Sunday, 29 March 2020 00:00

ለከርሞም እያሰብን እንትጋ - ወረርሽኝን እየተከላከልን!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 • መጪው የክረምት እርሻ፣ በማዳበሪያና በምርጥ ዘር እጦት ወይም በሌላ ሰበብ ከተጎዳ፣ መዘዙ እጅግ የከፋ ይሆናል:: በርካታ ሚሊዮን ሰዎች ለረሃብ ይጋለጣሉ፡፡ የአብዛኛው ዜጋ ኑሮም ይከብዳል፡፡ ረሃብና ችግር፣ የአገርን ሰላም ለሚያደፈርሱና የአገርን ህልውና ለሚያናጉ አደጋዎች ያመቻቸናል፡፡
   • በማቆያ ስፍራዎች ዙሪያ የሚታዩ፣ ስርዓት ያልተበጀላቸው፣ የአሰራርና የመቆጣጠሪያ፣ የኃላፊነትና የተጠያቂነት ደንብ ያልተተገበረባቸው የዝርክርክነት አዝማሚያዎች፤ በአፋጣኝ ካልተስተካከሉ፣ በሽታን የሚይዛምቱ ይሆናሉ፡፡
   • የበሽታ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚከናወኑ የጥንቃቄና የመፍትሄ እርምጃዎች፤… 3 መመዘኛዎችን እንደሚያሟሉ ማረጋገጥ አለብን፡፡
  • አንደኛ፣ ሳይንሳዊና የተቀናጁ መሆን አለባቸው፡፡ ሁለተኛ፤ አቅምን ያገናዘቡ፣ በአንስተኛ ወጪ ከፍተኛ ውጤት የሚያስገኙ (የሚያዋጡ)፣ ሦስተኛ፣ ለወደፊት የሚጠቅሙና ተጨማሪ አቅምን የሚፈጥሩ (የሚያዛልቁ) መሆን ይገባቸዋል - የዛሬ ውሳኔያችንና ተግባራችን፡፡
    • የእለት ጉርስን የሚያሳጡና የምርት ስራዎችን የሚያስተጓጉሉ እርምጃዎች መፍትሄዎች አይደሉም - ተጨማሪ ችግሮች ይሆናሉ፡፡
    • ዛሬን ወይም ዘንድሮን ከመኖር ባሻገር የማያራምዱ፣ የዜጎች የወደፊት የኑሮ ተስፋን፣ የአገር ኢኮኖሚ የወደፊት የእድገት ጭላንጭልን የሚያጨልሙ እርምጃዎች፤ ለአመታት የማናመልጣቸው ቋሚ በሽታዎች ይሆኑብናል፡፡
                      

              በአንድ በኩል፤ የሚያጣድፍ ከባድ በሽታን በትጋትና በጽናት መከላከል አለብን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ስር የሰደደና ለትውልድ የሚዛመት፣ ድህነትንና ረሃብን የመሰለ የረዥም አመታት ቁራኛ በሽታም አለብን፡፡ ይህንን፣ የመከላከልና የማሸነፍ አቅማችን መንኮታኮት የለበትም፡፡
