Saturday, 28 March 2020 11:28

የኮሮና ቫይረስ ወቅታዊ ሁኔታዎች፣ ሥጋቶችና ዝግጅቶች

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

      - እስካሁን በኢትዮጵያ የተመረመሩት 718 ሰዎች ብቻ ናቸው
         - ክልሎች ስርጭቱን ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እያወጡ ነው
         - 300ሺ የመንግስት ሠራተኞች ከቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ ታዝዟል
        - አንዳንድ ለይቶ ማቆያዎች ከፍተኛ ቅሬታ እየቀረበባቸው ነው
        - ኢሰመጉ ሰብአዊ መብቶችን ያላከበረ አያያዝ ታዝቤአለሁ ብሏል
                    
            በአገራችን እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ 718 ሰዎች ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን አስራ ስድስቱ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ታውቋል:: ከአዲስ አበባ ውጭ የመጀመሪያው ቫይረሱ የተገኘበት ግለሰብ በአዳማ መገኘቱ ትላንት ይፋ ተደርጓል፡፡ የህክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው፤ ምርመራ የሚደረግላቸው ሰዎች ቁጥር ቢጨምር በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል እየገለፁ ነው፡፡
የቫይረሱን ስርጭት ለመግታትና ህብረተሰቡን ከበሽታ ለመከላከል የሚያስችሉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ለመውሰድ ክልሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እያወጡ ሲሆን የትግራይ ክልላዊ መንግስት፣ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉ ዝውውሮችን ለአስራ አምስት ቀናት አግዷል፡፡ በክልሉ ከገጠር ወደ ከተማና ከሥፍራ ወደ ሥፍራ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ የተጣለ ሲሆን ሠርግና ተስካርን የመሳሰሉ ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ጉዳዮችና ህዝብ የሚበዛባቸው ገበያዎች እንዳይካሂዱ ወስኗል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በበኩሉ፣ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ከክልል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ግብረሃይል አቋቁሞ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል:: በዚሁ መሰረት፤ ክልሉ የሰራተኞች በአንድ ቦታ መቆየትና የስራ ቦታ መጣበብ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን ተጋላጭነት ለመቀነስ ነፍሰጡርና የሚያጠቡ እናቶች፣ የጤና እክል ያለባቸውና የአመት እረፍታቸውን መውሰድ የሚፈልጉ ሰራተኞች እረፍት እንዲወጡ አዟል:: አንዳንድ የግል ተቋማት፣ ሆቴሎች፣ የመዝናኛ ቤቶች እንዲሁም የእምነት ተቋማት በመንግስት ከሚተላለፈው መመሪያ በተቃራኒው እየተንቀሳቀሱ በመሆኑ በእነዚህ አካላት ላይ የህግ የበላይነትን የማስከበር እርምጃ የሚወስድ መሆኑንም ክልሉ አስታውቋል፡፡
የፌደራል መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከ300ሺ በላይ የመንግስት ሠራተኞች፣ ሥራቸውን በቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በመኖሪያ ቤታቸው ሆነው ሥራቸውን እንዲሠሩ የተደረጉት ከፌደራል መስሪያ ቤት ሠራተኞች ሰባ በመቶ ያህሉ እንደሚሆኑም ተገልጿል፡፡
መመሪያው እንደ ባንክ፣ መብራት ኃይልና ወሳኝ ኩነት የመሳሰሉ መስሪያ ቤቶችን የማይመለከት እንደሆነም ታውቋል፡፡ በመንግስት የተላለፈውን መመሪያ ተከትሎ በርካታ የመንግስት ሠራተኞች ወደ ስራቸው ያልሄዱ ቢሆንም፣ በቤታቸው እንዲቀመጡ የተሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ እያደረጉ ያሉት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞች እንደሆኑና አብዛኛዎቹ ሠራተኞች ግን በተለያዩ ምክንያቶች አሁንም በጐዳናዎችና በልዩ ልዩ ስፍራዎች እጅግ በተጠጋጋ ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ፣ ነው ተብሏል፡፡
