Saturday, 28 March 2020 12:26

ፍኖተ ጥበብ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

      “ጥበብ፣ መገለጥና መንቃት ላይ መድረስ የሚችሉት የበራላቸው ግለሰቦች ብቻ ናቸው፡፡ ለምትሰራው እያንዳንዱ ነገር ኃላፊነት መውሰድ ስትጀምር የማመዛዘን ብቃትህ
እየጨመረ ይመጣል፡፡ ማመዛዘንና ለምትሰራው ስራ ኃላፊነት እንዳለህ ስትረዳ፣ በቡድን ውስጥ የመዋጥ እድልህ ይቀንሳል፡፡”
              የሱፊ መምህሩ  ከአንድ ደቀመዝሙሩ እንዲህ የሚል ጥያቄ ቀርቦለት ነበር፡፡ “መምህር ሆይ፤ ጥበብና መገለጥ ለምንድነው በግለሰብ ደረጃ  ብቻ የሚከሰተው ወይም
የሚገለጠው? ጥበብና መገለጥ ለምንድነው ለህዝቦች ወይም ለቡድኖች የማይበራው” ብሎ ሲጠይቀው እንዲህ ብሎ መልሶለት ነበር፡፡
“ጥበብና መገለጥ ለብሔረሰቦችና ህዝቦች በፍፁም ሊገለጥ አይችልም፡፡ ብሔር በለው ብሔረሰቦችና ህዝብ እንደ ግለሰብ የራሱ የሆነ ነብስና የተጠማ ልብ የለውም:: ነብስና ልብ የግለሰብ እንጂ ህዝብ በጋራ የሚበራው ነገር አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ህዝብ የሰዎች ስብስብ እንጂ በራሱ መቆም የሚችልበት እንደ ግለሰብ ህልውና ያለውና ያለው አይደለም፡፡ ለምሳሌ እኔ እዚህ ለተሰበሰባችሁት ሳወራ፣ የማወራው ለእያንዳንዳችሁ እንደ ግለሰብ ነው እንጂ እንደ ቡድን ወይም እንደ ህዝብ አይደለም:: እናንተም ስታዳምጡኝ  በቡድን  ሳይሆን እያንዳንዳችሁ እንደ ግለሰብ ነው፡፡ አመንም አላመንም ህልው የሆነው ግለሰብ እንጂ ብሔር በለው ብሔረሰቦች አይደለም:: ብሔር በለው ብሔረሰብ የግለሰቦች ስብስብ ስም ብቻ ነው፡፡፡አንዳንድ ሰዎች ይሄን ህዝብ ወይም ያን ህዝብ እንወደዋለን ሲሉ ሰምታችሁ ታውቃላችሁ፡፡ እነዚህን መሰል ሰዎች ራሳቸውን አታለው ሌላውን የሚያታልሉ ናቸው፡፡ የትም ብትሄድ የምታገኘው ግለሰቦችን ነው እንጂ ብሔሮችን ወይም ብሔረሰቦችን አይለም፡፡ በጅምላና በደፈናው መውደድ የሚባል ነገር የቀልድ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች  ህዝቡን በጅምላ እንወዳለን ሲሉ ለግለሰብ ያላቸውን ፍቅርና መውደድ መግለፅና ማሳየት ስለማይችሉ ነው፡፡ ህዝቡን እወደዋለሁ ስትል ከቃላት ያለፈ ማሳያ ማቅረብ አይጠበቅብህም፡፡  ግለሰብን ስትወድ ግን ከቃላት በላይ ማሳያ ማቅረብ መቻል አለብህ፡፡ ይህን ማድረግ ስለማይችሉም ሁልጊዜ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚል ሽፋን ይፈልጋሉ፡፡ አንድ ሰውን ለመውደድ ትልቅ ጥበብና መሰጠት ይፈልጋል፡፡ እውነት ውበትና ፍቅር ሁልጊዜ በግለሰብ ደረጃ ብቻ ነው የሚገኙበት፡፡
