Saturday, 14 March 2020 15:42

የአበረ አያሌው “ፍርድ እና እርድ”

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

 ሳሙኤል ጆንሰን የሼክስፒርን የግጥም ሥራዎች ዘመን አይሽሬነት በተነተነበት ጽሑፍ፣ ያብከነከነው - ቅሬታ ድምፀት አለ:: ያም ቅሬታ ብዙ ጊዜ ሰዎች ለአድናቆት ወደ ሕያዋን ድንኳን ሳይሆን ወደ ሙታን መቃብር ጐራ እንላለን የሚል ነው፡፡ “All perhaps are more willing for hounour past than present excellence” ይላል፡፡ ይህ ጉዳይ በኛም ማህበረሰብ የበለጠና የከፋ ይመስለኛል፡፡ በየትኛውም የስራ መስክ፣ የጥበብ ሠፈር የሞተ ሰው “ታላቅ!” ነው ማለት አይከብደንም፡፡ ይህንን ስንል ሚዛን ላይ አስቀምጠን አይመስለኝም፡፡ አሁንማ በግልቡ የማህበራዊ ሚዲያ ጩኸትና ጋጋታ ቀሽሙን ታላቅ፣ ታላቁ ምንም “ወደ ማድረግ ዘመቻ” ግልቢያ የተጀመረ ይመስላል፡፡
ብዙ ጊዜ የተሻለ ሥራ የሚሠሩ ሰዎች ከበሮ አያስደበድቡም፤ አዋጅ አያስነግሩም፤ “እንዲህ ነኝ” ብለው አምባር አያጠልቁም፤ ስካርቭ አይጠመጥሙም፤ በራሳቸውና በስራቸው ይተማመናሉ፡፡
እኛ ሀገር እንኳ ባለው ጠባብ የጥበብ ክበብ ውስጥ የተባ ብዕር ያላቸው ሲንጫጩ አናይም፣ ስከን ብለው እንደ ልባም ጅረት በዝግታ ይፈስሳሉ፡፡ ጩኸታቸው ሀገር አይረብሽም፡፡ ይሁንና የዚህ ዓይነቶቹ ባለተ ተሰጥዖዎች በዚህ ነጣቂ ዘመን ውስጥ ግርግር የሚወድደው ተደራሲ፣ ማዕበል ላይ የተንጠለጠለው ጋዜጠኛ ተጨምሮ ትኩረት ላያገኙ ይችላሉ፡፡ ይሁንና የሰከነኑ አንባቢያን ግን አጥምደው ሥራዎቻቸውን ያገኛሉ፡፡ ያደንቃሉም!
በዚህ ዘመን ግጥም እንደ ጐርፍ ሲወርድ፣ ከገለባውና ከሞገዱ መካከል አልፎ አልፎ ደረጃቸውን የጠበቁ ስራዎች መኖራቸው ገሀድ ነው፡፡ አንባቢም የተሻሉትን እንዳቅሙ አጥምዶ ይይዛል፤ አጣጥሞ የሚያነብበው ደግሞ የወደዳቸውን ደጋግሞ ያነብላቸዋል፤ በዜማና ሃሳባቸው ነፍሱን ያስፈነጥዛል፡፡
በቅርብ ዓመታት ከታተሙት የግጥም መጻሕፍት ውስጥ የአበረ አያሌው “ፍርድ እና እርድ” ሸጋ ስራ ተብለው ከሚመደቡት ነው፡፡ ይህ ሥራ የሆሄ ስነጽሑፍ ሽልማት የመጀመሪያው ዙር ተሸላሚ መሆኑ አንድ እመርታ ቢሆንም፣ ገጣሚው አደባባይ ላይ ስለማይታይ፣ ዓይን አፋር ስለሆነ፣ ወይም በዚህ ጥበብ ላይ የሚሠሩ ጋዜጠኞች የግምገማ አቅም ማነስና የአደባባይ ድምጾች የሰውን ጫጫታ ተከትለው የሚሠሩ መሆን የስራውን ከፍታ የመጠነ ትኩረት እንዳያገኝ አድርጎታል፡፡ ስለዚህ የገጣሚው ስምና ስራ የጥበቡን አቅም ያህል አልተተመነም፡፡
