Saturday, 28 March 2020 11:22

ምርጫ ቦርድ በቀጣዩ ምርጫ ዕጣ ፈንታ ላይ ውሳኔውን ያሳውቃል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ የቀጣዩ ብሄራዊ ምርጫ ዕጣ ፈንታ ምን ይሁን በሚለው ጉዳይ ላይ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ድርጅቶች የቀረቡለት ሃሳቦች ላይ ተመስርቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ አስታውቋል፡፡
ቀደም ብሎ ቦርዱ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ከ45 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የኮሮና ቫይረስ ስጋት በምርጫው የጊዜ ሰሌዳ ላይ ስለሚኖረው ተፅዕኖ ውይይት አድርጎ የነበረ ሲሆን በፓርቲዎች ከተሰነዘሩ ሃሳቦችም ለውሳኔ የሚረዱ ግብዓቶችን ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
የቫይረሱ ስርጭት ስጋት በተለይ ለምርጫው ወሳኝ በሆኑና ሊከናወኑ ዕቅድ በተያዘላቸው የመራጮች ትምህርት፣ የአስፈፃሚዎች ስልጠና፣ የቁሳቁስ ስርጭት፣ ከሚያሳትፉት የሰው ብዛትና ከቦታ ቦታ ዝውውር አንፃር የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች በውይይቱ መቅረባቸው ተመልክቷል፡፡ አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የቫይረሱ ስርጭት የሚፈጥረውን ስጋት ታሳቢ ያደረገ ምርጫውን የማራዘም እርምጃ እንዲደረግ ሀሳብ ማቅረባቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አሁን ወቅቱ በበሽታው ምክንያት እንደ አገር የተጋረጠውን የህልውና አደጋ መቀልበሱ ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባም ከፓርቲዎቹ ሃሳብ ቀርቧል፡፡
ቦርዱ በበኩሉ፤ በቀጣይ ሁኔታዎችን ገምግሞ፣ ከፓርቲዎችና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ተጨማሪ ውይይት በማድረግ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ አስታውቋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ከፓርቲዎች ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ ቦርዱ ጉዳዩን እስከ ትናንት በስቲያ ሐሙስ ተሰብስቦ እንዳተመለከተውና አዲስ ውሳኔ አለመተላለፉን ለአዲስ አድማስ ያስገነዘቡት የቦርድ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ በቀጣይ ቦርዱ እልባት ያስቀምጣል ብለዋል፡፡

Read 1229 times