Saturday, 14 March 2020 15:38

ጃማይካዊቷ ጃህ 9፤ ዛሬ በቪላ ቨርዴ ሙዚቃዋን ታቀርባለች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

    - “ኖት ቱ ሰልፍ” የተሰኘ አዲስ አልበሟን በአዲስ አበባ ታስመርቃለች
          - “ኢትዮጵያ ለሙዚቃ ሕይወቴ መነሻና መድረሻ ናት” ብላለች
                
            ጃማይካዊቷ የሬጌ ሙዚቃ ድምፃዊ፤ ገጣሚና የዜማ ደራሲ ጃናይን ኤልዛቤት ከኒንግሃም (ጃህ 9) ባለፈው ሐሙስ ኢትዮጵያ የገባች ሲሆን በቆይታዋም ‹ዮጋ ኦን ደብ›› እንደምታስተዋውቅ አዲስ የዘፈን አልበሟን እንደምታስመርቅና የሙዚቃ ኮንሰርት እንደምታቀርብ ተገልጿል፡፡ ዛሬ ምሽት በቪላቨርዴ ልዩ የሬጌ ሙዚቃ ኮንሰርት የምታቀርበው ድምፃዊቷ፤ ትናንት በማሪዬት ኤክዚክቲቭ አፓርትመንት ከ50 በላይ ለሚሆኑ የዮጋ ስፖርተኞች ልዩ ስልጠና ሰጥታለች፡፡  “ኢትዮጵያ ለሙዚቃ ህይወቴ መነሻና መድረሻ ናት” የምትለው ድምፃዊቷ፤ “የኢትዮጵያን ታሪክ በማወቅ ራሴን አግኝቻለሁ” ብላለች፡፡
በጃማይካ “የእውነት ድምፅ” እየተባለች የምትደነቀው ሙዚቀኛዋ፤ በአውሮፓ፤ በሰሜን አሜሪካ፤ በካረቢያንና በአፍሪካ አገራት የሙዚቃ አድናቂዎቿ ዘንድ ‹‹ብላክ ማጂክ›› በሚል ትወደሳለች፡፡ በመድረክ የአዘፋፈን ስታይሏና በአስደናቂ የድምፅ ቅላፄዎቿ ብዙዎችን እንደምትመስጥ ይነገርላታል፡፡ የዘፈን ግጥሞቿ ሰላማዊ ድባብን የሚፈጥሩ፤ የላቁ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ እንዲሁም በበጎ አስተሳሰብና መነቃቃት የሚሞሉ ናቸው ይላሉ የሙዚቃ ባለሙያዎች፡፡
“Note to self” የተሰኘው አዲሱ አልበሟ የዛሬ ወር መተዋወቅ የጀመረ ሲሆን ሰሞኑን ለዓለም ገበያ በይፋ በአዲስ አበባ ይመረቃል ተብሏል፡፡  አልበሙን ለማስተዋወቅ  በወጣው ዘጋቢ ፊልም ላይ “ራስን የማወቅ፣ ራስን የመረዳትና ራስን የማስተማር ሂደት ነው” ትላለች ጃህ 9- ስለ አልበሟ ስትገልጽ::
ገና በ6 ዓመቷ የቤተ ክርስቲያን ዝማሬ የጀመረችው ድምፃዊቷ፤ ዘማሪነቷ ለሙዚቃ ሕይወቷ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ትገልጻለች፡፡ በትምህርት ቤት ቆይታዋም በተለያዩ የዝማሬ ቡድኖች ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ነበረች፡፡ ቀስ በቀስም የሬጌ፤ ጃዝ፤ ክላሲክና ሌሎች የሙዚቃ ዘውጐች  ፍቅር እያደረባት እንደመጣች ታስታውሳለች:: ከአንጋፋና ታዋቂ የራስ ተፈርያን ማህበረሰብ  አባላት ጋር የመገናኘት ዕድል ማግኘቷ አያሌ እድሎች እንደፈጠሩላት ትናገራለች፡፡ በተለይም ስለ ህይወት፤ ስለ ራስተፈርያኒዝም እምነት፤ ስለ አፍሪካ፤ ስለ ኢትዮጵያና ጥቁር ህዝቦች ብዙ እውቀት መቅሰሟን በመግለጽ::
የወጣቱን ትውልድ ብሩህ መጪ ዘመን በመስበክ የምትታወቀው ሙዚቀኛዋ፤ በኪነ ጥበባዊ ዘመቻ አገርን የመገንባት ቁርጠኝነት እንዳላት ይነገርላታል፡፡ በሙዚቃዋ አንድነትና ፍቅርን ለዓለም ማድረስ ጥልቅ ፍላጐቷ ነው፡፡
‹‹ኒው ኔም›› የተሰኘው የበኩር አልበሟ በ2016 (እኤአ) ለአድማጭ የበቃው ሲሆን አልበሙን የሰራላት በዳንስሆል የሙዚቃ ስልት ፈር - ቀዳጅነቱ የሚታወቀው ፕሮዱዩሰር ሮሪ ስቶን ነው፡፡ አልበሙ በመንፈሳዊ ህይወቷና በጥበብ ፍልስፍናዋ ያዳበረችውን ተመክሮ የሚያንፀባርቅ መሆኑን ዘፋኟ ትገልጻለች፡፡  በዓመቱ ደግሞ ‹‹9›› የተሰኘውን ሁለተኛ አልበሟን ያወጣች ሲሆን አልበሙ  በኬንያ ናይሮቢ ነው የተመረቀው፡፡  ሦስተኛ ሥራዋ የስቱዲዮ አልበም ሳይሆን፤ “ሪሚክስ” ነው፡፡ ‹‹ኢን ዘ ሚደስት ኦፍ ዘ ስቶርም›› የሚል ስያሜ የተሰጠውን ይሄን ሥራ፤ ከዕውቁ ዲጄና ፕሮዱዩሰር ማድ ፕሮፌሰር ጋር መስራቷ ታውቋል፡፡
ለ15 ዓመታት ገደማ በዘለቀው የሙዚቃ ህይወቷ፣ በአጠቃላይ ከ30 በላይ ስራዎችን ለጆሮ ማድረሷን ጃህ 9 ተናግራለች፡፡ ከ2013 እ.ኤ.አ አንስቶ “ዘ ደብ ትሪትመንት” ከተሰኘው የሙዚቃ ባንዷ ጋር በአውሮፓና በአሜሪካ በተካሄዱ ትላልቅ የሬጌ ሙዚቃ ፌስቲቫሎች ላይ ተሳትፋለች፡፡ ባለፉት 5 ዓመታት በዓለም ዙሪያ ከ80 በላይ ኮንሰርቶችን አቅርባለች፡፡ ከእነዚህም መካከል በካናዳ፤ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶችና ከተሞች፤ በእንግሊዝ ፤ ፈረንሳይ፤ ጀርመንና ስዊዘርላንድ  ያቀረበቻቸው ደማቅ የሙዚቃ ድግሶች ይጠቀሳሉ፡፡



Read 1101 times