መጽሐፉ ከሽፋን ውበት ጀምሮ የገፆቹ ብዛት፣ የስርዐተ ነጥቡ አጠቃቀም፣ የሙሉ መጽሐፉ ግጥሞች በጭብጥ መከፋፈል፣ የሀሳቡ ልዕቀት፣ ዜማውና አሠነኛኘቱ ሁሉ መልካም የሚባል ነው፡፡ ጭብጦቹም እምነትና እውነት፣ እግዜር፣ የሽንቁር እይታ፣ ፍቅር፣ ሀገር፣ ሕዝብ በሚል የተከፋፈሉ ሲሆን የገፆቹ ብዛት 208 ነው:: ወደ ውስጥ ስንዘልቅ “እውነትና እምነት” እንዲሁም “እግዜር” የሚሉት ግጥሞቹ ባብዛኛው የሃይማኖቱን ሠፈር የሚያስሱና የዘመኑን ችግሮች የሚዳስሱ ብሩሾች ናቸው:: አንዳንዶቹም በከፉ ሰዎች ትውልዱ ላይ የተተከሉትን እሾሆች ለመንቀል የተዘጋጁ ወረንጦዎች ናቸው፡፡ የሕይወትና የዘመን ንጽጽር፣ የእግዜርና የሰው ሙግት አለበት:: የካድሬ ባርኔጣና የቄስ ጥምጥም፤ የፓስተር ቃልና የካድሬ ጩኸት ወዘተ ይደመጡበታል፡፡ በጥቅሉ የፖለቲካው ቅርሻት፣ የኢኮኖሚው ጡንቻ፣ የማህበረሰቡ የዋለለ ስነ ልቡና፣ የሃይማኖቱ ፍንክትክት ሁሉ ይታይባቸዋል፡፡
ለምሣሌ ከሃይማኖቱ ሠፈር ግጥሞች “ማነው የተሾሙ?” እንዲህ ይላል፡፡
ከቤተምነት ደጃፍ
መላክ ይሁን ሰይጣን - ምኑን
የማላውቀው
“ስብከት ነው” እያለ ጩኸቱን ለቀቀው፡፡
***
“ያዕቆብ ከልጅነት ትግል ነው ዐመሉ
ከግዜሩ ጋር እንኳ - ስንተዜ ታገሉ!
አንደዜ አጭበርብሮ - በረከት ሲቀማ
ደሞ በኩር ሊሆን - ወንድሙን ሲያስማማ
ሲለው ከመላክ ጋር - ሌሊት ሙሉ ታግሎ
ካልባረከው በቀር - እንዳይለቀው ምሎ
ያዕቆብ ጽኑ ታጋይ - እግዜርን የረታ
በፀሎት አይደለም - ትግል ነው - እምቢታ”
እያለ ይሰብካል - ለገባ ለወጣ
መጽሐፍ ቢጠቅስም - በኔ አእምሮ ግን
ሰይጣን ነው የመጣ!
ጥቅል ሃሳቡ ማሸነፍ የሚቻለው በእምቢታ ሳይሆን “በፍቅር ነው” የሚል ነው፡፡ ሰባኪው ግን ያዕቆብን ይዞት የሕዝቡን ልብ እያሳመፀ፣ ከፀሎት ይልቅ፣ አመጽን እየቀሰቀሰ ነው፡፡ የካህን ስራ ሳይሆን የካድሬን ቦታ ይዞ እያገለገለ ነው፡፡ ገጣሚው ንቡር ጠቃሽ ዘይቤን ይዞ፣ የእምነቱን ጐራ  እየተቸ ነው፡፡
በቤት አመታትም ጠንካራ አናባቢ ባላቸወ ድምፆች፣ የውበቱን ሞገድ ከፍ አድርጐታል፡፡ ሰባቱ ስንኞች የበረታ ድምጽ እንዲኖራቸውና ዜማቸው የነፍስ አንጀት ውስጥ እንዲገባ አሽሞንሙኖታል፡፡
ይህ የግጥም ሃሳብ ያድጋል፤ እዚህ ያምታታው ሰባኪ ግቡ ዐመጽ መቀስቀስ ብቻ አይደለም፤ የመጨረሻው ባህር የራሱን ኪስ መሙላት ነው፡፡ ነቃፊው ካህን መለስ ብሎ ደግሞ ሼክስፒር “ሰይጣን ለዐመሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል” እንዳለው፣ ከቅዱስ መጽሐፍ ጠቅሶ “አትተቹኝ፣ አትናገሩኝ” ይላል፡፡
ከቤተምነቱ ደጅ - ወደ ቤተ እምነተ ውስጥ ሲገባ፡-
“የሚያበራይ በሬ - አፉ አይታሠርም
“በተቀባ ነቢይ” አፍ አይከፈትም…
ለሀገር መድሀኒት - ችግር የሚያደርቅ
ከተቀባው ነቢይ ከኔ ነው የሚፈልቅ
እግዚሃር ለሾመኝ - ለሰጠኝም ወንጌል
ማስፋፊያ እንዲሆነኝ - ብሩን ወደዚህ በል!
