Monday, 23 March 2020 00:00

ንግግራችንና ስራችን፣ በሥነ ምግባር ይሁን፤

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

             በሰከነ ንቁ አእምሮ፣ በእውነተኛ መረጃና በእውቀት፤ ሕይወትንና ጤናን በማክበር ይሁን!
                     
               ሥርዓት የሌለው የሃይማኖት ዓይነት የለም፡፡ መሠረታዊ እምነትን ከመቅረፅ ጀምሮ፣ ዋና ዋና መርሆችን ከነገፅታቸው በፈርጅ ገልፆ፣ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን አስከትሎ፣ ደንቦችን የሚዘረዝር የየራሳቸው ሥርዓት አላቸው - ሃይማኖቶች፡፡ ይሄ በጎ ነው፡፡  ብዙዎቹ የሃይማኖት ሥርዓቶች ደግሞ፣ እጅግ ጥብቅ ናቸው ችግሩ ምንድን ነው? ኢየሱስ እንዳስተማረው፤ የበዓል ቀን ማክበር ሕይወትን ከማዳ ይቅደም ከተባለ ነው ችግሩ፡፡ ዝርዝር ደንቦች፣ ዋና ዋና መርሆችን የሚጥሱ በሚሆኑበት ጊዜም ጭምር፣ በቁንፅል ደንቦቹ በጥብቅ የሚቀጥሉ ሲሆን ነው - ችግሩ፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ጭፍንነትንና ጭካኔን ማስፋፋት ለሚመኙ መጥፎ ሰዎች እንዲሁም ለአጥፊ አስተሳሰቦች ሲጋለጡ ይታያል፡፡ ይህንን መከላከል ያስፈልጋል፡፡ ደግሞም፣ የሃይማኖት ሥርዓቶች፣ የጥፋት አስተሳሰቦችን የሚከላከሉ ገፅታዎች አሏቸው፡፡ የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎችን እነዚህን ጠንካራ ገፅታዎች አጉልተው በማሳየት የሥነ ምግባር ሃላፊነታቸውን መወጣት ይገባቸዋል፡፡
በተለይ ፈተና በበዛባቸው እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራት፣ በተለይ የበሽታ ወረርሽኝ ስጋት በበረታበት በአሁኑ ወቅት፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ሃላፊነታቸውን ካልተወጡ እጅግ አሳዛኝ መከራ ሊፈጠርና ሊባባስ ይችላል፡፡ በሌላ ጊዜ ጥቅም እንጂ ጉዳት የሌላቸው ደንቦችና ተግባራት፣ ዛሬ ለበሽታ የሚያጋልጡ ከሆኑ፣ የበሽታ ወረርሺኝን ለመከላከል በማሰብ፣ እነዚህን ተግባራትና ደንቦች ለጊዜው ማስቀረት፣ ትክክለኛ የሥነ ምግባር ሃላፊነት ነው፡፡ መጨባበጥና መሳሳም፣ ትምህርትና የኪነ ጥበብ ሥነ ሥርዓቶች በባህርያቸው በጎና ጠቃሚ ቢሆኑም፣ ለጊዜው እንዲቋረጡ የተደረገው ለምን ሆነና?  
ለእውነተኛ መረጃዎችና ለሳይንሳዊ እውቀት፣ ለሕይወትና ለጤና፣ እንዲሁም ለትክክለኛና ለጠቃሚ ተግባራት ክብር በመስጠት ነው - ለጊዜው የእጅ ሰላምታና የትምህርት ስርዓት የተቋረጠው፡፡  የሃይማኖት ሥርዓቶችስ?
