Saturday, 21 March 2020 13:04

የቋንቋ ፖሊሲው ምን ይላል?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

    በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የፀደቀውን የቋንቋ ፖሊሲ በተመለከተ ከሰሞኑ  አንድነት ፓርክ ግቢ ውስጥ በሚገኘው የአፄ ኃይለሥላሴ ዙፋን ችሎት ቤት፣ ምሁራን በፖሊሲው ላይ ምክክርና ውይይት አድርገውበታል፡፡
በውይይቱ ላይም የቋንቋ ፖሊሲ ጥናቱን ያዘጋጁ ምሁራን፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁም ሌሎች በቋንቋና ስነጽሑፍ ዘርፍ አንቱታን ያተረፉ ሊቆች ተሳትፈዋል፡፡ አዲስ የተዘጋጀው የቋንቋ ፖሊሲ፤ ሀገሪቱ ከአማርኛ በተጨማሪ  አፋርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ሶማሊኛና ትግርኛ ቋንቋዎችን ለስራ እንድትጠቀምበት አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡
እነዚህ ተጨማሪ 4 ቋንቋዎች የተመረጡትም ከተናጋሪዎቻቸው ብዛት እንዲሁም ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ጐረቤት ሀገራት ጭምር የሚናገሯቸው በመሆናቸው ነው ተብሏል፡፡
ቋንቋዎቹን ከአማርኛ ጐን ለጐን፣ የፌደራል የሥራ ቋንቋ ለማድረግም መጠነ ሠፊ ቅድመ ዝግጅቶች መደረግ እንዳለባቸው ምሁራኑ ይመክራሉ፡፡ በፖሊሲ ማዕቀፉም የተቀመጡ ቅድመ ስራዎች ያሉ ሲሆን ቋንቋዎቹን ሙሉ ለሙሉ የስራ ቋንቋ ለማድረግም ከ10 እስከ 15 ዓመት ሊፈጅ እንደሚችል ተገልጿል፡፡
የሥራ ቋንቋ ታሪክ በኢትዮጵያ
በዘመናዊ የኢትዮጵያ አስተዳደር ስርአት ውስጥ ጐልተው የሚጠቀሱት ንጉሰ ነገስት አፄ ምኒልክ፤ ባልተፃፈ ህግ አማርኛን የመንግስታቸው ብሔራዊ ቋንቋ ማድረጋቸውን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ካሣው ተናግረዋል፡፡ አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን አንድ ከማድረግ አስተሳሰብ በመነሳት አማርኛን ብሔራዊ የስራ ቋንቋ አድርገው ባልተፃፈ ህግ ይጠቀሙበት የነበረ ሲሆን፤ የትኛውም የመልዕክት ልውውጥም በዚሁ ቋንቋ ሲከወን ነበር፡፡
ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ደግሞ በተፃፈ ህግ፣ አማርኛ የሀገሪቱ የሥራ ቋንቋ ሆኖ እንዲያገለግል ማድረጋቸው ተጠቁሟል:: አማርኛን ይፋዊ የስራ ቋንቋ ያደረገው የንጉሥ ነገስቱ ስርአት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ትግርኛ፣ አፋርኛ፣ ሶማሊኛና ኦሮሚኛ ቋንቋዎች የሬዲዮ ቋንቋ ሆነው እንዲያገለግሉ አድርጐም ነበረ፡፡ ወቅቱም የቋንቋ ብዝሃነትን ማስተናገድ የተጀመረበት ነበር ማለት ይቻላል ብለዋል - ዶ/ር ሂሩት፡፡
