Saturday, 14 March 2020 11:27

የአቶ ልደቱ የ2 ዓመት የሽግግር መንግስት ምን ይመስላል?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

   505 አባላት ባሉት “ሸንጐ” የሚመራ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው ያዘጋጁት ፕሮፖዛል ጠቁመዋል፡፡
የሁለት ዓመት ቆይታ የሚኖረውና ከገዥው ፓርቲ በሚመረጥ ጠ/ሚኒስትር የሚመራ “ህዳሴ የእርቅና የአንድነት የሽግግር መንግስት” የሚል ስያሜ ያለው የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ሃሳብ ያቀረቡት አቶ ልደቱ፤ የ0ዚህ የሽግግር መንግስት መቋቋም ለሀገሪቱ ቀጣይ ህልውና ወሳኝ ሚና እንዳለው ያስረዳሉ፡፡
ለነሐሴ የታቀደው አገራዊ ምርጫ ሊካሄድ እንደማይገባውና ከዚያ ይልቅ የሀገሪቱን ህልውና ሊያስቀጥል የሚችለውን የሽግግር መንግስት ማስቀደም እንደሚገባ ያሳስባሉ - ባቀረቡት ፕሮፖዛል፡፡
ምርጫ ሊካሄድ የማይገባበትን ምክንያት ሲያስረዱም፤ ሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ምርጫን ለማድረግ የሚያስችል ሁለንተናዊ ቁመና ላይ አለመድረሷን ይተነትናሉ፡፡ አምስት ዋነኛ ምክንያቶችን በማንሳትም ምርጫው ይራዘም ዘንድ ይጠይቃሉ አቶ - ልደቱ፡፡
ለውጡ የተሳካ አልሆነም የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሱት ፖለቲከኛው፤ ለውጡ ባልተሳካበት  በሀገሪቱ እርቀ ሠላምና መግባባት ባልተፈጠረበት ሁኔታ ወደ ምርጫ ተጣድፎ መግባቱ ሀገሪቱን ወደ ባሰ ብጥብጥና ትርምስ ማስገባት ነው ይላሉ፡፡ ይህ እንዳይሆንም በመጀመሪያ “እኔ አሸጋግራችኋለሁ” የሚባለው ጉዳይ ቀርቶ ከምርጫው በፊት ሀገሪቱን ወደ ብሔራዊ እርቅና መግባባት እንዲሁም መዋቅራዊ ችግሮችን ወደሚያስተካክል የሽግግር ሂደት መግባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ከምርጫው በፊት መቅደም አለበት ብለው የሚያነሱት ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ ሃገሪቱን የበለጠ ለአደጋ የሚዳርጉ ስንጥቆችን የመጠገን ጉዳይ ነው፡፡
በኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን መካከል፣ በቀድሞ አዴፓ እና ህወኃት፣ በብልጽግና እና ህወኃት  በብልጽግና እና በተቃዋሚ ፓርቲዎች በሻዕቢያና በህወኃት በአዲስ አበባ ከተማ ይገባኛል ጥያቄ አቅራቢዎች በፌደራል መንግስትና የክልልነት ጥያቄ በሚያቀርቡ ወገኖች፣ እስካሁን ትጥቃቸውን ባልፈቱ የኦሮሞ ልሂቃንና መንግስት መካከል ያሉ ዘርፈ ብዙ የቅራኔ ስንጥቆች በእርቀ ሠላምና ብሔራዊ መግባባት ሳይጠገኑ ወደ ምርጫ መግባት ወደ ጦርነት አውድማ እንጂ ወደ ዲሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር ሊወስደን አይችልም ባይ ናቸው - አቶ ልደቱ፡፡
“ከምርጫ በፊት ጠንካራ ሀገራዊ እርቅና ብሔራዊ መግባባት መፍጠር አለብን” የሚሉት ፖለቲከኛው፤ “አብዛኛው መገናኛ ብዙሃንና ማህበራዊ ሚዲያዎች የጽንፈኛ ብሔርተኝነት ማራመጃ በሆኑበት በአሁኑ ወቅት የሚካሄድ ምርጫ ሀገሪቱን ወደባሰ ብጥብጥና ትርምስ እንጂ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር አይወስዳትም” ይላሉ፡፡
አቶ ልደቱ በዚህ ጽሑፋቸው፤ በሀገሪቱ የህግ የበላይነት አለመኖሩን የሚያመላክቱ ማስረጃዎችን በመጥቀስም ምርጫው አሁን መካሄድ አይገባውም የሚሉበትን አራተኛ ምክንያትም ያቀርባሉ፡፡
