግ የሚፈጠሩ ችግሮች ተለይተው፣ ዝግጅት ተደርጎ ቤት የመዋል ጉዳዩ ቀዳሚው እርምጃ መሆን አለበት፡፡ ይሄ መንገድ ነው ለኛ የሚያዋጣን፡፡ እኛ በሽታውን  ለመቆጣጠር አቅማችን የሚችለው ቤት የመዋል እርምጃን መውሰድ ብቻ ነው፡፡ ለኔ ብቸኛው አማራጭ ይሄ ነው፡፡    


Read 1885 times