Saturday, 14 March 2020 15:44

የሜክሲኮ ሐውልት ዳግም ሕያው ሆነ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

     ‹‹ብዙ ሰው ሲናገር አድማጭ መኖር አለበት››

        በተለምዶ ሜክሲኮ አደባባይ እየተባለ በሚጠራው ቦታ ላይ የኢትዮጵያና የሜክሲኮን ወዳጅነት ለመግለጽ የቆመ ሀውልት ነበር፡፡ በ1950 ዓ.ም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ነበሩ ያሰሩት፡፡ ከ50 ዓመታት በላይ ለከተማው ውበት፣ ለሁለቱ አገራት ወዳጅነት መታሰቢያና የአካባቢው መጠሪያ ስም ሆኖ ለአምስት አስርት ዓመታት የዘለቀው ይህ ሀውልት፤ በ2003 ዓ.ም በልማት ምክንያት ፈርሶ ደብዛው ጠፍቶ ነበር፡፡ ይህ ቁጭት ከውስጡ ያልወጣው ገጣሚ ሰዓሊና ቀራፂ
ተባባሪ ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአለ የስነ ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ግቢ ውስጥ በኤክስፐርመንታል መልክ ሐውልቱን ሰርቶ ትላንት ረፋድ ላይ ተመርቋል፤ ውይይትም ተደርጐበታል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በሀውልቱ ሥራ ዙሪያ ከሰዓሊው ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡


             ትንሽ ጠፋ ብለሀል… ስራ በዝቶ ነው ወይስ ምንድን ነው?
ሰላም ነኝ… በጣም ሰላም ነኝ… አጠፋፌ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው፡፡ አንዳንዴ እኮ ዝም ማለት የሚያስፈልግበት ሰዓት አለ:: ብዙ ሰው ሲናገር የሚያዳምጥም መኖር አለበት… አይደለም እንዴ? አሁን ላይ ከአዳማጮቹ ወገን መሆን አስፈልጐኝ ነው… ትንሽ ጠፋ ያልኩት በተረፈ ግን ሰላም ነኝ፡፡
ሜክሲኮ አደባባይ ስለነበረውና በልማት ምክንያት ስለ ፈረሰው ሀውልት ጉዳይ ጥቂት አጫውተን?
ሀውልቱን እንግዲህ በኛ ግቢ ኤክስፐርመንታል ነው የምናደርገው፤ ምክንያቱም እኔም የማስተምረው እሱን ስለሆነ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሀውልቱን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለኢትዮጵያና ለሜክሲኮ ልዩ ወዳጅነት ውለታ ነው ያሰሩት:: ሜክሲኮ ሀውልት የተሰራው በ1950 ዓ.ም ሲሆን ሀውልቱ እንግዲህ እንደሚታወሰው ክብ ሆኖ ውሃና ጀልባ መሃሉ ላይ የነበረውና ፏፋቴም ጭምር ያካተተ፣ በጣም ማራኪ ሀውልት ነበር፡፡ ሜክሲኮ በጠላት ወረራ ማለትም በጣሊያንና ከዚያም በኋላ ባሉት ሁሉ የጠላት ወረራዎች ከኢትዮጵያ ጐን ሆና፣ ሀገራችን  በሊግ ኦፍ ኔሽን ውስጥ ወንበሯ እንዲከበርላት ካደረጉ አምስት አገራት አንዷ ነች፡፡ ሜክሲኮ በተጨማሪም አገሯ ላይ የኢትዮጵያ አደባባይ እንዲሁም በኃይለሥላሴ ስም ት/ቤትና መሰል ስያሜዎች በመስጠት የኢትዮጵያን ወዳጅነት አሳይታለች፡፡ ጃንሆይም እዛ ሄደው ከጐበኙ በኋላ እንደተመለሱ በፍጥነት ይህንን ሀውልት ስፖንሰር አድርገው ነው ያሰሩት:: ይህ ሀውልት እንደሚታወቀው፤ ሀምሌ 2003 ዓ.ም በመንገድ ስራው ምክንያት እንዲፈርስ ተደረገ፡፡
መቼም አንድ ታሪካዊ ሀውልት አይደለም ምንም ነገር ሲፈርስ፣ የአፈራረስና የአቆራረጥ ወግና ደርዝ አለው፡፡ ነገር ግን የተደረገው በጣም የሚያበሳጭ ነው፡፡ ሀውልቱ በጠራራ ፀሐይ፣ እንደ ጠላት ገንዘብ እየተደበደበ፣ ሜዳ ላይ እንዲጣልና ዱርዬዎች እያፈረሱ ብረቱን እንዲሸጡት ነው የተደረገው፡፡ እኔም በግርግር ሀውልቱ መሃል ከነበሩት ሶስት ጀልባዎች አንዷን ይዣት መጥቼ ነበር:: ሁለቱ እዛው ፈርሰዋል፡፡
እናም አንዷን ካየሁ በኋላ በሌላ አዲስ ማቴሪያል፣ ነገር ግን ያንን ጊዜ የሚያስታውስ አድርጌ፣ አዲስ የጥበብ ስራ ነው የሰራሁት፡፡
በርሊን ላይ የነበረው የቀድሞው የጀርመን የፓርላማ ጣሪያ (ዶም) በናዚ ቦምብ ነው የፈረሰው፡፡ አሁን ላይ የፓርላማው ዶም በመስታወት ተሰርቶ ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን በሁለት መንገድ ነው የቀድሞውን ሙሉ ለሙሉ ያልመለሱት፡፡ አንደኛ የፖርላማው ህንፃ አገልግሎት መስጠት ስላለበት መስታወት አደረጉት፡፡ ሁለተኛ መስተዋት የዘመኑ ቁስ ሆኖ፣ የአሁኑን ጊዜ ይናገራል፡፡ ነገር ግን የቀድሞውንም ትዝታ አላጣም፡፡ እናም ለሰዎች ሁልጊዜ በጥያቄ መልክ ትዝታን ያጭራል፡፡ ያንንም ጊዜ ያስታውሳል፤ የዘመኑንም ሁኔታ ይናገራል፡፡ ልክ እንደዛው ሁሉ እኔም የቀድሞውን ሙሉ በሙሉ ሳልሰራ፣ በአዲስ ማቴሪያል በአዲስ አቀራረብ ነው ለመስራት የሞከርኩት፡፡
ብቻህን ነው የሰራኸው ወይስ በስራው ላይ የተሳተፉ ሌሎችም ሰዓሊያን አሉ?
ሃሳቡን ያመጣሁት፣ ዲዛይኑንም የሰራሁት እኔ ነኝ፤ ስንሰራ ግን ከተማሪዎቼ ጋር በመሆን ነው፡፡
ሜክሲኮ አደባባይ ተመልሶ ቢቆም የሚል ምኞትና ናፍቆት አለህ?
አይ! አሁን እንደሱ የሚባል ነገር የለም፡፡ ያ ታሪክ… ያ ሁኔታ አልፏል በጊዜው ተደርጐ ሄዷል፡፡ ህይወት ይቀጥላል፤ አሁን ሌላ ታሪክ፤ ሌላ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እንደዚህ ነው የሚሰማኝ፡፡
በወጪ ደረጃስ ምን ያህል ገንዘብ ወጣበት?
ወጪውን በራሴ ገንዘብ ነው የሸፈንኩት 15 ወይም 16ሺህ ብር አካባቢ ወጥቶበታል፡፡
አሁንም በዩኒቨርስቲው እያስተማርክ ነው?
አዎ! አሁንም በማስተማር ላይ ነው ያለሁት፡፡
በፊት በጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ትጽፍ ነበር፡፡ አሁን ትተሃል፡፡ ምነው?
አሁን በጣም የተቀላቀለ ወቅት ነው፤ የመደማመጥም ሆነ የመከባበር ነገር ብዙ የለም፡፡ ሃሳብ ሲነሳ መሰዳደብ አለ:: የሚነሳው ሀሳብም ቢሆን ፍሬውም ገለባውም አንድ ላይ ነው፡፡ መድረኩም ሌቭል የለውም፤ ሁሉም ቦታ ሁሉም አለ፡፡ መስፈሪያው ተሰብሯል፡፡ ይህ ደሞ እርግጠኛ ነኝ አይቆይም፤ በዚሁም አይቀጥልም፡፡ ይመለሳል ይስተካከላል:: ያኔ አቧራው መሬት ሲይዝ፣ መስመር ሲለይና ሲረጋ፣ ከአድማጭነት ወደ ተሳትፎ እመለሳለሁ፡፡ አሁን የአገሪቱ ምስቅልቅል ሁኔታ እስኪለይለት በአድማጭነት ጐራ ነው ያለሁት፡፡ ቀደም ብዬም እንደነገርኩሽ ማለቴ ነው፡፡ በተረፈ በስራዬ ላይ ነኝ፤ በጥሩ ሁኔታ እገኛለሁ፡፡


Read 4473 times