Saturday, 14 March 2020 11:17

ሱዳናውያን ምሁራንና ባለ ሥልጣናት በግብፅ ላይ ተፅዕኖ እያሳደሩ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

  ግብፅ የያዘችው አቋሟ አያዋጣትም ብለዋል

           በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ግብጽ የያዘችው አቋም እንደማያዋጣት የሱዳን ታዋቂ ምሁራንና የመንግሥት ባለሥልጣናት የገለፁ ሲሆን አገሪቱ ኢትዮጵያን ይቅርታ ጠይቃ ወደ ሶስቱ አገራት የድርድር መድረክ እንድትመልስ ጠይቀዋል፡፡
ሰሞኑን በአልጀዚራ አረብኛ ፕሮግራም ላይ ቀርበው ስለ ድርድሩና የግብፅ አቋም ማብራሪያ የሰጡት የሱዳን የውጭ ዲፕሎማሲ ም/ሃላፊ አብዱራሂም መሃመድ ከሊል፤ የግብጽ መንግስት በግድቡ ላይ የያዘው አቋምና እየሄደበት ያለው መንገድ የሚያዋጣው አይሆንም ብለዋል፡፡
ግብፅ ከድርድር ውጪ ምንም አማራጭ እንደሌላት የተናገሩት ዲፕሎማቱ፤ በአረብ ሊግ በኩልም ሆነ በሌሎች አገራት አማካይነት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ልትፈጥር የምትንቀሳቀስበት መንገድ አያዋጣትም ብለዋል፡፡
ግብፅ የተመካችበት የአረብ ሊግም ቢሆን ጥርስ የሌለው አንበሳ መሆኑን በመጠቆም፤ ሊጉ በኢትዮጵያ ላይ ሊያሳርፈው የሚችለው ጫና እንደሌለ ዲፕሎማቱ ለአልጀዚራ አስረድተዋል::
ግብፅ ያላት ብቸኛ አማራጭ የአሜሪካንና የአለም ባንክን አደራዳሪነት ትታ ወደ ሶስቱ የተፋሰሱ አገራት የድርድር ማዕቀፍ መመለስ ብቻ ነው ብለዋል - ዲፕሎማቱ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ የአባይን ጉዳይ በቀላሉ ለድርድር አያቀርቡትም›› ያሉት አብዱራሂም መሀመድ ከሊል፤ ግድቡ በኢትዮጵያውያን አንጡራ ሃብት የሚገነባ የህልውናቸው መሠረት ነው ብለዋል፡፡
ሱዳን የግብጽን አካሄድ የምትቃወመው ለራሷ ብሄራዊ ጥቅም መሆኑን ያስረዱት ዲፕሎማቱ፤ “የሕዳሴው ግድብ ተስፋው ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም በግድቡ እኔም እንደ አንድ ሱዳናዊ ትልቅ ተስፋ አለኝ›› ብለዋል፡፡
“ግድቡ ተጠናቆም ስራ ሲጀምር የምስራቅ አፍሪካ ትልቁ የብርሃን ምንጭ ይሆናል፤ ኢትዮጵያን የሚጠቅመውን ያህል ሱዳንም ትጠቀማለች” ሲሉ ተናግረዋል - የሱዳን መንግስት ባለስልጣን፡፡
ሱዳን የወሰደችው አቋምም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የገለፁት ምሁሩ፤ የሱዳን መንግስት የአረብ ሊግን ውሣኔ ውድቅ ባያደርግ ኖሮ፣ የሱዳን ህዝብ ተቃውሞውን ያሰማ ነበር ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ በዲፕሎማሲው በኩል ስለ ግድቡ ለአለማቀፉ ማህበረሰብ የበለጠ ለማስረዳት ዲፕሎማቶችን ወደተለያዩ ሀገራት እንደሚያሰማራ አስታውቋል::

Read 12761 times