ከላይ ያየናቸው ስንኞች የሃሳቡን ግብ ይመታሉ፤ ቤት አመታታቸው ግን ያን ያህል የሚጥም አይደለም፡፡ ይሁንና በቤተ ክርስቲያን ክበብ፣ በአምላክ ስም የሚደረገውን የዘመኑን ሽቀላ አምርሮ ይተቻል! በአንድ ሌላ ግጥሙ ደግሞ “የህማም ምስጋና”  “የፃዲቅ ቅዳሴ” የሚለው ግጥምም፤ በሕይወት ትይዩ ገፆች አንዱ ሲስቅ ሌላው ሲያለቅስ የሚያሳየውን የሕይወት ፍርደ-ገምድልነት፣ የአምላክ መንገድ ፈተናና ነውጥን ይጐተጉታል፡፡
ልበ ሰባራው - እንዲህ ይላል፡-
“ለስዕለቴ መልስ እንዲሆነኝ - የሰጠኸኝ
አንድ ልጄ
ድሮ ሞቷል የማስገባው - አንድ ስለት
የለም በጄ
“ታማ ነበር” - ያልኩህ ሚስቴ የልጇ ሞት
ልቧን ሰብሮት
የሷም በድን - ከልጄ ጋር እኔን ሸሽቶ
ሄዷል አብሮት፡፡
ለነገሩ ታውቀዋለህ - ላስታውስህ ብዬ ነበር
ስለሁሉ ንገሥ ጌታ - ግነን - ግነን፣ ክበር
- ክበር፡፡
ይህ የሚያምም ግጥም ነው፡፡ ሰውየው በስዕለት ያገኘው ልጁ ሞታለች፤ ታማለች ብሎ የፀለየለት ሚስቱም በልጇ ሀዘን ልቧ ተሰብሮ አልፋለች፡፡ ይህን ሁሉ ሕመም ለፈጣሪ ሊነግረው አስቦ ነበር፤ በኋላ ግን ሁሉን እንደሚያውቅ አሰበና ተወው!!” የሚጠዘጥዘው ሕመም ደግሞ፣ መጽሐፉ “በሁሉ አመስግኑ” የሚለውን ቃል ለመፈፀም እዚህ እንባው ላይ ተዘፍዝፎ፣ የተሰፋው ቋንጣ፣ የትዝታው አበባ ላይ ቆሞ “ክበር ተመስገን” ሊል ይሞክራል…
ይህ የሕይወት አንደኛው ጥቁር ድንኳን ሲሆን፤ በዚያው የእምነት ሠፈር ደግሞ ሌላ ድንኳን ተጥሎ እልልታው ከአድማስ አድማስ ያስተጋባል፡፡ የእግዚአብሔር ጆሮ ይህንን ሰቀቀንና ፈንጠዝያ ያደምጣል፤ ይቀበላል!!
