Saturday, 21 March 2020 12:26

መቄዶኒያ ለሚያስገነባው ህንፃ 102 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አገኘ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

    መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል እሁድ መጋቢት 6 ቀን 2012 ባካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርና ግብር ከ102 ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ2ሺህ በላይ አረጋውያን የአዕምሮ ህሙማን አቅመ ደካሞች፣ በማዕከሉ ሰብስቦ ድጋፍ እያደረገ የሚገኘው መቄዶንያ በቀጣይ በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ የተረጅዎችን ቁጥር ወደ 10ሺህ ለማሳደግ የተለያዩ የማስፋፊያ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑ ታውቋል፡፡
በዚህም ማዕከሉ 1.2 ቢሊዮን ብር የሚፈጅ ባለ 2 ቤዝመንት ግራውንድ ፕላስ 11 የሆነ ዘመናዊ የሆስፒታል ህንፃ እና የአረጋውያን መኖሪያ ህንፃ በማስገንባት ላይ ሲሆን ለህንፃው ማስገንቢያም የተለያዩ ድምሮችን እያሰባሰበ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
እሁድ እለት በተደረገው የህንፃ ግንባታ ድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብርም ባለሃብቶች ግለሰቦች እና በጐ አድራጊዎች እንዲሁም ተቋማት ከ102 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡
ቃል ከገቡት መካከልም ባለሀብቱ አቶ ወርቁ አይተነው 20 ሚሊዮን ብር፣ መድህን ኢንሹራንስ በካሽ 1 ሚሊዮን ብር እና የ5 ሚሊዮን ብር የመድህን ዋስትና፣ በአዲስ አስተዳደርና መልክ የተዋቀረው ሜቴክ 2 ሚሊዮን ብር፣ ደርባ ፋውንዴሽን 1 ሚሊዮን ብር፣ ኢስት አፍሪካ ትሬዲንግ 1 ሚሊዮን ብር፣ ፉጂ ፊልም 1.5 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የኤክስሬይ ድጋፍ፣ ፒኬ ኢንተርናሽናል 1 ሚሊዮን ብር፣ ሞሃ ለስላሳ 5 መቶ ሺህ ብር፣ ጊፍት ሪል ስቴት 5 መቶ ሺህ ብር፣ ዛይራይድ 250ሺህ ብር፣ ኢትዮ ስካር የ50ሺህ ብር ሼር፣ ሲምባ ኮንስትራክሽን ለሙሉ ህንፃው ሳኒቴሪ እና ኢንስታሌሽን አቅርቦት ቃል መግባታቸው ታውቋል፡፡
በእለቱ 22ሺህ ሰዎች 8161 ላይ Ok ብለው የመቄዶንያ አባል ሆነው በቀን 1 ብር እየረዱ ከመሆኑም ባሻገር በርካቶች ከ5 መቶ ብር እስከ 10ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ማዕከሉ በእለቱ ፕሮግራሙን ስፖንሰር ያደረገውን ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
መቄዶንያ በአሁኑ ሰአት ለአረጋውያን የምግብ፣ ህክምናና ዳይፐር ወጪ በወር 5 ሚሊዮን ብር እና ለህንፃው ማሠሪያ በየወሩ 10 ሚሊዮን ብር በድምሩ 15 ሚሊዮን ብር እንደሚይወጣም ተጠቁሟል፡፡
በ3600 ካ. ሜትር ቦታ ላይ የሚገነባው ባለ ቴራሱን ጨምሮ ባለ 15 ወለል ህንፃ ሲጠናቀቅ ለህክምና ብቻ 1200 አልጋዎች ያሉት፣ 5ሺህ ሰው የሚይዝ አዳራሽ፣ 120 መኪኖች ማቆሚያ ስፍራ ያለው እንደሆነም ተመልክቷል፡፡
የማዕከሉ መስራች ቢኒያም በለጠ (የክብር ዶክተር) በእለቱ ለነበረው የህብረተሰቡ ተሣትፎ ምስጋናቸውን አቅርበው ድጋፉ ተጠናቅሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡   


Read 11257 times