Print this page
Saturday, 28 March 2020 14:59

ጋዜጠኞች ሙያችሁን ለማስከበር በራሳችሁ ላይ ዝመቱ!

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(1 Vote)

     የዛሬ ሳምንት በዚሁ ርዕስ ስር በቀረበው ክፍል አንድ ጽሑፍ ስለ ጋዜጠኛነት ምንነት (ትርጉም) እና ስለ ጋዜጦች ህትመት አጀማመር፣ ስለ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዢንና ዲጂታል ሚዲያ ታሪካዊ አመጣጥ አጠር ያለ ማብራሪያ መቅረቡ ይታወሳል፡፡ በዚህ በክፍል 2 ደግሞ ስለ ጋዜጠኛነት መርሆዎችና የስነ ምግባር ደረጃዎች (principles and ethical standards) ምንነት፣ የተለያዩ ሀገሮችን የጋዜጠኞችና የጋዜጠኛነት የስነ ምግባር ደንብ ይዘትና ተያያዥ ጉዳዮች በአጭር በአጭሩ ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል፡፡
ጋዜጠኛነትን በተመለከተ ዓለም እውቅና የሰጣቸው የጋዜጠኞች የስነምግባር መርሆዎችና ደረጃዎች አሉ፡፡ እነዚህን የስነ ምግባር መርሆዎች በተመለከተ የተለያዩ ወገኖች የተለያየ ስያሜ ይሰጧቸዋል:: አንዳንዶች “የጋዜጠኛነት ድንጋጌዎች” (canons of journalism) ሲሏቸው፤ ሌሎች ደግሞ “የጋዜጠኛነት ሙያ የስነ ምግባር ደንብ” (journalism’s professional code of ethics) ይሏቸዋል፡፡ ሌሎች ወገኖች ደግሞ የስነ ምግባር መርሆዎች፣ ደንቦች፣ ቻርተሮች፣ ቃል ኪዳኖች፣ እሴቶች፣ ወዘተ. የሚል ስያሜ ሲሰጧቸው ይስተዋላል፡፡ የአንዳንድ ሀገሮችን ሰነዶች ስያሜና ይዘቶች ጭምር አለፍ አለፍ እያልን እንያቸው፡፡
ዓለም አቀፍ የፕሮፌሽናል ጋዜጠኞች ማህበረሰብ (The Society of Professional Journalists’ Code of Ethics - SPJ) የስነ ምግባር መመሪያ ጋዜጠኞች ሊከተሏቸው የሚገቡ መርሆዎችን ዝርዝር የያዘ ሰነድ ነው፡፡ በዚህ ሰነድ ላይ የተጠቀሱት ሃሳቦች “አድርጉ” ወይም “አታድርጉ” የሚሉ ሳይሆን “ፕሮፌሽናል ጋዜጠኞች” ሊከተሏቸው የሚገቡ መርሆዎችን በማስቀመጥ ጋዜጠኞች በሚያሰራጩት መረጃ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን እና አሰራራቸውን በዚያ መልኩ እንዲያከናውኑ አቅጣጫ የሚያመላክት ነው፡፡  
የፕሮፌሽናል ጋዜጠኞች ማህበረሰብ ይህንን የስነ ምግባር መመሪያ በአባላቱ ላይ ለማስፈጸም የሚያስችለው ስልት አልተቀመጠም፡፡ መመሪያው የጋዜጠኛን የስነ ምግባር ባህሪያት ለመገምገም የሚያስችል ማእቀፍ በማስቀመጥ ጋዜጠኞች እንዲከተሉት ያበረታታል፡፡ አድርግ ወይም አታድርግ ያልተባለበት ምክንያት ሙያው ያለውን ልዩ ባህሪና የፕሬስን ነፃነትና ገለልተኛነት ለመጠበቅ ሲባል ነው ይላሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ለዓመታት የዘለቀ ክርክር ያደርጋሉ አባላቱ፡፡ ብዙዎቹ የቅጣት ስርዓት ሊቀመጥ ይገባል የሚል አቋም አላቸው:: ይሁን እንጂ ይህንን ማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም የማስፈጸሚያ ተቋምና ተጨማሪ የህግ ስርዓቶች ስለሚያስፈልጉ ይህንን ለማድረግ አስቸጋሪ ነው በሚለው ላይ እንደ ጸኑ ናቸው፡፡ ስለሆነም በትኩረት ደረጃ ጋዜጠኞች አዘጋገባቸውን ስርዓት ያለው እንዲያደርጉ በማስተማር ላይ ማተኮርን መርጠዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ1996 በወጣው የህንድ ፕሬስ ካውንስል የጋዜጠኞች የስነ ምግባር ደንብ መሰረት፤ የጋዜጠኛነት መሰረታዊ ዓላማ ፍትሀዊ፣ ሀቀኛ፣ ተገቢና የተረጋጋ ዜና፣ አስተያየት፣ ትችትና መረጃን በማቅረብ ህዝብን ለማገልገል መትጋት ነው ይላል:: ይህንን ግብ ለማሳካት ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያላቸው የሙያ ህግጋትን በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡ እነዚህ የሙያ መመሪያዎች ጋዜጠኞች በስራቸው ሂደት ራሳቸውን አርመውና አስተካክለው ስራቸውን እንዲያከናውኑ የታለመ መሆኑም በሰነዱ መግቢያ ላይ ተገልጿል፡፡ በዚህ ደንብ ውስጥ (ንዑሳን ነጥቦችን ሳይጨምር) 65 ዋና ዋና የስነ ምግባር ድንጋጌዎችና የአፈጻጸም መለኪያዎች ተቀምጠዋል:: ከዚህ በተጨማሪ 10 መመሪያዎች (Guidelines on specific issues)፣ ሌሎች 12 ድንጋጌዎች ደግሞ “Guidelines to communal disturbances” ተብለው እንዲሁም “አድርጉ” ወይም “አታድርጉ” (Dos and don’ts) የሚሉ  8 ትእዛዞች በደንቡ ውስጥ ተዘርዝረዋል፡፡
የፈረንሳይ ብሔራዊ የጋዜጠኞች ህብረት የተመሰረተው እ.ኤ.አ በ1918 ነው፡፡ ይህ ህብረት የ102 ዓመት ዕድሜ አስቆጥሯል ማለት ነው፡፡ በምስረታው ወቅት የነበረው ደንብ በ1938 ተሻሽሏል፡፡ በዚህ ደንብ መሰረት አንድ ሰው “ጋዜጠኛ” የሚለው ስም ሊሰጠው የሚችለው፤ ለሚጽፈው ነገር ሁሉ ኃላፊነትን የሚወስድ ከሆነ ብቻ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በጋዜጠኛነት ሙያ የሚሰማራ ሰው “የሙያውን ክብር ጠብቆ ለመስራት” ያለውን ፈቃደኛነት የመግለጽ ግዴታ አለበት፡፡ በፈረንሳይ ሀሜትና ውሸት መዘገብ እንዲሁም የሰነድ ማጭበርበርና እውነትን ማዛባት፣ትልቅ የሙያ ስነ ምግባር ጥሰት መሆኑ በዚሁ ደንብ ላይ ሰፍሯል:: በፈረንሳይ ጋዜጠኛ ገንዘብ አይቀበልም:: ሙያዊ ሚስጥር ይጠብቃል፡፡ ፍትህን ያከብራል፣ ቀዳሚ ተግባር ያደርጋል፡፡ ሙያዊ ተግባርንና ፖሊስነትን አይቀላቅልም፡፡ ይሄ ሁሉ በደንቡ ላይ ሰፍሯል፡፡
የታላቋ ብሪታንያ ብሔራዊ የጋዜጠኞች ህብረት እ.ኤ.አ በ1936 ነው የተቋቋመው፡፡ የህብረቱ አባል የሆነ ጋዜጠኛ የህብረቱን የስነ ምግባር መመሪያና የሙያውን መርሆዎች ጠብቆ ለመስራት መፈረም ግዴታው ነው:: በህብረቱ ደንብ መሰረት አንድ ጋዜጠኛ፡- ምንጊዜም የሚዲያ ነፃነትን፣ ሃሳብን የመግለጽ መብትን፣ ህዝብ መረጃ የማግኘት መብትን የመጠበቅ፤ ጉዳት የሚያደርስ ስህተትን የማረም፣ በሀቅና በአስተያየት መካከል ያለውን ልዩነት የማረጋገጥ፣ በግለሰቦች የግል ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት፣ የመረጃ ምንጭን ደህንነት የመጠበቅ… ኃላፊነት አለበት፡፡
