Sunday, 22 March 2020 00:00

ክቡር ጠ/ሚኒስትር፣ “ድርድሩን በእግሩ ያቁሙት”

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(3 votes)

    “ግድብ በእስልምና ኃይማኖት እንዴት እንደሚታይ በአንድ ወቅት ለማየት ሞክሬ ነበር፡፡ ነብዩ ሞሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) አንድ ሰው፣ ውኃ እኔ ጋ አለ፤ ገድቤ እጠቀምበታለሁ ሲል፣ ከእኔ በታች ያለው ሰው አትገደብ አለኝ አላቸው፡፡ ገድብና ተጠቀም፤ ገድበህ አታስቀርበት፤ ከተጠቀምክ በኋላ ልቀቅለት አሉት፡፡
ሰውየው እንዴት እንደዚህ ይሆናል፤ እሱ ተጠቅሞ ነው ወደ እኔ የሚለቀው አለ:: ገድብና ተጠቀም፤ እንዲያውም ከፈለክ አትልቀቅለት አሉት፡፡ በእስልምና ሃይማኖት ስለ ውኃ አጠቃቀም የማውቀው ይህ ነው”
(ኡስታዝ አህመዲን ጀሊል)
ኢትዮጵያ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ፣ ከሱዳንና ግብጽ ጋር ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ተደራድራለች፡፡ ወደፊትም ለስንት ዓመት እንደምትደራደር ባይታወቅም ትደራደራለች፡፡ ድርድሩ ሱዳንን፣ ይጨምር እንጂ ዋናው ድርድር ያለው በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል ነው ማለት ይቻላል:: ዘጠኝ አመት ያስቆጠረው የግብጽና የኢትዮጵያ ድርድር፣ አንድም እርምጃ ወደፊት አለመራመዱ የታወቀ ነው፡፡ ባለበት ለመቸከሉ ዋና ምክንያት፣ ግብጽ ግራና ቀኝ እየረገጠች ወይም ወደፊትና ወደ ኋላ እየተመላለሰች፣ የምታነሳውና የምታገላብጠው ጥያቄ አንድና የማይለወጥ መሆኑ ነው፡፡ ይሄም የግብፅ ታሪካዊ የዓባይ ውሃ ተጠቃሚነት መብትን የማስቀጠል ወይም እ.ኤ.አ በ1959 ከሱዳን ጋር ባደረገችው ስምምነት መሰረት የምታገኘውን የውሃ ድርሻ ማስቀጠል ነው፡፡
ኢትዮጵያ፤ ሱዳንና ግብጽ እ.ኤ.አ በ1959 ዓ.ም የተፈራረሙትን ስምምነት አትቀበልም:: ይህን አቋሟን ስምምነቱ ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ ደጋግማ ገልጻለች፡፡ ተቃውሞዋ እስከ አለም ዳርቻ ድረስ የታወቀ ቢሆንም፣ እያንዳንዱን እርምጃዋን፣ የሚያደናቅፍ ድንጋይ አድርጋ እያቆጠረችው እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ ለችግሯ አንድ መቋጫ ልታበጅለት ይገባል:: በጣም ቀላሉ እርምጃ ደግሞ በቀጥታም ይሁን በስውር አባይን የሚያስቡ ጉዳዮች ሲመጡ ከአጀንዳ ውጪ ማድረግ ነው፡፡ አለመቀበሏን ባሳየች ቁጥር ሁለተኛው ወገን ወዶ ሳይሆን ተገዶ፣ አዲስ መንገድ ይፈልጋል ወይም ይይዛል፡፡ እየተደረገ ስላለው ድርድር የሚነገሩና የሚጻፉ ጉዳዮች ተሰባስበው ሲታዩ የሚሰጡት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ በውኃ ሃብቷ ለመጠቀም እየታገለች ያለች አገር መሆኗን የሚገልጹ ናቸው፡፡ ለእኔ ይህ ትክክል አይደለም፡፡
