Saturday, 21 March 2020 12:38

አፍሪካ ለከፋ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መዘጋጀት እንዳለባት ተገለፀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(13 votes)

   - ህብረተሰቡ ስርጭቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች ሊቆጠብ ይገባል
       - ለጤና ተቋማት የሚደርሱ ጥቆማዎች ከአቅም በላይ መሆናቸው እየተነገረ ነው
       - ቫይረሱ ከአልባሳትና ከጫማዎች ጋር ከቦታ ቦታ ሊዘዋወር ይችላል
       - መንገደኞች ትኩሳት የሚቀንሱ መድሃኒቶችን በመውሰድ ፍተሻ ሊያልፉ ይችላሉ ተብሏል
       - ወደ አገራችን አንመለስም ያሉ ቻይናውያን፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመቆየት ቪዛ እየጠየቁ ነው፡፡
       - የጀርመኑ ሎፍታንዛ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደረጋቸውን በረራዎች ሁሉ ለአንድ ወር አቋርጧል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየዕለቱ
           መንገደኞችን ወደ ጀርመን እያጓጓዘ ነው፡፡
       - የሠራዊቱ አባላት ላልተወሰኑ ጊዜ ከካምፕ ውጪ መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡
       - በዓለም ላይ ከ250ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል፡፡
             
            የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ባለፈው እሮብ በሰጡት መግለጫ፤ አፍሪካ ለከፋ ቀን መዘጋጀት አለባት ብለዋል፡፡  ከሃምሳአራቱ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ከ34 በላይ የሚሆኑት በቫይረሱ የተያዙባቸው ሰዎች መኖራቸውን ማረጋገጣቸውን የጠቀሱት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ አፍሪካ ከእንቅልፏ ልትነቃ ይገባል፤ በሌሎች አህጉራት ቫይረሱ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንዴት እንደጨመረ አይተናል:: ይህ ሁኔታም መጪው ጊዜ ለአፍሪካ የከፋ ሊሆን እንደሚችል አመላካች ነው ማለታቸውን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
በአገራችን የመጀመሪያው በቫይረሱ የተጠቃ ሰው መያዙ ከተገለፀበት ከመጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ዘጠኝ ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸውንና ቁጥራቸው ከ1700 የሚልቁት ደግሞ ከታማሚዎቹ ጋር ንኪኪ አላቸው በሚል ተጠርጥረው በለይቶ ማቆያ ውስጥ መግባታቸው ተገልጿል፡፡
ይህንን ተከትሎ በህብረተሰቡ ውስጥ የተፈጠረው መደናገጥና ስጋት በሽታውን ለመከላከል መደረግ የሚገባው ጥንቃቄ ላይ መዘናጋት እንደፈጠረ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ሃኪም ዶ/ር ብሩክ ተስፋዬ እንደሚናገሩት፤ ለበሽታው ስርጭት ዋነኛው መንገድ ጥግግት ወይም የሰዎች በአንድ ቦታ ላይ ተሰባስቦ መገኘት ሆኖ እያለ፤ በአንዳንድ ቦታዎች ህብረተሰቡ እንደ አልኮልና ሳኒታይዘር ያሉ የንፅህና መጠበቂያዎችን ለመግዛት እርስ በርሱ ተዛዝሎና እጅግ ተጠጋግቶ ሲውል እያየን ነው፡፡ ህብረተሰቡ የበሽታው ዋነኛ መተላለፊያ የሆኑትን ነገሮች በስፋት እያደረገ ለበሽታው መከላከል በተወሰነ ደረጀ ያግዛል የተባሉ ነገሮችን ለማግኘት ይህን ያህል ሊረባረብ አይገባም ብለዋል፡፡ አያይዘውም በእኛ አኗኗር ሁኔታና ቅርርባችን የበሽታው ስርጭት ፈጣን ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው ኀብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሲያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡  የጤና ሚኒስቴር በትናንትናው ዕለት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ዘጠኝ የደረሰ ሲሆን ከአዲሶቹ የቫይረሱ ተጠቂዎች መካከል አንደኛዋ ኢትዮጵያዊት መሆናቸውን አመልክቷል፡፡ ከመጀመሪያው የቫይረሱ ተጠቂ ጃፓናዊ ጋር ንክኪ እንደነበራቸው የተጠቀሱት የ44 ዐመቷ ጃፓናዊትም በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠው 3 አዳዲስ ሰዎች መካከል ይገኙበታል፡፡ ሌላዋ በቫይረሱ የተያዙት የ39 ዓመት አውስትራሊያዊት ሲሆኑ፤ መጋቢት 6 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የገቡ መሆናቸውም ታውቋል፡፡