የደቡብ አፍሪካ ጋዜጠኞች ህብረት የስነ ምግባር ደንብ 9 ዋና ዋና ነጥቦችን የያዘ ሲሆን ከብሪታንያው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የሁለቱም ደንቦች ትኩረት ጋዜጠኛ የሙያ ስነ ምግባርን ያከበረና ደረጃውን የጠበቀ ሥራ መስራት እንዳለበትና በተቻለ መጠን ከስህተት የራቀ መሆን እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡
በግብጽ “የፕሬስ ካውንስል” የሚባል አካል አለ፡፡ የፕሬስ ካውንስሉ መንግስት የሚቆጣጠረው አካል ነው የሚሉ አሉ:: ይህ አካል እ.ኤ.አ በ1983 ያወጣው “ተጠያቂነትና ጋዜጠኛነት” የሚል ደንብ አለ፡፡ የግብጽ የጋዜጠኞች የስነ ምግባር ደንብ “እኛ የግብጽ ጋዜጠኞች” ብሎ ነው የሚጀምረው፡፡ ቀጥሎም “ጋዜጠኛ የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ከፕሬስ ነፃነት ጋር የተቆራኘ ሲሆን፤ ዋና ተቆጣጣሪውም ህዝብ ነው” ይላል፡፡ የፕሬስን ክብር መጠበቅ በህገ መንግስት ለግለሰቦችና ለህዝብ የተሰጠን ነፃነት ከመጠበቅ የተለየ አለመሆኑንም ይገልጻል ይኸው ደንብ፡፡ የጋዜጠኞች እንቅስቃሴ እውነትን በመናገርና ለሀገሪቱ፣ ለህዝቧ፣ ለሀገሪቷ ታሪክ፣ ነፃነት፣ ክብር፣ እሴቶች፣ መርሆዎችና ፍላጎቶች ታማኝ መሆንን መሰረት ማድረግ እንደሚገባውም በደንቡ ላይ ተደንግጓል፡፡ የጋዜጠኛው ክብር የሚመነጨው ከሀገሩና ከሙያው ክብር ነው፡፡ ይኸው ደንብ ጋዜጠኞች እርስ በራሳቸው ጉዳት እንዳያደርሱም ክልከላ አስቀምጧል፡፡ የዜና ዘገባዎችም ሆኑ የሚሰጡ አስተያየቶች የተረጋገጡ፣ ከብቀላ ወይም ውዥንብር ከመንዛት የራቁ መሆን አለባቸው፡፡ ጋዜጠኛ ለሰራው ስራ ሙሉ ኃላፊነት ያለበት መሆኑም በደንቡ ላይ ተመላክቷል፡፡
የናይጀሪያ የጋዜጠኞች የስነ ምግባር ደንብ ከላይ ከተጠቀሱት ጋር ተመሳሳይ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ ከሌሎች ለየት የሚያደርገው ጋዜጠኞች አለባበሳቸውን ጭምር እንዲያስተካከክሉና የህዝቡን ባህልና ወግ ጠብቀው እንዲለብሱ መደንገጉ ነው፡፡ ብሄርን፣ ሃይማኖትን፣ ፆታን ወይም አካላዊ ገጽታን መሰረት ያደረገ ትችት ማቅረብም በናይጄሪያ የተከለከለ ነው፡፡
የአውስትራሊያ ጋዜጠኞች ማህበር የስነ ምግባር ደንብ እውነትን፣ የህዝብን መረጃ የማግኘት መብትና የጋዜጠኛነት መሰረታዊ መርሆዎችን ማክበርን ቀዳሚ ያደርጋል፡፡ በአውስትራሊያ የጋዜጠኞች የስነ ምግባር ደንብ ላይ የጋዜጠኞች ዋና ተግባር ተብለው የተዘረዘሩት “መመርመር፣ ይፋ ማድረግ፣ መመዝገብ፣ መጠየቅ፣ ማዝናናት፣ ሃሳብ ማቅረብና ማስታወስ” የሚሉ ናቸው፡፡
የሀገራችንን የጋዜኞች የስነ ምግባር ደንብ ስላላገኘሁ እዚህ ላይ ማካተት አልቻልኩም:: ባደረግኩት ጥረት ደንብ ይኑር አይኑር ለማወቅም አልቻልኩም፡፡ በከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው የተለያዩ ሀገራት የተለያዩ ዓይነት የጋዜጠኞች የስነ ምግባር ደንብን አውጥተው በስራ ማዋላቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡ እነዚህ ደንቦች ተመሳሳይ ባህሪያት ያሏቸው አንቀፆችን በውስጣቸው ማካተታቸውንም ማስተዋል ይቻላል፡፡