ወደ አምልኮ  ቦታዎች ሄደን ስናመልክ በግለሰብ ደረጃ ነው እንጂ እንደ ቡድን ወይም እንደ ህዝብ ሆነን አይደለም:: በቡድን መፅደቅ የሚባል ነገር የለም፡፡ በኮሚኒዝምና በሀይማኖት መካከል ያለው ትልቁ አለመግባባት እዚህ ላይ ነው፡፡ ኮሚኒዝም የሚያስበው በቡድን፣ በማህበር፣ በላባደርና በሰፈራ ሲሆን ሀይማኖቶች ግን መሰረታቸውን ግለሰብ ላይ ነው ያደረጉት::
ኮሚኒዝም ህብረተሰብን መቀየር ይችላል ብሎ ሲያምን፣ ሀይማኖቶች ደሞ ግለሰብን የራሱን ነብስ እንዲያድን ምን መስራት እንዳለበት ያስተምራሉ፡፡ ህዝቡን በአንድ ላይ መለወጥ ወይም መቀየር አይቻልም:: ህዝብ ነብስና ስጋ ያለው ህልው አካል አይደለም፡፡ መለወጥ የሚቻለው በራሱ ህልውና ያለውን ግለሰቡን ብቻ ነው፡፡
ኮሚኒዝም ግለሰብ ሳይሆን ህዝብ ነው ህልውና ያለው ሲል፣ ሀይማኖቶች ደሞ የለም መዳን በግለሰብ ብቻ ነው ይላሉ፡፡ ይህ አለመስማማትን ወይም ጠላትነትን ፈጥሯል:: ኮሚኒዝም በተስፋፋባቸው ሀገሮች የግለሰብ ነፃነት የሚታሰብ አይደለም፡፡ ግለሰቦች እራሳቸውን ችለው ሳይሆን የህዝብ አንድ  ክፍል ወይም አካል ሆነው ነው መቆም የሚችሉት፡፡ በኮሚኒዝም አስተሳሰብ ግለሰቦች ልክ መኪና ውስጥ እንዳለ ብሎን ነው የሚቆጠሩት፡፡
በስታሊን የአገዛዝ ዘመን ሞስኮ ውስጥ ያለ አንድ ሰው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ቀርቦ ፓሮት እንደጠፋበት አመለከተ፡፡ ተረኛ ፖሊሱ መዝገቡን አውጥቶ እየመዘገበ እንዲህ ብሎ ጠየቀ፤
“ፓሮቱ መናገርና ማውራት ይችላል?” ሰውዬው የጥያቄው አላማ ገብቶታል፡፡ ሳያውቀው ራሱን ጣጣ ውስጥ በመክተቱ ተደናግጦ “ማውራቱንስ ያወራል ነገር ግን ማናቸውንም የራሱን አስተያየት ነው የሚገልጠው” ብሎ መለሰ፡፡
የፓሮቱ ባለቤት የደነገጠው ፓሮቱ  የሚናገረው ነገር መነሻው ከባለቤቱ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ጣጣው ይተርፈኛል ብሎ ነው፡፡ በኮሚኒዝም የራስ ብሎ ነገር የለም፤ ሀሳብ ቢኖር
እንኳን በህዝብ በኩል፣ በማህበር በኩል፣ ወይም በአደረጃጀት በኩል ነው መምጣት ያለበት፡፡ በግለሰብ ደረጃ ማሰብም ሆነ አስተያየት መስጠት  አይቻልም፡፡ ይሁን እንጂ ሁሌም
ጥበብና መገለጥ በግለሰብ ደረጃ  እንጂ በህዝብ ደረጃ አይመጣም፡፡ እንደ ማንዴላ፣ እንደ አልበርት አነስታይን፣ እንደ አበበች ጎበና፣ የመቀዶኒያው ቢኒያም ሰብዓዊ ልእልና ላይ
የሚደርስ ህዝብ የለም፡፡
ይልቁንም ለህዝብ ወይም ቡድኖች ቅርብ የሚሆነው ጥበብና መገለጥ ሳይሆን በአድማ ተደራጅቶ ትልቅ ጥፋት ማድረስ ነው፡፡ በተግባር እንደታየው በዓለም ላይ ትልልቅ ጥፋቶች
የተፈፀሙት በተደራጁ ቡድኖች እንጂ በግለሰቦች አይደለም፡፡ አንድ ግለሰብ ሰው ቢገድል እንኳን ከተወሰኑ ሰዎች በላይ መግደል እንጂ ዘር ማጥፋት አይችልም፡፡ አንድ ግለሰብ