ዛሬ፣ ከአደገኛ ወረርሽኝ ለማምለጥ፣ ዛሬ አስፈሪውን ጨለማ ለማብራት የምናደርገው ጥረት፣ ለመጪው ዘመን የሚያገለግሉ የህዳሴ የኤሌክትሪክ ማመንጫና የመስኖ ግድቦችን የሚያመክን ሳይሆን የሚባርክ እንዲሆን፣ በእጅጉ ጠንቅቀን ማሰብና ተግተን መስራት ይጠበቅብናል፡፡
ለነገ ጤናማ የተደላደለ ኑሮ፣ እንዲሁም ለነገ የአገር ብልፅግና የሚጠቅም ከሆነ፣… በእርግጥም የዛሬ የወረርሽኝ መከላከያ የተቀናጀ ጥረታችን፣ ትክክለኛ፣ የሚያዋጣና የሚያዛልቅ ሁነኛ መፍትሄ ነው፡፡
በተቃራኒው፣ ያልተቀናጀ የዘፈቀደ ዝርክርክ ልፋት፣… ወይም አቅምን ያላገናዘበና በሳምንት ውስጥ ባዶ እጅ የሚያስቀር የመደናበር ሩጫ፤… ወይም ደግሞ ለመጪዎቹ አመታት በረሃብና በችጋር አገርን የሚያንኮታኩት “ቅርብ አዳሪ” ስንፍና… ሦስቱም የስህተት፣ የጥፋትና የውድቀት መንገዶች ናቸው፡፡  
እጅ ለመታጠብ ወይም ሳሙና ለመግዛት፣ የሽሚያ ግርግርና ግፊያ ስንፈጥር አስቡት - ንፅህናን መጠበቅና ርቀትን መጠበቅ አልተቀናጁም፡፡ በአውሮፓና በአሜሪካ የምናያቸው  ዘመናዊ የህክምና ተቋማት፣ የተራቀቁና ውድ መሳሪያዎችን አለአቅም ለመገንባትና ለመግዛት በከንቱ ምኞት ከሞከርን፤ ጥረታችን መና ይቀራል:: ተቋማትን በወጉ ማዘጋጀት፣ መሰረታዊ ቁሳቁሶችን ማሟላት ተስኖን፣ ዜጐችንም ሃኪሞችንም ለአደጋ እናጋልጣለን፡፡
የህክምና ጣቢያ ለማዘጋጀት፣ ፎቆችን መምረጥ ወይም ጥቂት ውድ አልጋዎችን ማስገባት፣ ዛሬ ሲታይ ጥሩ ሊመስል ይችላል:: ለክፉ ጊዜ ግን አይበቁም፡፡ በጭንቅንቅና በግርግር፣ ታካሚዎችም ሃኪሞችም ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡
ከዚህ ይልቅ፣ ባለሙያዎች ስራቸውን በጥራትና በብዛት እንዲያከናውኑ፣ ለሕይወታቸውና ለጤናቸውም እንዲጠነቀቁ የሚያግዙ፣ በአገሬው አቅም በአነስተኛ ወጪ የሚዘጋጁ መሆን አለባቸው - የጤና ተቋማት፡፡
እነዚህን መረጃዎች በማስተዋል፤ አንድ ነገር እንገነዘባለን፡፡ ባለፉት ሳምንታት የተከናወኑ ተግባራትን ለመፈተሽና ለመመዘን፣ ለሚቀጥሉ ሳምንታትና ወራት የሚጠቅሙ ሀሳቦችንም ለማቅረብ፣ ዋና ዋና መርሆችን አጥርተን መጨበጥና በቅጡ አዋህደን መረዳት ይኖርብናል፡፡
የኮሮና ቫይረስ እንዳይዛመት፣ የበሽታ ወረርሽኝም እንዳይስፋፋ ለመከላከልና ጉዳቱን ለመቀነስ ታስበው፣ የሚተላለፉ ውሳኔዎችና የሚከናወኑ ተግባራት፣ በጥቅሉ፣ ሦስት መመዘኛዎችን ማሟላት አለባቸው፡፡
. ቀዳሚው መርህ፣ …ትክክለኛና በስርዓት የተቀናጀ ነው?