ጋዜጠኛ ህብረተሰብን መግለጽ፤ መረጃ፣ ሃሳብና አስተያየት ማስተላለፍ ትልቁ ሚናው መሆኑ በብዙዎቹ ደንቦች ውስጥ ተጠቀወሷል፡፡ ዜጎችን መንገርና ዴሞክራሲን እውን ማድረግ፣ ሃሳብን የመግለጽ ነፃነትን ተግባራዊ ማድረግ የጋዜጠኛ ተግባር መሆኑም በደንቦቹ ላይ ሰፍሯል፡፡ የመንግስት የስልጣን አካላትን መከታተልና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ የጋዜጠኞች ኃላፊነት መሆኑ ተደንግጓል፡፡ ተጠያቂነት ተዓማኒነትን የሚያረጋግጥ መሆኑና ያለ ተዓማኒነት ጋዜጠኞች ሙያቸው የጣለባቸውን ኃላፊነት ማሟላት እንደማይችሉም በተለያየ መልኩ ተጠቅሷል፡፡
ታማኝነት፣ ፍትሃዊነት፣ ገለልተኛነት እና የሌሎችን መብት ማክበር የጋዜጠኞች ቀዳሚ ተግባር መሆኑም ብዙዎቹ ሰነዶች ላይ ተጠቅሷል፡፡ የጋዜጠኞች የሪፖርታቸውና የትንታኔያቸው መሰረት ታማኝነት፣ ለትክክለኛነት መትጋት፣ ፍትሃዊነትና ሀቅን ማጋለጥ መሆን እንዳለበትም ተመላክቷል:: ሀቅን መሸፋፈንም ሆነ እውነትን አጣሞ ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑ፣ ምላሽ ለመስጠት ለሚፈልጉ ሰፊ እድል መስጠት አስፈላጊ መሆኑ፣ ለግለሰባዊ ተክለሰውነት፣ ለዘር፣ ለጎሣ፣ ለብሄር፣ ለፆታ፣ ለእድሜ፣ ለሃይማኖት፣ ለአካል ጉዳት… አላስፈላጊ የሆነ ዘገባ ማቅረብም ሆነ ከመጠን ያለፈ ትኩረት አለመስጠት ተገቢ አለመሆኑም በሰነዶቹ ተመላክቷል፡፡ ጋዜጠኛ የመረጃ ምንጭን በአግባቡ መግለጽ፣ ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለገን ምስጢሩን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መሆኑም ተመላክቷል:: የግል እምነትንና ፍላጎትን ማሰራጨት፣ ቃል መግባት፣ ስጦታ/ጥቅማ ጥቅም መቀበል ወይም መስጠት፣ (ተዓማኒነትን፣ ፍትሃዊነትንና ገለልተኛነት ስለሚያሳጣ) ተገቢነት የሌለው ተግባር መሆኑ ተገልጿል፡፡
አድርግ ወይም አታድርግ ከማለት አኳያ፤ “ጋዜጠኛነትን ልዩ ጥቅም ለማግኘት ማዋል ተገቢ አይደለም፡፡ መረጃ ለማግኘት ማንነትን መደበቅ ክልክል ነው፡፡ ግለሰቦችን ለማጋለጥ ሳይሆን መረጃን ለማሳወቅ ቅድሚያ ስጥ፡፡ ትክክለኛ ድምጽ ወይም ምስል ተጠቀም፡፡ የሌሎችን ስራ የራስህ አስመስለህ አታቅርብ:: የሰዎችን ኀዘን አክብር፣ የግል ምጢርን ጠብቅ፣ በሰዎች ህይወት ጣልቃ አትግባ፡፡ ስህተት ከሰራህ ፈጥነህ እርማት አድርግ፡፡ የብዙሃኑን ጥቅም ለማስጠበቅ፣ የግለሰቦችን መብት ላለመጨፍለቅ መስራት አስፈላጊ ነው” የሚሉት ድንጋጌዎች በብዙዎቹ ሰነዶች ላይ ሰፍረዋል፡፡
በአጠቃላይ፤ የጋዜጠኛነትን ሙያ በተመለከተ በዓለም ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የስነ ምግባር መርሆዎች፣ ደንቦች፣ ቻርተሮች፣ ቃል ኪዳኖች፣ እሴቶች፣ በተለያዩ ወገኖች ተዘጋጅተው ስራ ላይ መዋላቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህን ሁሉ በመጭመቅ አምስት መሰረታዊ የጋዜጠኛነት የስነ ምግባር መርሆዎችን አንጥሮ ማውጣት እንደሚቻል በመስኩ ምርምር ያደረጉ ምሁራን ይገልጻሉ:: እነዚህም፡- 1). ሀቀኛነትና ትክክለኛነት 2). ገለልተኛነት 3). ሚዛናዊነትና አለማዳላት 4). ሰብአዊነትና በሌሎች ህይወት ላይ ጉዳት አለማድረስ እና 5). ተጠያቂነት የሚሉ ናቸው፡፡