እውነትን፣ የተቃና መንገድን፣ የተቀደሰ ሕይወትን… እውነትና እውቀትን፣ ጥበብንና በረከትን፣ ጤንነትንና የመንፈስ ንፅህናን ማክበር እንደሚያስፈልግ የሚያስተምሩ መርሆች አሉ - በሃይማኖቶች ውስጥ፡፡
ሃሰትንና ቅጥፈትን፣ ሽንገላንና ሸፍጥን፣ ስንፍናንና ብልግናን፣ ጠማማነትንና ተንኮልን፣ የምቀኝነት ውድመትንና ግድያን፣ ስርቆትንና ዝርፍያን የማያወግዝ ሃይማኖት የለም ማለት ይቻላል፡፡
በተቃራኒው፣ ለእውነት መታመንና እውነትን መመስከር፣ በእውቀትና በጥበብ መበልፀግ፣ በጎ እንደሆኑ የሚገልፅ ታሪኮች በየሃይማኖቱ አሉ፡፡ ትጋትንና ፍሬያማነትን፣ ጤንነትና በረከትን፣ ቅንነትንና መልካምነትን በአጠቃላይ መልካም ሥነ ምግባርን በተለያየ መንገድና መጠን ያስተምራሉ፡፡
መልካም የሥነ ምግባር መርሆች፣ በአንድ ወገን እንደ ስማቸው መልካም ስለሆኑ፣ ተፈላጊ ናቸው፡፡ እናም ማንም ጤናማ ሰው ራሱን ብቻ ሳይሆን፣ የሚወዳቸው ልጆቹንም እንደየአቅሙ መልካም ሥነ ምግባርን ያስተምራል፡፡ ሰዎች ሁሉ፣ መልካም የሥነ ምግባር መርሆዎችን እንዲያውቁና ከሕይወታቸው ጋር እንዲያዋህዱ የመመኘት ንፁህ መንፈስንም ያላብሳል፡፡ መልካም ሥነ ምግባር አላቂ ነገር አይደለምና፡፡
በሌላ በኩልም፤ መልካም የሥነ ምግባር መርሆዎች የዳኝነት መመዘኛዎች ናቸው፡፡ ጥሩና መጥፎን፣ መልካምና ክፉን ለይተን መዳኘት፣ ከዚህም ጋር ምን ያህል ጥሩ፣ የቱን ያህል መጥፎ እንደሆኑ፣ የመልካምነት ደረጃውን፣ የክፋት ‹‹ውረጃውን››፣ የድክመት ዝቅታውን፣ የብቃት ከፍታውን መለካት የሚቻለው፣ በሥነ ምግባር መርሆዎች ነው::
የሳትን፣ ያጠፋን፣ የወረድን ጊዜ፤ ይህንን ተገንዝበን፣ ተፀፅተንና ተቆጭተን፣ ያጠፋነውን ክሰን፣ የሳትነውን አስተካክለን፣… እንደገና የእውነትን ብርሃን ተማምነን፣ የተቃና የበረከት መንገድን ይዘን፣ ወደ ተቀደሰ ክቡር ሕይወት ከፍ የምንልበት ነው - የሥነ ምግባር መርህ፡፡ ራሳችንን እንመዝንበታለን፣ እንዳኝበታለን፡፡ ራሳችንን እናስተካክልበታለን፣ እንመራበታለን - የሥነ ምግባር መርህ፡፡ ሌሎች ሰዎችን ለመዳኘትና ለመመዘን ሌላ መርህ አናመጣም፡፡ ራሳችንን ወይም ሌሎች ሰዎችን፣ በተለያየ መርህ ሳይሆን፣ በመልካም የሥነ ምግባር መርህ ብቻ መዳኘት ይገባል - ይሄ እውነተኛ የቅንነት መርህ ነው - ‹‹ሰውን እንደ ራስህ ውደድ››፣ ‹‹ባልንጀራህን፣ ጎረቤትህን፣… እንደራስህ ውደድ›› ሲባል፣ እጅግ ትልቅ ትርጉም የሚኖረው፤ ከዚህ የሥነ ምግባር መርህ ጋር አያይዘን ስናየው ነው፡፡
ለሁሉም ሰውና በሁሉም ጉዳይ፣ በሁሉም ቦታና በሁሉም ጊዜ፤ ከቶ በማይዛነፍና በማይናወጥ፣ ለግል በመረገጥነውና በወደድነው፣ በዚሁ ትክክለኛ መልካም የሥነ ምግባር መርህ አማካኝነት፣ ሌሎች ሰዎችንም እንዳኛለን፣ እንመዝናለን፣ እናደንቃለን፣ እንወቅሳለን፡፡ በአግባቡ ካየነው ይሄ ብዙም አይገርምም፡፡ ትክክለኛ የሥነ ምግባር መርህ፣ የትክክለኛ እውቀት አንድ ገፅታ ነው፡፡ ጥንት የኢትዮጵያ አዋቂዎች የፈጠሩት የማባዛት ዘዴ፣ ትክክለኛ ስለሆነ፣ ጥንትም ዛሬም፣ በአገር ውስጥም ከባህር ማዶም ይሰራል፡፡
