Saturday, 21 March 2020 12:32

የአራዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ብልሽት እና ምዝበራ መፍትሔ አላገኘም

Written by  ዓለማየሁ አንበሴ (ልዩ ሪፖርታዥ)
Rate this item
(3 votes)

 • ያለ አግባብ በሚፈጸሙ ከፍተኛ የግንባታ ክፍያዎች ደብሩ እየተመዘበረ እንደኾነ ተጠቆመ
       • ዋና አስተዳዳሪው እና ጸሐፊው ተነሥተው ሒሳቡ በውጭ ኦዲተር እንዲመረመር ተጠየቀ
       • ለዘገባ ወደ ደብሩ ጽ/ቤት የተላኩ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኞች ወከባና ዘለፋ ደርሶባቸዋል
            
               በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር (አራዳ ጊዮርጊስ)፣ አስተዳደራዊ ችግር እና የገንዘብ ምዝበራ እልባት እንዲሰጠው ተጠየቀ፡፡
በታሪካዊው ደብር በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የአስተዳደር ችግር እና የተደራጀ የገንዘብ ምዝበራ መኖሩን፣ በዚህም ሳቢያ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለመቀጠል እና በአግባቡ ከፍጻሜ ለማድረስ የሚያስችል የፋይናንስ ሀብቱ መሟጠጡን የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አባላት ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
በደብሩ አስተዳደር ላይ የታዩ እና ሊስተካከሉ ካልቻሉ ጉልሕ ችግሮች መካከል፥ ለአንድ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የአገልግሎት ዘመን፣ በቃለ ዐዋዲው የተደነገገው የጊዜ ገደብ አለመከበሩ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የተመረጠ የሰበካ ጉባኤ (ሥራ አስፈጻሚ)፣ በሥራ ላይ ሊቆይ የሚችለው እስከ ስድስት ዓመት ብቻ እንደኾነ የመተዳደሪያ ደንቡ ቢደነግግም፣ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ግን ያለምንም የምርጫ ሒደት፣ ሰባት ዓመት ከአራት ወራት በላይ በሥልጣን ላይ መዝለቁ ይጠቀሳል፡፡
ይህም ኾኖ፣ ያለው ሰበካ ጉባኤ በወጉ ተሰብስቦ እንደማይወስን፣ የደብሩ ጠቅላላ የሒሳብ እንቅስቃሴም በአንድ ሰው ቁጥጥር ሥር ወድቆ ከፍተኛ ውሎች አላግባብ እየተፈረሙ እና ከፍተኛ ክፍያዎች እየተከፈሉ እንደሚፈፀም ለአዲስ አድማስ የደረሰው የሰነድ ማስረጃ ያስረዳል፡፡
ከሚያዝያ 2010 እስከ ጥቅምት 2011 ዓ.ም. ድረስ ያለክፍያ ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት እና ያለአማካሪ ውሳኔ፣ ብር 13ሚሊዮን 778ሺሕ 469 መክፈሉ፤ በዚሁ ተመሳሳይ ወቅት፣ ያለሰበካ ጉባኤ እና የልማት ኮሚቴ ውሳኔ፣ ቃለ ጉባኤም ሳይያዝ፣ 24ሚሊዮን 298ሺሕ 143 ብር ለተቋራጭ ያለአግባብ እንደተከፈለ ታውቋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያትም፣ 9.4 ሚሊዮን ብር ያህል ብድር፣ ተገቢውን የፋይናንስ ሥርዓት ሳይከተል ለተቋራጮች ከመሰጠቱም በላይ፣ ብድሩ እስከ አሁንም እንዳልተመለሰ ተገልጿል፤ ተበዳሪው፥ መጀመሪያ የወሰደውን ብድር ሳይመልስ፣ በላይ በላዩ ተጨማሪ ብድር እንዲወስድ አላግባብ መፈቀዱም ተጠቁሟል፡፡
