Saturday, 14 March 2020 11:25

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ህብረተሰቡ ከእጅ ንክኪና አላስፈላጊ ስብሰባዎች እንዲቆጠብ ተጠየቀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(15 votes)

  - ጃፓናዊው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ወደ አገር ውስጥ ከገባ 10 ቀናት ሆነውታል
     - ከግለሰቡ ጋር ግንኙነት የነበራቸው 25 ግለሰቦች በለይቶ ማቆያ ውስጥ ገብተዋል
                 

              ከቡርኪናፋሶ ወደ አዲስ አበባ ባመራው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የካቲት 25 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ አገራችን የገባው ጃፓናዊ የኮሮና ቫይረስ እንዳለበት ማረጋገጡን የጤና ሚኒስቴር ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
የ48 ዓመቱ ጃፓናዊ ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ ከ13 ቀናት በፊት ነበር ከአገሩ ጃፓን ወደ ቡርኪናፋሶ የገባው፡፡ ከቀናት ቆይታ በኋላም ከቡርኪናፋሶ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ውስጥ የተለመደውን የሙቀት ልኬት ምርመራ አድርጓል፡፡
ግለሰቡ በመዲናችን አዲስ አበባ ለአምስት ቀናት ያህል ጉዳዩን ሲያከናውንና በሥራም ሆነ በግል ወዳጅነት ከሚያውቃቸው ሰዎች ጋር ሲገናኝ ከቆየ በኋላ ይታመምና ለሕክምና ወደ ጤና ተቋም ይሄዳል፡፡ በተደረገለት ምርመራም፣ በበሽታው በመጠርጠሩ፣በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቀመጥ ተደርጎ ምርመራና ክትትሉ ይቀጥላል፡፡ በዚህ ምርመራም ጃፓናዊው የኮሮኖ ቫይረስ ተጠቂ እንደሆነ መረጋገጡን የጤና ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ ላይ አስታውቋል፡፡
ከግለሰቡ ጋር ንኪኪ አድርገዋል የተባሉ 25 ሰዎችም በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የጤና ሚኒስቴር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አመልክተዋል:: ግለሰቡ ከሕብረተሰቡ ጋር ያለ ጥንቃቄ ተቀላቅሎ በቆየባቸው ቀናት ውስጥ በሽታውን ሊያስተላልፍባቸው የሚችላቸው ሰዎች ቁጥር የተጠቀሰው ብቻ ሊሆን እንደማይችልና ሌሎች ተጠርጣሪዎችም ሊገኙ የሚችሉበት ዕድል እንደሚኖር ተገልጿል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንደተናገሩት፤ ሕብረተሰቡ የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠርና በሽታውን ለመከላከል የሚወስዱ እርምጃዎችን በንቃት እንዲከታተልና የመከላከል እርምጃው አጋር እንዲሆን አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ በበኩላቸው፤ በአገሪቱ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ በሽታ ታማሚ መገኘቱ መረጋገጡን ጠቁመው፤በሽታው እንዳይስፋፋና እንዳይሰራጭ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ ሊሰራ ይገባል፤ይህንን ለማድረግም ሌት ተቀን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
መንግሥት ለበሽታው መከላከልና መቆጣጠር ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ያመለከቱት የጤና ሚኒስትሯ ተጨማሪ በጀት ለመመደብና ገንዘብ በእርዳታ የሚገኝበትን ሁኔታ ለመፈለግ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ ሕብረተሰቡ በጋራ የሚገለገልባቸውን ነገሮች በጥንቃቄ እንዲጠቀምና በጋራ ከሚያሰባስቡ የሕብረት ግንኙነቶች በሚችለው መጠን እንዲጠነቀቅ፣ በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ውስጥ መስኮቶችን እንዲከፍት፣ በሚችለው መጠንም በእግሩ መሄድን እንዲያዘወትር እንመክራለን ብለዋል፤ዋና ዳይሬክተሩ፡፡  
በአገራችን የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ታማሚ መገኘቱን ተከትሎ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ፤ ሕብረተሰቡ ከእጅ ንኪኪዎችና ካላስፈላጊ ስብሰባዎች እንዲቆጠብ አሳስበዋል፡፡
