Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 07 July 2012 09:35

ስልሳዎቹ ቀደምት የደርግ የግፍ በትር ሰለባዎች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከአዘጋጁ፡- ሰኔ 9 ቀን 2004 ዓ.ም በጥበብ ገፅ ላይ ለንባብ የበቃው “ቄሳር እና ብርሃኑ ድንቄ” የተሰኘ መጣጥፍ፡፡ ፀሃፊ ባየህ ኃይሉ ተሰማ ሲሆን የተለያዩ ፅሁፎችን ለጋዜጣችን በማቅረብ ይታወቃል፡፡ ከፅሁፉ ጋር ስሙ ሳይጠቀስ በመቅረቱ ፀሃፊውንና አንባቢያንን ይቅርታ እየጠየቅን በዚህ አጋጣሚ ፀሃፊው ለሚያቀርባቸው ፅሁፎች ልባዊ ምስጋናችንን ልናቀርብ እንወዳለን፡፡1969 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ልዩ ልዩ ፈተናዎችን ያስከተለ ከባድ ጊዜ ነበር፡፡ በወሎ በደረሰው ድርቅ ሕዝብ ተራበና በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ረገፉ፡፡ ረሐቡን ያመጣው ድርቅ እንጂ መንግሥት ባይሆንም “ያንን ያህል ሰው በምግብ እጦት ሲያልቅ ችግሩ ለምን ተሰወረ?” በማለት መንግሥት ብርቱ ውግዘት ደረሰበት፡፡

መላው ያገሪቱ ጦር ሠራዊት ከነገሌ እስከ አሥመራ፤ ከሐረር እስከ ጅማ የአመጽ እሳትን አቀጣጠለ፡፡ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በከተሞች ታይቶ ያልታወቀ ተቃውሞን አስከተለ፡፡ ታክሲ ነጂዎች የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን፣ መምህራን ደግሞ “ሴክተር ሪቪው” የተባለውን አጠቃላይ የትምህርት ጥናት በመቃወም የሥራ ማቆም አድማ መቱ፡፡ የዩኒቨርሲቲና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች “መሬት ላራሹ” በማለት በሠልፍ እየወጡ በከተማው ውስጥ በመዘዋወር ከፖሊስ ኃይል ጋር የሚፈጥሩት ግጭት የከተማው የእለት ከእለት ክስተት ሆነ፡፡

በነዳጅ ላይ የተደረገውን ጭማሪ በመቀነስና ለሠራዊቱ የደሞዝ ጭማሪ በማድረግ መንግሥት ተቃውሞውን ለማለዘብ ሞከረ፡፡ ይሁን እንጂ ተቃውሞው በመብረድ ፈንታ ከዕለት ወደ ዕለት እየተጋጋመ ይሄድ ጀመር፡፡ ከተለያየ አቅጣጫ የሚጎርፈው ኃይሉም እለት ከእለት እየበረታ የመጣውን ወጀብ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ኃብተ ወልድ ሊቋቋሙት አልቻሉም፡፡ በመሆኑም የካቲት 20 ቀን 1969 ዓ.ም ለንጉሠ ነገሥቱ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ካቢኔያቸው ፈርሶ እንዲሰናበት አደረጉ፡፡

የካቲት 21 ቀን 1966 ዓ.ም ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው በሬዲዮ አስታወቁ፡፡ ወዲያው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለካቢኔ ሚኒስትርነት የመረጣቸውን ሰዎች አቅርቦ በንጉሠ ነገሥቱ እንዲሾሙ አደረገ፡፡ ተማሪዎች፣ ወታደሮችና የመንግሥት ሠራተኞች ግን “ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም” በሚል አዲስና ወቅታዊ መፈክር ሥር ተሰባስበው ጸረ - መንግሥት ተቃውሟቸውን አጧጧፉ፡፡