በአምስተኛ ደረጃ የሚያነሱት ጉዳይ ሀገሪቱ ለምርጫ ያለመዘጋጀቷን በአሁኑ ወቅት መንግስት፣ ገዥው ፓርቲ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ መራጩ ህዝብ እንዲሁም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ የህሊናም ሆነ የድርጅት ዝግጁነት የላቸውም ሲሉ በማስረጃዎ አስደግፈው ይሞግታሉ:: ብልጽግና ከተመሠረተ ገና አጭር ጊዜ እንደሆነውና ካድሬዎቹን እንኳ በሚገባ ስለ ፕሮግራሙ አሠልጥኖ አለማጠናቀቁን፣ ጠቅላላ ጉባኤ አለማድረጉን፣ አብዛኛው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገና ህጋዊ እውቅና ለማግኘት 10ሺህ ፊርማ የማሠባሰብ ሂደት ላይ መሆናቸውንና 90 በመቶ የሚሆኑት የፖለቲካ ድርጅቶች ምርጫው እንዲራዘም ፍላጐት ያላቸው መሆኑን በመጠቆም በነሐሴ ይካሄዳል የተባለው ምርጫ ጊዜውን የጠበቀ አይደለም ይላሉ - ፖለቲከኛው፡፡
በምርጫ ቦርድ በኩልም የምርጫ አስፈፃሚዎች ዝግጅት አለመጀመሩን፣ ምርጫ ማስፈፀሚያ የሚሆኑ ህጐችን አውጥቶ አለማጠናቀቁን በመጥቀስ በቦርዱ በኩልም ዝግጁነት ይጐድላል የሚሉት አቶ ልደቱ፤ ህዝቡም በነፃ ህሊና በፓርቲዎች መካከል ያለን ልዩነት በአግባቡ መዝኖ ድምጽ ለመስጠት ይቅርና ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የማይችልበት የህልውና ፈተና እንደተጋረጠበት ይገልፃሉ፡፡ ከምርጫው ይልቅ ስለ ሀገር ሠላምና የሀገሪቱ ህልውና የሚጨነቅበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ በዚህም የተነሳ ለምርጫው ህሊናዊ ዝግጅት የለውም ይላሉ ፖለቲከኛው፡፡
በእነዚህ ሁሉ ውጥንቅጦች መሃል ሆኖ ምርጫው የግድ በነሐሴ ይካሄድ ከተባለም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ግምታዊ ሁነቶችንም (ሴናርዮ) ያስቀምጣሉ፡፡ በመጀመሪያው ግምታቸው “ምርጫው ተካሂዶ በአንፃራዊነት ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ሆኖ ይከናወናል፤ ይህ ከሆነ የኛ ግምት ስህተት ይሆናል፤ “ግምታችን ስህተት ከሆነም ከማንም በላይ ደስተኞች እንሆናለን” ይላሉ ሁለተኛው ግምታቸው ደግሞ ምርጫው ተካሂዶ ግጭት፣ አፈናና ማጭበርበር የተሞላበት ሆኖ ይጠናቀቃል የሚል ሲሆን፤ በዚህም ውጤት መሠረት የለውጥ ሃይል የተባለው ወገን የለየለት አምባገነን ሆኖ በስልጣን ይቀጥላል፤ ይህ በመሆኑ ባንደሰትም ያን ያህል አንከፋም፤ ምክንያቱም ቢያንስ ሀገሪቱን ከመፍረስ ያድናታል” አቶ ልደቱ፡፡
በሦስተኛ ደረጃ የሚያስቀምጡት ግምት፤ በምርጫው እለት ወይም ከምርጫው ቀድሞ ብጥብጥ ተፈጥሮ ሀገሪቱ ሳትወድ በግድ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር የመተዳደር እድል ሊገጥማት ይችላል የሚል ነው፡፡
በ4ኛነት የሚያስቀምጡት ግምት ደግሞ “ምርጫው ተጭበርብሯል” በሚል ሊፈጠር የሚችልን ብጥብጥ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ብጥብጥ ከተፈጠረ ደግሞ መንግስት ሁኔታዎችን መቆጣጠር ይሳነውና አገሪቱ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ወይም ሀገሪቱ መንግስት የለሽነት ልታመራ ትችላለች ሲሉ ያስቀምጣሉ፡፡
“ምርጫው ተካሂዶ በአንፃራዊነት ሰላማዊ ሆኖ ይጠናቀቃል፤ በምርጫው ውጤት መሠረትም አንድ ፓርቲ ብቻውን መንግስት ለማቋቋም የሚያስችል ድምጽ ሳያገኝ ይቀርና ፓርቲዎች የጥምር መንግስት ለማቋቋም ይገደዳሉ” የሚለው ደግሞ በአምስተኛነት ያስቀመጡት ግምታዊ ሁነት ነው፡፡ በዚህ ግምት መሠረት፤ የሚቋቋመው ጥምር መንግስት ግን እርባና እንደሌለውና ብዙም ሳይቆይ እንደሚፈርስ የሚገልፁት ፖለቲከኛው፤ ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ ሀገሪቱ አስቀድማ የብሔራዊ እርቅና መግባባት ሂደትን አለማከናወኗ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
