Sunday, 22 March 2020 00:00

ፈተና፣… ምንም ቢከብድ፣… ‹‹ሆረር›› አይደለም፡፡

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

   ምሳሌያዊትዋ የገነት ዛፍ፣ የእውነትና የእውቀት ዛፍ፣ የሥነ ምግባርና የበረከት ዛፍ፣ ጣፋጭ የሕይወትና የክብር ዛፍ ናት፡፡ እነዚህን ማክበር ነው - የሰው አለኝታና ዋስትና፣ የሰው አልፋና ኦሜጋ፡፡
እነዚህን የሚያጠወልጉ፣ የሚገዘግዙና የሚገነድሱ ናቸው - የሆረር ታሪክ 3 መሰረታዊ ባህሪያት፡፡ እነዚህን ጠንቅቆ ማወቅ ለዘወትር ኑሮ ይጠቅማል:: የበሽታ ወረርሽኝ ለመከላከልም ይረዳል፡፡
የእውነትና የእውቀት ዛፍ፡፡
እውነት እና ሐሰት፣ እውቀትና ቅዠት፣ አስተዋይነትና ጭፍንነት ተደበላልቀው፣ ልዩነታቸው ጠፍቶ፣ ትርጉም ካጡ፣… ‹‹ሰው በሆረር ዓለም ውስጥ›› የሚል ርዕስ ያለው ፊልም እንዳያችሁ ቁጠሩት፡፡
ሁሉም ሰው፣ ‹‹ከእንቅልፍ ልብ›› መባነንና መንቃት ቢያቅተው ብላችሁ አስቡት፡፡ ተራራንና ገደልን ለይቶ መለየት የማይችል፣ ጫካንና ደመናን የሚያምታታ፣ ሚስኪን ቅዠታም ፍጡር ቢሆን፣ ይታያችሁ፡፡
ጠባቧ ቧንቧ፣ እንደ ዘንዶ የምትውጠው ከመሰለው፣ የዘወትሩ የመኝታ ቤት በር፣ የሲኦል መግቢያና የእንጦሮጦስ መውረጃ አፋፍ ሆኖ ከታየው፣ ጠረጴዛውም አድፍጦ የሚጠብቅ አደገኛ አውሬ ሆኖ የሚታየው ከሆነ፤ በጣም አያስፈራም? ሰዎች ሁሉ ከእንዲህ አይነት ቅዥት ማምለጥ ሲያቅታቸው የሚያሳይ ፊልም፣ ያለ ጥርጥር የሆረር ፊልም ነው፡፡
እውነትም፣ የሰው አእምሮ፣ እውኑን አለም የማስተዋልና የማወቅ አቅም ባይኖረው… ለማሰብም ይዘገንናል፡፡ እባቡ እንደ ስካርፍ ወይም እንደ ቀበቶ ሆኖ ከታየው፣ ምድጃውም ምቹ ሶፋ፣ አስፈሪው ዥጉርጉር ነብር ደግሞ ያማረ ትራስ መስሎ ቢታየው፣ ያው፣… ነገሩ ‹‹ሆረር›› ይሆናል፡፡
እንዲህ አይነት የሆረር ፊልሞች ወይም ታሪኮች፣ የአእምሮን አቅም በሚያመክንና ዋጋ በሚያሳጣ ቅኝት ላይ የተመሰረቱ ትረካዎች ናቸው፡፡ እውኑ ዓለም፣ እንደ ወትሮው፣ ‹‹ቅጥ ያለው የሚጨበጥ ዓለም›› ቢሆንም፣… የሰው አእምሮ ግን…. ‹‹ከእለታት አንድ ቀን በድንገት ቀዥታም ሆነ›› በማለት የሚጀምር የሆረር ታሪክ ይኖራል፡፡ ወይም፣ ቀስ በቀስ ውስጥ ለውስጥ እየተመረዘ፣ ‹‹የሰው አእምሮ ሁሉ ዘባራቂ ሆነ›› ከማለት ሊነሳ ይችላል - የሆረር ታሪክ፡፡
