Saturday, 21 March 2020 12:26

‹‹ኮሮና›› ቀጣዩን ሀገር አቀፍ ምርጫ ስጋት ላይ ጥሏል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

      በኢትዮጵያ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ስጋት በቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ እንደሚያስከትል የገለፁ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲዎች ጋር መክሮ ውሣኔ ሊያሳልፍበት ይገባል ብለዋል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ስጋትና በቀጣዩ ምርጫ እጣ ፈንታ ጉዳይ አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ድርጅቶች፤ የቫይረሱ ስጋት ምርጫውን ጥያቄ ምልክት ውስጥ የከተተ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋር ውይይትና ስብሰባ ማድረግ የማይችሉበት ሁኔታ መፈጠሩን ያመለከቱት የኦፌኮ ዋና ፀሐፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ፤ የቫይረሱ ስጋት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የቀጣዩን ምርጫ እንቅስቃሴ ጥያቄ ላይ ይጥለዋል ብለዋል፡፡
ይሄን ስጋት ተገንዝበው ምርጫ ቦርድ እና ባለድርሻ አካላት ተማክረውበት በጉዳዩ ላይ ውሣኔ ማሳለፍ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
የቫይረሱን ስርጭት ስጋት ለመቀነስ የተለያዩ የእንቅስቃሴ ገደቦች መኖራቸው የማይቀር መሆኑን ያስገነዘቡት የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ በበኩላቸው ፓርቲያቸው የቫይረሱን ስጋት ተከትሎ ከወዲሁ ስብሰባዎችን ማገዱን አስታውቀዋል፡፡ አስፈላጊ የሚሆኑ ስብሰባዎችም በተመጠነ የሰው ቁጥር እና ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረጉ ኢዜማ በመላ ሀገሪቱ ለሚገኘው መዋቅሩ መመሪያ ማስተላለፉንም አቶ ናትናኤል አስገንዝበዋል፡፡
ኢዜማ ከምንም በላይ ቅድሚያ ለዜጐች ጤንነት ነው ትኩረት የሚሰጠው ያሉት አቶ ናትናኤል በቫይረሱ ስጋት እንቅስቃሴዎችን መደገቡን ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
የቫይረሱ ስጋት አይሎ የስብሰባ ገደቦች በተጨማሪ ጊዜ የሚራዘሙ ከሆነም በቀጣዩ ምርጫ እጣ ፈንታ ጉዳይም በጋራ ተማክሮ መወሰን እንደሚገባ አቶ ናትናኤል ጠቁመዋል፡፡
የሁለት አመት የሽግግር ጊዜ ያስፈልጋል የሚል አቋም ያለው ኢዴፓ በበኩሉ የኮሮና ቫይረስ ስጋት በራሱም ተጨማሪ የምርጫውን መራዘም የግድ የሚል ነው ብሏል፡፡
የቫይረሱ ስጋት ምርጫውን ማስኬድ ከማያስችሉ ሁኔታዎች ተጨማሪ እንጂ ዋናው ጉዳይ አይሆንም ያሉት የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ አዳነ ታደሰ የቫይረሱ ስጋት በምርጫ ቦርድ ዝግጅት ላይም ተጽእኖው የጐላ ነው ብለዋል ምርጫ ቦርድ ገና 250ሺህ ያህል ምርጫ አስፈፃሚዎችን ሰብስቦ ማሰልጠን እንደሚጠበቅበት በመጠቆም፡፡
ለእነዚህ ምርጫ አስፈፃሚዎች እንዴት ነው ስልጠና ሊሰጥ የሚችለው ሲሉ የጠየቁት አቶ አዳነ የኮሮና ስጋቱ ፈጽሞ ውጤታማ ምርጫ ለማከናወን አያስችልም ብለዋል፡፡
የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበም በተመሳሳይ የቫይረሱ ስጋት በፖለቲካ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ገደብ የሚጥል በመሆኑ ሀገሪቱን በምርጫ ዝግጁ አያደርጋትም ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ፓርቲዎች በቫይረሱ ስጋት ምንም አይነት እንቅስቃሴ እያደረጉ አለመሆኑን በመጠቆምም ከወዲሁ ተጽእኖው እየጐላ መምጣቱን አስገንዝበዋል::
ፓርቲዎቹ ህብረተሰቡ በአሁኑ ወቅት ቫይረሱን በመግታት ጉዳይ ላይ ትኩረቱን እንዲያደርግም ፓርቲዎቹ አሳስበዋል፡፡
በዚሁ የኮሮና ቫይረስ ስጋት ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ያወጣው ኦፌኮ መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የወሰዳቸዋንና እየወሰደ ያለውን እርምጃ አድንቆ ህብረተሰቡም የራሱን ጥንቃቄዎች እንዲያደርግ መክሯል፡፡
ት/ቤቶች መዘጋታቸው፣ የብዙ ሰዎች ስብሰባ እንዳይደረጉ መንግስት መመሪያ ማውጣቱን ኦፌኮ ያበረታታል ያሉት አቶ ጥሩነህ መንግስት አሁን በኮማንድ ፖስት ስር ላሉ አካባቢዎች፣ ለታሠሩ ሰዎች ከበሽታ ተጠብቀው በህይወት የመኖር ሰብአዊ መብታቸውን ተገንዝቦ መረጃ የሚያገኙበትን አውታር ሊዘረጋ ይገባል ብለዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ በሀገር የመጣ ችግር ነው ያሉት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ አዳነ በበኩላቸው ፓርቲዎችም ሆኑ ሌሎች ይሄን በሽታ ለመግታት ያለ ልዩነት ከመንግስት ጐን መቆም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ህብረተሰቡም የራሱን የጥንቃቄ እርምጃዎች ሳይዘናጋ መውሰድ አለበት ብለዋል፡፡
ተመሳሳይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል በበኩላቸው ቫይረሱን ለመግታት የሁሉም ማህበረሰብ ርብርብ እንሚያስፈልግ ጠቁመው በተለይ በንግድ ላይ የተሠማሩ አካላት በወርሺኙ ምክንያት በሸቀጦች ላይ የሚደረጉ ጭማሪዎች ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ይገባል፤ በዚህ ሰአት ነው ዜጐች እርስ በእርስ መተሳሰብና መደጋገፍ የሚገባቸው ብለዋል፡፡
በቫይረሱ ወረርሽኝ ምክንያት ንግዳቸው የሚጐዳባቸው የቱሪስት፣ የጉዞ ድርጅቶች እና መሰል ተቋማትን ሁኔታም መንግስት ሊገነዘብ እንደሚገባ አቶ ናትናኤል አውስተዋል፡፡
ቫይረሱን ለመግታት ማንኛውም ዜጋ ሊረባረብ እንደሚገባው ያስገነዘቡት የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ በበኩላቸው መንግስትም ተገቢውን እርምጃዎች ሁሉ ወስዶ የዜጐቹን ህይወት መታደግ አለበት ብለዋል፡፡    


Read 1002 times