ኋላም በደርግ ዘመነ መንግስት 15 ገደማ የሚደርሱ ቋንቋዎችን ለመሠረተ ትምህርት ማስተማሪያነት እንዲውሉ መደረጉን ሚኒስትሯ አውስተዋል:: በዚህ ሂደትም የቋንቋዎችን ብዝሃነት ከፍ ወደ ማድረግ መኬዱንም ይገልፃሉ፡፡ በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ፤ በ1964 ዓ.ም የአማርኛ ቋንቋን ማበልፀግን ታሳቢ ያደረገ የቋንቋ አካዳሚ ተቋቁሞ የነበረ ሲሆን፤ በደርግ ዘመነ መንግስት ደግሞ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚን በመመስረት፣ 15 ቋንቋዎች ተለይተው፣ የማበልፀጊያ ጥናት ሲደረግባቸው መቆየቱን ዶ/ር ሂሩት ያስረዳሉ፡፡
በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት፤ ለሁሉም ቋንቋዎች እኩል እውቅናን የሠጠን ህገ-መንግስት ከመደንገግ ባለፈ ሁሉንም ቋንቋዎች ለትምህርትና ለስራ የመጠቀም ተግባርም ተከናውኗል፡፡ 53 የሀገሪቱ ቋንቋዎች የትምህርት ቋንቋ መሆንም ችለዋል፡፡ ክልሎችም የየራሳቸው የስራ ቋንቋዎችን መርጠው እንዲጠቀሙ ተደርጓል፡፡ በደርግ ዘመነ መንግስት 15 ቋንቋዎች ላይ ምርምር ያካሂድ የነበረው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚም፣ ወደ ኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች ጥናት አካዳሚ አድጐ፣ በአሁኑ ወቅት 80 ቋንቋዎችን በስፋት በማጥናት ላይ ይገኛል፡፡
እነዚህ ተግባራት ሲከናወኑ በቆዩባቸው አመታት ግን ሀገሪቱ የጠራና ግልጽነት ያለው የቋንቋ ፖሊሲ አልነበራትም፡፡
በዚህም ሳቢያ ቋንቋዎች ተመርጠው ለትምህርት፣ ለስራና ለብሔራዊ መግባባት የሚውሉበት አመራር አልነበረም፡፡ ቋንቋዎችንም ለማበልፀግ አልተቻለም:: አዲስ የፀደቀው ፖሊሲ ከዚህ አንፃር የሀገሪቱን ብዝሃ ቋንቋ የበለጠ የሚያበለጽግ፣ ዋና መሠረት መሆኑ በውይይቱ ተጠቁሟል::
“በሀገሪቱ ግልጽ የቋንቋ ፖሊሲ ባለመኖሩ ኢትዮጵያ የብዝሃ ቋንቋ ባለቤት ብትሆንም ቅሉ ብዝሃ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ አልፈጠረችም” ይላሉ፤ ዶ/ር ሂሩት፡፡ አንድ ሰው ቢያንስ ከሁለት በላይ የሀገሩን ቋንቋ ቢያውቅ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር እንደሚቻልና አዲሱ የቋንቋ ፖሊሲም የብዝሃ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ የሚፈጠርበትን አቅጣጫ ያስቀመጠ መሆኑ ተመልክቷል - በውይይቱ መድረኩ፡፡
የቋንቋ ፖሊሲው ዝግጅት ምን ይመስላል?
