Saturday, 04 April 2020 11:29

ኮሮና የዓለም የስፖርት ኢንዱስትሪ አቃውሶታል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

   • ኦሎምፒክ የተራዘመው ከ124 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው
   • የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ውዝግባቸውን ለመፍታት ተጨማሪ ጊዜ አግኝተዋል
   • ጃፓን 6 ቢሊዮን ዶላር ከወዲሁ ከስራለች፤ የቱሪዝም ኢንዱስትሪዋ 2.5 ትሪሊዮን ዶላር ገቢ ያጣል

             በመላው ዓለም ከ200 አገራት በላይ የተዛመተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የዓለምን የስፖርት  እንቅስቃሴ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ከቶታል፡፡ በወረርሽኙ ሳቢያ ትልልቅ የስፖርት ውድድሮች በመራዘማቸው፣ በመሰረዛቸው እና በመስተጓጐላቸው ኢንዱስትሪውን ከፍተኛ ገቢ እንደሚያሳጣው የተለያዩ ትንበያዎች አመልክተዋል፡፡ የስፖርት ኢንዱስትሪውን በስፖንሰርሺፕ የሚደግፉ ትልልቅ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች የበጀት ቀውስ ውስጥ መግባታቸው፣ ከትኬት ሽያጭ ከማርኬቲንግና ከተለያዩ ንግዶች የሚገኙ ገቢዎች መቆማቸው ሁሉንም ስፖርት ይጐዳቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቶኪዮ 2020
32ኛው ኦሎምፒያድ የተሸጋሸገው   የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ብሔራዊ አዘጋጅ ኮሚቴና/አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዕሰጥ አገባ በገቡበት ማግስት እንደነበር ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኦሎምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴ ከ100 በላይ አትሌቶችን ወደ አምባሳደር ሆቴል/የስፖርተኞች ካምፕ ገብተው ከመጋቢት 9 ጀምሮ ዝግጅታቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአንፃሩ መጋቢት 14 ላይ በኮረና ምክንያት አትሌቶች አንድ ላይ መሰባሰባቸው ያሰጋናል፤ላልተወሰነ ጊዜያትም ቢሮውን ዘግችያለሁ በሚል ውሳኔው ያለውን ውዝግብ አመልክቷል፡፡ የ32ኛው ኦሎምፒያድ በ1 ዓመት መሸጋሸግ በኦሎምፒክ ኮሚቴው እና በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኩል ለተፈጠረው እሰጥ አገባ መርገብ ምክንያት ሆኗል፡፡ በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች የኢትዮጵያን ስፖርት በሚመሩና ከፍተኛ ልማድ ባላቸው የስፖርት ሰዎች መካከል በየጊዜው ውዝግብ መፈጠሩ ግን አሳስቧቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኦሎምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴው በኮረና ስጋት የተሸጋሸገውን የ32ኛ ኦሎምፒያድ ተሳትፎ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ይኖርበታል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝን ለመዋጋት በሚካሄደው ዘመቻ ድጋፍ እንዲሆን ለኦሎምፒክ ኮሚቴው 3ሚሊየን ብር ሰጥቷል፡፡ በሚቀጥሉት 16 ወራት ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርጐ የኦሎምፒክ አካዳሚውን ለመገንባት መሠረቱን መጣል አለበት፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የኦሎምፒክ አትሌቶችን እንዲሁም የብሔራዊ ቡድን አትሌቶችን ወደየቤታቸው ከሸኘ በኋላ አበል መስጠቱና ትጥቅ ማከፋፈሉ ተምሳሌትነት