Saturday, 21 March 2020 12:57

ኦልማርት ከመቶ ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ ለገሰ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     ገርጂ መብራት ሀይልና ጀሞ የሚገኘው ኦልማርት ሱፐር ማርኬት፤ በአገራችን የኮሮና ቫይረስን  መከሰት ተከትሎ፣ ለአቅመ ደካሞች ከመቶ ሺህ በላይ ብር የሚያወጡ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ለገሰ፡፡
ሱፐር ማርኬቱ ይህንን በጎ አድራጎት ያደረገው በተለይም ቫይረሱ በብዛት ያጠቃቸዋል ለተባሉት አረጋዊያን ሲሆን በዚህም ምክንያት ለመቄዶኒያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን ማዕከል፣ ለሜሪ ጆይና ገርጂ መብራት ሀይልና ጀሞ ቅርንጫፎቹ ለሚገኙበት ሁለት ወረዳዎች አረጋውያን ለግሷል፡፡
ድርጅቱ በረኪና፣ ዲቶል፣ ላይፍ ቦይ ሳሙና፣ የልብስ ሳሙናና ላርጎ ፈሳሽ ሳሙናዎችን የለገሰ ሲሆን ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነው ኮሮና ቫይረስ በአገራችን ሲቀሰቀስ እጅን አጣጥፎ ከመቀመጥ ሁሉም እንደ ዜጋ የሚጠበቅበትን በማድረግና በመረዳዳት ይህን ክፉ ቀን ማለፍ ይገባል ብለዋል የኦልማርት ሱፐር ማርኬት ቃል አቀባይ ወ/ሪት ዘኢማ አህመድ፡፡
ሱፐር ማርኬቱ ያደረገውን በጎ አርአያ ተከትለው፣ ሌሎችም የአቅማቸውን በማድረግ የቫይረሱንና ስርጭት በመቆጣጠር በጋራ ታሪክ መስራት አለብን ብለዋል፡፡
የሜሪ ጆይ የተራድኦና የልማት ማህበር፣ የመቄዶንያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል፣ እንዲሁም ሱፐር ማርኬቶቹ የሚገኙባቸው ሁለት ወረዳዎች ተወካዮች ገርጂ መብራት ሀይል በሚገኘው የሱፐር ማርኬቱ ዋና መስሪያ ቤት ተገኝተው ቁሳቁሶቹን ከተረከቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ ሱፐር ማርኬቱ በተለይ ቫይረሱ በቀላሉ የሚያጠቃቸውን አረጋዊያን ታሳቢ በማድረግ ለቅድመ ጥንቃቄ የሚረዳቸውን የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ በመለገሱና በቀድሞ ደራሽነቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው ሌላውም በዚሁ አርአያነት ድጋፉን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አረጋውያንን የመታደግ ሥራ ኮሮና ቫይረስ በዕድሜ ገፋ ያሉና ሌላ የጤና ችግር ያለባቸውን እንደሚያጠቃ መነገሩን ተከትሎ መቄዶንያ የሚደግፋቸውን ከ2 ሺህ በላይ አረጋዊያንና የአዕምሮ ሕሙማን ከቫይረሱ ለመጠበቅ ምን አይነት ሥራ እየተሰራ ነው በሚል ላቀረብነው ጥያቄ፣ በመቄዶኒያ የማዕከሉ ነርስ ዮናስ ሙሉጌታ ሲመልሱ፤ በአሁኑ ወቅት የቅድመ መከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ አዳዲስ አረጋዊያን ወደ ማዕከሉ ማስገባት ማቆማቸውን፣ ድንገተኛና ከባድ የጤና ችግር ካላጋጠመ በስተቀር ሕሙማንን ወደ ተለያዩ ሆስፒታሎች እንደማይወስዱ፣ ጎብኚዎች ሲመጡ በአስተናጋጆች በኩል የሚለግሱትን ለግሰውና ቃል ገብተው ከመሄድ ውጭ አረጋዊያኑን መጎብኘት መከልከሉንና የማዕከሉ ሰራተኞች ለሥራ ወጥተው ሲገቡ፣ የእጅ ማስታጠብና የአልኮል አቅርቦት እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ፤ የአረጋውያኑን ክፍሎች በአልኮልና በበረኪና በማፅዳትና በማናፈስ የቅድመ መከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ነርስ ዮናስ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለቅድመ መከላከል ሥራ የሚረዱ ቁሳቁሶችን በማቅረብ በኩል በተቋምም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ድጋፎች እየመጡ መሆኑን የገለፁት ባለሙያው፤ ከተቋማቱ መካከል ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ልገሳ ያደረገው ኦልማርት ሱፐር ማርኬት ይገኝበታል ብለዋል፡፡   


Read 3452 times