የቋንቋ ፖሊሲውን ዝግጅትና አስፈላጊነት በተመለከተ በመድረኩ ማብራሪያና ገለፃ ያቀረቡት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋና ስነ ጽሑፍ እና ትርጉም ዳይሬክተር የሆኑትና በቋንቋ ፖሊሲ ዝግጅት የተሳተፉት አቶ አውላቸው ድልነሳ ሲሆኑ ስለ ፖሊሲ ዝግጅቱ ሂደት  አብራርተዋል፡፡
ፖሊሲው በይፋ ዝግጅት የጀመረው በ2003 ነበር፡፡ ያኔ ወደ ተግባራዊ የፖሊሲ ዝግጅት በሚገባበት ወቅት ሁለት ቡድን ተቋቁሞ ነበር፡፡ ዋናውን የፖሊሲ ጥናት ያዘጋጁትም ሶስት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን፡- ዶ/ር ሞገስ ይገዙ፣ ዶ/ር ታዬ አሰፋና ፕ/ር ባዬ ይማም ነበሩ፡፡ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ደግሞ ራሣቸው አቶ አውላቸውና አቶ አለማየሁ ጌታቸው እንዲሁም አሁን በህይወት የሌሉት ዶ/ር ብቅአለ ስዩም የኮሚቴው አባል ሆነው ስራው መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡ አብይ ኮሚቴ ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በተውጣጡ ስምንት  ባለሙያዎችም ተቋቁሞ ነበር፡፡ አብይ ኮሚቴው በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሠረትም፤ በምሁራን የተዋቀረው የቴክኒክ ኮሚቴ፤ ጥናትና ምርምሮችን ሲያደርግ መቆየቱን ያወሳሉ - አቶ አውላቸው፡፡
ጥናቱ ሲካሄድም በሁሉም ክልሎች በመዘዋወር ጥናት መደረጉን፣ የቋንቋዎች አካዳሚ ውስጥ የነበሩ ጥናቶች፣ የብሔረሰቦች ም/ቤት ያጠናቸው ጥናቶች እንዲሁም አለማቀፍ የሰብአዊ መብትና ቋንቋ ተኮር ጥናቶችን በማሰባሰብ ለፖለሲው ግብአት መዋሉ ተጠቁሟል፡፡ እነዚህ የተሰባሰቡ ጥናቶችም በዘርፉ አንቱታን ባተረፉ ምሁራን በተደጋጋሚ መገምገማቸውን አቶ አውላቸው አስረድተዋል፡፡
ከውጭ ሀገራትም ልምዶችን መቅሰማቸው ተገልጿል፡፡ የቴክኒክ ቡድኑ በዋናነት በህንድና ደቡብ አፍሪካ ጉብኝት በማድረግ ጭምር፣ ቋንቋዎቻቸውን በምን አግባብ እየተጠቀሙ እንዳሉ  ተሞክሮ መውሰዱን ይናገራሉ፡፡ እነዚህን መረጃዎችና የጥናት ውጤቶች በማሰባሰብም፣ የመጀመሪያው ረቂቅ ፖሊሲ በ2004 ዓ.ም የተዘጋጀ ሲሆን በግንቦት ወርም ለመጀመሪያ ጊዜ በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ባለድርሻ አካላት ውይይት አድርገውበታል:: በውይይቱ ከተገኘው ግብአት በመነሳትም በረቂቁ ላይ ማሻሻያዎች ተደርገው በድጋሚ ለባለሙያዎችና ለባለድርሻ አካላት ውይይት መቅረቡን፣ በዚህ ሁለተኛ ዙር ውይይትም ጥሩ ግብአቶች መገኘታቸውንና ለረቂቁ ማዳበሪያ መዋላቸውን አቶ አውላቸው ገልፀዋል፡፡
ረቂቁን ከ2004 ጀምሮ እስከፀደቀበት ጊዜ ድረስ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ደግመው  መምከራቸውንና የመሰላቸውን የማሻሻያ ሃሳብ ማቅረባቸውም ተወስቷል:: በሁሉም ክልሎች በመዘዋወርም ረቂቅ ፖሊሲው ላይ ውይይት መደረጉን  ጠቁመዋል፡፡
የቋንቋ ፖሊሲ ለምን አስፈለገ?
