Saturday, 14 March 2020 13:32

ጃህ 9 “ዮጋን በደብ” ኢትዮጵያ ላይ አስተዋወቀች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 ጃማይካዊቷ የሬጌ ድምፃዊ፣ ገጣሚ፣ የዜማ ደራሲና የዩጋ አሰልጣኝ ጃናይን ካኒንግሃም በትናንትናው ዕለት በማሪዮት ኤክሲክዩቲቭ አፓርትመንትስ ‹‹ዮጋን በደብ›› Yoga on Dub በኢትዮጵያ አስተዋውቃለች፡፡  ከ50 በላይ የዮጋ ስፖርተኞችን ያሳተፈው የትውውቅ መርሐግብሩን ለሁለት ሰዓታት በልዩ የአሰለጣጠን ትኩረት የመራችው ጃህ9 ስትሆን   ከክሁል ሆሊስቲክ ማዕከል ጋር በመተባበር ያዘጋጀችው ነበር፡፡ በዮጋ ስፖርተኛነት እና አሰልጣኝነት ከ15 ዓመታት በላይ ልምድ ያላት ጃህ 9፤  በ‹‹ዮጋ ኦን ደብ›› ያካበተችውን ልምድ ኢትዮጵያ ውስጥ በማስተዋወቋ ደስተኛ ነች፡፡
ሰሞኑን ከዚሁ ዓለም አቀፍ ንቅናቄዋ በተገናኘ በኬንያ ቆይታ የነበራት ጃህ 9፤ ከአዌይ አፍሪካ ቱርስ ጋር በመተባበር የተመረጠ የዮጋ ስፖርተኞች ቡድንን ለተወሰኑ ቀናት አስተምራለች፡፡ የዮጋ ስልጠናዎቹንም በሞባባሳ እና ናይሮቢ ከተሞች እንዲሁም ላሙ እና ዲያኒ ባህርዳርቻዎች ላይ ተካሂደዋል፡፡
ጃህ 9 በዮጋ አሰልጣኝነቷ በመላው ዓለም ትታወቃለች፡፡  በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እና የስራ ፈቃድም ተሰጥቷታል፡፡ ኬሜቲክ፤ አሽታንጋ እና ሊዮንጋር በተሰኙ የዮጋ ፍልስፍናዎች  ከፍተኛ እውቀትና ልምድ አላት፡፡ በተለይ በምድረ አፍሪካ በተለይም በጥንታዊ የግብፅ ስልጣኔ ተፈጥሯል በሚባለው ኬሚቲክ  ዮጋ ተክናበታለች፡፡  ኬሚቲክ ዮጋ ከሙዚቃ ፍልስፍናዋ ጋር ያዋሀደችው ልዩ ክህሎቷ መሆኑንና በአሰልጣኝነት  ከፍተኛ ደረጃ መድረሷንም የስራ ልምዷ ይገልፃል፡፡ ጃህ 9 እንደምትናገረው በዮጋ ፍልስፍናዋ የቀሰመችው ትምህርት እና ያዳበረችው እውቀት ሙዚቃዋን እያጎለበተው ሄዷል፡፡ የዮጋ እንቅስቃሴን ከሙዚቃ በማዋሃድ የምትሰራበትን አጋጣሚ ሁሉ መንፈስን የሚያድስ ብላ ትገልፀዋለች፡፡
ለጃናይን ካኒንግሃም የዮጋ እውቀቷ ከመንፈሳዊ ጥንካሬ እና የአካል ብቃት ባሻገር ሙዚቃዋን አዲስ መልክ እንድትፈጥርለት እና በአዲስ ስያሜ ፈርቀዳጅ  እንድትሆን አድርጓታል፡፡  ‹‹ዮጋ ኦን ደብ›› በሚባል ስያሜ ሙዚቃና ዮጋ ስፖርትን ያዋሃደ ልዩ መዝናኛ   ስልት ፈጥራለች፡፡  ዮጋ ኦን ደብ በሚል ስያሜ በየጊዜው በዩቲውብ ገጿ ለዓለም የምታቀርባቸው ቪዲዮዎች አሉ፡፡ ጃናይን ኦንላይን በተባለው ድረገጽ ደግሞ ሰፊ መረጃዎችን ታሰራጫለች፡፡ በሌላ በኩል ሰሞኑን በኬንያ ናይሮቢና እና ሞምባሳ ከተሞች እንዲሁም በአዲስ አበባ እንዳደረገችው ሁሉ ‹‹ዮጋ ኦን ደብ››ን እንድታሰለጥን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በመጋበዝ እየሠራች ነው፡፡ በግዙፍ የሬጌ ሙዚቃ ዝግጅቶች እና ፌስቲቫሎች ላይ ሙዚቃዋን እየተጫወተች ጎን ለጎን  የምታቀርባቸው የዮጋ ትርኢቶች ተወዳጅ እየሆኑላት መጥተዋል፡፡
‹‹ዮጋ ኦን ደብ›› ተፈጥሯዊ ይዘት ያለው ልዩ መዝናኛ እንዲሁም  ስፖርትና ሬጌ ሙዚቃን ያጣመረ ነው፡፡ በሁሉም ፆታዎች፤ የእድሜ ደረጃዎች፤ የአኗኗር ዘይቤዎች እና ባህሎች መከወን ይቻላል፡፡ በጭንቀት፤ በስቃይ ለሚገኙ ሁሉ ፍቱን መድሃኒት የሆነ ፍልስፍና እና የአኗኗር ዘይቤ ነው፡፡