ከዚህም ባሻገር፣ በደብሩ በተገነቡ ሕንፃዎች ውስጥ ኪራይ ሳይከፍሉ ከአስተዳደሩ ሓላፊዎች ጋር በመግባባት የሚኖሩ፣ በነፃ ይዘው ሲያበቁ ለሦስተኛ ወገን የሚያከራዩ ግለሰቦች መኖራቸውን እንዲሁም፣ ተከራዮች ቤቶቹን ከተከራዩ በኋላ ለአንድ ዓመት በነፃ እንዲገለገሉባቸው በማድረግም፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለምዝበራ መጋለጧ ተመልክቷል፡፡
ይኸው፣ የደብሩ አስተዳደር ብልሹነት እና ምዝበራ እንዲታረም በየጊዜው ጥያቄ የሚያነሡ አካላት፣ ያለአግባብ ከሥራቸው እንደሚባረሩ እና ጥቃትም እንደሚፈጸምባቸው፣ አቤቱታ አቅራቢዎች ገልፀዋል፡፡
በሚመለከተው የበላይ አካል፣ የደብሩን አስተዳደር ለብልሽት እና ከፍተኛ ምዝበራ የዳረጉትን አለቃ እና ጸሐፊ ከቦታው በማንሣት እና ሕጋዊ የውጭ ኦዲተር በመሠየም፣ ባለፉት ዓመታት ሲደርስ የቆየው ጥፋት ተመርምሮ ርምጃ እንዲወሰድ፣ የሕንፃ ተቋራጩም ውላቸው ታግዶ ማጣራት እንዲደረግ በአጠቃላይ የታሪካዊውን የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደራዊ መዋቅር፣ በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት የማስተካከል ተግባር እንዲከናወን፣ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ጠይቀዋል፡፡
በደብሩ አስተዳደር ላይ የቀረበውን አቤቱታ አስመልክቶ አዲስ አድማስ የደብሩን ዋና አስተዳዳሪ መልአከ መንክራት ኀይሌ ኣብርሃ፣ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም በስልክ አነጋግሯል፡፡ በሰጡትም ምላሽ፤ “የቀረበው አቤቱታ ሁሉ ውሸት ነው፤” ካሉን በኋላ፣ “በአካል መጥታችኹ መነጋገር እንችላለን፤ ይህ የሚኾነው ግን ከፆሙ በኋላ ነው፤” ብለዋል፡፡
ከቆይታ በኋላ ግን፣ የደብሩ የልማት ኮሚቴ ሊቀ መንበር እንደኾኑ የገለጹልን አቶ ካሳሁን ግርማ ወደ ዝግጅት ክፍሉ ስልክ ደውለው፣ ወደ ቢሮአችን መጥታችኹ መነጋገር እንችላለን፤ በማለት ለማክሰኞ፣ መጋቢት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በቀጠሩን መሠረት፣ በደብሩ ጽ/ቤት ተገኝተን፣ ዋና አስተዳዳሪውን መልአከ መንክራት ኀይሌ ኣብርሃን ለማነጋገር ጥረት አድርገን ነበር:: ኾኖም፣ ዋና አስተዳዳሪውንና አቶ ካሳሁን ግርማን ጨምሮ “የሰበካ ጉባኤ አባላት ነን” ያሉ ግለሰቦች፣ የአቤቱታ አቅራቢዎችን ማንነት ጠይቀውን ከተረዱ በኋላ፣ “ፖለቲካዊ ዓላማ እና ብጥብጥ የመፍጠር ፍላጎት” እንዳላቸው በመግለጽ፣ ለጥያቄአችን ቀጥተኛ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይኾኑ ቀርተዋል፡፡
“ለዚህ ጉዳይ ምላሽ ልንሰጥ አንችልም፤ ጉዳዩ በሌላ አካል የተያዘ ነው፤” ብለውናል፡፡ በዚህ ብቻ ግን አላበቁም፡፡ ጉዳዩን ከመዘገብ እንድንታቀብ አስጠንቅቀው፣ በካሜራ ስንቀርጽ የቆየነውን የንግግራችንን እና የምስል ማስረጃዎች፣ አብረዋቸው በነበሩ ግለሰቦች በኃይል አሰርዘው፣ ከፍተኛ ወከባና ዘለፋ ካደረሱብን በኋላ ከጽ/ቤቱ ለቀን እንድንወጣ ተደርጓል፡፡
በአራዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ላይ የሚነሡና በማስረጃዎች የተደገፉ አቤቱታዎችን አስመልክቶ፣ አዲስ አድማስ ጉዳዩን በሚዛናዊነት ለማቅረብ ሲሞክር የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ኾኖም፣ የደብሩን ሓላፊዎች አስተያየት በሚጠይቅበት ጊዜ የሚሰጠው ምላሽ፣ ቀጥተኛ ግንኙነት የሌለው ማስፈራሪያ የተቀላቀለበትና ሥነ ምግባራዊነትም የጎደለው ሆኖ አግኝተነዋል:: እንዲያም ሆኖ ለአቤቱታ አቅራቢዎች ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ለማግኘት ጥረታችን ይቀጥላል::

Read 13796 times