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ብቻ ሳይሆን አባይም የኢትዮጵያ ሃብት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ ለመጠቀም ፈቃድ የምትጠይቀው ወይም ፈቃድ የመስጠት ሥልጣን ያለው አካል እንደሌለ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ድርድሩም መሆን ያለበት “ኢትዮጵያ እንዴት በውሃ ሃብቷ ትጠቀም” ሳይሆን “ኢትዮጵያ ምን ብታደርግ የሱዳንና የግብጽን የውኃ ፍላጐት መመለስ ትችላለች” የሚል  ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ፤ ኢትዮጵያ እንዴት አሳቢነቷን ታሳይ ነው፡፡
አንድ ሰው ከያዘው አስር ዳቦ፣ አምስቱን ቢሰጥ፣ ሰጪው ለተሰጪው፣ ከራሱ እኩል አስቦለታል ማለት ነው፡፡ ስድስቱን ወይም ሰባቱን ዳቦ ቢሰጠው ደግሞ ሰጪው ከራሱ በላይ ለተቀባዩ እንዳሰበ ያስረዳል፡፡
ስምንተኛውን ዳቦ ሰጥቶት ተቀባዩ አሁንም ሌላ ዳቦ ፈልጐ እጅ ከዘረጋ፣ የተቀባዩን ስግብግብነት በግልጽ የሚያሳይ ተግባር ይሆናል፡፡ በአንፃሩ ሰጪው ከዚህ መጠን ካለፈ፣ ለጋሥነቱ ሳይሆን የዋህነቱ ይጐላል፡፡ ተቀባዩም ሰጪውን እንደ ቂል ይቆጥረዋል እንጂ አያከብረውም፡፡
የአባይ ገዳይ እንዲህ ቀላል ባይሆንም መሠረታዊ መንገዱ ግን ከዚህ መውጣት የለበትም፡፡ የሱዳንና የግብጽ ህልውና በአባይ ውኃ  ላይ የተመሠረተ መሆኑን ኢትዮጵያ ታምናለች፡፡ ቢሆንም በምንም አይነት ምክንያት ሁለቱን ለማኖር ራሷን መጉዳት አይኖርባትም፡፡ ድንበሯን አቋርጦ የወጣ  ውሃ ስለማይመለስ፣ ኢትዮጵያ በውሃ  ሃብት አጠቃቀሟ ላይ ብርቱ ጥንቃቄና ቁጥጥር ማድረግ አለባት፡፡  “ተራራው ወደ እናንተ ካልመጣ እናንተ ወደ ተራራው ሂዱ” ይባላል፡፡ ተራራው ላይ ያለችው ኢትዮጵያ፤ ወደ ግብጽ ሃሳብ መሄድም መውረድም የለባትም፡፡ ወደ ተራራው መምጣት ያለባት ግብጽ ናት፡፡ ግብጽ የምትፈልገውን ውሃ ለማግኘት የውኃው ባለቤት በሆነችው ኢትዮጵያ ፈቃድ ሥር ገብታ የምትሻውን ለማግኘት መዘጋጀት ይኖርባታል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን ከቆመበት ከፍታ አንድ ሳንቲም እንኳን መውረድ የለበትም፡፡ የአባይንና የሕዳሴውን ግድብ ጉዳይ መያዝ ያለበት መብቱን ለማስጠበቅ ሳይሆን ለሱዳንና ለግብጽ የሚገባቸውን ከመስጠት አንፃር ነው፡፡ ማንም ለኢትዮጵያ በአባይ ውኃ እንድትጠቀም መብት ሰጪ ሊሆን አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ ግን ለሱዳንም ሆነ ለግብጽ የሚገባቸውን ውኃ ትሰጣቸዋለች፡፡ በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት የነብዩ ቃል የሚያረጋግጠውም፤ ይህንኑ ኢትዮጵያ በአባይ ውኃ ያላትን ሙሉ ባለቤትነት ነው፡፡ ድርድሩን  በእግሩ ማቆም ማለት ደግሞ፣ መብትን ለማስከበር ከመሄድ ይልቅ ባለመብትነትን አምኖና ተቀብሎ፣ የሌሎችን ፍላጐት ለማሟላት ፍቃደኝነትን ማሳየት ነው፡፡ ክቡር ሚኒስትር ፈረሱም ዛቡም በአጅዎ ነው፡፡


Read 2693 times