የ85 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋዋ ቫይረሱ የተገኘባቸው ኢትዮጵያዊት  ከውጪ አገር የካቲት 23 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ሲሆን፤ እራሳቸውን አግልለው በህክምና ላይ  እንደነበሩም ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁለቱ አዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች፤ በጥሩ ጤንነት ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ የሰማንያ አምስት አመቷ ኢትዮጵያዊት ግን በጠና ህመም ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ምልክቶች ከጉንፋን ምልክቶች ጋር በጣም ተቀራራቢ መሆን ለጥቆማ ተቀባይ ተቋማት የሚደርሱ ጥቆማዎችን ከቁጥጥር በላይ እንዳደረጋቸው ተጠቁሟል፡፡
የውስጥ ደዌ ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ብሩክ ተስፋዬ እንደሚናገሩት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታየው እንቅስቃሴ ገደብ ሊበጅለትና ለበሽታው መስፋፋት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ እንዲቀንስ ሊደረግ ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች መስተንግዶ ክፍል ሠራተኛ የሆኑና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ሠራተኛ እንደሚገልፁት፤ በመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል ውስጥ ለገቢ መንገደኞች የሚደረገው ምርመራና የሙቀት ልኬት  አስተማማኝ ነው ሊባል አይችልም፤ ምክንያቱም የበሽታው ምልክት የሆነውን የሙቀት መጠን መጨመር ሊያስታግሱ የሚችሉ መድሃኒቶችን በመውሰድ ጤነኛ መስለው ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ መንገደኞች አሉ ብለዋል፡፡ ብዙውን ጊዜ በገቢ መንደገኞች ላይ ከሙቀት ልኬት የዘለለ ምርመራ የማይደረግ በመሆኑ የበሽታው ተጠቂ የሆኑ ሰዎች ትኩሳትን ሊያስታግሱ የሚችሉ መድሃኒቶችን እየወሰዱ ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ ሲሉም አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከሰላሳ አራት በላይ በሆኑ የአፍሪካ አገራት የተዳረሰውና ለአስራ ስድስት ሰዎች ህልፈት ምክንያት የሆነው የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት አገራት የሰዓት እላፊን ከማወጅ፣ ድንበራቸውን ከመዝጋትና የውጪ በረራዎችን ከማቆም ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡
የአለመ ጤና ድርጅት ይፋ ያደርገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ እስከ ትላንት ድረስ በአፍሪካ ከ600 በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 147 የሚሆኑት በበሽታው የተያዙት  ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ ነው፡፡ ግብፅ በበሽታው የተያዙ ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ የሚገኙባት አገር ሆናም ተመዝግባለች፡፡
ከ250 በላይ ግብጻውያን በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡ ደቡብ አፍሪካም ከ200 በላይ ዜጎቿ በበሽታው ተይዘውባታል፡፡