የአእምሮን አቅም ማምከን፣ የማስተዋልና የማወቅ ብቃትን መሰረዝ አንድ ገጽታ ነው - ‹‹አእምሮ ቅዠታም ነው›› የሚል የሆረር ገፅታ፡፡ ሌላኛው መንትያ ገፅታ ደግሞ፣ ‹‹ሰማይ ምድሩ የቅዥት ዓለም ነው›› በሚል ቅኝት የተቀረፀ የሆረር ታሪክ ነው፡፡
የሰው አእምሮ፣ የማስተዋልና የማወቅ አቅም ቢኖረውም፣… እውነትን ሀሰትን የመለየት ድንቅ ብቃት ቢቀዳጅም፣… ምን ዋጋ አለው? ሌሎቹ እንስሳትና እፅዋት፣ የቅርብና የሩቅ፣ ግዙፍና ደቂቅ፣ ፈሳሽና ጠጣር ግዑዝ ነገር ሁሉ፣ በፍፁም ሊታወቅ የማይችል፣ ‹‹የቅዠት›› ዓለም ከሆነ፣ የሰው አእምሮ ከንቱ ነው የሚል አስፈሪ መልዕክት አላቸው፡፡ እውኑ ዓለም፣ በብዥታ ይጠፋና፣ በዚሁ ምትክ፣ ‹‹በውን›› ሊታወቅ የማይችል ‹‹የቅዠት›› ዓለምን ፈጥረው ለማሳየት ይሞክራሉ - የሆረር ፊልሞች፡፡ እናም እውነትና ሐሰት ትርጉም ያጣሉ፡፡ በእውን የነበረው ነገር፣ እልም ይላል - እንደ ህልም፡፡
የእውቀትና የቅዠት ልዩነት ይጠፋል::  ዳቦው ድንገት ጊንጥ ይሆናል፡፡ ተራራው ጎርፍ ይሆናል፡፡ የዛፉ ቅርንጫፎች፣ እንደ ሀረግ እየተመዘዙ፣ እንደ እባብ እየተወረወሩ ያሳድዳሉ፡፡ ጠልፈው ይጥላሉ፣ ተብትበው ይጨመድዳሉ፡፡ ‹‹እውኑ›› ዓለም፣ ‹‹ውጥን ቅጥ›› የለውም፡፡ ውጥንቅጡ የወጣ የቅዠት ዓለም፡፡
በአጭሩ፣ ከሦስት ‹‹የሆረር ታሪክ›› መሰረታዊ ባህርያትና ዓይነቶች መካከል አንዱ፣ ‹‹ዓለም ቅዠት ነው››፣ ወይም ደግሞ፣ ‹‹አእምሮ ቅዠታም ነው›› በሚል ቅኝት ዙሪያ የሚያጠነጥን የታሪክ ባህርይና አይነት ነው፡፡
ደግነቱ፣ እውኑ ዓለም፣ ቅጥ ያለው ዓለም ነው፡፡ የሰው አእምሮም፣ እውን የሆነውንና ያልሆነውን (ማለትም እውነትንና ሀሰትን) የመለየት፣ በቅጡም እውቀትን የማስፋትና የማዳበር አቅም አለው፡፡
በከባድ የፈተና ወቅትም ቢሆን፣ ይህንን እውነት ለአፍታ መዘንጋት የለብንም፡፡ ካሁን በፊት ጠንቅቀን የማናውቃቸው ነገሮች ሲጋረጡብን፣ እውነትንና ሐሰትን ለመለየት እስክንቸገር ድረስ የሚያምታቱ መረጃዎች በገፍ ሲዛመቱ፣ በውዥንብር ማዕበል መናወጥና መቃወስ ሲበረክትብንም እንኳ፣ ዘላለማዊውንና የማይናወጠውን እውነታ መዘንጋት የለብንም፡፡
እንዲያውም በፈታኝ ወቅቶች ላይ፣ ይህንን እውነት በፅናት መጨበጥ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ሰማይ ምድሩ የቅዠት ዓለም አይደለም -  ‹‹እውን ዓለም›› ነው፡፡ የሰው አእምሮም፣ እጅግ ድንቅ የማወቅ አቅም አለው፡፡ ድንቅ የአእምሮ አቅሙን በአግባቡ ለመጠቀም የመምረጥ፣ የተቃና መንገድን የመቀየስና በተግባር የመትጋት ጉዳይ ነው ቀጣዩ ቁም ነገር፡፡ ይሄ ወደ ሁለተኛው ነጥብ ይወስደናል፡፡
