Saturday, 21 March 2020 12:53

ሀሌሉያ ሆስፒታል ለተገልጋዮች የሙቀት ልየታ ሥራ ጀመረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

   እስካሁን በሙቀት ልየታ የተጠረጠሩ 6 ሰዎችን አስረክቧል
                       
                  ሀሌሉያ አጠቃላይ ሆስፒታል ለተገልጋዮች የሙቀት ልየታ ምርመራ መጀመሩን አስታወቀ:: ሆስፒታሉ ሀሙስ ረፋድ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ኮረና ቫይረስ (ኮቪድ 19) በሀገራችን መከሰቱ ከተነገረ ጊዜ ጀምሮ 300ሺህ ብር በጀት በመመደብ፤ ኮሚቴ በማቋቋምና ለ400 የሆስፒታሉ ሰራተኞች ሥልጠና በመስጠት እንዲሁም ጓንት፣ ጭንብልና የመፀዳጃ ቁሳቁሶችን በማሟላትና ለይቶ ማቆያ ክፍል በማዘጋጀት ለታካሚዎችም ሆነ ለአስታማሚዎች የሙቀት ልየታ ሥራ መጀመሩን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዶ/ር ቃለአብ ደረጀ ተናግረዋል፡፡
በሙቀት ልየታው እስካሁን ስድስት ሰዎች ተለይተው፣ በለይቶ ማቆያው ከተቀመጡ በኋላ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ማስረከባቸውን፤ ነገር ግን እስካሁን ከስድስቱ ሰዎች ውስጥ ቫይረሱ የተገኘበት ሰው ሪፖርት እንዳልተደረገላቸው ዶክተር ቃለአብ ተናግረዋል፡፡
ሀሌሉያ ጠቅላላ ሆስፒታል ወረርሽኙን ለመከላከል ከግልም ሆነ ከመንግስት ሆስፒታል ቀድሞ የሙቀት ልየታ ሥራ የጀመረ የግል ሆስፒታል ሲሆን፤ አሁን ካለው የወረርሽኙ አሳሳቢነት አንፃር ለሌሎችም ሆስፒታሎች አርአያ ለመሆን ወደ ሥራው መግባቱን ሜዲካል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ስለ ሆስፒታሉ የተሳሳተ መረጃ እየተሰራጨ ነው ያሉት ዶክተሩ፤ “የእኛ ሆስፒታል ከሙቀት ልየታ ስራ ውጭ አይሰራም፤ መርምሮ ፖዘቲቭ ኔጌቲቭ የሚለው መንግስት ብቻ ነው” ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል:: ሆስፒታሉ በአሁኑ ወቅት ለታካሚዎችም ሆነ ለአስታማሚዎች የሙቀት ልየታ፣ የእጅ ማስታጠብና መሰል አገልግሎቶችን በማቅረብ ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረገው ርብርብ የበኩሉን እየተወጣ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

Read 3571 times