በዚሁ ጊዜ የአየር ወለድ ጦር አዛዥ በነበሩት ኮሎኔል የዓለም ዘውድ ተሰማ የሚመሩና የአዲስ አበባና የአካባቢዋን የጦር ክፍሎች እንወክላለን የሚሉ መሥመራዊ መኮንኖችና የበታች ሹሞች “የጦር ኃይሎች ኮሚቴ” የተሰኘ ቡድን ፈጥረው፣ በአራተኛ ክፍለ ጦር ጠቅላይ መምሪያ ውስጥ ድርጅታቸውን መሠረቱ፡፡ ይህ ኮሚቴ ስራውን የጀመረው “ሀገርና ሕዝብ በድለዋል፤ ፍትሕ አዛብተዋል” የተባሉ የቀድሞ ካቢኔ አባላት በጥበቃ ሥር ሆነው እንዲመረመሩ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልካቸውን በመጠየቅ ነበር፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ልጅ እንዳልካቸው መኮንንም የወታደሮቹን ጥያቄ መቀበል ውጥረቱን የሚያረግብ ስለመሰላቸው፣ ንጉሱን በማግባባት ለወታደሮቹ አዎንታዊ መልስ እንዲሰጥ አደረጉ፡፡ ሚያዝያ 18 ቀን 1966 ዓ.ም ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ኃብተ ወልድ እና በቅርብ የተገኙ የቀድሞ ሚኒስትሮች፤ ከንጉሠ ነገሥቱ ፊት እንዲቀርቡ ተደርጎ ለጥቂት ጊዜ በጦሩ ጥበቃ ሥር እንዲቆዩ መወሰኑ፣ በመከላከያ ሚኒስትሩ በጀነራል አብይ አበበ አማካይነት ተነገራቸው፡፡ በዚሁ ዕለትም ተይዘው ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ሠፈር ተወሰዱ፡፡

ሌሎች ባለሥልጣኖችም ተጨምረው ሚያዝያ 20 ቀን 1966 ዓ.ም እስረኞቹ ጎፋ ሰፈር ይገኝ ወደነበረው የ17ኛ እግረኛ ሻለቃ መኮንኖች ክበብ እንዲዘዋወሩ ተደረገ፡፡ በግንቦት ወር 1966 ዓ.ም በዚሁ ሥፍራ 25 ባለሥልጣኖች በጥበቃ ሥር የነበሩ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ 18 ሚኒስትሮች፣ አምስት ሌፍተናንት ጀነራሎች እና ሁለት የጠቅላይ ግዛት እንደራሴዎች ይገኙበት ነበር፡፡

እሥረኛ ባለሥልጣናቱ እጃቸው ከተያዘ ሁለት ወር ስላለፈውና የተዘነጉ ስለመሰላቸውም ሰኔ 4 ቀን 1966 ዓ.ም ሁሉም የፈረሙበትን ደብዳቤ ለመከላከያ ሚኒስትሩ ጀነራል አቢይ አበበ ልከው እንዲያነጋግሯቸው ጠየቁ፡፡ ጀነራል አብይ አበበ ከአራት ቀን በኋላ በሰጧቸው መልስ፤ ጉዳዩን ለሚመረምረው ኮሚሽን አባሎች በመመረጥ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው “ሥራ ሲጀምሩ ጉዳያችሁ መልክ ይይዛል” ብለው ነበር፡፡

የመከላከያ ሚኒስትሩ ምላሽ ያላጠገባቸው እሥረኞች፤ ሰኔ 16 ቀን 1966 ዓ.ም አቤቱታቸውን በጽሁፍ ለአጼ ኃይለ ሥላሴ ላኩላቸው፡፡ በዚህ አቤቱታቸውም ቤተሰቦቻቸው ስንቅ በማመላለስ መጎዳታቸውን አስታውሰው፣ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡

ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም ከመላው ሠራዊት በተውጣጡ 109 ወታደሮች ደርግ በአራተኛ ክፍለ ጦር መመሥረቱ ተሰማ፡፡ ደርግ የአቶ አክሊሉ ካቢኔ አባላትን ያገኛቸው በጎፋ ሠፈር “በጥበቃ ሥር” ሆነው ነው፡፡ ከደርግ ምሥረታ ጀምሮም በጥበቃ ሥር የነበሩ የቀድሞ ባለሥልጣናት አያያዝ እየጠበቀና ቁጥራቸውም በየጊዜው እየጨመረ መጣ፡፡

ከሐምሌ 2 ቀን 1966 ዓ.ም ጀምሮ እስረኞቹ ጋዜጣና ራዲዮ እንዳያስገቡ ተከለከሉ፡፡ ጠያቂዎች እስረኞችን የሚጎበኙት በሳምንት አንድ ቀን ቅዳሜ ጧት ብቻ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከሳምንት በኋላ ሐምሌ 9 ቀን 1966 ዓ.ም ደግሞ እሥረኞች ከነበሩበት የጎፋ ሠፈር ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ሠፈር እንዲዘዋወሩ ተደረገ፡፡

በእሥረኛ ባለሥልጣናቱ ላይ የነበረው ቁጥጥር እየጠበቀ መጥቶ ከነሐሴ 3 ቀን 1966 ዓ.ም ጀምሮ መጻሕፍት ወደ ቤት እንዲመለሱ፣ ሁሉም ጸጉራቸውን እንዲላጩ፣ ከቤት ውጪ ለመናፈስ በቀን የተፈቀደው 30 ደቂቃ ብቻ እንደሆነ፣ ገላን ለመታጠብ የሚቻለው በወር አንድ ጊዜ ብቻ መሆኑን እንዲያውቁት ታዘዘ፡፡ በሐምሌ አጋማሽ ላይ የልጅ እንዳልካቸው ካቢኔ ተሽሮ ልጅ ሚካኤል እምሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ፤ ራሳቸው ልጅ እንዳልካቸውና በርከት ያሉ የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸው እየተያዙ ከነባሮቹ እሥረኞች ጋር እንዲቀላቀሉ ተደረገ፡፡

መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ ከሥልጣን መውረዳቸውን፣ ህገ መንግሥቱ መሻሩን፣ ፓርላመንት መዘጋቱን፣ አላግባብ በለጸጉ፣ ፍርድ አጎደሉ፣ አስተዳደር በደሉ የተባሉ የቀድሞ ባለሥልጣናት ሁሉ በጦር ፍርድ ቤት የሚዳኙ መሆኑን ደርግ በአዋጅ አስታወቀ፡፡ በዚሁ ዕለት የንጉሡ የልጅ ልጅ እና የባህር ኃይል አዛዥ የነበሩት ሪር አድሚራል እስክንድር ደስታ ተይዘው ከእሥረኞቹ ጋር እንዲቀላቀሉ ሆነ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ከዙፋናቸው ከወረዱ ወዲህ የሚታሰሩ ባለሥልጣናት ቁጥር በዓይነትና በብዛት እለት ከእለት እየጨመረ ክፍሎች በእሥረኞች ተጣበቡ፡፡ የክብር ዘበኛ የደርግ አባል የነበረው ሻምበል ደምሴ ደሬሳ፤ ጥቅምት 1 ቀን 1967 ሲታሰር ከቀድሞ ባለሥልጣናት ጋር የታሰረ የመጀመሪያው የአዲሱ መንግሥት ባለሥልጣን ሆነ፡፡

ጥቅምት 14 ቀን 1967 ዓ.ም ከጠዋቱ በአንድ ሠዓት ተኩል እሥረኛ ባለሥልጣኖች በሙሉ ወደ ታላቁ ቤተ መንግሥት እንዲዘዋወሩ ተደረገ፡፡ አዲሱ ወህኒ ቤት በቤተ መንግሥቱ ዙፋን ቤት እየተባለ ከሚጠራው ክፍል ሥር በሚገኘው ምድር ቤት ውሥጥ ነበር፡፡ ምድር ቤቱ ሁለት ክፍሎች የተሰሩለትና ቀዝቃዛና ጠባብ መስኮቶች ያሉት ነበር፡፡