እነዚህን ሁሉ ችግሮች ለማሸነፍና በዋናነት የሀገሪቱን ህልውና አስቀጥሎ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመሸጋገር የግድ ብሔራዊ የሽግግር መንግስት ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ልደቱ፤ እንዴት የሽግግር መንግስት መቋቋም ይችላል? እነማን ይሳተፋሉ? ምን ያህል ቆይታ ይኖረዋል ለሚለውም ሃሳባቸውን ያጋራሉ፡፡
የሚቋቋመው የሽግግር መንግስት አላማ በዋናነት በሀገሪቱ ብሔራዊ እርቅ እንዲወርድ፣ የሽግግር ጊዜ ፍትህ እንዲሰፍን፣ የፖለቲካ ቅራኔዎች በድርድር እንዲፈቱ፣ በሀገሪቱ ሠላምና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን በመሆኑ የሽግግር መንግስቱ ስያሜ “የኢትዮጵያ ህዳሴ የእርቅና የአንድነት የሽግግር መንግስት” ሊሆን ይገባዋል የሚሉት ፖለቲከኛው የሽግግር መንግስቱ ቆይታም ሁለት አመት ሊሆን እንደሚገባ ይገልፃሉ፡፡ ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም የሚቆይ እንደሚሆንም ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡
ይህ የሽግግር መንግስት ሊቋቋም የሚገባውም በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል በሚደረግ ውይይትና ድርድር ሲሆን የሽግግር መንግስቱ አሁን ባለው ፓርላማ መጽደቅ አለበት ይላሉ፡፡
የሽግግር መንግስቱን አደረጃጀትና አወቃቀር በተመለከተም፣ ቢሆን የሚሉትን ሃሳቦች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
ተጠሪነቱ “ለህዳሴ ሸንጐ” የሆነ የስራ አስፈፃሚ ካውንስል ያለው የሚኒስትሮች ካቢኔ፣ የብሔራዊ ደህንነት አስከባሪ ኮሚሽን፣ የህገ መንግስት ማሻሻያ ሀሳብ አርቃቂ ኮሚሽን፣ የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚሽን፣ የእርቀ ሰላምና የሽግግር ጊዜ ፍትህ አስፈፃሚ ኮሚሽን፣ የክልሎች የሽግግር አስተባባሪ ኮሚሽን እንዲሁም የክልሎች የሽግግር ስራ አስፈፃሚ ካውንስል ያለው የሽግግር መንግስት መዋቅርን ያቀርባሉ - አቶ ልደቱ፡፡
ፓርላማውን የሚተካው “የህዳሴ ሸንጐ”፤ 150 አባላት ከገዥው ፓርቲ፣ 150 ደግሞ በሁለት ጐራ ከተከፋሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ 150 አባላት ከልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚመረጡ ግለሰቦች፣ 55 አባላት ከዘጠኝ ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ተውጣጥተው የሚወከሉበት በአጠቃላይ 505 አባላት ያሉት እንደሆን ሃሳብ አቅርበዋል፡፡
የስራ አስፈፃሚ ካውንስሉ ደግሞ 30 አባላት ያሉት ሆኖ፤ አስሩ ከገዥው ፓርቲ፣ አስሩ ከተቃዋሚዎች፣ አስሩ ከሌሎች የሸንጐ አባላት እንዲሆኑ ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡
አንድ የሽግግር ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትርና ሁለት ምክትሎች እንዲኖሩት፣ አሁን በስልጣን ላይ ካለው ገዥው ፓርቲና ሁለቱ ምክትሎች ደግሞ ከተቃዋሚ እንደሚመረጡ በፕሮፖዛሉ ይጠቁማሉ፡፡
ሌሎች በመንግስቱ መዋቅር ስር ያሉ የስልጣን ተዋረዶችን ስራና ኃላፊነትም በዝርዝር አቅርበዋል፡፡   


Read 2677 times