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፤ አቶ ታጉ ዘርጋው ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በኢንስቲቲዩቱ እስካሁን በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጡ ዘጠኝ ሰዎች መኖራቸውንና ማረጋገጢም ጠቅሰው ከእነዚህ ሰዎች ጋር ንኪኪ ይኖራቸዋል ተብሎ የሚገመቱ ሰዎችን የመለየቱ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ አያይዘው ህብረተሰቡ ከተለያዩ የእርስ በርስ መጠጋጋትና ትፍግፍግ በመጠበቅና እጆቹን በየጊዜው በመታጠብ፣ ለበሽታው ስርጭት መግታት የሚደረገውን ጥረት ሊያግዝ ይገባል ብለዋል፡፡
በአገሪቱ የሚታየው የበሽታ ስርጭት መጠን አነስተኛ መሆን በሽታው በአለም አቀፍ ደረጃ ካለው የስርጭት መጠን ጋር ባለመጣጣሙ ስጋት እንዳሳደረባቸው የሚናገሩት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የድንገተኛ ጽኑ ሕክምና ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ወልደሰንበት ዋጋ ነው፤ ምናልባት ሳይደርስባቸው የቀሩ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይጠረጥራሉ፡፡     
እንደ ህክምና ባለሙያዎች ገለፃ፤ በሽታው እጅግ በቀላሉና በዕለት ተዕለት ህይወታችን ውስጥ በምንጠቀምባቸው ቁሳቁሶች ሊዛመት ይችላል፡፡ የበር እጀታዎች፣ የምንጠቀምባቸው ስልኮች፣ የህንፃ መወጣጫ አሳንሰሮች ወዘተ ከፍተኛ የበሽታ አስተላላፊዎች ናቸው፤ ቫይረሱ በባህርይው በቁሶች ላይ ለቀናት የመቆየት እድል እንዳለው የተነገሩት ዶ/ር ብሩክ የምንለብሳቸው ልብሳችና መጫሚያዎቻችን ለበሽታው ስርጭት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡
እጃችንና ወደ አፍና አፍንጫችን ከማስጠጋታችን በፊት በሳሙናና በውሃ መታጠብ የሚገባን ሲሆን ከሰዎች ጋር የሚኖረንን መቀራረብ መቀናነስ የሰዎችን ልብስ ከመልበስ መታቀብም ይኖርብናል ብለዋል፡፡
በሽታውን ለመከላከል ተብለው የሚወሰዱ እንደ ነጭ ሽንኩርት፣ ሎሚና ዝንጅብል ያሉ ነገሮች በተለምዶ ታስበው የሚደረጉ ቢሆንም ለበሽታው መከላከል ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ እነዚህን ነገሮች መጠቀሙ የሚበረታታ ጉዳይ ነው ብለዋል ሃኪሙ፡፡
የአለም ጤና ድርጅት ትናንት ይፋ ያደረገው አንድ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የእጅ ስልካችን በሽታውን ለማስተላለፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል ዋነኛው በመሆኑ በየጊዜውና በየሰዓቱ ስልካችንን አልኮል በነካው ዋይፐር ማጽዳት እንደሚገባን አመልክቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም የአለም ጤና ድርጅት የኮሮና ባይረስ እንዲያዛቸው የሚጠራጠሩ ሰዎች ሀኪም ሳያማክሩ መድሀኒቶችን ከመውሰድ እንዲታቀቡ አሳስቦ በተለይ ኦቦፕሪፊን የተባለውን መድኃኒት ከመውሰድ ሊታቀቡ ይገባል ብሏል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ስጋትን ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው ቻይናውያን ወደ አገራቸው ባለመመለስ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመቆየት የሚያስችላቸውን ቪዛ ለማግኘት ጥያቄ እያቀረቡ ሲሆን የአንድ ወር የቆይታ ቪዛ እየተሰጣቸው መሆኑንም ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ከበሽታው መከሰት ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ በሚገኙ የውጪ አገር ዜጐች ላይ አግባብ ያልሆነ ጥቃት እየተፈፀመባቸው ነው ተብሏል፡፡
ከጥቃቶቹ መካከልም መሳደብ ማዋከብ፣ የትራንስፖርትና የሆቴል አገልግሎት መከልከል ይገኙባቸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጐቹ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቦ፣ በዜጐቹ ላይ እየተፈፀመ ያለው ጥቃት በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል ብሏል::