ያለው ተግባር ነው፡፡ ለ211 አትሌቶችና 56 አሰልጣኞች 4 ሚሊዮን ብርና የስፖርት ትጥቆችን አበርክቶ ነው፡፡ ይሁንና ከኦሎምፒክ ኮሚቴው ጋር በየጊዜው እሰጥ አገባ መግባት  አይጠቅመውም፡፡ አትሌቲክስ  በኦሎምፒክ መድረክ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበ እንደመሆኑ በሌሎች የኦሎምፒክ ስፖርቶች ኢትዮጵያ የሚኖራትን ተሳትፎ ከኦሎምፒክ ኮሚቴው ጋር በመሆን ማገዝ ያለበት ኃላፊነት ነው፡፡ በ32ኛው ኦሎምፒያድ ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በቴኳንዶ ስፖርት በወንዶች እንዲሁም በብስክሌት በሴቶች መካፈሏ ይጠበቃል፡፡
በጃፓንና በኦሎምፒክ ባለድርሻ አካላት የደረሰው ኪሳራ
ጃፓን የገነባቸው የኦሎምፒክ ስታድዬም 277 ሚሊዮን ዶላር፤ NBC በኦሎምፒክ ስርጭት በማስታወቂያ ከሚያገኘው ገቢ 1.25 ቢሊየን ዶላር፣ የአውሮፓ 5 ታላላቅ ሊጐች ከ4.5 ቢሊየን ዶላር በላይ ኪሣራ አጋጥሟቸዋል:: ጃፓን እና ዋና ከተማዋ ቶኪዮ ከፍተኛው ኪሣራ ደርሶባቸዋል፡፡ በ2020 እ.ኤ.አ አዲስ ዓመት መግቢያ ላይ የ2020 ኦሎምፒክንና ፓራ ኦሎምፒክ ውድድሮችን ለማስተናገድ በ1.4 ቢሊዮን ዶላር ወጭ በማድረግ የገነባችውን የኦሎምፒክ ስታድዬሙ ጃፓን አስመርቃለች፡፡ በአጠቃላይ ጃፓን የኦሎምፒክ መስተንግዶውን ካገኘችበት ከ2013 ጀምሮ እስከ 2030 እ.ኤ.አ በኢኮኖሚያዊ ላይ እስከ 294 ቢሊዮን ዶላር ለማስገባት አቅዳ ነበር፡፡ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ኦሎምፒኩን ለአንድ ዓመት ካሸጋሸገች በኋላ ግን ኪሣራዋ 6 ቢሊዮን ዶላር አልፏል፡፡ ትልልቅ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎችም ኦሎምፒኩን በስፖንሰርሺፕ ለመደገፍ ከ3.2 ሚሊዮን ዶላር በላይ አውጥተዋል፡፡ አበበ ቢቂላ ሁለተኛውን የማራቶን ድል ለኢትዮጵያ ባስመዘገበበት የ1964 ቶኪዮ ኦሎምፒክ የተሳካ መስተንግዶ ጃፓን ከ2ኛው የዓለም ጦርነት አገግማ ነበር፡፡ ቶኪዮ 2020ን ደግሞ በዓለም ኢኮኖሚ ተጽእኖ ፈጣሪ ለመሆን አነጣጥራበት ሳይሆንላት የሚቀር ይመስላል፡፡ የጃፓኗ ቶኪዮ ከተማ 32ኛውን ኦሎምፒያድ ለማካሄድ 122 ቀናት እየቀራት ነው መርሐ ግብሩን ለማሸጋሸግ የተገደደችው::  በኮረና ወረርሽኝ ሳቢያ የዓለማችን ግዙፍ የስፖርት መድረክ በ2021 እ.ኤ.አ እንዲካሄድ አዘጋጅ ኮሚቴው እና ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በሙሉ አቋም ወስነዋል፡፡ ኦሎምፒክ ከመላው አለም አቅም በላይ በሆነ ችግር ሲሸጋሸግ ከ124 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ጃፓን ኦሎምፒኩን ለማስተናገድ የመጨረሻ ዝግጅት ምዕራፏ ላይ ስትደርስ የቱሪዝም ገቢዋ እያደገ ነበር፡፡ በ2019 እ.ኤ.አ ብቻ ከ32 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶችን አስተናግዳ ነበር፡፡ በ2020 እ.ኤ.አ ይህ ቁጥር ወደ 34 ሚሊዮን እንደሚያድግ ተጠብቆም ነበር፡፡ 2 ሚሊዮን በኦሎምፒክ ምክንያት ጃፓን የሚገቡ ቱሪስቶች ነበሩ፡፡  ጃፓን 32ኛውን ኦሎምፒያድ ለማስተናገድ ባደረገችው ዝግጅት እና በስፖርት መሠረተልማቶች ግንባታ አጠቃላይ ወጭዋ 28 ቢሊዮን ደርሶ ነበር፡፡ በ1 ዓመት እንዲሸጋሸግ ከተወሰነ በኋላ እስከ 6 ቢሊዮን ዶላር ኪሣራ እንደሚገጥማት ተገልጿል፡፡ ያለ ኦሎምፒክ ውድድር የሚቆዩት የስፖርት መሠረተ ልማቶች ጉዳት እንደሚደርስባቸውም ስጋት ተፈጥሯል፡፡
ዓለምአቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ እና የጃፓን መንግስት በሚቀጥሉት 18 ወራት ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ክትባት ካልተገኘና ወረርሽኙ የሚደርሰው ጥፋት ከተባባሰ በአጠቃላይ 32ኛው ኦሎምፒያድ ሊሰረዝ እንሚችልም የገለፁ ዘገባዎች አሉ፡፡  ጃፓን 32ኛውን ኦሎምፒያድ ወደ 2021 እ.ኤ.አ ማሸጋሸጓ በውድድሩ የስፖንሰርሺፕ ድጋፍን የውል አፈጻፀም ጫና መፍጠሩም የማይቀር ይሆናል፡፡ ከዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፣ እና ከጃፓን የኦሎምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴ ጋር በአጋርነት የሚሠሩ 14 ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ኩባንያዎች ለ2020 እ.ኤ.አ ብቻ እያንዳንዳቸው 500 ሚሊዮን ዶላር ከፍለዋል:: በአጠቃላይ ለ4 ዓመታት የኦሎምፒክ መርሐ ግብር ከስፖንሰርሺፕ የተገኘው 4 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ እስከ 2032 እ.ኤ.አ ከኦሎምፒክ ጋር ለመስራት የተዋዋሉት ትልልቆቹ ኩባንያዎች የኦሎምፒክ መድረክ ከተፈጠረው ሁኔታ እንደሚያገግም ተስፋ አድርገዋል፡፡  
ዓለምአቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ (IOC) እና የጃፓን ብሔራዊ አዘጋጅ ኮሚቴ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ባወጡት መግለጫ የተሸጋሸገው 32ኛው ኦሎምፒያድ ጁላይ 23,2021 እ.ኤ.አ ላይ እንደሚጀመር ገልፀዋል፡፡ በሚቀጥሉት 1 ወራት ይህን መርሐ ግብር ከዓለም የስፖርት ኢንዱስትሪ አጠቃላይ ቀውስ ጋር በማጣጣም ለመተግበር ከፍተኛ ስራ ይጠበቅባቸዋል፡፡  ዓለምአቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ኦሎምፒክን በማዘጋጀት ሲሰራ ዋና ገቢውን የሚያገኘው ከሚዲያ መብትና ከስፖንሰርሺፕ ነው:: የ2014 ሶቺ የክረምት ኦሎምፒክን መነሻ አድርጐ በ2016 እ.ኤ.አ የብራዚሏ ሪዮ ዲጄኔሮ እስካስተናገደችው 31ኛው ኦሎምፒያድ የኦሎምፒክ ኮሚቴው 5.7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል፡፡ በ32ኛው ኦሎምፒያድ መስተጓጉል ግን ይሄው የሚዲያና የስፖንሰርሺፕ ገቢ በግማሽ ሊያንስ እንደሚችል ነው የተወሳው፡፡ ከትልልቅ ኩባንያዎች ጋር የተደረጉ የስፖንሰርሺፕን የውል ስምምነቶች እንዳይሰረዙ፣ እንዳይቀንሱ እና ለኪሣራ የሚዳርጉ እንዳይሆኑ የዓለምን ስፖርትን በሚመሩ ከፍተኛ ተቋማት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከኦሎምፒክ መሸጋሸግ ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን በዓለም የስፖርት ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ያላቸው ትልልቅ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች የበጀት መቃወስም ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ በጃፓን ውስጥ የሚገኝ አገር አቀፍ ኩባንያዎች የኦሎምፒክ መሸጋሸግ ተቋቁመው ዓለምአቀፍ የስፖርት መድረኩን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ያላቸውን እቅድ አመልክተዋል፡፡ ዓለምአቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በስሩ 33 የስፖርት ፌዴሬሽኖች (የበጋ ስፖርት) ፤ 206 ብሔራዊ የኦሎምፒክ  ኮሚቴዎች፤ 7 የክረምት ስፖርት ውድድሮችን የሚያስተዳድሩ ዓለምአቀፍ ተቋማትና 220 የአትሌት ተወካዮችን እንደሚያሰባስብ ይታወቃል፡፡
በዓለምአቀፍ ደረጃ የስፖርት ወድድር አዘጋጆች ስፖንሰሮች፣ የብሮድካስት አሰራሮች ከሚገናገራቸው ኪሣራ ባሻገር ተጐጂዎቹ በሁሉም ስፖርቶች የሚወዳደሩ አትሌቶች ናቸው፡፡ ከኦሎምፒክ ጋር በተያያዘ ሚኒማውን ያሟሉ አትሌቶች በውድድሩ ወቅት መራዘም ዝግጅታቸውን ያስተጓጉለዋል ሚኒማ ያላሟሉ አትሌቶች ደግሞ የውድድር ዕድሎች አለመኖራቸው ፈተና ውስጥ ይከታቸዋል፡፡ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ እንደገለፀው ለ32ኛው ኦሎምፒያድ 122 ቀናት ሲቀሩ ከ6000 በላይ ኦሎምፒያኖች ሚኒማቸውን አሟልተው ነበር፡፡ 1000 በላይ ደግሞ በቀረው ጊዜ ሚኒማውን ለማሟላት እየተዘጋጁ ነበር፡፡ በ32ኛው ኦሎምፒያድ 206 አገራትን የሚወክሉ 11091 ኦሎምፒያኖች እንደሚሳተፉ ይጠበቅ ነበር፡፡
