Saturday, 04 April 2020 11:34

“የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል ጓንትና ማስክ መቼና በምን ሁኔታ ነው መጠቀም ያለብን?”

Written by  ከተመስገን ጌታሁን (temesgengt@gmail.com
Rate this item
(3 votes)

   “በሽታ አምጭ የሆኑ ህዋሳት በወረርሽኝ መልክ ሲስፋፉ የሰው ልጅ ከእነዚህ ሕዋሳት ራሱን ለመጠበቅ በታወቁ መንገዶች፣ የቻለውን ያህል ራሱን
ሲከላከል ኖሯል፡፡ ከእምነት አንጻር የሰው ልጅ እንዲህ ማድረጉ በእግዚአብሔር ጥበቃ የሚተማመን መሆኑን ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ራስን ለአደጋ አሳልፎ ሰጥቶ እግዚአብሔር ጠባቂ መሆኑን ማመን፣ እግዚአብሔርን መፈታተን ነው የሚሆነው፡፡”
                
          መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም እኩለ ቀን ላይ በኢቲቪ 57 ስለ ማስክና ጓንት አጠቃቀም ሐኪሞችን ዋቢ በማድረግ የተሰራጨውን ዜና ተከታትዬአለሁ:: ከሐኪሞችና ሕመሙ ካለባቸው ሰዎች አጠገብ ከሚገኙ ሰዎች በስተቀር ጓንትና ማስክ መጠቀም ጉዳቱ እንደሚያመዝን በአንድ የጤና ባለሙያ የተሰጠው ማብራሪያ አሳሳች ሊሆን እንደሚችል፣ እንደ አንድ ተራ ዜጋ ስጋት ስለአደረብኝ ነው ይህንን ማስታወሻ የጻፍኩት፡፡ ያልተሟላ መረጃ ጉዳት ያስከትላልና፡፡
እንደዚህ ዓይነቱን የተጓደለ መረጃ የሚያስተላልፉ ሐኪሞች አንድ ነገር ልብ ሊሉ ይገባል፡፡ ዘመኑ የዕውቀት ዘመን ነው:: ምንጫቸው አስተማማኝ ከሆኑ የህክምና ሙያ ሳይንሳዊ ማህበረሰብ (Health Scientific community) ስለ ኮቪድ 19 የሚያሰራጩትን መረጃዎች ስራዬ ብሎ የተከታተለ የእኔ ብጤ የህክምና ሙያ የሌለው ግለሰብ፣ በተሻለና በበቂ ሁኔታ መረጃ ማግኘት ይችላል፡፡ በችኮላና በጥድፊያ የተላለፉ ሙሉእነት የሚጎድላቸውን የመረጃ ሕፀፆችንም መለየት ይችላል፡፡ ይሁንና፤ ሐኪሞቻችን በጥንቃቄና በኃላፊነት ትክክለኛውን መረጃ ማስተላለፍ ካልቻሉ፣ የጉዳቱን መጠን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ከንቱ ያደርገዋል፡፡
አሁን ካለው የወረርሽኙ ስርጭት አንጻር በገበያ ላይ ያለው ጓንትና ማስክ መጠን አነስተኛ ስለሆነ በስራ ላይ የተሰማሩ የሕክምና ባለሙያዎች እጥረቱ እንዳይገጥማቸው ያለውን ስጋት በማሰብ ስለ እነዚህ መከላከያዎች አጠቃቀም በቂ መረጃ መስጠት፣ ራሳቸውን ቤዛ ያደረጉ ሐኪሞቻችንን ሕይወት ለማትረፍ ያለው ሚና እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ይህንን እውነት