አ-መ-ስ-ግ-ኑ…
እዳችሁን ለከፈለ - ጤናችሁን ለጠበቀ…
ፍሰሀችሁን ላበዛ - ክፉዋችሁን ላራቀ…
አ-መ-ስ-ግ-ኑ
ጐተራችሁን ለሞላ ደስታችሁን ለጨመረ
ቤታችሁን ለባረከ - ታሪካችሁን ለቀየረ…
አብረሃም እቅፍ ውስጥ የነበረውን አልዐዛር የሚባል ሰው ታሪክና በውሃ ጥም በሲዖል ተቃጥሎ፣ “ምላሴ ነደደ ጠብታ ውሃ” እያለ የሚጮኸውን ሰው ሁለት ዓለም ይመስላል፡፡ ልዩነቱ ያ ከሞት በኋላ ሲሆን፣ ይህ በምድር ሕይወት መሆኑ ነው፡፡
“ፍቅር” ከሚለው ርዕስ ስር ካሉት ግጥሞች “ኪዳን - አልባ ኪዳን” ከሚለው ጥቂት እንመልከት፡--
በፌሽታ ዘመኑ - ባማረ ጉባዔ - በዜማ ታጅቦ
ወይ ሜዳ ተንጋሎ - በለምለም ሳርና
በአበቦች ታጅቦ
እሷን ብቻ እያየ - ዓለሙን ረስቶ - በገባው
ውድ ቃል
“እንደ’ዜ” እያለ በተኛበት አልጋ - ሺህ ጊዜ
ይወድቃል!!
ሰው ነገረኛ ነው…” ሚስትህስ?...” እያለ
ይሳለቅባታል
ከሚስቱ ተኝቶ - ቃሉን ካስታወሰ -
ዘመናት ሆኖታል!!
(“እና ቃሉ የታል?”)
   “ካንቺ የተሻለች - እንስትን እስካገኝ -
    ዓይኔም እስኪበራ
    በውርነት ቃሌ “ዘላለም” ያንቺ ነኝ -
    ነይ ፍቅር እንስራ”
    የምትል አንድምታ
    ኪዳን መሀል ገብታ
    ዛሬም ከላይ ሰፈር አልጋ እየሰበረ
   ኪዳኑን በትጋት ሲፈጽም - ነበረ፡፡
ተራኪው በሰውየውና በቃል ኪዳኑ፣ በመሀላውና በኪዳኑ መንሸራተቱ ላይ እያላገጠ ነው፡፡ ነገሩ ስላቅ ነው፤ ሽሙጥ ነው፡፡ ፍቅር ያሳወረው ዐይኑ - ሲበራ፣ በብርሃን ያገኘውን እየያዘ በአልጋ መውደቅ ሆነ፡፡ “መኝታው ንፁህ ነው” የሚባልለት ትዳር፤ በዝሙት ጨቅይቶ፣ ጐጆዋቸው መከርፋቱን - በዜማ - አጫወተን፡፡ “ግብረ ይሁዳ” የሚለው ግጥምም - በእንቶኔ ዘይቤ - ከፈጣሪ ጋር -ሙግት የሚገጥም ነው፡፡ ምናልባት ከዘማሪው እምባቆም ጋር የሚመሳሰል፤ “ይህ ሲሆን የታለህ?” ዐይነት ይመስላል፡፡
ምን ትላለህ አንተ?
ሃይማኖት ሲዋለድ ፍቅር እንዴት ሞተ?
ከቀዳሾችህ ልብ የድሆችን ልቅሶ ማነው
የጐተተ?
እግዜር ሆይ አደራ!
አንተም እንደነሱ - ጥያቄ ለማምለጥ
ሰይጣንን አትጥራ፤
በሰበብ አስባቡ “መልስ ነኝ” እያለ እሱም
እንዳይኮራ፡፡
ሃሳቡ የዚህን ዘመን የሃይማኖት ቁጥር መብዛትና የቅድስና ማጣት ዕድፈትን የሚሞግት ነው፡፡ ሃይማኖት በቁጥር ሲጨምር “ፍቅር” የሚባለው እሴት ጠፍቷል፡፡ የሃይማኖት መሪዎች ደግሞ ልባቸው ውስጥ ደሀ የለም፤ ይልቅስ ሃብት ተሰግስጐበታል፡፡ ብር የሞላበት ልብ፤ ደሀ የለም ይልና ስለዚህ ጉዳይ ፈጣሪን ይጠይቃል፤ ጠይቆ ዝም አይልም፤ “የሰይጣን ስራ ነው አትበለኝ” ይላል፤ በዚህ በመጠራቱ ሰይጣን ክብር እንዳይሰማው!
