Saturday, 14 March 2020 11:01

ሁለተኛው የህፃናት ንባብ አመታዊ ጉባኤ ትላንት ተጠናቀቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

    መቀመጫውን አሜሪካ ሚኒሶታ አድርጐ ከ17 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ መስራት የጀመረው “ኢትዮጵያ ሪድስ” በጐ አድራጐት ድርጅት ለሁለት ቀናት በማግኖሊያ ሆቴል ሲያካሂድ የነበረውን የህፃናት ንባብ አመታዊ ጉባኤ ትላንት አርብ መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም አጠናቀቀ፡፡
ሐሙስ ጠዋት በተጀመረው በዚህ ጉባኤ ድርጅቱ ከትምህርት ሚኒስቴርና ከአገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ በመተባበር ከውጭና ከሀገር ውስጥ በተውጣጡ ምሁራን የተዘጋጁና ትኩረታቸውን በህፃናት ንባብ ላይ ያደረጉ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጐባቸዋል፡፡ በትላንትናው ዕለትም በህፃናት መጽሐፍትና ሌሎች ግብአቶች አዘጋጆች የሚቀርብ አውደ ርዕይ ለእይታ የቀረበ ሲሆን፣ በሀገራዊ የህፃናት ግብአቶች ዝግጅት፣ ጥራትና የገበያ ስርጭት ላይ በዘርፉ በተሰማሩ ባለድርሻ አካላት መካከል የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡ “ኢትዮጵያ ሪድስ” ባዘጋጀው በዚህ በሁለተኛው የህፃናት ንባብ ጉባኤ አስፈላጊ ግብአቶችንና ጠቃሚ አስተያየቶችን ከጉባኤው ይዘው መውጣታቸውን የኢትዮጵያ ሪድስ የሀገር ውስጥ ተጠሪ ወ/ሮ የምስራች ወርቁ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮትየ ሪድስ ባለፉት 17 ዓመታት ቋሚና ተንቀሳቃሽ ቤተመጽሐፍትን በመላው አገሪቱ የመንግስት ት/ቤቶች በማቋቋም፣ የመማሪያ መጽሐፍትን በማሳተምና በማከፋፈል በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የንባብ ባህል እንዲዳብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡


Read 1307 times