Saturday, 14 March 2020 15:42

የአድማስ ትውስታ

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(3 votes)

        ሦስቱን የዘመናችን በሽታዎች ለመፈወስ የሚረዳ፣ የ‘ወርቄ’ ፍልስፍና
                              
        የዛሬ አራት መቶ ዓመት፣ ወጣቱ ተማሪ መፈላሰፍ ጀመረ ግን፣ የዘርዓያዕቆብ (ወርቄ) ፍልስፍና፣ ለዛሬም ያገለግላል።
        • • ጭፍን እምነትን ሳይሆን፤ እውነትንና አእምሮን የሚያከብር፤
         • መስዋዕትነትን ሳይሆን፣ ትጋትንና ሃብት ማፍራትን የሚያደንቅ፤
         • ዘረኝነትን ሳይሆን፣ የግል ማንነትንና ብቃትን የሚያወድስ ፈላስፋ
                     ዮሃንስ ሰ.


              በየጊዜው የሚፈጠሩ ውዝግቦችን ተመልከቱ። ከየአቅጣጫው የሚዥጎደጎዱ ንግግሮችና ፅሁፎች፣ መግባባትን ለመፍጠር የሚያግዙ ናቸው ወይስ ውዝግቡን የሚያባብሱ? ውይይት ወይም ክርክር ተብሎ ቢጀመር እንኳ፤ ውሎ ሳያድር፣ ወደ ስድብና ዛቻ ይሸጋገራል።
ደህና ጨዋ የሆኑ ሰዎች ድምፃቸው ይጠፋል። የስድብና የጭፍን ጥላቻ ፊታውራሪዎች ጎልተው ይወጣሉ። ቀሪው፣ በጭፍን ቲፎዞነት ተቧድኖ ያራግባል። ይሄ የሚሆነው አለምክንያት አይደለም።
ዘርዓያዕቆብ፣ ከ400 ዓመት በፊት፣ ኢትዮጵያን ሲያተራምስ የነበረውን ቀውስ ሲገልፅ፤ እውነትን ከሃሰት ለመለየት ከመጣር ይልቅ፣ “ሰው ሁሉ ወቃሽና እርስበርስ ተወቃቃሽ ሆኗል” ይላል። “ለመመርመር አይፈቅዱም። ከሰው የሰሙትን ያለምርምር ማመንን ያስቀድማሉ”።
በየጊዜው የሚከሰቱ የኑሮ ችግሮችንም ተመልከቱ። ከየአቅጣጫው አስተያየቶች ይሰነዘራሉ። ያንንም ተከትለው፣ የተለያዩ ድርጊቶች ይመጣሉ። ግን ምን ዋጋ አለው? መፍትሄ ሲሆኑ አይታዩም። ጭራሽ፣ ችግርን ያባብሳሉ፤ ወይም ተጨማሪ ችግር ይፈጥራሉ።
እንዲህ አዙሪቱ ያለማቋረጥ ሲደጋገም፤ “ምናልባት፣ ተሳስተን ይሆን?” ብሎ ማሰብ የለም።
“አስፈላጊ ነው” ብለን የመረጥነው የዘወትር ግብ፤ ጠቃሚ ሳይሆን አጥፊ ከሆነ፤... ወይም “ትክክለኛ ነው” ብለን የመረጥነው ልማዳዊው መንገድ፣ በተሳሳተ አቅጣጫ ወደ ገደል የሚያደርሰን ከሆነ፤... ቆም ብለን ማሰብ አይኖርብንም? ማሰብ ነበረብን።
ፈላስፋው ወርቄ እንደሚለው፤ ብዙ ሰው፤ ከራሱ ተፈጥሮ ጋር የማይስማማና የራሱን ሕይወት የሚጎዳ ተግባር ይፈፅማል። ይህም እንደ “መልካም ምግባር” ይቆጠርለታል፤ ይጨበጨብለታል። ሰዎች፣ እንዲህ ከተፈጥሮና ከሕይወት ጋር ፀብ የሚገጥሙት ለምንድነው? “መመርመርን አይሹም።... የሰውን ቃል ማመንን ይመርጣሉ” ብሏል - ወርቄ። ሃብት ከማፍራት ይልቅ ምናኔን፣ ከጋብቻ ይልቅ ምንኩስናን የምናስበልጥ ከሆነ፤ የሚጠቅመንን ነገር ለይተን ለማወቅ አልፈቀድንም ማለት ነው፤ ትክክለኛ የስኬት መንገድ ለመምረጥም ተስኖናል ማለት ነው። ይህም ብቻ አይደለም።
እውነትን ለመለየት፣ የሚጠቅመንን ለመምረጥ አለቻላችን ላይ ምን ይጨመርበታል?
