Saturday, 28 March 2020 12:26

ዋጋ እየናረ፣ ጨጓራ እየተላጠ እስከ መቼ!?

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ስንት መቶ ሱቆች ናቸው ታሸጉ የተባለው?! ይሄ ሁሉ ነጋዴ ያለ አግባብ በመሰረታዊ እቃዎች ላይ ዋጋ መቆለሉ…አለ አይደል…የግለሰቦቹ ‘ክፋት’ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የስርአትና ህግ የማስከበር ጉዳይም ነው፡፡
የምር እኮ፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል…… በዋጋ መናር ስናለቅስ እኮ ብዙ ጊዜያችን ነው፡፡ ቀደም ሲል በዓላትን እየጠበቀ የሚጨምረው ዋጋ አሁን፣ አሁን በሀያ አራት ሰዓት ውስጥ ሲለዋወጥ እያየን ነው፡፡ ማታ ቤታችሁ ስትገቡ የሰማችሁት የሆነ እቃ ዋጋ፣ ጠዋት ተመልሳችሁ ስትወጡ ጨምሮ የምታገኙበት ጊዜ ሆኗል፡፡
“ሽንኩርት ስንት ኪሎ ነው የገዛሽው?”
“ሦስት ኪሎ፡፡”
“ሦስት ኪሎ! ምኑን ከምኑ ልታደርጊው ነው? ጨመር አታደርጊም ነበር?!”
“አንቺ ደልቶሻል፡፡ እንኳን ልጨምርበት ይሄም ወገቤን ሰብሮኛል፡፡”
“ኪሎውን ስንት ብትገዥው ነው?”
“ሀያ አንድ ብር!
“ሀያ አንድ ብር! እኔ ከሶስት ቀን በፊት ኪሎውን አስራ ሰባት አይደል እንዴ የገዛሁት!”
እናላችሁ…ነገሩ እንዲህ ሆኖላችኋል:: የሰሞኑ ጭማሪ ግን እንደ ሌላው ጊዜ “ስግብግቦች!” “በልተው የማይጠግቡ!” ምናምን ተብሎ የሚበቃው አይደለም:: ምክንያቱም ጭካኔ ነውና!
የለየለት ኢ-ሰብአዊነት ነውና! “ጨካኞች!” የምንለው የስድብ አምሮት ስላለብን ሳይሆን ለድርጊቱ ሌላ መገለጫ ስለሌለው ነው! የፈለገ ጥቅም የማጋበስ አምሮት ቢኖር፣ እዚህ ደረጃ
መድረሱ ያሳዝናል፡፡ ድፍን ዓለምን “እግዚኦ!” እያሰኘ ያለ በሽታ ሀገር ውስጥ መግባቱ ሲነገር፣ “ጠንቀቅ በሉ፣” ምናምን ሲባል በችግሩ እንዴት ማትረፍ እንደሚቻል የሚያስብ ምን አይነት አእምሮ ነው! የአሁኑ እኮ ዝም ብሎ የዋጋ ጭማሪ ብቻ አይደለም! ዝም ብሎ የባንክ ሂሳብ የማወፈር ጉዳይ ብቻ አይደለም! የአሁኑ እኮ የህይወት ጉዳይ ነው፡፡
እኔ የምለው….ችግሩ እኮ በር እየለየ የሚያንኳኳ አይደለም! ሀብታም ከድሀ፣ ነጭ ከጥቁር፣ ባለቪላ ከባለላስቲክ ቤት እያለ የሚለይ አይደለም፡፡ ነጋዴዎች ሆይ… ተዉ እንጂ! ጀልባው ላይ
ያለነው እኮ ሁላችንም አንድ ላይ ነን፡፡ “ለመደበኛ አምስት መቶ፣ ለቪ.አይ.ፒ. አንድ ሺህ፣” ምናምን የሚባልበት አይደለም እኮ!
የምር እኮ…አለ አይደል…ዋጋ አጨማመሩ ነጋዴው ሁሉ በጠቅላላ ጉባኤ ተሰብስቦ የወሰነው ነው የሚመስለው፡፡ ባለ ሱቁም፣ መንገድ ላይ ዘርግታ የምትሸጠውም፣ ፊሽካ ነፍቶ እኩል ያስጀመራቸው ያለ ይመስል አንድ ላይ ሲጨምሩ፣ በርህራሄና በጭካኔ መሃል ያለው መስመር ይጠፋባችኋል፡፡
የሆነ ምርት ወይ አገልግሎት ላይ ዋጋ የጨመረ ነጋዴን ልክ አለመሆኑን ብትነግሩት ምን ይላችሁ መሰላችሁ… “ዋጋ መጨመር መብቴ ነው፡፡” ስለ ነጻ ገበያ ክርክር ሊገጥማችሁ ሁሉ ይችላል፡፡ እኔ የምለው…ይሄ ነጻ ገበያ ምናምን የሚሉት ነገር አንዳንዴ “አይደለም እኛ ተራዎቹ ሰዎች፣ ከበላያችን ያሉትና ሊያውቁት የሚገባቸው ሁሉ ያውቁታል ወይ?” ያስብላል:: አንድ ነጋዴ በነጻ ገበያ እንደፈለገው (‘በምርቃናም ይሁን በመረቅ’ እንደ ማለት) ዋጋ መጨመርና መቀነስ መብቱ ነው የሚል ነገር ካለ ይነገረንና ከቸርቻሪ እስከ አከፋፋይ የረግማናቸውን ነገር እንተውማ፡፡ ነገሩ… አለ አይደል… “ህጉ ከደገፋቸው እናንተ ምን ቤት ናችሁ!” ሊያስብል ይችላል!
