“ዘ ፖዬተሪ ፓረንሰስ” ፕሮግራሙን ባለፈው ማክሰኞ የጀመረ ሲሆን ከተለያዩ አገራት የተጋበዙ ገጣሚዎች በየራሳቸው ቋንቋ የጻፏቸው 100ሺ ግጥሞች በለንደን በምትገኘው ሳውዝ ባንክ በሄሊኮፕተር ከሰማይ ላይ ተበትነዋል፡፡ ከኦሎምፒያኑ ጋር ተያይዞ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የግጥም ጉባዔ ላይ የተገኙ ገጣሚዎች ብዛት በታሪክ የመጀመሪያው የተባለ ሲሆን ለአንድ ሳምንት የሚቆየው ዝግጅቱ ገጣሚያን በቋንቋቸው ግጥማቸውን የሚያቀርቡበት፤ ዎርክሾፖችና የተለያዩ ውይይቶች የሚያካሂዱበት እንደሆነ ታውቋል፡፡ በ”ፖዬተሪ ፓረንስስ” ድረገፅ ቃለ ምልልስ ያደረገው በዕውቀቱ ስዩም፤ በፌስቲቫሉ መሳተፉ የመበረታታት ምንጭ እንደሚሆነው ገልፆ፣ የተለያዩ ቋንቋዎችና ባህሎች ካሏቸው ገጣሚዎች ጋር መገናኘት በአንድ ሳምንት ዓለምን እንደማሰስ ነው ብሏል፡፡