በርካታ የስፖርት ዘገባዎች እንዳወሱት በኦሎምፒክ የሚሳተፉት አትሌቶች በሽግሽጉ የአቋም መዋሸቅ ሊሆንባቸው ይችላል:: ብዙዎቹ ኦሎምፒያኖች በ4 ዓመት አንዴ ለሚዘጋጀው ኦሎምፒክ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች በተለየ መርሃ ግብሮችን አቅፈው ይዘጋጃሉ፡፡
ይህን ዝግጅታቸውን በሽግሽጉ ምክንያት ለመከለስ አንዳንዶቹም የመጨረሻ ዕድላቸው በመሆኑ ለማቆም ግድ ይሆንባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል በዓለም ዙሪያ በሽግሽጉ ሳቢያ ሁሉም መርሃ ግብሮችን እና እቅዳቸውን ለመከለስ ይገደዳሉ፡፡ በኦሎምፒክ መድረክ በ33 የስፖርት ዓይነቶች 339 ውድድሮች እንደሚካሄዱ ይታወቃል፡፡ 32ኛው ኦሎምፒያድ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ መሸጋሸጉ ለስፖንሰሮች፣ ለአዘጋጅ ኮሚቴው፣ ከፍተኛ ዝግጅት ላደረጉ አትሌቶች በተለያየ መልኩ ተፅእኖ የሚፈጥር ሆኗል፡፡ የጃፓን መንግስትና የኦሎምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴው በቀጣይ 1 ዓመት የ32ኛው ኦሎምፒያድ መርሐግብሮችን ለማሸጋሸግ ከፍተኛ ስራ ይጠብቃቸዋል፡፡ የኦሎምፒክ መሸጋሸግ በሌሎች የዓለም ስፖርት እንቅስቃሴዎች ከሚፈጥረው ተፅእኖ ባሻገር፤ በቀጣይ ኦሎምኮችም ላይ መስተጓጐልን ያመጣል፡፡ በ2024 እ.ኤአ 33ኛውን ኦሎምፒያድ የምታስተናግደው የፈረንሳይ ከተማ ፓሪስ በሽግሽጉ መታወኳ አይቀርም፡፡ የ4 ዓመት የኦሎምፒክ መርሐ ግብር አዘጋጁን፣ ስፖርተኛውን ስፖንሰሮቹን በተዛባ የዝግጅት መርሐ ግብር ውስጥ ይከታቸዋል፡፡
በከፍተኛ ኪሣራ ውስጥ የሚገባው እግር ኳስ
የኮሮና ወረርሽኝ ከስፖርቶች በተለይ በእግር ኳስ ላይ ያደረሰው ኪሣራ ከፍተኛ ነው፡፡ የአውሮፓ 5 ታላላቅ ሊጐች ሁሉም ውድድሮች በመቋረጣቸው ለአስተዳደራዊ ውሳኔዎች የሚያስቸግሩ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ የውድድር ዘመኑን ሻምፒዮናዎች የሚወሰኑ መርሐ ግብሮች ተቋርጠዋል፡፡ በአውሮፓ ውድድሮች በቀጣይ የውድድር ዘመን የሚሳተፉትን ለመወሰን ያልተቻለ ሲሆን፣ ከየሊጐቹ እነማን ይወርዳሉ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ አለመኖሩ የውድድሩን አስተዳደር ያሳስበዋል፡፡ የጨዋታ መርሐግብሮች መሸጋሸግ በቀጣይ የውድድር ዘመናት የሚደረጉትን የ5 ታላላቅ ሊጐች አጠቃላይ እንቅስቃሴን በከፍተኛ ደረጃ ያቃውሳል፡፡ በተለይ አምስቱን የአውሮፓ ታላላቅ ሊጐችን ከፍተኛ ገቢያቸውን የሚያጡበትም ይሆናል:: KPMG የተባለ ተቋም በሰራው ጥናት የአውሮፓ 5 ታላላቅ ሊጐች በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ያጡት ገቢ ከ4.54 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በማጣት የመጀመሪያው ሲሆን፤ የስፔን ፕሪሚዬር ሊጋ፤ 1 ቢሊዮን የጀርመን ቦንደስ ሊጋ 850 ሚሊዮን፣ የጣሊያን ሲሪኤ 750 ሚሊዮን እንዲሁም የፈረንሳዩ ሊግዋን 450 ሚሊዮን ዶላር ከገበያቸው ያጣሉ፡፡
በኮሮና ወረርሽኝ የተነሳ ወደ 2021 እ.ኤ.አ ላይ የተሸጋሸጉ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በሺዎች የሚቆጠሩ መሆናቸው ብዙዎችን ግራ የሚያጋባ ሆኗል፡፡ ወደ 2021 እ.ኤ.አ ከተሸጋሸጉት ውድድሮች መካከል የ2020 አውሮፓ ዋንጫ እና የደቡብ አሜሪካው ኮፓ አሜሪካ ይጠቀሳሉ::


Read 11753 times