Saturday, 14 March 2020 11:23

ኮሮና ቫይረስ በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ጫና እያሳደረ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(8 votes)

   - የተያዙ ሆቴሎች፣ በረራዎች፣ ጉባኤዎችና ጉብኝቶች እየተሰረዙ ነው
     - ከ1 ሺ ሰው በላይ የሚሳተፉበት አለማቀፋዊ ስብሰባ ተሰርዟል
             
         በተቀሰቀሰ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ አለምን በከፍተኛ ፍጥነት ያዳረሰውና አምስት ሺ የሚጠጉ ሰዎችን ለህልፈት የዳረገው የኮሮና ቫይረስ በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መሆኑ ተነግሯል፡፡ በርካታ ሆቴሎችና የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ኪሳራ እያጋጠማቸው መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በሽታው ባስከተለው አለማቀፋዊ ስጋትና አደጋ የተነሳ በአዲስ አበባ ከተማ ሊካሄዱ ታቅደው የነበሩ ስብሰባዎች እየተሰረዙ እንደሆኑ ታውቋል፡፡
ከአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር በተገኘ መረጃ መሰረት በአገሪቱ ሊካሄዱ የታቀዱ በርካታ ስብሰባዎችና የጉብኝት ፕሮግራሞች እየተሰረዙ ሲሆን፤ ይህም በሆቴሎቹ ገቢ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ከወራት በፊት የተያዙና አሁን በመሰረዝ ላይ ከሚገኙትና በሺዎች የሚቆጠሩ የውጪ አገር እንግዶች ይሳተፉበታል ተብለው ከሚጠበቁ ፕሮግራሞች መካከል ከመጋቢት 9 እስከ መጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ሊካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት 53ኛው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጉባዔ ይገኝበታል፡፡ በሽታው አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከዚህ በተጨማሪ በበሽታው መስፋፋትና ባስከተለው ስጋት ሳቢያ ወደፊት በማስታወቂያ እስከሚገለጽ ድረስ ሁሉንም ሕዝባዊ ስብሰባዎች ለሌላ ጊዜ ማስተላለፉን አስታውቋል፡፡
በቀጣዩ ሚያዝያ ወር በአዲስ አበባ ከተማ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረውና ከአንድ ሺ በላይ ይካፈሉበታል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ዓመታዊ ጉባዔም መሰረዙ ታውቋል፡፡ ለጉባዔው ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቁ ለነበሩ እንግዶች ሆቴሎች ተይዘው የነበሩ ቢሆንም የጉባኤውን ለሌላ ጊዜ መተላለፍ ተከትሎ ተሰርዟል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እስካሁን በአለማችን ውስጥ በሚገኙ ከአንድ መቶ አስር በላይ በሆኑ አገራት መስፋፋቱን ተከትሎ በርካታ አገራት እንቅስቃሴዎችን በማገዳቸውና ዜጎችም ወደ ተለያዩ አገራት የሚያደርጓቸውን ጉዞዎች በመግታታቸው ምክንያት አየር መንገዶች፣ ሆቴሎች፣ የጉዞ ወኪሎችና የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ገቢያቸው በእጅጉ መቀነሱንና ለኪሳራ መጋለጣቸውን ይገልጻሉ፡፡
የኔክስት ስታይል አስጎብኚና የጉዞ ወኪል ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ዮሴፍ ታምራት ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ የበሽታው መከሰትና በተለያዩ አገራት በአስገራሚ ፍጥነት መዛመትን ተከትሎ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡና ወደተለያዩ ስፍራዎች ለጉብኝት የሚሄዱ ቱሪስቶች ቁጥር እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል:: ለዚህም እንደ ማሳያ ከሁለት ሳምንት በፊት ከካናዳ፣ ጣሊያንና ሳውዲም ወደ ኢትዮጵያ መግባት የነበረባቸው 42 ቱሪስቶች የጉዞ ዕቅዳቸውን መሰረዛቸውን አሳውቀውናል:: ይህም በድርጅታችን ላይ ያስከተለው ኪሳራ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም ብለዋል፡፡
ድርጅታችን ለጉብኝት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ቱሪስቶችን የማስጎብኘት ሥራ ብቻ አይደለም የሚሰራው፤ ለጎብኚዎቹ የጉዞና የማረፊያ ቦታዎችን የማመቻቸቱን ሥራ ሁሉ ይሰራል፡፡ በዚህ ምክንያትም እነዚህ ቱሪስቶች ወደ አገር ውስጥ ከመግባታቸው አስቀድሞ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ በሚገባ መሟላቱን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የምናወጣው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ አሁን የደረሰብን ኪሳራም ከዚህ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው ሲሉ ተናግረዋል:: የናይል የጉዞ ወኪል ሥራ አስኪያጅ አቶ እዮብ ግርማ በበኩላቸው፤በሽታው  በእኛ በዚህ ዘርፍ ላይ ተሰማርተን በምንገኝ ሰዎች ላይ እያስከተለ ያለው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ዘርፉ በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ ለኪሳራ ሲጋለጥ የቆየ ነበር ያሉት አቶ እዮብ አሁን ደግሞ የተሻለ ጊዜ መጣ ብለን ለሥራ እየተንቀሳቀስን ባለንበት ጊዜ እንዲህ አይነት ችግር መፈጠሩ በስራችን ላይ ያስከተለው ጉዳት ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ አሁን ወቅቱ ከተለያዩ የአውሮፓ አገራት ጎብኚዎች በስፋት የሚመጡበት ወቅት ቢሆንም የበሽታው ስጋት ግን አንድ ቱሪስት እንኳን እንዲናፍቀን አድርጎናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ የበሽታው መስፋፋትና ስጋት በዚሁ ከቀጠለ በመጪዎቹ የክረምት ወራት ሥራቸው ሙሉ በሙሉ የሚቋረጥ እንደሆነም አቶ እዮብ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
በመላው ዓለም ከመቶ ሃያ ሺ በላይ ሰዎችን የያዘው የኮሮና ቫይረስ ስጋት በኢኮኖሚያቸው ላይ ጫና ካሳደረባቸው አገራት መካከል ኬንያ ተጠቃሽ ስትሆን በአገሪቱ በዚህ ዓመት ሊካሄዱ ታቅደው የነበሩ አለማቀፋዊ ስብሰባዎች በሙሉ እንዲሰረዙ መደረጋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ በመጪው ሰኞ በአገሪቱ ታቅዶ የነበረውና ከሰባ ዘጠኝ አገራት የተውጣጡ ከ2 ሺ በላይ እንግዶች “ዘ ኔክስት ኢንስታይን ፎረም” ተሰርዟል፡፡      

Read 13234 times