በመጥቀስ ህብረተሰቡ አስፈላጊ ያልሆነ ቦታ ጓንትና ማስክ ከመጠቀም እንዲቆጠብ፤ ከተቻለም እቤት እንዲቀመጥ ማሳሰብ ተገቢ ነው፡፡  ይሁንና በልዩ ልዩ አስገዳጅ ሁኔታዎች የህብረተሰቡን እንቅስቃሴ መግታት እስካልተቻለ ድረስ ህብረተሰቡ አካላዊ ርቀቱን ጠብቆ ያለ እንከን መንቀሳቀስ ፈጽሞ እንደማይችል እየታወቀ፣ ጓንትና ማስክ መጠቀም ጉዳት እንዳለው መግለጫ የተሰጠበት መንገድ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡
ግብይት፤ የገንዘብ ልውውጥ፤ መድሃኒት ለመግዛት ፋርማሲ ውስጥ የሚደረግ ንክኪ፤ የመጓጓዣ መገልገያዎች ላይ የሚደረግ ንክኪ፤ የምንነካቸውን የቤት በር እጀታዎች፤ መወጣጫ ደረጃዎችን ስንወጣ የምንደገፋቸውን ስፍራዎች፤ ...ወዘተ ለአብነት ብንጠቅስ፣ የንክኪ መንገዶቹ እጅግ በርካታ መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ ይህንን ንክኪ ፈጽሞ ማስቆም አይቻልም፡፡ ማስቆምም ከተቻለ ረጅም ጊዜያት ይፈጃል:: በእነዚህ ንክኪዎች ምክንያት ቫይረሱ ሊተላለፍ የሚችልበት ዕድል ከፍተኛ ስለሆነ አቅም በፈቀደ መጠን በበቂ ሁኔታ በሳሙናና በውኃ በመታጠብ እንዲሁም በግልጽ በተነገሩ ሌሎች ዘዴዎች ንጽህናችንን በመጠበቅ ሙሉ በሙሉ ችግሩን ማስወገድ እንደሚቻል ሐኪሞቻችን መክረውናል፤ እየመከሩንም ነው፡፡
ከዚህ ውጭ በእንቅስቃሴ ወቅት ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል፡፡ ለምሳሌ በተለያየ አቅጣጫ የሚጓዙ መንገደኞች በመንገድ ላይ አጠገብ ለአጠገብ ሲተላለፉ የተፈለገውን ርቀት ለመጠበቅ ቢፈልጉ እንኳን ይህንን ለመፈጸም ይቸገራሉ፡፡ ሰዎች በጉዞ ላይ ያለ ሰው ድንገት ሲያስነጥስ (ሳይንሱ ያልደረሰባቸው ሌሎችም በርካታ መንገዶች እንዳሉ ሳንረሳ) ያ ሰው በክንዱ ወይም በሌላ ዘዴ የመተንፈሻ አካሉን ካልከለለ፤ ወይም በዚያች ቅጽበት በሚደረግ ጥግግት፣ ከየሰው በሚወጣው ትንፋሽ (አለመተንፈስ ስለማይቻል) ቫይረሱ ያለበት ሰው ወደ ሌለበት እንዳያስተላልፍ ማስክ መጠቀም እጅግ ወሳኝ ስለሆነ፣ በጉዞ ላይ እያለን ማስክ መጠቀም ይኖርብናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ማስክ ባይኖረን እንኳን በንጹህ እራፊ ጨርቅ የመተንፈሻ አካላችንን ብንሸፍን ቫይረሱን የማስቀረት ዕድል ሰፊ ነው፡፡