ጋዜጠኞች ምንጊዜም ማስታወስ የሚገባቸው ቁም ነገር ስራቸው ከሰዎች ህይወት ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው፡፡ ኃላፊነት የሚሰማው ጋዜጠኛ ለሰራው ስራ ራሱን ተጠያቂ/ኃላፊ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ስህተትን ማረም፣ የታዳሚዎችን (ኦዲየንስ) ፍላጎት ማዳመጥ፣ የጋዜጠኛነትን ሙያ የተሟላ ያደርጋል፡፡ ስነ ምግባር የተሞላበት ጋዜጠኛነት እንደ ጉዳዩ አግባብነት ጥንቃቄ የተሞላበት ውሳኔ መወሰንን ግድ ይላል፡፡ በስራ ሂደት ጋዜጠኛ ስህተት ሊሰራ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ እናም ከጋዜጠኛነት የስነ ምግባር መርሆዎች ውስጥ ዋነኛው የጉዳት መጠንን ለመቀነስ መጣር ነው፡፡ በዚህ ረገድ አንድ መረጃ ወደ ህዝብ ቢለቀቅ የሚያደርሰውን ጉዳት ወይም የሚያስገኘውን ጥቅም ቀድሞ መመዘን የጋዜጠኞች ትልቁ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የብቃታቸው መለኪያም ጭምር እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
ጋዜጠኛ የብዙሃኑን ህብረተሰብ ተጠቃሚነት ከሚደርሰው ጉዳት ጋር በንጽጽር ማየት አለበት፡፡ ስሆነም፡- “ስራህ በሰዎች ላይ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑንና አለመሆኑን አረጋግጥ፡፡ ጉዳት ሳይደርስ መልእክቱን ለማስተላለፍ ስለ መቻል አለመቻሉ አረጋግጥ፡፡ ልቅ ስድብን፣ ጉዳት የሚያመጣ ድምጸትን፣ መላምትን አስወግድ፡፡ ቢገለጽ ለህዝብ የሚሰጠውን ጥቅም ለማስቀደም ካልሆነ በስተቀር የግለሰቦችን ምስጢር ጠብቅ፡፡ ህፃናትን፣ የወንጀል ተጠርጣሪዎችን፣ የበሽታ ወይም የሌላ ጉዳት ተጋላጭነትን በተመለከተ በጥንቃቄ ተመልከት” የሚሉ ድንጋጌዎች የጋዜጠኛ መርሆዎች ተደርገው በልዩ ልዩ ሰነዶች ላይ ተገልጸዋል፡፡
ቁልፍ የሆኑ የጋዜጠኛነት የስነ ምግባር ደረጃዎችን (standards) በተመለከተ “ሀቅን መፈለግ፣ ለብዙሃኑ ህዝብ ፍላጎት የሚበጀውን ተግባራዊ ማድረግ እና ጉዳትን መቀነስ” የሚሉት የጋዜጠኛነት ሙያ ጥራትና ደረጃ መስፈርቶች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፤ “እውነትን መዘገብ፣ ገለልተኛ የዓይን እማኞች ከሁለት በላይ እንዲሆኑ መጣር፣ አወዛጋቢ ነገሮችን ማብራሪያ ጨምሮ መዘገብ፣ መረጃን ከተለያየ ምንጭ ማጣራት እና ስህተት ሲገኝ በአስቸኳይ ማረም” ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ዘገባ ለማቅረብ አስፈላጊ መስፈርቶች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡
“ጋዜጠኞች ሙያችሁን ለማስከበር በራሳችሁ ላይ ዝመቱ” ያልኩበትን ምክንያት፤ እንዲሁም ስለ ሀገራችን ሜዲያዎችና ስለዘመኑ የሀገራችን ጋዜጠኞች ያለኝን አስተያየት በሚቀጥለው ሳምንት ለማቅረብ እሞክራለሁ!
ጸሐፊውን Email: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 2085 times