Saturday, 28 March 2020 11:22

መንግስት ኮሮናን ለመቋቋም ብሔራዊ ዝግጅት እያደረገ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

     የፖለቲካ ድርጅቶች ተጨማሪ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጠይቀዋል

                በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ስጋት የሆነውን የኮሮና ቫይረስ  ወረርሽኝ ለመቋቋም መንግሥት ተጨማሪ ጠንካራ እርምጃዎችን እንዲወስድ የፖለቲካ ድርጅቶች የጠየቁ ሲሆን መንግስት በበኩሉ፤ የኮሮናን ሥርጭት ለመከላከል ኮሚቴ አቋቁሞ ብሔራዊ ዝግጅት እያደረገ ሲሆን ትላንት ተጨማሪ አዳዲስ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
መንግስት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት በየጊዜው ከሚያወጣቸው መመሪያዎች በተጨማሪ የከፋ ችግር ቢመጣ ለመቋቋም እንዲቻል በሚል ብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ያቋቋመ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ አስተዳደርም ድጋፎችን ሲያሰባስብ መሰንበቱ ይታወቃል፡፡  
የፖለቲካ ድርጅቶች፤ መንግስት ቫይረሱን ለመከላከል እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው፤ ተጨማሪ ጠንካራ እርምጃዎችን እንዲወስድ አስረግጠው ጠይቀዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ስጋትን አስመልክቶ ህብረተሰቡ መንግሥት በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሰረት ራሱን ከበሽታው እንዲጠብቅ የጠየቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፤  መንግስት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች አበረታች ቢሆኑም ተጨማሪ እርምጃዎችም ሊወሰዱ ይገባል ብሏል፡፡
ቫይረሱን አስመልክቶ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው መዘናጋት አስፈሪ ነው ያሉት የኢዜማ መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፤ አሁን ያሉት የጤና ተቋሞቻችን ከዚህ ችግር ያወጡናል ብለን ሙሉ ለሙሉ መተማመን ተገቢ አይደለም፤ አንዴ የቫይረሱ ወረርሽኝ ቁጥሩ ከገፋ የጤና ተቋሞቻችን ከስራ ውጪ ነው የሚሆኑት፤ አይቋቋሙትም፤ ስለዚህ ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ከወዲሁ ነው ብለዋል፡፡
የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የኢዜማ አባላትና ደጋፊዎች፣ ተገቢውን እገዛ እንደሚያደርጉ የገለፁት ፕ/ር ብርሃኑ፤ ከምንም በላይ ህብረተሰቡ እንቅስቃሴውን በመገደብ ራሱንና ቤተሰቡን ከበሽታው እንዲከላከል መክረዋል፡፡
መንግሥትም አሁን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ሆነው ተጨማሪ እርምጃዎችን እንዲወስድ በመግለጫው ያሳሰበው ኢዜማ፤ ውሳኔዎችም ተፈፃሚ መሆናቸውን በንቃት ሊከታተል ይገባል ብሏል፡፡ መንግሥት በተጨማሪነት ሊወስዳቸው ይገባል ተብለው በኢዜማ ከተጠቆሙት እርምጃዎች መካከል ለነጋዴዎች የታክስ እፎይታ ማድረግ፣ የታክስ መክፈያ ጊዜን ማራዘም፣ የጡረታ መዋጮዎችን መቀነስ የሚሉት ይገኙበታል:: ቫይረሱን ለመቆጣጠር በሚል በሚወሰዱ እርምጃዎች የኢኮኖሚ ጫና ተፅዕኖ ለሚያጋጥማቸው የንግድ ዘርፎች፤ የብድር መክፈያ ጊዜ ማራዘምና የብድር ወለድ ቅናሽ እንዲሁም የብድር ምህረት የመሳሰሉትም ተጨማሪ ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች ናቸው - ብሏል ኢዜማ፡፡