የሥነ ምግባርና የበረከት ፍሬያማ ዛፍ፡፡
የመናፍስት፣ የጭራቅ፣ የሰይጣን፣ የጂኒ፣ የዞምቢና፣ የቫምፓየር ሆረር ታሪኮች ጋ ገና አልደረስንም። የሆረር ታሪክ ሦስተኛው መሰረታዊ ባህርይና ዓይነት ላይ እነ ጭራቅን በምሳሌነት እናነሳቸዋለን። በቅድሚያ ሁለተኛውን፣ የሆረር ባህርይና አይነት እንመልከት፡፡
በኤደን ገነት መሃል ላይ ያለችውን ምሳሌያዊ ዛፍ አስታውሱ፡፡ በአንድ በኩል እውነትንና ሀሰትን ለመለየት የምታስችል የእውቀት ዛፍ ናት፡፡ በሌላ በኩልም፣ ጥሩና መጥፎን  ለመምረጥ የምትጠቅም፣ የበረከት ዛፍ ናት፡፡ ሦስተኛም፣ የከበረና የረከሰ፣ የላቀና የወረደ መንፈስን ለማዳኘትና የተቀደሰ ማንነትን ለመቅረፅ ታግዛለች - የሕይወት ዛፍ ናትና፡፡
የሆረር ታሪክ አንደኛ ባህርይ፣ የእውቀት ዛፍን በመገንደስ ዙሪያ እንደሚያጠነጥን አይተናል፡፡ የበረከት ዛፍን መገንደስ ደግሞ ሁለተኛው የሆረር ታሪክ ባህርይ ነው:: ጠቃሚውንና ጎጂውን፣ የሚበጅውንና የሚፈጀውን፣   የሚያዋጣውንና የሚጥለውን፣ የሚያተርፈውንና የሚያከስረውን፣ የሚያፀናውና የሚፀናበትን ለይቶ የማወቅ ብቻ ሳይሆን፣ መዝኖ የመምረጥ፣ ተፈጥሯዊ አቅም አለው - የሰው ልጅ፡፡ የእለት የእለቱን ብቻ ሳይሆን፣ በአጭር የሚቀጨውን ትቶ በረዥሙ የሚያዘልቀውን አላማ አፅንቶ፣ ትክክለኛውን መንገድ ይዞ፣ በውጤታማ መላ፣ በትጋት ለመጣር፣… የሰው ልጅ፣ እነዚህን ሁሉ የመምረጥና በእውን የማሳካት እምቅ አቅም አለው፡፡
በእርግጥ፣ በተለያዩ ምክንያቶች፣ የሰዎች የኑሮ አቅም፣ በርካታ እንቅፋቶች ሊገጥሙት ይችላል - በድንገተኛ አደጋ፣ በህመም፣ በከባድ ስህተት፣ በወንጀለኞች ጥቃትና በሌሎች አልፍ ሰበቦች፣ ብዙ ፈተናዎች ይደራረቡበታል፡፡
እንዲያም ሆኖ፣ ኑሮን በትንሽ በትንሹ ከማሻሻል ጀምሮ፣ የቢሊዮን ሰዎችን አኗኗር ወደ ብልፅግና የሚያሸጋግሩ ብዙ ስኬቶች እውን ሆነዋል፡፡ በእውኑ ዓለም ውስጥ፣ ስኬትን የመቀዳጀት፣ ድንቅ የኑሮ አቅም አለው - የሰው ልጅ፡፡
እቅፋቶችና አደጋዎች ቢበረክቱም እንኳ፣ የሰውን የኑሮ አቅም የሚያስክዱ አይደሉም:: ጥሩና መጥፎን፣ ጊዜያዊውንና ዘላቂውን አመዛዝኖ የመምረጥ፣ በትጋትም የማሳካት፣ በረከትን የመፍጠር ትልቅ የኑሮ አቅም አለው - የሰው ልጅ፡፡ ለዚያውም ድንቅ የስኬት አቅም ነው - እንደ ኤዶም ገነት የበረከት ዛፍ፡፡