ማስክና ጓንት በመጠቀም ጉዳት ሊደርስ የሚችለው እነዚህን የመከላከያ ቁሶች በምን ሁኔታ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለብንና ከተጠቀምንም በኋላ በተጠቃሚው ላይ ጉዳት ሳያደርስ፣ እንዴት ማስወገድ እንዳለብን ካላወቅን ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ያጋጠመኝን እዚህ ጋ ባነሳው መልካም ይሆናል የሚል እምነት አለኝ:: ሰሞኑን በሹፍርና ሙያ ከተሰማራች የጥንት ወዳጄ ጋር ስልክ ተደዋውለን ነበር:: ስለ ስራ፤ ስለ ወቅቱ ሁኔታ በጣም ብዙ ጉዳዮችን አወራን፡፡ የተሰማራችበት የሥራ ባህሪ ከሽያጭ ጋር የተገናኘ ስለሆነ፣ በየቀኑ ብዙ ሰው በሚገኝበት መሀል መርካቶ  ገብታ ትወጣለች፡፡
ዕቃ ጭና ስትሄድ ሁለት የሽያጭ ሠራተኞች የመኪናው የውስጥ ክፍል (ጋቢና) አብረዋት ቀኑን ሙሉ እንደሚቀመጡ በጨዋታ መሀል ነገረችኝ፡፡ “እንዲያው ለመሆኑ መሀል መርካቶ ስትሄዱ ጓንትና ጭምብል ትጠቀማላችሁ?” ብዬ ስጠይቃት የሰጠችኝ መልስ፣ በብዙ ሰዎች ሲነገር እንደሰማሁት ዓይነት ነበር፡፡
“ጓንት፤ ጭምብልና የንጽህና መጠበቂያ (sterilizer) ለሁላችንም ተሰጥቶናል፡፡ ጭምብሉን ሞክረነው ረጅም ጊዜ አጥልቀን መቆየት ስለደበረን ትተነዋል፤ በተሠጠን የንጽህና መጠበቂያ የመኪናውን በር እጀታ፤ መሪውን፤ ማርሹንና፤ የቀበቶ መታጠቂያ (safety belt) ሳይቀር አጸዳዋለሁ” ስትለኝ፤ እኔም የምትወስደውን ጥንቃቄ በማድነቅ፣ ጓንት ባትጠቀም እንኳን በውኃ በመታጠብ መከላከል እንደሚቻል ተነጋግረን በትንፋሽ ምክንያት ሊተላለፍ የሚችለውን አጋጣሚ ለማስቀረት፣ በተለይ ስምሪት  ላይ ሲሆኑ ማስክ መጠቀም እንደሚኖርባቸው ሀሳቤን አካፈልኳት፡፡
የምታውቀውን መረጃ መነሻ በማድረግ “ህሙማን ባሉበት አካባቢ ካልሆነ በቀር ጭምብሉ ምንም ጥቅም አይሰጥምኮ፤ በዚያ ላይ እግዚአብሔር ይጠብቀኛል” ስትለኝ መደማመጥ እንደማንችል ገባኝና የወሬ አርእስታችንን ቀየርኩ፡፡
“በይ አሁን ከተቀመጥሽበት ተነስተሽ በመስኮት በኩል ወደ ውጭ ተመልከች” አልኳት፤
“ለምን?” አለችኝ፡፡  
“ግዴለሽም ወደ መስኮቱ ጠጋ በይና ተመልከቺ” አልኳት፡፡
“እሽ አሁን እየተመለከትኩ ነው” አለችኝ::
“መስኮቱን ክፈቺና ዝለይ” ስላት ሃሳቤ ገብቷት ዘለግ ላለ ጊዜ ሳቀች፡፡ እኔ ግን ፈጽሞ አልሳቅኩም፡፡ “እግዚአብሔር ይጠብቀኛል አይደል ያልሽው? በይ በመስኮቱ ዘለሽ ውረጂና እግዚአብሔር እንደሚጠበቅሽ አረጋግጭልኝ” አልኳት፡፡ የምትኖረው ኮንዶሚኒየም ሰፈር አንደኛ ፎቅ ነው፡፡ ለጥቂት ሰኮንዶች ያህል ዝም ብላ ቆየችና በረጅሙ ስትተነፍስ ሰማኋት፡፡
“ያና ይህ ምን አገናኘው? በመስኮቱ ከዘለልኩማ ባልሞት እንኳን የእግሮቼ አጥንቶቼ ይሰባበራሉ” ነበር ያለችኝ፡፡ ስለ እግዚአብሔር ጠባቂነት አንዳችን ከአንዳችን ያለን አረዳድ የተለያየ መሆኑ ጠፍቶኝ አይደለም እንዲህ ያልኳት፡፡ ዶስቶቭስኪ የተባለ ዕንቁ የሆነ የሩሲያ ደራሲ ለዓለም ካበረከታቸው ምርጥ ስራዎች መካከል “The Brothers