የበሽታውን መከሰት ተከትሎም የኢንተርናሽናል ኮሚዩኒቲ ት/ቤት፣ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚያደርገውን የመማር ማስተማር ሂደት እስከ ሚያዝያ 11 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ማቋረጡንና ተማሪዎች በኦንላይን ትምህርታቸውን በቤታቸው ውስጥ ሆነው መከታተል እንደሚችሉ ገልጿል፡፡
የሕብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው ከአምስት መቶ ሃያ ሺ በላይ መንገዶች በሁሉም ወደ አገር መግቢያ ጣቢያዎች ላይ የሙቀት ልኬት ሥራ ተሰርቷል፡፡ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በሰባቱ መግቢያዎች ከሶስት መቶ ሺ በላይ መንገደኞች በሙቀት መለያ ውስጥ አልፈዋል ከእነዚህ መካከል ከሰባት ሺ አንድ መቶ በላይ ሰዎች በሽታውን ሪፖርት ካደረጉ አገራት የገቡ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ከአንድ ሺ ሁለት መቶ ሃያ በላይ መንገደኞች የአስራ አራት ቀናት ክትትል አድርገው ያጠናቀቁ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ዘጠኝ መቶ ሰባ አራት ሰዎች የጤና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ ከኢንስቲቲዩቱ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆይ ከተደረጉ አምሳ አራት ሰዎች መካከል አርባ ዘጠኙ ከበሽታው ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ የምርመራ ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡ በመንግሥትና የግል ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢዎችና ክሊኒኮች ውስጥ በሽታውን ለመቆጣጠር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን ዝግጅቱ ግን በሽታውን በአግባቡ ለመከላከል የሚያስችል ነው ለማለት እንደሚያስቸግር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የድንገተኛ ፅኑ ሕክምና ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ወልደሰንበት ዋጋነው ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ሆስፒታሉ በሽታውን ለመከላከልና ስርጭቱን ለመቆጣጠር የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉንና ይህም በሰው ሃይልና በማቴሪያል የተደገፈ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎችን ለመመርመር የሚያስችሉ መሳሪያዎች በሆስፒታሉ የሚገኙ ቢሆንም ተጠርጣሪዎቹን በርቀት ለመመርመር የሚያስችል መሳሪያ ባለመኖሩ ችግሮች ያጋጥማሉ ብለዋል፡፡ ወቅቱ ሁሉም አገራት ይህን አይነት የሕክምና መመርመሪያ መሳሪያዎችን በስፋት የሚፈልጉበት ጊዜ በመሆኑ እጥረት ማጋጠሙ የማይቀር ጉዳይ መሆኑን ያመለከቱት ዶ/ሩ የአፍ መሸፈኛ ማክስ እጥረቱም ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ነው ብለዋል፡፡ በአለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ ባለሙያዎች የተሰጠውን ስልጠና የወሰዱ ባለሙያዎች በየተቋማቸው ስልጠናውን በመስጠት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚደረገውን ርብርብ እያገዙ ነው ብለዋል፡፡
የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የግል ሆስፒታሎችም ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረጉ የሚገኙ ቢሆንም ለጥንቃቄ የሚረዱ የሕክምና መሳሪያ ግብአቶች እጥረት መኖሩ ከፍተኛ ፈተና እንደሆነባቸው የስራ ኃላፊዎች ይገልፃሉ፡፡ የሰላም ክሊኒክ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ሀይለማርያም ታዩ እንደሚናገሩት መንግሥት የበሽታውን ስርጭት የሚከሰተው በመንግሥት ጤና ተቋማት ብቻ አለመሆኑን ከግምት ውስጥ አስገብቶ የግል የጤና ተቋማትም አስፈላጊው የማቴሪያል፣ የሥልጠናና የሕክምና መሳሪያ አቅርቦት ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በትናንትናው ዕለት በሰጡ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በሁሉም የጤና ተቋማት ውስጥ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡  


Read 13206 times