ግርም የሚል ነው…. በአንድ ኩንታል ጤፍ ላይ አምስት መቶ ብር መጨመር፣ የሎሚ ዋጋ እስከ ሁለት መቶ ሀምሳ በመቶ መጨመር የመሳሰሉትን በሚወስኑበት ጊዜ ምን እያሰቡ ነው ያሰኛል! ቤተሰብ የላቸውም! ወላጆች፣ የትዳር ጓደኞች፣ ከአብራካቸው የወጡ ልጆች፣ የሚወዷቸው ዘመዶች የሏቸውም!
ሚኒባስ ታክሲዎች ላይ እኮ ትርፍ ሰው መጫን መደበኛ ከሆነ ከርሟል…ልክ ህጎቹ በውስጥ ሰርኩላር ምናምን የሆነ ማሻሻያ የተደረገ ያህል! ”ትራፊኩ እዛ ጋ ቆሟል ጎንበስ በል!”
“መጋረጃውን ዝጋው፣” ምናምን አይነት ጥንቃቄ እንኳን ከስንት አንዴ ነው የሚሰማው፡፡ ሰዉም ጭቅጭቁ ሰልችቶት “ጠጋ በል፣” ሲሉት እስከ ጥግ የሚጠጋ ሆኗል፡፡ አሁን
ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ እርምጃው ጠበቅ ሲል ለብዙዎቹ ህግን ማክበር ዳገት ቢሆንባቸው አይገርምም፡፡
በቀደም ከፒያሳ ወደ ሀያ ሁለት የሚሄድ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ነው፡፡ ገብርኤል መሳለሚያ ላይ አምስት ተጨማሪ ሰዎች ይጫናሉ፡፡  ከሾፌሩ ጎን የነበረ አንድ ሰውዬ… “ተው ይይዙሀል…”
ሲለው ሾፌር ሆዬ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ተዋቸው እባክህ፣ ምን እንዳያመጡ ነው!”
ኮሚክ አይደል…ህግ አስከባሪዎች “ምን እንዳያመጡ ነው!” በሚል ህግ የሚጣስባት ሀገር ሆናለች፡፡
ታዲያላችሁ… መናኸሪያን አለፍ እንዳልን መጡለታ! ሾፌር ሆዬ ወርዶ እንደ ሁልጊዜ ለመለማመጥ ቢሞክር የሚሰማው አላገኘም:: የቅጣት ትኬቱን ይዞ ሲመለስ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ሠርተን መብላት እኮ አልቻልንም፡፡”
“ጉድ በይ ጦቢያ!” ማለት ይህን ጊዜ ነው::
ስሙኝማ…የሐምሌ የግብር ወቅት ሲመጣ በሆነ ግብር መክፈያ ስፍራ ብቅ በሉና እዩልኝማ! አሁን እኛን በጭማሪ መአት ኑሮን እንድናማርር አድርጎ እያበሳጨን ያለው ነጋዴ በተራው
ሲበሳጭ ታገኙታላችሁ:: “ያልሠራሁትን ከየት አምጥቼ ነው የምከፍለው!” “ቤተሰብህን በትን ነው እንዴ የምትሉኝ!” ምን በወጣህ! የጠላት ጆሮ አይስማው፡፡ ምን በወጣህና ነው ምስኪን ቤተሰብህን የምትበትነው! ግን እኮ… የእኛ ነገርስ! የእኛስ ቤተሰብ ለምን ይበተናል! አንድ ኩንታል ጤፍ ላይ የምንጨምረው አምስት መቶ ብር ከየት እናመጣለን! አንድ ኪሎ ነጭ ሽንኩርት ላይ የምንጨምረው መቶ ሀምሳ ብር ከየት እናመጣለን! እኛንስ… ቤተሰቦቻችሁን በትኑ ነው የምትሉን!