በተቃራኒው፣ የሆረር ታሪኮች ሁለተኛው መሰረታዊ ባህርይ፣ ይህንን የበረከት ዛፍ በማጠውለግና ገዝግዞ በመጣል ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ እንግዲህ አስቡት፡፡ ሰው ሁሉ፣ እንደ ወትሮው ተኝቶ፣ በነጋታው ነገረ ስራው በሙሉ፣ ‹‹በእንቅልፍ ልብ›› ብቻ ቢሆን፣… እውነትና ውሸትን ከማምታት አልፎ፣ ማልማትና ማጥፋትም፣ ልዩነት የሌላቸው ጭፍን ተግባራት ቢሆኑ ይታያችሁ፡፡
በስካር መንፈስ፣ መኪኖች እንደ ጉድ ወደሚከንፉበት የፍጥነት መስመር የሚንደረደር ወይም ወደ ገደል አፋፍ የሚንገዳገድ፣ እንደ ጭፍን ፍጡር የሚደናበር ሰው ሲበዛ አስቡት፡፡ ወይም መብረር እፈልጋለሁ ብሎ ከ20ኛ ፎቅ የሚወረወር፣ ትናንት የወጠነውን በማግስቱ ማስታወስ የማይችል፣ ዛሬ በመከራ የገነባውን ነገ እንደ እንቅፋት እየናደ የሚባክን… አንድም እንደቀሽም በስካር ከመደናበር፣ አሊያም እንደ ሕፃን በሚስኪንነት ከመንፏቀቅ ውጭ ሌላ ምንም አይነት አቅም ባይኖር፣ በድርሰት ይቅርና እንዲሁ በደፈናው ሲታሰብ እንኳ፣ ይዘገንናል - ሆረር ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡
በርካታ የሆረር ታሪኮች፣ የዚህን መንትያ ገጽታ አጉልተው ያሳያሉ፡፡
‹‹ዓለም ከቅዥትም አልፎ ጠማማ ነው›› በሚል ቅኝት የተዋቀሩ ሆረር ታሪኮች፣ የሰው ተፈጥሮ፣ ድንቅ ቢሆንኳ፣ ዋጋ እንደሌለው ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡ የሰው ልጅ የሚበጀውን የመምረጥ፣ ትክክለኛውን አላማ የመያዝ፣ በጥበብ ሁነኛ መላዎችን የመቀየስና በትጋት የመጣር አቅም ቢኖረውምንኳ፣ ‹‹ምን ዋጋ አለው?››… እውኑ ዓለም ጠማማ ከሆነ፣ የሰውን ጥረት ለማምከን የተቃኘ ከሆነ፣ ነገሩ ሁሉ ከከንቱም ከንቱ፣ ይባስ ብሎም፣ መላ የሌለው “ሆረር” ይሆናል፡፡
ሰዎች፣ ከመጥፎ እጣ ፈንታ ለማምለጥ የቱንም ያህል ቢጠበቡና ቢዘጋጁ፣ የቱንም ያህል ቢጠነቀቁና ቢተጉ፣…ዋጋ እንደሌለው የሚያሳዩ የሆረር ድርሰቶችን ወይም ፊልሞችን ማስታወስ ይቻላል፡፡
እንዲያውም፤ ማንኛውም የሰው፣ ከጥፋት ለማምለጥ በጥበብ የሚፈጥራቸው ዘዴዎችና የሚያከናውናቸው ዝግጅቶች፣ ወደ ጥፋት እጣ ፈንታ የሚወስዱ መንገዶች ይሆኑበታል፡፡ ከመዓት ለመትረፍ በጥንቃቄ መትጋቱ፣ እጣፈንታውን ሲያፋጥኑበት ያሳያሉ - ሆረር ታሪኮች፡፡
ደግነቱ፣ እውኑ አለም፣ የተፈጥሮውን ስርዓት ጥሶ፣ ሰውን ለማሰናከል አይጣመምም፡፡ ውሃው ከሰማይ መዝነብ፣ ከላይ ወደታች መፍሰስ እና መጉረፍ፣ በጐድጓዳ ቦታ መጠራቀም፣ በአሸዋማ አፈር ወደ ስር መስረግ፣ በሙቀት መትነን፣ በቅዝቃዜ ጤዛ፣ ዝናብና በረዶ መሆንን ትቶ፣ የሰውን አላማ ለማሰናከል፣ ጥረቱን ለማምከን አያሴርም፡፡ ግዑዙ ዓለም የሰዎችን እጣፈንታ አይወስንም፡፡