የፖሊሲ ማዕቀፉ መዘጋጀት በዋናነነት የሀገሪቱን ቋንቋዎች አጥንቶና ለይቶ የበለጠ ለማበልፀግ ይጠቅማል፡፡ በአሁኑ ወቅት 53 ቋንቋዎች በትምህርት መስጫነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በቀጣይ ሌሎችንም በፖሊሲው መሠረት በማበልፀግ ተጨማሪ የትምህርት ቋንቋዎችን ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ ከዚህ ባሻገር የማህበረሰብ የእርስ በእርስ ትስስርን፣ እንዲሁም ቀጣናዊ ትስስርን ለማጐልበት የቋንቋ ፖሊሲው በእጅጉ ጠቃሚ ነው፡፡
የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን የሣይንስና ቴክኖሎጂ ቋንቋዎች በማድረግ ረገድ የፖሊሲ ማዕቀፍ ጠቀሜታው የጐላ ነው:: ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስም በሀገር አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡ በመገናኛ ብዙሃን የቋንቋ አጠቃቀም ላይም ስርአትና መመሪያ በማስቀመጥ የሚፈጠርን የቋንቋ መበረዝ ለመከላከል ፖሊሲው ጠቃሚ መሆኑን አቶ አውላቸው አስረድተዋል፡፡
የፖሊሲው ይዘትና አቅጣጫ ምንድን ነው?
ይሄን አስመልክቶ በመድረኩ ማብራሪያ ያቀረቡት የቴክኒክ ኮሚቴው አባል የሆኑት የቋንቋና ስነልሣን ምሁሩ ዶ/ር ሞገስ ይገዙ ናቸው፡፡ ፖሊሲው በዋናነት ለቋንቋ መብቶች ጥበቃ የቆመ መሆኑን ዶ/ር ኢዮብ ያስገነዝባሉ፡፡ አንደኛው የፖሊሲው አቅጣጫ፣ ቋንቋዎችን ማልማት ነው:: ቋንቋዎችን በባለሙያዎች በማልማት የትምህርት፣ የሣይንስና የብዙሃን መግባቢያ ማድረግ የፖሊሲው ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ነው፡፡ ማየትና መስማት የተሳናቸው ዜጐች የሚጠቀሙባቸውን ቋንቋዎችም ማልማት፣ የመገናኛ ብዙሃን ቋንቋ ማድረግ ሌላው የፖሊሲው አቅጣጫ መሆኑ በዶ/ር ሞገስ ተጠቁሟል፡፡
አሁን ከአማርኛ በተጨማሪ የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ ከተረመጡት አራት ቋንቋዎች በተጨማሪ በቀጣይም ሌሎች ቋንቋዎች ተጠንተው፣ የፌደራል የስራ ቋንቋ የሚሆኑበት አቅጣጫም በፖሊሲ ማዕቀፉ ተቀምጧል፡፡ የመገናኛ ብዙሃን የቋንቋ አጠቃቀም ላይም ፖሊሲው አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ሲሆን መገናኛ ብዙሃን በቀጣይ በህግ የተዘጋጀ የቋንቋ አጠቃቀም እንዲኖራቸው አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ይህም የጉራማይሌነት ተግዳሮትን ለመቅረፍ ያስችላል ብለዋል - ዶ/ር ሞገስ፡፡
ቋንቋዎች እንዴት የትምህርት ቋንቋ መሆን እንደሚችሉም የፖሊሲ ማዕቀፉ አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡ በተለይ የራሣቸው ፊደልና ሰዋሰው ስርአት ተሟልቶላቸው እንዴት የስርአተ ትምህርት ማሳለጫ ይሆናሉ የሚለው በፖሊሲው ተቀምጧል፡፡ በቀጣይም በዚህ በኩል የህግ ማዕቀፍ እንደሚኖር የፖሊሲው አቅጣጫ ያመላክታል፡፡ አሁን ሀገሪቱ ለትምህርት መስጫነት የምትጠቀመው እንግሊዝኛ ቋንቋም በሂደት በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች የሚተካበትን አቅጣጫም ፖሊሲው ያስቀምጣል፡፡ እንግሊዝኛ ቋንቋ ግን ለተግባቦት ያህል በትምህርት ስርአቱ እንዲካተት ያደርጋል፡፡