በቡና ቤቶች፣ ሆቴሎችና የመዝናኛ ስፍራዎች ውስጥ የሚደረጉ መሰባሰቦችንም ማስወገድ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ቢነገርም፣ ተግባራዊነቱ ላይ ከፍ ያለ ቸልተኝነት እንደሚታይ ተገልጿል:: ይህን ዓይነቱ ቸልተኝነት በዚህ መልኩ እንዳይቀጥል መንግስት በቅርቡ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምር ገልጿል፡፡
ቫይረሱ በአለም አቀፍ ደረጃ ከዕለት ወደ ዕለት በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራጨ መሄዱን ተከትሎ፣ አገራት ድንበሮቻቸውን ሙሉ በሙሉ እየዘጉና ወደተለያዩ አገራት የሚያደርጓቸውን የአየር ጉዞዎች ሙሉ በሙሉ እያቋረጡ ነው:: ከእነዚህ አገራት መካከልም ባለፈው ሐሙስ ሶስት ተጨማሪ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ያገኘችው ኤርትራ ትጠቀሳለች፡፡ መጋቢት 12 ቀን 2012 ዓ.ም በኤይር አረቢያ ተሳፍረው ከዱባይ አስመራ የገቡ 3 ዜጐቿን መርምራ በቫይረሱ መያዛቸውን ያረጋገጠችው ኤርትራ፤ ሶስቱ የቫይረሱ ህሙማን በተሳፈሩበት አውሮፕላን ወደ አስመራ የመጡትን መንገደኞች በሙሉና ከታማሚዎቹ ጋር የቅርብ ንኪኪ ነበራቸው የተባሉትን በሙሉ በለይቶ ማቆያ ውስጥ አስገብታ ምርመራ እያደረገች እንደሆነ የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ይህንኑ ክስተት ተከትሎም አገሪቱ ከሐሙስ መጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አስመራ የሚደረጉትንም ሆነ ከአስመራ የሚነሱትን በረራዎች ሙሉ በሙሉ አግዳለች፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ወደ አገሪቱ የሚገባ ማንኛውም መንገደኛ ለአስራ አራት ቀናት በለይቶ ማቆያ ውስጥ መቆየት እንደሚገባቸውና በዚህ ወቅትም የሚኖረውን ወጪ ሁሉ በራሱ መሸፈን እንደሚገባው መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ለዚህም የስካይ ላይት ሆቴልና ግዮን ሆቴሎች ድርጅት ለለይቶ ማቆያነት የተመረጡ ሆቴሎች ሆነዋል፡፡
በእነዚህ ሆቴሎች ውስጥ መቆየት የማይችሉ ገቢ መንገደኞችን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ በቦሌ መሰናዶና፣ በቂሊንጦ ነፃ የለይቶ ማቆያ ቦታዎች ማዘጋጀቷን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እንደሚዛወሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት አስታውቀዋል፡፡
ይህንን ሁኔታ ተከትሎም ከዱባይ መጋቢት 15 ቀን 2012 ወደ አዲስ አበባ የገቡና በለይቶ ማቆያ ሆቴሎች ውስጥ ከፍለው መቆየት ያልቻሉ ገቢ መንገደኞች፤ በቦሌ መሰናዶ ት/ቤት ውስጥ እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን የመንገደኞቹ የቆይታ ሁኔታ የበሽታውን ስርጭት የሚያባብስ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በት/ቤቱ ውስጥ እንዲያርፉ የተደረጉት ገቢ መንገደኞች የጤና ሁኔታም ትኩረት የተነፈገው መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በዚህ የማቆያ ስፍራ ውስጥ ለመቆየት ያልቻሉና ሁኔታው ለጤናቸው እጅግ አስጊ መሆኑን የተረዱ ከሰላሳ በላይ ገቢ መንገደኞች በአነስተኛ ገንዘብ የሆቴልና የመኝታ አገልግሎት ሊያገኙ የሚችሉበት ቦታ እንዲፈለግላቸው ጥያቄ አቅርበው፣ ወደ ሐራምቤ ሆቴል የተወሰዱ ሲሆን በሆቴሉ ውስጥ ካረፉት መካከል ያነጋገርናቸው ሁለት ግለሰቦች፤ ‹‹በሆቴሉ ውስጥ በገንዘባችን እንኳን ከፍለን መመገብም ሆነ ትኩስ ነገሮችን ማግኘት አልቻልንም፤ የሆቴሉ ሰራተኞች የሚያዩን በቫይረሱ እንደተያዘ በሽተኛ ሰው ነው›› ብለዋል::
በሌላ በኩል፤ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት መሠረታዊ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን ባከበረ መልኩ እንዲሆን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሠመጉ) ጠይቋል፤ በለይቶ ማቆያ ቦታዎች ያለው አያያዝ ሰብአዊ መብትን ባከበረ መልኩ እየተከናወኑ እንዳልሆነም አመልክቷል፡፡