የሰዎችን ማንነትና ክብር የምንለካበት ሚዛን ተበላሽቷል።
በተወላጅነት ወይም በዘር ሃረግ፣ የሰውን ማንነት መለካት ተገቢ እንዳልሆነ የሚገልፀው ወርቄ፤ እያንዳንዱ ሰው ባለ አእምሮ ነው፤ በተፈጥሮም የምግባሩ ባለቤት ነው ይላል። በተወላጅነት ወይም በጅምላ ሳይሆን፤ እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምርጫ ነው፤ ማንነቱን የሚወስነው። እውነተኛና በጎ ለመሆን የመምረጥ አቅም እንዳለው ሁሉ፤ “ክፉ እና ሐሰተኛ ለመሆንም መምረጥ ይችላል” ሲል ይገልፃል።
ስለዚህ፣ እያንዳንዱን ሰው መመዘን የሚገባን፤ ተግባሩን፣ ብቃቱንና ባሕርይውን በመመርመር እንጂ፤ በዘር እና በተወላጅነት በማቧደን አይደለም። ክርስትያን ወይም ሙስሊም በሚል የጅምላ ፍረጃም አይደለም።
የእኔነት ክብር ለመቀዳጀት ከፈለግንም፤ የእውነትንና የአእምሮን፣ የጥረትንና የስኬትን መንገድ በመምረጥ፤ ጠንካራ የብቃት ሰብዕናን መገንባት አለብን። አለበለዚያ፣ በባዶነት ቀውስ እንዋጣለን። ይህንን ባዶነት፣ በሐሰት ለመሙላት (ማለትም፣... በዘር፣ በቲፎዞ፣ በሃይማኖት በመቧደን፣ አንዳች ክብር ለማግኘት) የምናደርገው ሙከራ ሁሉ፤ ከንቱ ነው። ለምን? ምክንያቱም፤ “በሐሰት... የተፈጥሮ ስርዓትን ልናጠፋ አንችልም። እኛ ሐሰተኞቹ እንጠፋለን እንጂ” ይላል ወርቄ።
በሦስቱም የሰው ልጅ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ፤ (ሐሰትንና እውነትን ለይቶ የማወቅ፤ ኑሮን የሚያሳምርና የሚያጠፋ ተግባርን ለይቶ የማወቅ፤ የሚከበር እና የማይከበር ሰብዕናን ለይቶ የማወቅ ጉዳዮች ላይ)... ብልሽት ካለ፤... በየጊዜው የሚፈጠሩ ውዝግቦችና ችግሮች ላይ እኝኝ ማለት ለውጥ አያመጣም። እዚያው የቀውስ አዙሪት ነው የምንሽከረከረው። ከአዙሪት መውጣት የምንችለው፤ መሰረታዊዎቹን ሦስት ጉዳዮች ማስተካከል ከቻልን ብቻ ነው።   
ወርቄ (ዘርዓያዕቆብ)፣ ይህንን ትልቅ ስራ ለመሥራት ሞክሯል - የዛሬ 400 ዓመት፣ ገና ከወጣትነት እድሜው ጀምሮ።
ወጣቱ ፈላስፋ፣ ጅምር ምርመራ
በ15 ዓመቱ ገደማ፤ ቅኔንና ሰዋስውን ካጠና በኋላ፤ የሃይማኖት መጻሕፍት ትንታኔን ለአስር ዓመታት፣ እንደተማረ ይገልፃል። “የአገራችን [የኦርቶዶክስ እምነት] ምሁራን፣ መጻሕፍትን እንዴት እንደሚተነትኗቸው፤ ፈረንጆቹ [የካቶሊክ እምነት ምሁራንም] እንዴት እንደሚተነትኗቸው ለይቼ ተማርሁ። ትንታኔያቸው፣ ብዙውን ጊዜ ከአእምሮዬ ጋር አይስማማም። ነገር ግን ሐሳቤን ሁሉ በውስጤ ሸሽጌ ዝም አልሁ” ይላል - ገና የፍልስፍና ጫፍ ጫፉን መነካካት መጀመሩን ሲጠቁም።
ትምህርቱን አጠናቅቆ፣ በሙያው የላቀ መምህር ወደመሆን ሲሸጋገርም፤ ዋና ዋናዎቹን ጥያቄዎች መፈታተሽ ቢጀምርም፤ ገና ወደ ጥልቅ ምርመራ አልደረሰም ነበር። በወቅቱ ተስፋፍተው የነበሩ የተለያዩ የትንታኔ አቅጣጫዎችን፤ ለምርመራ በሚያመች መንገድ እያደራጃቸው ነበር። “መፃሕፍትን ሳስተምርና ስተነትን፣  ‘ፈረንጆቹ [የካቶሊክ ምሁራንም]... እንዲህ እና እንዲህ ይላሉ። ግብጻዊያን [የኦርቶዶክስ ምሁራን ደግሞ] እንዲህ እና እንዲህ ይላሉ’ ብዬ እናገራለሁ”:: ግን ነገሩን በዚህ ብቻ አያልፈውም፡፡