ብሄራዊ ባንክ ከግል ባንኮች በቦንድ ግዥ የሰበሰበውን ገንዘብ በፍጥነት ለባንኮቹ ቢመልስ፣ የግል ባንኮች የሚያበድሩት በማጣት ከገቡበት ችግር ሊላቀቁ ይችላሉ ያለው ኢዜማ፤ ይህም በገንዘብ እጥረት እየተሰቃየ ለሚገኘው የንግዱ ማህበረሰብ በቂ ገንዘብ ከባንኮች እንዲያገኝ፣ ሠራተኛውን ሳይበትንም ስራውን እንዲቀጥል ያስችለዋል ብሏል፡፡ በዚህም ኮሮና በኢኮኖሚው ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጨማሪ ጫና መቋቋም እንደሚቻል ኢዜማ ጠቁሟል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ስጋትን ለመቋቋም ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው በተለያየ ምክንያት በስራ ላይ የማይገኙ የሕክምና ባለሙያዎችን ወደ ሥራ ማስገባት አስፈላጊ ነው ያለው የኢዜማ ምክረ ሀሳብ፤ ለባለቤቶቹ ያልተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የማቆያ ማዕከላትን ከወዲሁ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም አስታውቋል፡፡
የዳበረ የገንዘብ አቅም ባይኖረኝም ካለኝ ውስን ገንዘብ ላይ ወጪ በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ገዝቼ አሰራጫለሁ ያለው የኢትዮጵያ ተራማጅ ፓርቲ (ተራማጅ) በበኩሉ፤ አባላቶቹ በየሙያ ዘርፋቸው መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚያደርገውን ጥረት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርቧል፡፡
መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች ተገቢ ናቸው ያለው ፓርቲው፤ ሁሉም ህብረተሰብ ለእርምጃዎቹ ተፈፃሚነት ድጋፍ እንዲያደርጉና ሌሎች የተጠኑ ተጨማሪ እርምጃዎችም እንዲወሰዱ ጠይቋል፡፡
በተመሳሳይ ቫይረሱን በመከላከል በኩል ከመንግሥት ጎን እንደሚቆም የገለፀው ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ፤ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ተግባራዊ የድጋፍ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ፓርቲው ከማክሰኞ ጀምሮም በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወረ የእጅ መታጠቢያ ሳሙናና ሌሎች የንፅህና መጠበቂያዎችን ለአቅመ ደካሞች መስጠቱን ጠቁሞ፤ ይህን ተግባሩንም  አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክቷል፡፡
መንግሥት በቫይረሱ ስርጭት ዙሪያ በተለይ የመረጃ አቅርቦቱን ግልጽና ለሁሉም ተደራሽ የሚያደርጉ ተጨማሪ እርምጃዎችን እንዲወስድም ፓርቲው ጠይቋል፡፡
ከፖለቲካ ድርጅቶችም በተጨማሪ ፖለቲከኞችና ምሁራን መንግሥት ሊወስዳቸው ይገባል ያሏቸውን ተጨማሪ እርምጃዎች ያመለከቱ ሲሆን የቢዝነስ ባለሙያው አቶ ክቡር ገና፤ መንግስት ጉዳዩን የያዘበት መንገድ በሽታው ከጋረጠው ስጋት አንፃር እምብዛም መሆኑን ጠቁመው፤ በከፊል ተቋማትን መዝጋት፣ እንቅስቃሴን መገደብንና እጅ ታጠቡ ተራራቁ ከሚለው በላይ የተቀናጀ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡
በዚህ ወቅት ባንኮች ከደንበኞቻቸው ተቀብለው ያስቀመጡትን ብር እንኳ በደንበኞቻቸው ሲጠየቁ መልሰው መክፈል ተቸግረዋል ያሉት አቶ ክቡር፤ ከበሽታው ጋር በተያያዘ የፋይናንስ ዘርፉን ከወድቀት ለመታደግ የፖሊሲ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡
በርከት ያሉ ተጨማሪ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ የሚሉት የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሙሸ ሰሙ በበኩላቸው፤ መንግሥት አስፈላጊውን ስንቅ አዘጋጅቶ ለ15 ቀናት ያህል ሙሉ ለሙሉ እንቅስቃሴዎችን ገድቦ፤ የበሽታውን ስርጭት መጠን መለየትና መከላከል እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡
መንግሥት በበኩሉ ቫይረሱ በኢትዮጵያ ተገኘ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ት/ቤቶችን የመዝጋት፣ የስብስቦች መጠን ላይ ገደብ የማበጀት፣ ስብሰባዎችን የማስቆም፣ የመንግስት ሰራተኞች በቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ የማድረግ፣ የአየር መንገድ የጉዞ መዳረሻዎችን የመቀነስ ከውጭ የሚመጡ ራሳቸውን ለ14 ቀናት አግልለው እንዲቆዩ የማድረግና ሌሎች እርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን የከፋ ሁኔታ ቢፈጠር ለመቋቋም ከወዲሁ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችን ዘርግቶ አቅሙን እያደረጀ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ለዚህም ብሄራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ በጠ/ሚኒስትሩ ተዋቅሯል:: ጠ/ሚኒስትሩም የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለግሰዋል ከሳቸው ጋርም 50 ያህል የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ደሞዛቸውን ለግሰዋል፡፡
ኮሚቴው ገንዘብ ማሰባሰብ የሚችልበት የባንክ ሂሳብ መክፈቱንና የአጭር መልዕክት ገንዘብ ማሰባሰቢያ መንገድ መዘጋጀቱን፣ አርሶ አደሮችና ባለሃብቶች ለምግብ አቅርቦት የሚረዱ ምግብ ነክ ቁሶችን እንዲለግሱ የምግብ ባንክ መዘጋጀቱን እንዲሁም እጅግ ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች የሚያስፈልጉ ሸቀጦችን የማዘጋጀት ስራ መጀመሩን ጠ/ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ትናንት ባሳለፉት ውሳኔውም አዲስ አበባ የሚደርሱና ለለይቶ መከታተያ በተዘጋጁ ሆቴሎች ለመቆየት አቅም የሌላቸው መንገደኞች ወደ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተዛውረው ለ15 ቀን የሚቆዩ ይሆናል ተብሏል፡፡
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ት/ቤቶች በተጨማሪ 15 ቀናት ዝግ ሆነው  ይቆያሉ፤ የማህበራዊ ርቀት ድንጋጌን በሕግ ተግባራዊ ያደርጋል፣ ሁኔታው ተጨማሪ ድጋፍ የሚጠይቅ ከሆነ ሁሉም ጡረታ የወጡ እንዲሁም በትምህርት ላይ ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ለብሄራዊ ግዳጅ እንዲዘጋጁም መንግስት ጥሪ አድርጓል፡፡
134 ተቋማት ለለይቶ ሕክምና መከታተያነት መዘጋጀታቸውን ለማዕከላቱም ግብዓት የሚሆኑ መሳሪያዎች እየተሰባሰቡ መሆኑም ለመንግስት አዲስ ውሳኔ ተመልክቷል፡፡
የኢኮኖሚው ዘርፍ በሂደቱ እንዳይጎዳ የሚያስከትሉ እርምጃዎች ከባለድርሻዎች ጋር ምክክር ተደርጎ መወሰዳቸው ተመልክቷል፡፡
ኢኮኖሚውን ለማረጋጋትና የፋይናንስ ዘርፉን ጤንነት አስጠብቆ ለመቀጠልና ባንኮች በቫይረሱ ለተጎዱ ደንበኞቻቸው ጊዜያዊ የብድር እፎይታና ተጨማሪ ብድር ለመስጠት እንዲያስችላቸው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ተጨማሪ 15 ቢሊዮን ብር ለግል ባንኮች እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስፈልጉ የገቢ ዕቃዎችና ግብዓቶች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ይደረጋል፤ ለቫይረሱ መከላከያ የሚውሉ ዕቃዎችን ለሚያስመጡም ባንኮች ቅድሚያ ሰጥተው እንዲያስተናግዱ ይደረጋል ተብሏል፡፡
በፋይናንስ አገልግሎት የተሰነሳ ገጽ ለገጽ መገናኘትና የብር ንክኪን ለመቀነስ እንዲቻል ብሄራዊ ባንክ በሞባይል አማካኝነት የሚደረግ ክፍያና የገንዘብ የማስተላለፍ ጣሪያውን ከፍ ያደርጋል እንዲሁም ብሄራዊ ባንክ ለውጪ ገበያ በሚቀርብ አበባ ላይ የጣለው ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ገደብ በጊዜያዊነት እንዲነሳ ይደረጋል ተብሏል፡፡
የትግራይ፣ ደቡብና ሶማሌ ክልሎች የሰዎች ዝውውርና ስብሰባ ገደቦችን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎች የወሰዱ ሲሆን የአዲስ አበባ አስተዳደር በበኩሉ ለለይቶ ማቆያ የሚያገለግሉ ህንጻዎችን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ከህብረተሰቡ በማሰባሰብ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

Read 1260 times