ቀዳሚዎቹ እሥረኛ ባለሥልጣናት እጃቸው ተይዞ መጀመሪያ ጎፋ ሰፈር፤ በመቀጠል አራተኛ ክፍለ ጦር፣ በመጨረሻም ታላቁ ቤተ መንግሥት ከተዘዋወሩ በህዳር ወር 1967 ዓ.ም ስምንት ወራት ሆኗቸዋል፡፡ በነዚህ ወራት እሥረኞቹ የተከሰሱበት ወንጀል አልተነገራቸውም ወይም ክስ አልተመሰረተባቸውም፡፡

ቅዳሜ ህዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም የደርግ አባላት እና ንዑስ ደርግ በመባል የሚታወቁ ጭፍሮቻቸው በታላቁ ቤተመንግሥት ተሰብስበዋል፡፡ የስብሰባው አጀንዳ የደርጉ ተቀዳሚ ሊቀመንበር የነበሩት ጀነራል አማን አንዶም ከደርግ አባላት ጋር የፈጠሩትን አለመግባባት አስመልክቶ ለመወያየትና ውሳኔ ለማሳለፍ ነበር ይባላል፡፡ ይሁን እንጂ ጀነራሉ እጃቸውን ለመንግሥት አልሰጥም ብለዋል ስለተባለ ጉባኤው በተገኙበት “እንዲደመሰሱ” ወሰነ፡፡

ጉባኤው ቀጥሎ የተነጋገረው በአጀንዳው ላይ አስቀድሞ ባልሰፈረው በእሥር ስለሚገኙ የቀድሞ ባለሥልጣኖች ጉዳይ ነበር፡፡ በስብሰባው ላይ የእሥረኛ ባለሥልጣናቱ ኃጢአት ተዘረዘረና ጉዳያቸው በጦር ፍርድ ቤት ሳይሆን በዚሁ ጉባኤ አሁኑኑ መወሰን አለበት የሚል አቋም ተወስዷል፡፡ ደርጎቹ በዚህ ድንገት ደራሽ አጀንዳ ላይ ተመካክረው “ቀንደኞቹ” መኳንንትና መሳፍንት በሞት መቀጣት አለባቸው ሲሉ “አብዮታዊ ፍትሕ” ሰጡ፡፡

መጀመሪያ “እርምጃ እንዲወሰድባቸው” ስማቸው የቀረበው 250 ሰዎች የነበሩ ሲሆን በመጨረሻ ቁጥራቸው ወደ 141 ዝቅ ብሎ፣ ከመካከላቸው ለግድያ የተመረጡት ባለሥልጣናት ስም ተራ በተራ እየተነበበ ድምጽ እንዲሰጥባቸው ተደረገ፡፡ በዚህም መሰረት 59 ሰዎች በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ በአብላጫ ድምጽ ተወሰነ፡፡

እንዲገደሉ ከተወሰነባቸው 59 እሥረኞች ውስጥ ሀምሳ ሁለቱ የቀድሞ ባለሥልጣናት፣ 5 ወታደሮች እና 2 የደርግ አባላት ይገኙበታል፡፡ በመኖሪያ ቤታቸው በዚሁ እለት ሲታኮሱ የተገደሉት ጀነራል አማን አንዶም ሲጨመሩበት ደግሞ የሟቾች ቁጥር 60 ይሆናል፡፡ ደርግ ሞት የፈረደባቸውን እሥረኞች ማንነት ለማወቅ ያደረገው ምንም ጥረት አልነበረም፡፡

ይህንንም ኮሎኔል መንግሥቱ ሲገልጹት “መጀመሪያ ነገር እኔም ሆንኩ ሌሎቹ የደርግ አባላት ከተገደሉት ሰዎች በጣም ጥቂቶቹን ነበር የምናውቃቸው፡፡ በበኩሌ በሠራዊቱ ውሥጥ ከነበሩ ከፍተኛ አዛዦች ጥቂቶቹን ከማወቄ በስተቀር አብዛኛዎቹን ራስ እከሌ፣ ደጃዝማች እከሌ ሲባል ከምሰማ በስተቀር አላውቃቸውም፤ መዳን አለባቸው፤ መሞት አለባቸው ብሎ ለመወሰን የሚያስችለን እውቀትም ሆነ ግንዛቤ አልነበረንም” ብለዋል፡፡