ሌላው ፖሊሲው የሚያስቀምጠው አቅጣጫ የአደባባይ ቋንቋን በተመለከተ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ የአደባባይ ቋንቋ - የፕሮቶኮል ቋንቋ አጠቃቀም መመሪያ የነበራት ሲሆን፤ ፖሊሲው ግን ለዚህ አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡ ለምሣሌ መሪዎች ውጭ ሀገር ሲሄዱም ሆነ ከውጭ ከመጣ እንግዳ ጋር ተነጋግረው ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ በህግ የተደነገገ የፕሮቶኮል ቋንቋ አጠቃቀም እንደሚያስፈልግ በፖሊሲው ያመለክታል፡፡
ቋንቋና “ዘዬ” ንም አጣጥሞ እውቅና ስለ መስጠትም ፖሊሲው አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡
የትርጉምና የአስተርጓሚ የሙያ ብቃትም እንዲዳብርና ተርጓሚነት ራሱን የቻለ ሙያ ሆኖ እውቅና የሚያገኝበት ስርአት ያስፈልጋል በሚልም ፖሊሲው አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ የትርጉም ሙያም ተቋም ተበጅቶለት ሊሠራ የሚገባው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ሀገሪቱ የቋንቋ ሀብቷን በአግባቡ ባለመንከባከቧም 28 ቋንቋዎቿ በመጥፋት ላይ መሆናቸውን ዶ/ር ሞገስ አመልክተዋል - የዩኔስኮን ሪፖርት በመጥቀስ፡፡
ፖሊሲው እንዴት ሊተገበር ይችላል?
ይሄን በተመለከተ ማብራሪያ ያቀረቡት የቋንቋ መምህርና ተመራማሪው ዶ/ር ታዬ አሠፋ ናቸው፡፡ የቋንቋ ፖሊሲውን በስራ ላይ ለማዋል ሰፊ የገንዘብ አቅምና የተቋማት ግንባታ ያስፈልጋል የሚሉት ዶ/ር ታዬ፤ የቋንቋ ልማት መርሃ ግብር ሊዘረጋ ይገባል ይላሉ፡፡
ብዙዎቹ የሀገሪቱ ቋንቋዎችም በባለሙያዎች በቂ በጀት ተመድቦ፣ በቋንቋ ልማት መርሃ ግብሩ መሠረት መጠናት እንዳለባቸው ዶ/ር ታዬ ያብራራሉ፡፡
በዚህ የቋንቋ ልማት በቋንቋና በዘዬ መካከል ያለ ልዩነትም በሚገባ በስነ ልሣን ባለሙያዎች ተለይቶና ተጠንቶ መቀመጥ እንዳለበትም ተገልጿል፡፡
የቋንቋ ተናጋሪዎችን ብዛት፣ የቋንቋ ቆጠራና እንዲሁም የተናጋሪዎች ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ በካርታ ተዘጋጅቶ ሊቀርብ እንደሚገባም ዶ/ር ታዬ አስረድተዋል፡፡
ለቋንቋዎች መዝገበ ቃላት፣ ስነ ጽሑፎችን በየቋንቋው የታሪክ የስነጽሑፍ፣ ለህፃናት የተረት መጽሐፋም በየቋንቋም ሊዘጋጅ ይገባል፡፡ ይሄን ለማሳለጥ ደግሞ የቋንቋ ማዕከላት በክልልና በፌደራል ደረጃ ሊቋቋሙ እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡
ፖሊሲውን በእቅድ መርቶ ለመተግበር የሚቋቋሙ የቋንቋ ማዕከላት በባለሙያዎች፣ በገንዘብ አቅምና በቁሳቁስ በሚገባ የተደራጁ፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ገለልተኛ የሆኑ፣ በባለሙያ ብቻ የሚሠራባቸው ተቋማት ሊሆኑ ይገባል ይላሉ - ዶ/ር ታዬ፡፡
ከአማርኛ በተጨማሪ የስራ ቋንቋ የሚሆኑ ቋንቋዎችን ለመተግበር ከወዲሁ ቋንቋዎቹ የሚበለጽጉበት ተቋምም ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ ፖሊሲውን ስራ ላይ ለማዋል ሶስት ዋና ዋና ተቋማት ሊመሠረቱ እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡
አንደኛውና ዋንኛው የቋንቋ ጉዳዮች ምክር ቤት ነው:: የቋንቋ ጉዳዮች ም/ቤት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ  ሊባል እንደሚችል የሚያወሱት ዶ/ር ታዬ፤ ይህ ተቋም ዋነኛ ሃላፊነቱ ቋንቋዎችን ማጥናትና መመርመር ይሆናል፡፡ ይሄ ተቋም አጥንቶ የሚያቀርባቸው ውጤቶች በቋንቋዎች አጠቃቀም ላይ ወሳኝ መሆኑንም ያወሳሉ፡፡
ሶስተኛው ተቋም የትርጉም ተቋም ነው፡፡ የተለያዩ አዋጆችደ፣ ሕጎች፣ አለማቀፍ ስምምነቶች፣ ሌሎች መመሪያዎችን በየቋንቋው የሚተረጉም ራሱን የቻለ ተቋም ነው፡፡ ይህ ተቋም በትርጉም ባለሙያዎች የተጠናከረ በጥናት ላይ የተመሰረተ ከፍተኛ በጀት የሚያስፈልገውም ነው፡፡ የህንዶች የትርጉም ተቋም ሕጎችን ወደየ ቋንቋዎች ከመተርጎም ባለፈ የመማሪያ መጻሕፍትም ወደ የቋንቋው የሚተረጉም ግዙፍ ተቋም መሆኑም በጥናቱ ተመላክቷል፡፡
ለእነዚህ ተቋማት የገንዘብ ምንጭ ተብለው ከተመላከቱት መካከልም አባላት ያሉት ሆኖ አገራዊ መርሃ ግብር መዘርጋትና ተፈጻሚነቱን የሚከታተልም ሊሆን ይገባዋል ይላሉ ዶ/ር ታዬ፡፡ ለዚህም የሕንድና የደቡብ አፍሪካ የቋንቋ ጉዳዮች ም/ቤት ተጠቃሽ ነው፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤትም የፖሊሲ ማስፈፀሚያ ሕጎች ሊያወጣ እንደሚገባው ተጠቁሟል፡፡ የቋንቋዎች ጉዳይ ም/ቤትም የሕጎቹን ተፈፃሚነትና የፖሊሲውን ተፈፃሚነት የመከታተል ሃላፊነት ይኖረዋል፡፡
ፖሊሲውን በዚህ ም/ቤት በኩል ለማስፈፀም የስራ ልሳን፣ የቋንቋ፣ ከጽሑፍ ባለሙያዎች በገፍ መሰልጠን ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለዚህ መንግሥት አጥንቶ አስፈላጊውን በጀት መመደብ አለበት ባይ ናቸው - ዶ/ር ታዬ፡፡
ሁለተኛው ተቋም ደግሞ ቋንቋዎች ላይ ምርምርና ጥናት የሚያደርግ ተቋም የመቋቋም አስፈላጊነት ነው፡፡ ስያሜው የቋንቋ ማዕከል የቋንቋ አካዳሚ ወይም የቋንቋ ተቋም ቀጥተኛ የመንግሥት በጀት፣ የቋንቋ ልማት ፈንድ የሚባል ተቋምን ማቋቋም እንዲሁም ለቋንቋ የሚሰጡ ድጋፍና እርዳታዎችን ከአጋር ተቋማት ማግኘት እንደሚቻል ተመላክቷል፡፡ የትርጉም ተቋሙም ከሚሰጠው አገልግሎት ክፍያ በመጠየቅ የራሱን ገቢም ማመንጨት እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡


Read 674 times