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደተለያዩ አገራት የሚያደርገውን በረራ እንደቀጠለ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በርካታ አገራት በራቸውን ዝግ እያደረጉ በመሆኑ የአየር መንገዱ መዳረሻዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ እንዲመጡ አድርጓቸዋል፡፡
የጀርመኑ የሉፍታንዛ አየር መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጋቸውን በረራዎች ካለፈው እሮብ ጀምሮ ያቋረጠ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጀርመን በየዕለቱ የሚያደርጋቸውን በረራዎች እንደቀጠለ ነው፡፡
የበሽታውን ስርጭት ለመግታት እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች መካከል ትምህርት ቤቶችን ለመጪዎቹ 15 ቀናት መዝጋት ፍርድ ቤቶችን ለ14 ቀናት እንዲዘጉ ማድረግ፣ የተለያዩ ስብሰባዎች እንዲሰረዙ ማድረግ፣ ሆስፒታሎችንና ማረሚያ ቤቶችን ከጠያቂዎች ነፃ ማድረግና መሰል እርምጃዎች ይገኙበታል፡፡
የመከላከያ ሰራዊትም ከካምፕ ውጪ፣ ያለ ስራ እንቅስቃሴ ማድረግን ያገደ ሲሆን የሠራዊቱ አባላት በካምፕ ውስጥ በመሆንና አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠብቁ የኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል አዳም መሐመድ አሳስበዋል፡፡
የበሽታውን ስርጭት ለመግታትና ህብረተሰቡ የግል ንፅህናውን በአግባቡ እንዲጠብቅ  የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚያግዙ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ሲሆን ከእነዚህ መካከልም በቅርቡ በማረሚያ ቤት ለሴት ታራሚዎች የተደረገው ድጋፍ የሚጠቀስ ነው፡፡ በኢፌድሪ ሴቶችና ሕፃናት ሚኒስቴር የተደረገውን ድጋፍ አስመልክቶ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ፈልሰን አቡዱላኢ ሲናገሩ፤ ብዙ ጊዜ እንዲዚህ አይነት ችግሮች በሚያጋጥሙበት ወቅት ማረሚያ ቤቶች የሚዘነጉ ሲሆን ችግሩ ግን በስፋት የሚያጋጥማቸውም እነዚህን አካባቢዎች ነው፡፡ እናም በአሁኑ ወቅት አስፈላጊ የሆኑ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርገናል ብለዋል፡፡
በኮልፌ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት ማሳደጊያ ውስጥም ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጋቸውን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ በዚህ ስፍራ ላይ የእጅ ማስታጠቢያዎችን ለማሳደጊያው በሰጡበት ወቅት ከህፃናቱ የተነገራቸውና ማስታጠቢያ ከምታመጡልን ውሃውን ብታመጡልን፤ ውሃ ሳይኖረን ማስታጠቢያ ምን ያደርግልናል የሚለው አስተያየታቸው በእጅጉ ልብ የሚነካ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
አሁንም የተለያዩ አካላትን በማስተባበርና ድጋፎችን በማሰባሰብ አስታዋሽ ለሌላቸውና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አካላት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
ኮሮና ቫይረስ ከተከሰተበት ካለፈው ታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከአሁን በዓለማችን ከ250ሺ በላይ  ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 10ሺዎቹ በዚሁ በሽታ ሳቢያ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ከዚሁ በሽታ መከሰት ጋር ተያይዞ አገራት የየራሳቸውን የመከላከያ እርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡
ከዘጠኝ ሺ በላይ ዜጐቿ በዚሁ በሽታ የተያዘባት ፈረንሳይ ከቤት ውጪ በሚገኙ ዜጐቿ ላይ የ138 ዩሮ ቅጣት ጥላለች፡፡ አንደም ዜጋዋ በበሽታው ያልተያዘባት ዚምባቤዌ  በበኩሉ ብሔራዊ የአደጋ መከላከል አዋጅ አውጃለች - ኬኒያ ደግሞ በመስጊዶችና ቤተ ክርስቲያናት አምልኮን ማካሄድ ከልክላለች፡፡


Read 13103 times