ሰውም ለጥፋት ብቻ የተቃኘ አይደለም፡፡ በስካር ከመደናበር፣ በጨቅላነት ከመንፏቀቅ ውጭ ሌላ አቅም የሌለው ፍጡር አይደለም::
እናም፤ የሰውን የስኬት አቅም የሚያናንቅና የሚያዳክም አጥፊ አስተሳሰብን ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዴ ፈተናው ከብዶ፣ ኑሯችንና አላማችን ቢናጋም፣ ምን ማቀድና መስራት እንዳለብን ግራ  ብንጋባም፤ ችግርና እንቅፋት በዝቶ፣ ሰማይ ምድሩ የጠመመብን ቢመስለንም እንኳ፣ ለአፍታም ቢሆን፣ ምሳሌያዊዋን የበረከት ዛፍ ልንረሳ አይገባም:: ሰው፣ ድንቅ የስኬት አቅም እንዳለው፣ እውኑ ዓለም ደግሞ እንደተፈጥሮው ሆኖ እንደሚቀጥል መዘንጋት የለብንም፡፡
ጣፋጭ የሕይወትና የእርካታ ዛፍ፡፡
በእርግጥም፣ እውነትንና ሃሰትን የመለየት፣ እውነተኛ መረጃዎችን የማገናዘብ፣ በቅጡ የማወቅ፣… ከዚህም በተጨማሪ፣ የሚበጀውንና የማይበጀውን፣ ውጤታማውንና የሚያዛልቀውን አመዛዝኖ፣ ትክክለኛ አላማንና ሁነኛውን መላ የመምረጥ፣ በትጋትም የመጣር የሰው ልጅ አቅም፣… እጅግ ከፍተኛ፣ እጅግ ድንቅ ነው፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የሰው ልጅ፣ የግል ማንነቱን፣ በንጽህና፣ በጽናትና በብቃት የመቅረጽ ድንቅ የሥነ ምግባር አቅም አለው:: ይሄ በግል ኃላፊነት ላይ የተመሰረተ ክቡር አቅም ነው፡፡
የግል ማንነትንና የግል ሃላፊነትን የሚያናንቅ፣ የሚያጣጥል፣ የሚያዳክም ማናቸውንም አስተሳሰብ፣ እጅግ ክፉ ነው:: ውጤቱም “ሆረር” ነውና፡፡ ሦስተኛው የሆረር ድርሰቶች መሰረታዊ ባህርይም፣ ሌላ አይደለም - የግል ማንነትን በማሳጣት፣ የግል ኃላፊነትን በማምከን ላይ የተመሰረተ ነው - ሦስተኛው የሆረር ታሪኮች ባህሪ፡፡
በአንዳች መንፈስ፣ ወይም ባልታወቀ ሃይል፣ የሰዎች ማንነት ሲቀየርና “ዞምቢ“፣ ወይም “አውሬ”፣ ቫምፓየርና ጭራቅ ሲሆኑ፣… ወይም ሌላ ፍጡር የሚቆጣጠራቸው አገልጋይ አሻንጉሊት ሲሆኑ የሚያሳዩ ናቸው - አብዛኞቹ የሆረር ፊልሞች፡፡  
ሰዎች  በሥነ ምግባር ሕይወታቸውን የመምራትና ስብዕናቸውን የመቅረፅ አቅም እንደሌላቸው በማስመሰል - የግል ማንነትን በማቅለል፣ የግል ሃላፊነትን በማጥፋት ላይ የተመሰረተው የሆረር ታሪኮች ባህርይ፣ የሰዎችን የሕይወት ዛፍ እንደ መገንደስ የሚቆጠር ነው፡፡

Read 981 times