አንደኛ ነገር፣ በእውነተኛ መረጃ ላይ ብቻ የተመሰረቱ፣ በሳይንሳዊ ዘዴ የተመሳከሩና የተረጋገጡ፣ እንደየባህሪያቸው በአይነትና በመጠን፣ በጊዜና በአግባብ፣ በተጓዳኝና በቅደም ተከተል የተቀናጁ እርምጃዎች መሆን አለባቸው፡፡
እጅ የመታጠብና ከንክኪ የመታቀብ፣ የበሽታ ምልክቶችን የማጣራትና የማረጋገጫ ምርመራ፣ የማቆያና የህክምና ተግባራት፣… አንዱ ሌላውን በሚደግፍ፣ የላቀ ውጤትን በሚያስገኝ መንገድ፤ ተዋህደውና ተቀናጅተው፣ ሊከናወኑ ይገባል፡። በቁንፅል ወይም እርስ በርስ በሚጣረስ ችኮላ፣ አልያም በዝርክርክነት የሚከናወኑ ከሆነ፣ ነገሩ ሁሉ፣ ከንቱ ብክነትና ኪሳራ ይሆንብናል፡፡
ለይቶ ማቆያ ስፍራዎች፣ ቅጥ ባለው ስርዓት፣ ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን በግልጽ በሚያሳይ መመሪያና አሰራር ካልተመሩ፣ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለጥንቃቄ ከመጥቀም ይልቅ፣ መዘናጋትንን የቫይረስ መዛመትን ሊያባብሱ ይችላሉ፡፡
ከባድ ኃላፊነትን የሚሸከሙት፣ ወደ ማቆያ ስፍራ ከተወሰዱ ሰዎች በላይ የወሰዱ ሰዎች ናቸው፡፡ ኃላፊነታቸውን ጠንቅቀው በስነስርዓት ማከናወን ይኖርባቸዋል፡፡ ወደ ማቆያ ስፍራ ለመውሰድ ከሚያገለግሉ መስፈርቶች፣ ከአነጋገርና ከአቀራረብ ደንቦች ጀምሮ፣ ስርዓት ይዟል?
መሰረታዊ የምግብ፣ የመጠለያ፣ የልብስ፣ የንጽህናና የጤና መጠበቂያ አገልግሎቶች እንዴት እና በማን እንደሚሟሉ፣ በዝርዝር ታስቦበት ተሰናድቷል? በምን ገንዘብ፣ በማን ኃላፊነትና ተጠያቂነት፣ በምን አይነት የአሰራር ሂደትና ደንብ፣ በማን ተቆጣጣሪነት ስራው እንደሚከናወን በቅጡ ተደራጅቷል? አለበለዚያ መዘዙ ክፉ ነው፡፡
በሌላ በኩል፣ ‹‹ሊፍት›› የሌለው ሕንጻ ላይ፣ ጊዜያዊ የህክምና ጣቢያ መክፈትም ብልህነት አይደለም፡፡ ሌላውን ተውት፡፡ ታማሚዎችን መሸከም ብቻ ከባድ ነው፡፡
. አቅምን ያገናዘበና የሚያዋጣ ነው?
ሁለተኛ ነገር፣ የወረርሽኝን መከላከያ ጥረቶች ሁሉ፣ የኢኮኖሚና የኑሮ አቅምን ያገናዘቡ መሆን አለባቸው፡፡ ለምን ቢባል፣ ‹‹አቅም››፣ ባሰኘን ጊዜ፣ ባስፈለገን መጠን የምንፈጥረው ነገር አይደለም፡፡ ዛሬ፣ የበሽታ ወረርሽኝን ለመከላከልና ጉዳቱን ለመቀነስ ብለን፣ ትናንት ያልነበረ አዲስ ብልፅግና ዛሬ እንዲወለድልን ብንጠብቅ… ትርጉም የለውም፡፡ ባላፉት ዓመታት የተገነባውን አቅም ነው መጠቀም የምንችለው፡፡
ለአፍታ የማይቋረጥ የህክምና መስጫዎችን፣ በአፋጣኝ በአንድ ሺ እና በሁለት ሺ ለማሟላት፣ ለዚያውም እጅግ ታዋቂና ውድ የሆኑ መሳሪያዎችን ለመግዛት መሞከር ይቻላል፡፡ ነገር ግን የሚሊዮን ሰዎችን ሕይወት ለማትረፍ የሚችሉ አነስተኛ ምርመራዎችንና ቀላል ህክምናዎችን ለማከናወን የሚያስፈልግ ገንዘብ እናጣለን፡፡
‹‹ከእጅ ወደ አፍ›› የሚባል ዝቅተኛ የኑሮ ችግር በበረከተበት አገር፣ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል፣ ትምህርት ቤቶችን ለሁለት ሳምንት መዝጋት፣ አንድ ነገር ነው:: የገበያ ስፍራዎችን መዝጋት ግን ሌላ ነገር ነው፡፡ ይሄን ልዩነት ባለማገናዘብ፣ የሌሎች አገራትን ውሳኔ በጭፍን መኮረጅና የምርት ተቋማትን ስራ በዘፈቀደ ማስተጓጎል፣ ለብዙዎች፣ የእለት ጉርስን የሚያሳጣ ይሆናል፡፡ የኑሮ አማራጮችን ይዘጋል፡፡
በዚህ መመዘኛ ሲታይ፣ እስከ ዛሬ የተከናወኑ ዋና ዋናዎቹ የጥንቃቄ ተግባራት፣ ትክክለኛ ናቸው፡፡
. ያዛልቃል? ወይስ የወደፊት ተስፋን ያጨልማል?