እስካሁን የጠቀስኳቸው ግጥሞች የሞራል ውድቀት ላይ ያነጣጠሩ ናቸው፡፡ ግን ሰባኪዎች አይደሉም፡፡ የሞራል ግጥሞች ከስብከትነት ከወጡ፣ በእጅጉ የሚደነቅ ዐይነት ክብር የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ ቀጥታ መስበክና ማስተማር እንጂ በውበት ከልለህ ቁምነገር ሹክ ማለት የተሻለ ከፍታ ተደርጐ እንደሚቆጠር የዘርፉ ምሁራን ምስክርነት አለው፡፡
ገጣሚው አበረ አያሌው፤ ቋንቋው በዘይቤ ያበደ ባይሆንም በሰከኑ ቃላት ሸጋ አድርጐ ጽፏል፡፡ በዚያ ላይ የአብዛኛዎቹ ግጥሞቹ ዘውግ፣ የቃላት ምርጫና ልዕቀት የማይጠይቅ ነው፡፡ ቅርፃዊ መዋቅሮቹ በእጅጉ የተሳኩና በቡድንና በሃሳብ ቅርጽ ተመሳሳይነት፣ በቤት አመታት፣ በምጣኔ ስልትና በስንኞች ቅንጣት የተሻለ አደረጃጀት ያላቸው ናቸው፡፡ የቤት አመታት ስልቱ ሀሀ - ሀሀ የሚባለው ነው፡፡ ይህ አመታት እንዳይሰለች፤ በጥንቃቄ ከተጠቀሙበት የሚያዋጣ ነው፡፡ የሀለ ቤት አመታት ስልትን ያህል ግን የደመቀና የተከበረ አይደለም፡፡
የአበረ ግጥሞች እንደ ሀገራችን የዘመኑ ግጥሞች ስሜት ንክር ግላዊ አይደሉም፡፡ ተራኪ ግጥሞችን ይዘው፤ ከፍ ባለ ሃሳብ፣ የዘመኑን እምነት፣ ፍልስፍናና ስነልቡናዊ ድንኳኖች የሚነቀንቁ ናቸው፡፡ በቁመናም ከአጫጭር ግጥሞች ይልቅ ወደ ረዣዥሞቹ ያደላል፡፡
ይሁንና በመጽሐፉ ውስጥ “ብትንትን” በሚለው ርዕስ ስር የተካተቱት ግጥሞች ቢቀሩ እመርጣለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ግጥሞች አጨራረስ ላይ ያለባቸው ድክመት ቢታረም ከዚህ የበለጠ ያምሩ ነበር፡፡ ለምሳሌ “የሰንበሌጥ አጥር” ሁለት ስንኞች፣ “ሕይወት በየፈርጁ” የመጨረሻዋ ስንኝ፤ “የሀገሬ ልጅ የእምነቴ ልጅ” የሚለው አጨራረሱ በተለይ “ገብርኤል በጥፊ” የሚለው ከማማው ላይ አውርዶታል፡፡
ስርዓተ ነጥብ አጠቃቀሙ ጥንቃቄ የተሞላበትና እስካሁን ከታተሙት መጻሕፍት በእጅጉ የላቀ ነው፡፡ ይሁንና በተለይ መገደፍ የሌለባቸውን ሁሉ በመግደፍ የተፈጠሩ ችግሮች አሉ፡፡
ሳጠቃልል ግን አበረ አያሌው፣ በዘመናችን በፈረጠመ የጥበብ ጡንቻ፣ ተነሱ ከምንላቸው በጣት የሚቆጠሩ ኃያላን መካከል - “ዋነኞቹ” ከሚባሉት ነው፡፡ በዚሁ አካሄድ፣ በተሻለ ጥንቃቄና ንባብ ከታገዘ፣ ዘመን ተሻጋሪ ግጥሞች ያኖርልናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በዘመኔ ከተፈጠሩት አንዱ ስለሆነም መጽሐፉ ዘወትር ከራስጌዬና ጠረጴዛዬ አይርቅም!...ሌላ እስኪደግመን ደጉን እመኝለታለሁ፡፡  Read 601 times