 ዮጋ ፍልስፍናዋን ከሙዚቃ ጋር በማስተሳሰር በመላው ዓለም ማስተዋወቋ እንደሚያኮራት  ጃህ 9 ተናግራለች፡፡  በተለይ በሬጌ የሙዚቃ ስልት አፍቃሪዎች ዘንድ ስፖርቱ እና ፍልስፍናው እንዲዘወትር ያላትን ፍላጎት በኬንያ እና በኢትዮጵያ መቀጠሏ የራስተፈርያኒዝም እምነት እና አስተሳሰብ ከዮጋ ፍልስፍና ጋር ተመሳሳይ ይዘት እንዳላቸው ታስረዳለች፡፡   ‹‹ዮጋ ኦን ደብ›› ለመልካም አኗኗር፤ በፀጋ ለተሞላ ህይወት እና ስነምግባር፤ ቁምነገረኛነት ለማብዛት፤  ብልሃተኛ ለመሆን፤ ጥሩ እና ቀና መንፈስ ለመጎናፀፍ ያግዛል፡፡ አተነፋፈስን በማስተካከል  ጤናማ ያደርጋል፡፡ ብሩህ አዕምሮን በመፍጠር አካላዊ ቅልጥፍና  ይሰጣል፡፡
በጥንታዊቷ ህንድ የተጀመረው ዮጋ በሂንዲይዝም እና ቡዲሁዝም እምነቶች ውስጥ የታለያዩ ስርዓቶች አሉት፡፡  ከህንድ ተነስቶ በዓለም ዙርያ ሲስፋፋ የተለያዩ የአሰራር ዘዬዎች ተፈጥረውለታል፡፡ ፓወር ዮጋ፤ ካርማ ዮጋ፤ ባክቲ ዮጋ፤ ኩንደሊን ዮጋ፤ ጃንጋ ዮጋ የሚሉ ስያሜዎች ያሏቸው ይጠቀሳሉ፡፡ ልዩነታቸው በእንቅስቃሴው ወቅት ትኩረት በሚሰጠው የሰውነት አካል፤ ወይም በሚሰራው ሰው ፍላጎት ሊወሰን ይችላል፡፡  ዮጋ ከመንፈሳዊ አካል ጋር ውህደት ለመፍጠር ፤ ለመረጋጋት፤ አንድ ነገር ላይ ለማተኮር እና ራስን ለማዳመጥ ይረዳል፡፡ ደብ እና ሬጌ ደብ የሙዚቃ ስልቶች የሚያጅቡትና የሚዋሃዱት  እንቅስቃሴ ሲሆን ደግሞ አዝናኝነቱ ይጨምራል፡፡
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በመላው ዓለም ሚሊዮኖች ዮጋን የሚሰሩት ራስን ከማረጋጋት እና መንፈስን ነፃ ከማድረግ ጋር አያይዘው ነው፡፡ ዮጋ አዕምሮን ፀጥ በማድረግ እና በማዝናናት ሊረዳ ይችላል፡፡ ጡንቻዎችንም ያፍታታል፡፡ ዮጋን በመስራት ከሚገኙ ጠቀሜታዎች መካከል  ድብርትን ማጥፋት፤ ጥሩ የሰውነት ቅርፅ እና አካላዊ ጥንካሬን መስጠት፤ የአዕምሮ ንቃትን ማዳበር፤ የተስተካከለ የልብ ምት፤ አተነፋፈስና የደም ዝውውር ማግኘት ይጠቀሳሉ፡፡
ዮጋ በዓለም ዙርያ ከ60 በላይ አገራት በሚገኙ ህዝቦች ይዘወተራል፡፡ በየዓመቱ  ከ80 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚንቀሳቀስበት መስክ ነው፡፡  በዮጋ ስፖርት ኢንዱስትሪ ትልቁን የገበያ ድርሻ የሚወስደውና በዓመት እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀስበው በሰሜን አሜሪካ ነው፡፡ በህንድ ደግሞ ዮጋ ከ50 በላይ ፍልስፍናዎች እና የእውቀት ደረጃዎች ያሉትና  በከፍተኛ ደረጃ ያደገ ነው፡፡ ከዚያም በሌሎች ኤሽያ አገራት፤ በሰሜን አሜሪካ፤ በአውሮፓ በመካከለኛው ምስራቅ በደቡብ አሜሪካም ተስፋፍቷል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየዓመቱ ጁን  21 የዓለም ዮጋ ቀን ብሎ የሚያከብር ሲሆን ዘንድሮ 10ኛ ዓመቱን እንደያዘ ታውቋል፡፡ ዓለም አቀፉ የዮጋ ፌደሬሽን በዓለም ዙርያ ከ300 ሚሊዮን በላይ አባላትን በማቀፍ የሚሰራ ነው፡፡ ከዮጋ ማሰልጠኛ ማዕከሎች ባሻገር በመፅሄቶች ልዩ አምድ፤ በቴሌቭዥን ቻናሎች ዋና መርሃ ግብር ፤ እንዲሁም በተለያዩ የመዝናኛ ዝግጅቶች አጃቢነት ዮጋ የስርጭት ሽፋን የሚያገኝ ነው፡፡  ጃህ 9 እና ዘ ደብ ትሪትመንት የተባለው ባንዷ ‹‹ዮጋ ኦን ደብ›› በማለት  ከሬጌ ሙዚቃ ፌስቲቫሎች ጋር እያስተሳሰሩት ይገኛሉ፡፡

Read 1389 times