እንዲህ አይነት የትንታኔ ልዩነት መኖሩ ችግር የለውም - “እኛ ጥሩ እስከሆንን ድረስ” በማለትም ይመክራቸዋል።
ፈላስፋው ወርቄ፣ “የትንታኔ ልዩነት መኖሩ ችግር የለውም - እኛ ጥሩ እስከሆንን ድረስ”…ሲል
ምን ማለቱ ነው? “አእምሯችንን ተጠቅመን መመርመር እስከቻልን ድረስ፤ አእምሯችንን ተጠቅመን... እውነትንና ሐሰትን፣ ትክክልንና ስህተትን ለመለየት እስከቻልን ድረስ፣ ... ማለትም ጥሩ እስከሆንን ድረስ፤ የትንታኔ ልዩነቶች ቢያጋጥሙን ችግር የለውም። እንመረምራቸዋለን” ማለቱ ነው፡፡
ጥሩ መሆን ካልቻልን ግን፣ ችግር ይፈጠራል። እውነትንና ሐሰትን ለይተን ለማወቅ የማንመረምር ከሆነ፤ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፤ የሐሰትና የክፋት ተካፋይ ለመሆን እንገደዳለን። ያኔም፣ አንድ ብቻ ሳይሆን ብዙ ችግሮች ይፈጠራሉ፤ ይራባሉ፣ ይዋለዳሉ። የሐሰት ልጆች በማለት ይዘረዝራቸዋል - ፀብ፣ ስደት፣ ድብደባ፣ እስር፣ ግድያ። አገሪቱም፣ በጥላቻ የተመረዘች የአውሬ ምድር ትሆናለች። ችጋርና ረሃብ ወዘተ ይነግሳል።
ወርቄም አልቀረለትም። እንዳይታሰርና እንዳይገደል ሰግቶ፣ ተሰደደ። አእምሮ ሲደፈን ማንም ቢያሸንፍ ልዩነት የለውም
ያኔ፤ በአፄ ሱስንዮስ ዘመን፣ የካቶሊክ እምነትን የሚመሩ ፈረንጆች፣ የበላይነትን  አግኝተው ነበር፤ “ሃይማኖታችን እውነተኛና መልካም ናት።
 የግብፆች የኦርቶዶክስ እምነት ግን ሐሰት ናት፤ እውነተኛዋን ሃይማኖት ክደዋል፤ የፈጣሪ ጠላት ሆነዋል” በማለት ወርቄ ይሰብካሉ፤ ያሳድዳሉ። ግን ክፋት የነገሰው፣ በነሱ ላይ ብቻ አይደለም። በተቃራኒ አቅጣጫ ተቧደነው፣ በደል የሚፈፅሙ ግብፃዊያን የኦሮቶዶክስ መሪዎችም ነበሩ። ከሁሉም በላይ ክፋት የሰሩ የአገራችን ሰዎችም ጥቂት አይደሉም ይላል ወርቄ።
በየፊናቸው፤ “የእኛ ሃይማኖት እውነት ናት፤ የናንተ ሃይማኖት ሐሰት ናት” እያሉ ይሟገታሉ። ሙግቱ ግን መቋጫ የለውም። ወደ ስድብና ውግዘት፣ ወደ ዛቻና ወደ ፀብ፣ ከዚያም ወደለየለት ጦርነት ይሸጋገራል። ብዙ ሰውም፤ የአክራሪዎቹን መንገድ ተከትሎ፣ በየጎራው ተቧድኖ ይዘምታል። አገሪቱ ተተራመሰች፡፡
ቀድሞውንም፣ በወርቄ አእምሮ ውስጥ ሲዋልሉ የነበሩ ጥያቄዎች፤ አሁን ገንፍለው ወጡ።
“[ፈጣሪ]... በእርሱ ስም በደል ሲፈፀም፣ እንዴት በሰዎች ክፋት ላይ ዝም ይላል? ብዬ አሰብኩ” ይላል ወርቄ።
የሰዎችንም እብደት በመመልከት፣ “... ተፈጥሯቸው እንዴት እንዲህ ጠፋ?” ሲል ጠየቀ፤ አሰበ። ወዲያውኑ መልስ አላገኘም።
“ብዙ ባስብም፤ ነገሩን አልተገነዘብኩትም” ይላል ወርቄ። ቢሆንም፤ ማሰቡን አላቋረጠም።
ሰዎች አእምሯቸውን ለመጠቀም አይፈልጉምን?