Karamazov” ተብሎ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ የተተረጎመው መጽሐፍ (እስከ ዛሬ ድረስ በአማርኛ ቋንቋ የተተረጎመ አይመስለኝም)፤ ስለ እግዚአብሔር ጠባቂነት ተወላግዶ ስለሚቀርብ የተሳሳተ አስተሳሰብ እጅግ ቁም ነገር ያለው ነጥብ ያነሳል፡፡ በመጽሐፉ እንደተጠቀሰው፤ የሰው ልጆች ሁሉ ከሚጋፈጧቸው ሶስቱ ዋና ዋና ፈተናዎች መካከል አንዱ ስለሆነው እግዚአብሔርን ስለመፈታተናቸው ነው የሚያብራራው፡፡
መጽሐፉ አዲስ ኪዳንን ጠቅሶ እንዲህ ይለናል፡፡ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ በመንፈስ ወደ ምድረ በዳ ተወሰደ፡፡ ከአርባ ቀንና ሌሊትም ጦም በኋላ ተራበ፡፡ ለፈተና ከቀረቡለት ሶስት ፈተናዎችን መካከል አንዱ የሆነውን ለማጠየቅ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደና እርሱን በመቅደሱ ጫፍ ላይ አወጣው፡፡
ከዚያም “መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፤ እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል” ተብሎ የጻፈውን በመጥቀስ “የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንክ፤ ወደ ታች ራስህን ወርውር” አለው፡፡
ኢየሱስም “ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል” አለው፡፡ ስለ ሰው ልጅ ንፉግነት (አሥራት አለመክፈል) እና ስለ አሥራት በረከት እግዚአብሔር “ፈትኑኝ” ስለ ማለቱ በነቢዩ ሚልክያስ አንደበት ተነግሯል፡፡ ብዙም ማሰላሰል ሳይጠይቅ “ፈትኑኝ” እና “እግዚአብሔር አምላክህን አትፈታተነው” ተብሎ የተጻፈው የተለያዩ ሀሳቦች ናቸው፡፡
አንድ ሰው ከሌላ ሰው ጋር ሳይግባባ ሲቀርና አንዱ አንዱን ሲገዳደረው የተበሳጨው ወገን “እባክህ አትፈታተነኝ” ይላል፡፡ “ምን ታመጣለህ?” የመሳሰሉት ቃላት የተለመዱ የንቀት ቃላት ናቸው- ባላንጣን ለመፈታተን፡፡ አማኞች እንደሆኑ የሚያስቡ ምዕመናን እግዚአብሔርን የሚፈታተኑበት መንገድና አስተሳሰብ ደግሞ እጅግ ከልክ ያለፈ ሲሆን እናያለን:: በሽታ አምጭ የሆኑ ህዋሳት በወረርሽኝ መልክ ሲስፋፉ የሰው ልጅ ከእነዚህ ሕዋሳት ራሱን ለመጠበቅ በታወቁ መንገዶች፣ የቻለውን ያህል ራሱን ሲከላከል ኖሯል፡፡ ከእምነት አንጻር የሰው ልጅ እንዲህ ማድረጉ በእግዚአብሔር ጥበቃ የሚተማመን መሆኑን ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ራስን ለአደጋ አሳልፎ ሰጥቶ እግዚአብሔር ጠባቂ መሆኑን ማመን፣ እግዚአብሔርን መፈታተን ነው የሚሆነው፡፡ ሰላም!!



Read 1366 times