ሦስተኛ ነገር፣ የዛሬ ተግባራችን ለዛሬ ብቻ ሳይሆን፣ ለወደፊትም የሚያራምድ፣ ለነገ ተጨማሪ አቅምን የሚፈጥር መሆን ይኖርበታል፡፡
“የበሽታ ወረርሽኝን ከመከላከል ጎን ለጎን፣ ለመጪዎቹ አመታት ትልቅ ፋይዳ የሚያስገኘውን የህዳሴ ግድብን መገንባት ያስፈልጋል” ቢባል፣ አንድ ምሳሌ ነው፡፡
ወደፊት፣ የኢኮኖሚ እድገትን የሚያጠፋና አገርን የሚያዳክም፤ ለሚቀጥለው አመት ምግብን የሚያሳጣ መሆን የለበትም - የዛሬ ውሳኔና ተግባራችን፡፡ ለከርሞም ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
በተለይ የመጪው ክረምት የእርሻ ስራ በማዳበሪያ፣ በምርጥ ዘር ወይም በሌላ እጥረት ከተስተጓጎለ፣  ለሰው ህይወትም ለአገር ሰላምም አደገኛ ይሆናል፡፡
ዛሬ ከበሽታ ወረርሽኝ ለማምለጥ የምናደርገው ጥንቃቄና ጥረት፤ ለሚቀጥለው ዓመት ህይወትና ኑሮም የሚጠቅም መሆን አለበት፡፡
የእለት ጉርስን የማያሳጣ ብቻ ሳይሆን፤ የአገር ኢኮኖሚ የወደፊት እድገትንና የዜጎችን የኑሮ ተስፋ የማያጨልም መሆን ይኖርበታል፡፡
የአገር ህልውናም ሆነ የሰው የግል ኑሮ፣ “በርካታ ቁም ነገሮችን ጎን ለጎን ለማሟላትና ለማዋሃድ በሚደረግ ጥረት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ተሻለ ደረጃ የመጓዝ” ጉዳይ ነው፡፡ አንዱን ብቻ በቁንፅል ለማሟላትና ለማሻሻል፣ ሌሎቹን ቁም ነገሮች መዘንጋትና መናድ፣ ሁሉንም የሚያፈርስ ይሆናል፡፡
የበሽታ ወረርሽኝን ለመከላከል፣ አገር ምደሩን ሁሉ ዘጋግቶ መቀመጥ፤… ወይም ደግሞ የአገር ኢኮኖሚ እንዳይቀዛቀዝና የዜጎች ኑሮ እንዳይንገጫገጭ በማሰብ… ጊዜያዊ ጥንቃቄዎችን መዘንጋት… መፍትሄዎች አይደሉም፡፡
ሁለቱንም ያጣመረ፣ ለወረርሽኝን የማያጋልጥ የወደፊቱንም ኑሮ የማያጨልም መፍትሄ ነው - ቁልፉ፡፡  የኮሮና ቫይረስ እንዳይዛመት፣ ጎን ለጎንም የህዳሴ ግድብ እንዳይስተጓጎል መጣር እንደማለት ነው፡፡

Read 3674 times