ቅዳሜ ሕዳር 14 1967 ዓ.ም አመሻሽ ላይ እስረኞች የዘወትር ጸሎታቸውን አድርሰው ራታቸውን ለመብላት ሲዘጋጁ፣ ለወትሮው ማምሻው ላይ ከተዘጋ በኋላ ሲነጋ ብቻ የሚከፈተው የወህኒ ቤቱ በር በድንገት ተበረገደና ስማቸው የሚጠራ እስረኞች ብቻ ወደ ውጪ እንዲወጡ ታዘዘ፡፡

ግቢው በፓውዛ ብርሃን ደምቆ የነበረ ሲሆን ሸራ የለበሱ ሁለት ካሚዮኖች እልፍ ብለው ቆመዋል፡፡

በዚህ ጊዜ ታመው በፖሊስ ሆስፒታል ተኝተው የነበሩት ሌ/ጀነራል ኢሣያስ ገብረ ሥላሴ እና ዶ/ር ተስፋዬ ገብረ እግዚእ ከላንድሮቨር መኪና ላይ ወርደው ስማቸው ከተጠራው እሥረኞች ጋር ተቀላቀሉ፡፡ ከዚህ በኋላ የነበረውን አሰቃቂ ትዕይንት በወንጀል መዝገብ ቁጥር 1/87 (401/85) የልዩ ዐቃቤ ሕግ አምስተኛ ምስክር እንዲህ አስታውሰዋል፡-

“እሥረኞቹ ከምድር ቤቱ በየተራ በየስማቸው እየተጠሩ ወጥተው፣ እኛ ዘንድ ሲደርሱ በተሰጠን ትዕዛዝ መሠረት የአንዱን እሥረኛ ግራ እጅ እና የሌላውን እሥረኛ ቀኝ እጅ አንድ ላይ በማድረግ በካቴና እናቆራኛቸዋለን፡፡ ከዚያ በኋላ መኪና ላይ ሚሊተሪ ፖሊሶቹ ያሳፍራሉ፡፡ በዚህ ዓይነት በግምት ከአምሳ በላይ ሰዎች ተቆራኝተው መኪና ላይ ተጫኑ፤ መኪና ላይ ገባንና ጉዞ ተጀመረ፡፡

በጉዞ ላይ እሥረኞቹ “የት ነው የሚወስዱን ወቴ?” ቢሉኝ “እኔም አላወቅኩም” አልኳቸው፡፡ ሜክሲኮ አደባባይ ደርሰን ወደ ወህኒ ቤት አቅጣጫ መኪናው ሲጠመዘዝ ደስታ ተሰማቸውና “ወህኒ ቤት ከገባን ጥሩ ነው፤ ቤተሰቦቻችንም ይጠይቁናል” ብለው ተወያዩ፡፡

ጉዞው ቀጠለና የአዲስ አበባ ወህኒ ቤት ግቢ በር ተከፍቶ መኪናው እሥረኞቹን እንደያዘ ሲገባ፣ በመኪናው መብራት ሳንጃ የተሰካበት መሣሪያ ይዘው የተደረደሩ ወታደሮችን እሥረኞቹ ሲመለከቱ በመደናገጥ ተንጫጩ፡፡ ራስ መስፍን “”ይህ ባሪያ ሊፈጀን ነው፤ ለፍርድ ሳንቀርብ፤ ፍርድ ይታይልን” ብለው ጮሁ፤ ሌሎቹ አስተጋቡ፡፡