እኔ የምለው…በዋጋ መናር በጮህን ቁጥር የሆነ መሥሪያ ቤት “የማረጋጋት ሥራ ይሠራል፣” ምናምን ይባላል፡፡ እኛም…አለ አይደል…“እሰየው፣ ለጣይም ምናምን አለው፣” እንላለን፡፡
ተከላካይ አገኘና! “ምን የቆረጠው ነው ጫፋችሁን የሚነካ!” የሚል አገኘና! ልክ የሆነ የሠፈር ጉልቤ አላስወጣ፣ አላስገባ ሲለን እንደሚደርስ ታላቅ ወንድም አይነት፡፡ ግን ምን ያደርጋል…
ምኑንም ነገር ሳናየው ሁሉም ነገር ‘ዘ ሴም ኦልድ ስቶሪ’ ሆኖ ቁጭ፡፡ እናማ… ዋጋ ይረጋጋልናል ብለን ስንጠብቅ ደማችን ሊረጋ ምንም አይቀረው:: ልክ ነዋ…እስቲ ያልጨመረ ነገር አስቡ፡፡
ስሙኝማ….እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺ ጅብ ከሄደ በኋላ እንዳለችው ጩኸት የምትመስል ነገር ተለምዳለች፡፡ አለ አይደል… የሆነ አገልግሎት፣ የሆነ ምርት ላይ ችግር ደረሰ ተብሎ በሚዲያውም በምኑም ማጉረምረም ሲበዛ ይመለከተኛል የሚለው መስሪያ ቤት የሆነ ባለስልጣን በቲቪ ብቅ ይልላችኋል፡፡
“እንደሚያወቁት በአሁኑ ጊዜ ሰዉ አገልግሎቱን በተገቢው መንገድ እያገኘን አይደለም፡፡ አቤቱታችንን  ሊሰሙልን እንኳን ፍቃደኛ አይደሉም፣ እያለ ነው፡፡ እዚህ ላይ እርሶ ምን ይላሉ?”
እሱዬው እንዴት ብሎ ይጀምራል መሰላችሁ…“በመጀመሪያ እናንተ በዚህ ጉዳይ ማብራሪያ እንድንሰጥ እድሉን ስለሰጣችሁን…“ ኸረ ወደ ጉዳይህ ግባ! መቅድም፣ መግቢያ ምናምን

ሳይልማ ወደ ጉዳዩ አይገባም!  “ድርጅታችን ከተመሰረተ ጀምሮ ባለፉት አርባ አምስት ዓመታት…” ምናምን ብሎ ከተመደበለት አምስት ደቂቃ ውስጥ ሦስት ተኩሉን ይጨረግደዋል!
(‘ይጨረግደዋል’ የሚለው ‘ያባክነዋል’ ከሚለው የበለጠ ጉልበት አለው…አይደል!) እኔ የምለው… አንዳንዶች በሆነ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ የሚቀርቡ ሰዎች ለዘጋቢ ፊልም
ምናምን የተዘጋጀ ስክሪፕት ነው እንዴ የሚያነቡት! ልክ ነዋ…እኛ አገልግሎት እያገኘን አይደለም አልን እንጂ ድርጅቱ አርባ አምስት ዓመት ሞላው፣ ስድስት ወር ምን አገባን!
“…በእርግጥ ከደንበኞች የቀረቡትን ቅሬታዎች ሰምተናቸዋል፡፡ የድርጅታችንን አገልግሎት ለማዘመን በአሁኑ ጊዜ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡” (ስሙኝማ…ይቺ “ሥራዎች እየተሠሩ
ነው፣” የምትለዋ ሀረግ ከሆነ ምርት ጋር በምርቃት አይነት ለሁሉ የምትታደል ነው እኮ የምትመስለው! ስለሆነ ጉዳይ ሲጠየቅም…ሳይጠየቅም… “ሥራዎች እየተሠሩ ነው፣” የማይል
መግለጫ ወይም ማብራሪያ ሰጪ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ግን ከዛ በኋላ ምነው “ሥራዎች ተጠናቀው እንዲህ አይነት ውጤት ተገኝቷል፣” ሲባል አንሰማሳ!)
ታዲያላችሁ…ተገልጋዩ በአገልግሎት አሰጣጥ እየተማረረ መሆኑን የተጠየቀው ሰውዬ ጉዳዩን በቀጥታ የሚመለከት ምንም ነገር ሳይል፣ ጭራሽ ቤታችን ድረስ በአየር ሞገድ መጥቶ
እኛንም አማርሮን ያርፈዋል:: እናማ…በዋጋ መናር እየተላጠ ያለውን ጨጓራችንን ለመከላከል “ሥራዎች እየተሠሩ ነው፣” የምትሉ ክፍሎች ካላችሁ “እዚህ ነን፣” በሉን! ዋጋ እየናረ፣ ጨጓራ
እየተላጠ እስከ መቼ ልንዘልቀው ነው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!






Read 1843 times