ከውጭ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች ተለይተው ከሚቆዩባቸው ስፍራዎች አንዱ በሆነው ግዮን ሆቴል ምልክታ ማድረጉን ያስታወቀው ኢሠመጉ፤ የሆቴሉን አያያዝ የገመገመ ሪፖርት አውጥቷል፡፡ በሆቴሉ ለሚገኙ 163 መንገደኞች የተመደቡት የህክምና ባለሙያዎች 3 ብቻ መሆናቸውን፣ ለእነርሱም ሆነ በቦታው ለሚገኙ የሆቴሉ ሠራተኞችና ህግ አስከባሪዎች ከቫይረሱ የመከላከያ ቁሳቁስ አለመሟላቱን እንዲሁም ሌላ የጤና እክል ያለባቸው መንገደኞች በቂ ህክምና እያገኙ እንዳልሆነ ማረጋገጡን ኢሠመጉ አስታውቋል፡፡
በራሳቸው ወጪ በለይቶ ማቆያ የሚቆዩ መንገደኞችም በቂ መረጃ ስለማይሠጣቸው ከሆቴል የማምለጥ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን መታዘቡን የጠቆመው ኢሠመጉ፤ በመንግስት በኩል ቫይረሱን ለመቋቋም እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን አበረታትቶ፣ በመሠረታዊነት የሰብአዊ መብቶች በሂደቱ እንዲጠበቁ አሳስቧል፡፡
በዚህም መሰረት፤ በቂ የህክምና ባለሙያዎች እንዲመደቡ፣ ሠራተኞች፣ ሃኪሞችና ጥበቃዎች ለጤንነታቸው ደህንነት አስፈላጊው ሁሉ እንዲደረግ፤ ተጓዦች ራሳቸውን አግልለው በሚቆዩበት ሁኔታ ላይ በቂ መረጃ እንዲሠጣቸው ኢሠመጉ አሳስቧል፡፡
በተጨማሪም ስለ ቫይረሱ ለሁሉም የሀገሪቱ ህዝብ እኩል መረጃ እንዲሠራጭ በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ የተዘጋው የኢንተርኔትና ስልክ አገልግሎት እንዲከፈትና ህብረተሰቡ መረጃ አግኝቶ ጤንነቱን የመጠበቅ ሰብአዊ መብቱ እንዲከበር ኢሠመጉ በሪፖርቱ አስገንዝቧል፡፡
እኛ ወደሆቴሉ ስንገባ የሆቴሉ ሠራተኞች ለቀው ወጥተዋል፡፡ በበርካታ ሆቴሎች የተለመደውን የቁርስ አገልግሎት እንኳን ለማግኘት አልቻልንም - በቴክአዌይ መውሰጃ ዕቃ መውሰድ እንጂ እዚህ መመገብ አትችሉም እየተባልን ነው ብለዋል፡፡ ገቢ መንገደኞቹ ያለንበት ሁኔታ እጅግ አስፈሪና አሳሳቢ ነው:: ከመካከላችን የህመም ስሜት ያላቸውና ህክምና ማግኘት የሚገባቸው ሰዎች ቢኖሩም የት መሄድ ምን ማድረግ እንደምንችል ባለማወቃችን ምክንያት እስከአሁን ህክምና ማግኘትም አልቻሉም፡፡ የሚመለከተው ክፍል ወዳለንበት መጥቶ ሁኔታውን ለመመልከትና ተገቢውን ህክምናም ሆነ የምግብ አቅርቦት ማግኘት እንድንችል ሊያደርገን ይገባል፡፡ ምግብ ከቤተሰቦቻችን እንኳን እንዳይመጣልን ወዳለንበት ማንም ሰው እንዳያደርስ ተደርጓል:: ራሳችንን እንደበሽተኛ እና እንደእስረኛ እየቆጠርን ነው ያለነው ይህ ደግሞ አካላችንንም ሆነ አዕምሮአችንን በእጅጉ እየጐዳው ነው ብለዋል፡፡
ስለጉዳዩ ያነጋገርናቸው የኮቪድ 19 ቅድመ ዝግጅትና ምላሽ ዋና አስተባባሪ አቶ ዘውዱ አሰፋ መንገደኞቹ ከውጪ አገር ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ትኬት በሚቆርጡበት ጊዜ ራሳቸውን ለአስራአራት ቀናት በሆቴሎች ውስጥ በራሳቸው ወጪ መቆየት እንዳለባቸው አውቀውና የግዴታ ውል ፈርመው ነው የሚመጡት ከማረሚያ ቤት የሚወጡትንና ምንም ገንዘብ የሌላቸው መንገደኞች ደግሞ የአዲስ አበባ አስተዳደር ባዘጋጀላቸው የነፃ ማቆያ ቦታዎች እንዲቆዩ ያደርጋል፡፡
ይህ ሁኔታ እስከመቼ ይቀጥላል የሚለው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ መንገድ እየተቀበሉ ማስገባቱ ብዙም የሚያስኬደን አይመስለኝም፡፡ ሆቴሎቹም እየሞሉ ነው:: እንግዲህ መንገደኞቹን አለመስገባት ነው የሚኖረን አማራጭ፡፡ ስለሚባሉት መንገደኞች ያወኩት ነገር የለም፡፡ ስለጉዳዩ ለማጣራትና ለችግሮቹ መፍትሔ ለመስጠት እንሞክራለን ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳድር ገቢ መንገደኞቹ በተሻለ መንገድ የሚቆዩበትን መንገድ ለማመቻቸት ጥረት እንደሚያደርግና እንደየሁኔታው ኮንዶሚኒየሞችንና ሌሎች ሥፍራዎችን ለማቆያ ለመጠቀም እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው በኮሮና ቫይረስ ለተያዙና ለተጠረጠሩ ሰዎች ማቆያ የሚሆኑ ቦታዎችን ለማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አስታውቀው ሚሊኒየም አዳራሽ ለዚሁ አገልግሎት እንዲውል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


Read 12467 times