መኪናው ወደፊት ሄደና አዙሮ ቆመ፡፡ እሥረኞች ወርደው በሠልፍ መደዳ የሕንፃው ግንብ ከኋላቸው ሆኖ ቆሙ፡፡ የመኪና መብራት ይበራባቸዋል፡፡ የፊሽካ ድምጽ ተሰማ፡፡ ማን እንደነፋው አላውቅም፡፡ ሁለት ጊዜ እንደተነፋ በተደረደሩት እሥረኞች ላይ የእሩምታ ተኩስ ተከፈተ” ሲሉ የዓይን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የጥይት ናዳ በእሥረኞቹ ላይ መውረድ እንደጀመረ በፉከራ፣ በጩኸት፣ በዋይታና በሲቃ አካባቢው ተሞላ፤ ሬሳ በሬሳ ላይ ተደራረበ፡፡አካባቢው እርጭ ያለው ወታደሮች ሕይወት ያላቸዉን እያገላበጡ በፍተሻ ተኩስ ካጠናቀቁ በኋላ ነበር፡፡ ጭፍጨፋው ከምሽቱ 4 ሠዓት አካባቢ ተፈጸመ፡፡

የባለሥልጣናቱ አስከሬን አስቀድሞ በቡልዶዘር ተቆፍሮ በተዘጋጀ የጅምላ መቃብር ውስጥ እንደማናቸውም ጉድፍ ተጣለና ሬሳቸው ላይ ኖራ እንዲነሰነስበት ተደረገ፡፡

ግድያው በትክክል መፈጸሙን የሚያረጋግጥ በደርግ የተወከለ ከተራ ወታደሮችና ከበታች መኮንኖች የተውጣጣ ቡድን በስፍራው ተገኝቶ ጭፍጨፋውን ተመልክቷል፡፡ የወህኒ ቤቱ ኃላፊ የ60 ሰዎች አስከሬንን መረከቡን (አንዱ አስከሬን በመኖሪያ ቤታቸው የተገደሉት የጀነራል አማን ነው) የሚያሳይ ደረሰኝ ቆርጦ ሰጠ፡፡ የጭፍጨፋው ጠቅላላ ሪፖርትም በሻለቃ ጌታቸው ሺበሺ አማካይነት ለደርጉ ቀረበ፡፡

በዚሁ ረፖርት መሠረትም ሻለቃ ጌታቸው ሺበሺና ሻምበል ኃይሌ መለስን ጨምሮ 11 ሰዎች በ59ኙ እሥረኞች ላይ 393 ጥይቶች መተኮሳቸው ተጠቁሟል፡፡

ይህም ለአንድ ሟች በአማካይ 7 ጥይት ተተኩሷል እንደማለት ነው፡፡ ግድያው ሲጀመር በተፈጠረው መደናገጥና መደናበር ምክንያት ከደርጉ ወገን የነበሩ 6 ወታደሮች መቁሰላቸውና በወቅቱም በደርጉ የህክምና ሀላፊ ህክምና እንደተደረገላቸው በሪፖርቱ ተገልጧል፡፡

በዚህ ዕለትን የተጨፈጨፉት ኢትዮጵያውያን ከ18 ዓመት እስከ 75 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ከሲቪሎች አንድ ልዑል፣ 2 ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ 17 ሚኒስትሮች፣ 11 የጠቅላይ ግዛት እንደራሴዎች እና የአውራጃ ገዢዎች፣ ከወታደሩ ክፍል ደግሞ 9 ሌፍተናንት ጀነራሎች፣ 3 ሜጀር ጀነራሎች፣ 3 ብርጋዴር ጀነራሎች፣ 3 ኮሌኔሎችና 9 መስመራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንት ይገኙባቸው ነበር፡፡