በግሪክ አዋቂዎች የተቀመሩና በዩክሊድ የተቀናበሩ የጂኦሜትሪ መሰረታዊ መነሻዎች፣ ግኝቶችና እውቀቶች… ያኔም፣ ዛሬ ከሁለት ሺ ዓመታት በኋላም፣ በጃፓንና በአሜሪካ፣ በራሺያና በኢትዮጵያ፣ በሁሉም ስፍራ፣ ያው… እውነትና እውቀት ናቸው፡፡ ከ7ኛ እና ከ8ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ዩኒቨርሲቲ ድረስ፣ ዛሬም መሰረታዊ የሒሳብ ትምህርት ነው - የዮክሊድ ጅኦሜትሪ፡፡ ቁጥር ስፍር በሌላቸው እልፍ አእላፍ ጉዳዮች ላይም እንገለገልበታለን፡፡
በእርግጥም፣ ከእውነተኛ መረጃ የሚነሳና፣ ሁሌም እየተመሳከረ የሚረጋገጥ፣ በትክክል ተገናዝቦ በቅጡ የተበጀ እውቀት፤… Omnipresent, Omniscient, Omnipotent … ነው ቢባል፤ እጅግ ጥበበኛ የዘይቤ አነጋገር ነው፡፡ እውቀት… ከአንድ ስፍራ ተነቅሎ ወይም ተቀንሶ አይደለም ወደ ሌላ ቦታ የሚስፋፋው፡፡    
በወረፋና በኮታ…ዛሬ ለሷ፣ ነገ ለሱ በዙር የሚታደል፣ ግማሽ ለእከሌ፣ ግማሽ ለእከሊት የሚሸነሸን አይደለም- እውቀት፡፡
በአንድ ጊዜ፣ በብዙ ሰዎች አእምሮ ውስጥ መከሰት፣ በሁሉም ስፍራ መስፋፋት የሚችል ነው - እውቀት፡፡ ከእገሌ አእምሮ አምልጦ፣ ተቀንሶ፣ ወይም ተነጥቆ ወደ እከሌ አእምሮ የሚሄድ አይደለም፡፡
በዚያ ላይ፣ ጂኦሜትሪን ለጠረጴዛ ሥራ እንጂ፣ ለድንበርና ለመንገድ ቅየሳ፣ ለህንፃና ለግድብ ግንባታ አትገልገልበት ተብሎ የሚታገድ አይደለም፡፡
‹‹የጄኦ ሜትሪ እውቀት፣ ለግድብ ግንባታ ከተጠቀምክበት፣ ያልቃል፡፡ የመድፍ ኢላማ ለማስተካከልና ሳተላይት ለማምጠቅ ሊጠቅምህ አይችልም›› …የሚባል አይደለም:: እውቀት፣ ተሟጥጦና አቅሙ ተመናምኖ የሚጠፋ አላቂ ነገር አይደለም፡፡ ሁሌም በሁሉም ስፋራ፣ በእልፍ አእላፍ ጉዳይ ላይ የሚያገለግል፣ እጅግ የተትረፈረፈ፣ መቼም የማያልቅ ዘላለማዊ ሃይል ነው - በሙሉ አቅም የሚያገለግል ነው፡፡
ትክክለኛ የስነምግባር መርሆችም፤ እንደሌሎቹ መሰረታዊ እውቀቶች፣ በሁሉም ቦታ፣ ሁልጊዜ፣ ለሁሉም ጉዳይ ነው መርህነታቸው፡፡ ‹‹ለወላጆችህ አትዋሽ፤ ለጓደኞችህና ለጐረቤት ግን መዋሸት ትችላለህ›› የሚል አይደለም - የሥነ ምግባር መርህ፡፡ ‹‹ቀን በጠራራ ፀሐይ አትስረቅ:: ማታ ጨለማን ተገን አድርገህ መስረቅ ትችላለህ›› የሚል አይደለም የሥነ ምግባር መርህ፡፡
ሰውን መመቅኘት፣ ማጥቃትና መግደል እጅግ የወረደ ክፋትና ወንጀል እንደሆነ ያስተምራል እንጂ፣ የዚህና የዚያ ጐሳ፣ መጤና ነባር፣ ጥቁርና ነጭ፣ የዚህና የዚያ ሃይማኖት ተከታይ፣ የእንትን ቋንቋ ተናጋሪ፣ የእከሌ ብሔር ተወላጅ፣ እያለ በጭፍን ፍረጃ… ‹‹ያኛውን ንፁህ ሰው ማጥቃት ሃጥያት ነው፣ ይሄኛውን ንፁህ ሰው ማጥቃት ጽድቅ ነው›› አይልም -  ትክክለኛ የሥነ ምግባር መርህ፡፡
መርህነታቸው፣ ለሁሉም ሰውና ለሁሉም ጉዳይ በየትኛውም ቦታና ሁልጊዜ ነው፡፡
አዎ፣ የሁሉም ነገር መሰረት፣ ‹‹እውነት›› ነው፡፡
ጉዞን ሁሉ የሚያሳካና የሚያቃና ደግሞ በእውነትና በእውቀት ላይ የተመሰረተ የሥነ ምግባር መንገድ ነው፡፡
ይሄ ሁሉ ትርጉም የሚኖረው ግን፣ የእያንዳንዱ ሰው ህልውና (አእምሮ፣ አካልና ስብዕና)፣ ክቡር ህልውና እንደሆነ ከተገነዘብን ብቻ ነው፡፡