ፋሺዝምን ወይም ናዚዝምን ብቻውን መርቶ ሚሊዮኖችን መግደል አይችልም፡፡
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅን ተከትሎ፣ የተያዙት የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ቀርበው ጥፋተኞች አይደለንም ብለው ሲከራከሩ ነበር፡፡ ማስረጃቸውም “እኛ የተደረገውን ነገር ሁሉ የፈፀምነው ከበላይ አለቆቻችን ታዘን ነው እንጂ የግል ፍላጎታችንን  ለመፈፀም አይደለም” የሚል ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ለአንድ ዓላማ የተሰበሰቡ ቡድኖች አባል መሆናቸውን አልተረዱትም:: በግለሰባዊ ህይወታቸው ሂትለርም ይሁን ሙሶሎኒ እጅግ ስሱ ሰዎች ነበሩ፡፡ ሂትለር እንዲያውም ለስለስ ያሉ ሙዚቃዎችን አብዝቶ ይወድ ነበር:: ኸረ እንዲያውም ስዕል መሳል ሁሉ ይሞክር ነበር፡፡ ለአርት ፍቅር የነበረው ሂትለር፤ ሚሊዮኖችን ያለ ምንም ርህራሄ ሲያስጨፈጭፍ ጉንዳን እንደገደለም የስሜት ለውጥ አይታይበትም ነበር፡፡ ሂትለርም ቢጠየቅ “እኔ ተጠያቂ አይደለሁም” ነበር የሚለው፡፡ ምክንያቱ ደሞ “እኔ የናዚ መሪ እንጂ የማጎሪያ ጣቢያዎቹ አዛዥ አይለሁም” የሚል ይሆን ነበር፡፡ ተጠያቂ መሆን ያለበት ቡድኑ እንጂ እኔ አይደለሁም፤ የሁሉም የወንጀል ተባባሪዎችና ፈፃሚዎች የመጨረሻ ንግግር ነው፡፡
በቡድን ስትንቀሳቀስ ማናቸውንም ጥፋት ለመፈፀም ቅርብ ነህ፡፡ ብቻህን ለመፈፀም ብዙ የምታስብበትን ድርጊት፣ በቡድን ሲሆን በቀላሉ ትፈፅመዋለህ፡፡ “እኔ ብቻ አይደለሁም
ሌሎችም እያደረጉት ነው” በሚል ለጥፋት በቀላሉ ትተባበራለህ:: በቡድን ስትሆን ተጠያቂነት የለም፣ በራስ አእምሮ ማሰብ የለም፣ ማገናዘብ የለም፣ ክፉና ደግ መመርመር የለም፤
በቡድን ውስጥ ስትሆን ትዋጣለህ፡፡ የአለምና የሀገራት ታሪክ ያሳየን ቡድኖች ተደራጅተው ሲጨፋጨፉና ጥፋት ሲፈፅሙ ነው እንጂ በጥበብና መገለጥ ተሞልተው የብርሃን ዘመን
ሲያበስሩ አይደለም፡፡
ጥበብ፣ መገለጥና መንቃት ላይ መድረስ የሚችሉት የበራላቸው ግለሰቦች ብቻ ናቸው፡፡ ለምትሰራው እያንዳንዱ ነገር ኃላፊነት መውሰድ ስትጀምር የማመዛዘን ብቃትህ እየጨመረ ይመጣል፡፡ ማመዛዘንና ለምትሰራው ስራ ኃላፊነት እንዳለህ ስትረዳ፣ በቡድን ውስጥ የመዋጥ  እድልህ ይቀንሳል:: ቡድንን የምትፈልገው በራስህ መቆም ሲያቅትህና  የደህንነት ዋስትና ለማግኘት ስለምትፈልግ ብቻ ነው፡፡
ጥበብና መገለጥ ሀድራዋን እንድትከፍትልህ ከፈለግህ፣ ከቡድናዊ አስተሳሰብና የኔ ብሔር፣ የኔ ሰፈር ከሚል አመለካከት መውጣት መቻል አለብህ:: በራስህ አስብ፣ ጠይቅ፣ ተመራመር፣ አንብብ፣ ራስህን ለማግኘት ሞክር፡፡ ጥበብን ከብሔር በፍፁም አታገኘውም፡፡


Read 1675 times