በጅምላ ግድያው ማግሥት፤ እሁድ ህዳር 15 ቀን 1967 ዓ.ም “ከጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ የተሰጠ ከፍተኛ የፖለቲካ ውሳኔ” የሚል ርዕስ ያለው የደርጉ መግለጫ በወታደራዊ ማርሽና በፍየል ወጠጤ ቀረርቶ ታጅቦ፣ በራዲዮና በቴሌቪዥን ለህዝብ ቀረበ፡፡ “የረሱህን አልረሳናቸውም፤ መሣቂያ መሣለቂያ ያደረጉህን ሁሉ አልዘነጋናቸውም” ያለው መግለጫው፤ የቀድሞ ባለስልጣናቱ፤ ፍትህ በማጓደል፣ በረሐብ ህዝብ በመጨረስ፣ የደሀውን መሬት በመቀማት፣ በጎሳና ሃይማኖት በመለያየት፣ በምዝበራና ጉቦ በመብላት፣ የእናት ሀገርን ምስጢር በመሸጥ፣ አገሪቱን “የዓለም ሥልጣኔ ጭራና ተመጽዋች ደሀ አገር” በማድረጋቸውና በመሳሰሉት ወንጀሎች በጅምላ በተገደሉ ማግስት ክስ አቅርቦባቸዋል፡፡

መግለጫው በመጨረሻም “የኢትዮጵያን ሕዝብ መብትና ነጻነት ረግጠው ግፍ ሲሰሩበት የኖሩት ጨቋኞች ላይ ዛሬም ሆነ ወደፊት የሚወሰደው እርምጃ በንጹህ ሰዎች ላይ እንደተወሰደ ወይም ንጹህ ደም እንደፈሰሰ የማንቆጥረው መሆኑን እናረጋግጣለን” ሲል የገዳዮቹን አለመጸጸት እንዲሁም ወደፊትም ተመሳሳይ የግፍ በትር እንደሚሰነዝሩ ያለውን ተስፋ አረጋግጧል፡፡

በዚህ የጅምላ ግድያ “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” የተሰኘው የደርጉ መፈክር የይስሙላ መሆኑ ገሐድ ወጣ፡፡

የወታደሮቹም የሥልጣን ጉዞ በደም አደፈ፡፡ ይህ ግድያ የመጨረሻው ሳይሆን እንዲያውም በመጪዎቹ አመታት በመላው አገሪቱ የሚነግሰው ደም መፋሰስና ሽብር በር ከፋች ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

የሥልጣን ወንበሩን በደም ገንብቶ፣ የእልፍ አእላፍን ደም ጠጥቶ በደም ጎዳና ሲጓዝ የነበረው የደርጉ መንግሥት ሲንኮታኮት “የማይገለጥ የተከደነ፤ የማይታወቅ የተሰወረ ምንም የለም” እንደተባለው፤ ደርጉ እያረደ ሬሳቸውን እንደ ጉድፍ የትም የጣላቸው ኢትዮጵያውያን አጽም እየተፈለገ ከጅምላ መቃብር የሚወጣበት ጊዜ መጣ፡፡

እነሆ የነዚህ ቀደምት የደርግ የግፍ አገዛዝ ሰለባዎችም በስውር ተገድለው የተጣሉበት የጅምላ መቃብር በጥቆማ ተገኝቶ፣ የካቲት 6 ቀን 1984 ዓ.ም የ60ዎቹ ሟቾች አጽምን ሙሉ በሙሉ በቁፋሮ ለማውጣት ተቻለ፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በሐምሌ ወር 1971 ዓ.ም ከታላቁ ቤተ መንግሥት እሥር ቤት ተወስደው የተገደሉት የአቡነ ቴዎፍሎስ እና የሌሎች 9 ባለሥልጣናት አጽም ተቆፍሮ ወጣ፡፡ የእነዚህ በሁለት የተለያዩ ሥፍራዎች የተገደሉ 68 ባለሥልጣናት አጽም በአንድ ላይ (የአቡነ ቴዎፍሎስን ሳይጨምር) ሐምሌ 20 ቀን 1984 ዓ.ም የሟቾች ቤተሰቦችና ዘመድ አዝማድ በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በተዘጋጀለት ዘላቂ ሥፍራ እንዲያርፍ ሆነ፡፡

 

 

Read 4208 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 10:02

Latest from