በእርግጥም፣ በግልፅ እንደምናየው፣ በተፈጥሮው፣ እያንዳንዱ ሰው፣ በየራሱ፣ የህልውናው ባለቤት ነው፡፡ ቅያሪ ወይም ምትክ የለውም፡፡ በውሰት ወይም በውርስ አይተላለፍም፡፡ አገልጋይ መሳሪያ ወይም መስዋዕት መቀበያ አይደለም፡፡
የእያንዳንዱ ሰው ህልውና ክቡር ነው፡፡ ክቡር ካልሆነ፣ የትኛውም እውቀትና ሃሳብ፣ የትኛውም አላማና ተግባር፣ የትኛውም አይነት ማንነትና ባህርይ ምንም ትርጉም አይሰጥም፡፡ አንዳች ፋይዳ ወይም ቅንጣት ክብር ሊኖረው አይችልም፡፡ አእምሮው፣ የኑሮ አላማው፣ የእኔነት ማንነቱ ሁሉ በተናጠልና በቁንፅል ዋጋ ቢስ የሚሆንብን፣ የእያንዳንዱ ሰው ሙሉዕ ህልውና፣ እጅግ ክቡር መሆኑን ካልተገነዘብን ነው፡፡
‹‹ያለ ክብር መኖር አይችልም?›› የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ያለ ክብር እንዴት? እንደ ነፍሳት ወይም እንደ ዱር አራዊት? እንደ ሳር ወይም እንደ ዱር እጽዋት? ማለትም አእምሮውን ሳይጠቀም ያለ እውቀት፣ የትናንቱን ከዛሬ ሳያገናዝብ፣ የዛሬውን ከነገ አያይዞ ሳያመዛዝን? ሰው ያለ ተፈጥሮው፣ መኖር አይችልም፡፡
ሰው፣ ወፍ ዘራሽ ፍሬ ለመሸምጠጥ የጦጣና የዝንጀሮ ያህል አቅም የለውም፡፡
አድብቶ አይጥን ለመያዝ የቀበሮ ያህል፣ አጋዘንን አባርሮ ለመጣል የነብርና የአንበሳ አይነት አቅም የለውም - ሰው፡፡ በዚህ በዚህ፣ ከዝንጀሮም ከቀበሮም ያንሳል፡፡ በዱር በበረሃ፣ ያለ እውቀት፣ እንደ ሌሎች እንስሳት ልኑር ቢል፣ የሰው የመኖር ተስፋው ኢምንት ነው፡፡
ከነአካቴው እጅና እግሩን አጣምሮ፣ በአንድ ቦታ ተጐልቶና ደንዝዞ፣ በህይወት መሰንበትም አይችልም፡፡ የሳር የቁጥቋጦ አይነት አቅም የለውም - ሰው፡፡
ሰው፣ በተፈጥሮው ‹‹ሰው››ነቱን ትቶ፣ በሕይወት የመቆየት አቅም የለውም፡፡ ሰው፣ በራሱ ሃሳብና እውቀት፣ በራሱ ምርጫና ጥረት፣ በራሱ ብቃትና ማንነት ነው፤ ሃላፊነትንም ወስዶ ነው፣ በሕይወት መኖር የሚችለው፡፡ ይሄም ነው የሰው የህልውና ክብሩ፡፡
በአጠቃላይ ሦስቱን ነጥቦች ስናቀናጃቸው፣
እውነትንና እውቀትን፣ ኑሮን የሚያሻሽል የሥነ ምግባርና በረከት መንገድን፣ የእያንዳንዱን ሰው የግል ማንነትንና ሕይወትን ማክበርን ያዋሃደ ስልጡን ሥርዓት ይሆንልናል፡፡
ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት፣ እንደ ትምህርት ተቋማትና እንደ ፍትህ ተቋማት፣ የሃይማኖት ተቋማትም፣ እውነትን፣ ሥነ ምግባርንና ሕይወትን ማክበር እንደሚያስፈልግ የሚያስተምሩ መርሆች አሏቸው። እነዚህን መርሆች አጉልቶ በማሳየት፣ በተለይ ዛሬ የበሽታ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ውሳኔዎችን በመተግበር፣ ለእውነት፣ ለሥነ ምግባርና ለሕይወት ክብር የመስጠት ሃላፊነታቸውን መወጣት ይገባቸዋል:: መንግሥት፣ ለሃይማኖት ሥርዓት መሰባሰብን እስኪከለክል ድረስ መጠበቅ የለባቸውም - የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎች፡፡    


Read 9674 times