የአይሁድም ሆነ የኦርቶዶክስ፣ የእስልምናም ሆነ የካቶሊክ እምነት ሰባኪዎች፤ በየፊናቸው “የኛ ሃይማኖት እውነተኛ፤ የናንተ ሐሰተኛ”... እያሉ ይናገራሉ። “ለኔ፣ ሃይማኖቴ እውነት እንደሚመስለኝ፤ ለሌላውም ሃይማኖቱ እውነት ይመስለዋል። ነገር ግን እውነት አንዲት ናት” በማለት አሰበ። ታዲያ እውነትን ከሐሰት ለይቶ ማወቅ አያስፈልግም? ያስፈልጋል። ግን ብዙ ሰዎች፣ ጥረት ሲያደርጉ አይታዩም።
ለምን?
“ምንም ሳያውቁ፣ የሚያውቁ እየመሰላቸው፣ የሚዋሹ ይመስለኛል” በማለት ለጥያቄዎቹ ምላሽ መስጠት ይጀምራል - ወርቄ። ሰዎች “በመሰለኝ” ብቻ እየዘለሉ በስሜት መነዳትን ከመረጡ፤ የሐሰት ተሸካሚ ከመሆን አያመልጡም።
ነገር ግን፤ ሰዎች ከውሸት ጋር የሚጣበቁበት ምክንያት፣ ይሄ ብቻ አይደለም።
“እውነትን ለማግኘት አይመራመሩም። ከቀደምት አባቶቻቸው በሰሙት ነገር ልባቸው ረግቷል። እውነትም ቢሆን ሐሰት አልመረመሩም” በማለት ወርቄ ሁለተኛውን ምክንያት ገልጿል። ጭራሽ፣ እውነትና እውቀት፣ በዘር የሚወረስ አስመስለው የሚቧደኑም አሉ። “እውነተኛ ትምህርት፣ ፅድቅ፣ በረከት የተሰጠው፤ ለአባቶቻችን፣ ለኛ ዘር፣ ለእገሌ ሕዝብ ነው” በማለት በጭፍን ይተማመናሉ። በአእምሮ ምትክ፣ በጭፍን የዘረኝነት ስሜት መንጋጋትን ይመርጣሉ፡፡ ሌላ ምክንያትም አለ፡፡
“የሃጥአንና የሐሳውያን መምህራን” ይሁንታን በመናፈቅ፤ የሐሰተኞችን ሰብከት፣ ያለምርመራ አምነው የሚቀበሉ አሉ- ጭፍን እማኞች:: ከመመርመርና እውነትን ከማወቅ ይልቅ፣ በመንጋው ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት የሚመርጡም አሉ - ከህዝብ ወይም ከጐረቤት ተለዋዋጭ ስሜት ጋር የሚነፍሱ፡፡
ሰዎች እንዲህ በጭፍን ስሜት እየተነዱ ለማመን፣ ከወላጆች፣ ከጎረቤት ወይም ከሰባኪ የሰሙትን ነገር ያለምርመራ ለማመን የሚቸኩሉት ለምን ይሆን?  
“በአውቶማቲክ” ወይም “በአንዳች ምትሃት”፤ እውነትን ማወቅ አይቻልም። ጥረትን ይጠይቃል። በትጋት መመርመር ያስፈልጋል። በሌላ አነጋገር፤ “ትልቅ ሥራ” ነው።
እውነትን ለማወቅ የሚፈልግ ሰው፤ ይህንን ትልቅ ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆን ይገባዋል  ይላል - ወርቄ።
Saturday, 06 February 2016 11:03


Read 418 times